Saturday, 04 December 2021 13:06

ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


          “ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እያቀረቡ ያሉትን የተዛባ ዘገባ ከሙያው ሥነ ምግባር ያፈነገጠ በመሆኑ ሊታረም ይገባል”
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን የህዝብ ፣የንግድ፣የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃንንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራት በአባልነት በማቀፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፤
የምክር ቤታችን አባል የሆኑ የሚዲያ ተቋማት ምንም እንኳ የባለቤትነት ይዞታቸውና የተመሰረቱበት አላማ ልዩነት ያለው ቢሆንም ሀገራችን አሁን የገጠማትን ፈተና ለመወጣት እውነተኛ፣ትክክለኛና ወቅታዊ ዘገባዎችን  ለህብረተሰቡ ከማቅረብ ጎን ለጎን፣በሀገሪቷና በህዝቧ ላይ ያንዣበበውን የተቀናጀ አፍራሽ የሚዲያ ዘገባ ለመመከት በጋራ መቆም እንዳለባቸው ምክር ቤቱ ያምናል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የመገናኛ ብዝሃን፣ ሀገራችን የገባችበትን ጦርነት በተመለከተ እያሰራጩት ያሉት ዘገባ ከተጨባጩ እውነታ ያፈነገጠ ብቻ ሳይሆን ከትክክለኛ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ጋር የሚያጋጨ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ በተለይም አንዳንድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን፣አዲስ አበባና ዙሪያዋን እንዲሁም በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ እያሰራጩት ያለው ዘገባ፣ ህዝብን የሚያሸብርና ስጋት ላይ የሚጥል ከመሆኑም በላይ ከተማዋን የጦርነት ቀጠኛ አድርጎ የማቅረብ ዝንባሌ እንዳለባቸው ታዝበናል፣የከተማው ህብረተሰብ ግን እንደወትሮው ሁሉ የዕለት ተዕለት ተግባሩን ያለምንም መስተጓጎል እያከናወነ ይገኛል፡፡ መገናኛ ብዙሃን በጦርነት ጊዜም ቢሆን በህዝብ ላይ ተጨማሪ ጉዳት በማደርስ መልኩ ከወገናዊነት ነፃ ሆነው መረጃን ለህብረተሰቡ ማቅረብ ያለባቸው ቢሆንም፣ እነዚህ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ግን በጋዜጠኝነት ሙያ የማይፈቀድ ኢ-ሚዛናዊ ዘገባን በስፋት እያሰራጩ ነው፡፡ በመሆኑም ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እያካሄዱ ያሉት የተዛባ ከሙያው ሥነ ምግባር ያፈነገጠ በመሆኑ ሊታረም ይገባል እንላለን፡፡
ፈቃድ አግኝተው በሀገር ውስጥ የሚሰሩ የውጭ ሀገር ወኪል ጋዜጠኞች ወቅቱ ከምንም ጊዜ በላይ ፈጣንና ተዓማኒ መረጃ ማቅረብ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ያለን መሆኑን በመገንዘብ እንዲሁም ማንኛውም ነገር መስራት የሚቻለው ሀገር ስትኖር መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የህዝቡን አብሮ የመኖር ባህልና ትውፊት የሚሸረሸር እንዲሁም ስጋት ላይ የሚጥል ዘገባ እንዳይተላለፍ ከፍ ያለ ያለ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንም በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የሚሠራጩ ያልተረጋገጡና ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ያፈነገጡ ዘገባዎችን እንዳለ ወስዶ ከማስተላለፍ በመቆጠብ፣ የህዝብና ሀገር ውግንናቸውን እንዲሁም ለሙያዎች ያላቸውን ታማኝነት በተግባር ሊያሳዩ ይገባል፣ በተለይም ለዘመናት አብሮ በኖረው ህዝብ መሀል የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችን ደግሞ ባለመሰራጨት ህብረተሰቡን ማንቃትና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግንዛቤ ማስጨበጥ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ተቋማት ይጠበቃል፡፡
በመጨረሻም መንግስት ተገቢውን ወቅታዊ መረጃ ለህዝብ ከማድረስ እንጻር ተከታታይ መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ በሚዲያዎች በኩል የማቅረብ ፍጥነቱን እንዲያሻሽል እያሳሰብን፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም ሀገርን ከብተና ለማዳን አደጋውንና ስጋቱን የሚመጥን ደረጃ የተረጋገጡ መረጃዎች በየዕለቱ በተቀናጀ ስልት በማቅረብ፣ግንዛቤ የመፍጠር ስራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል እንላለን፡፡
(የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ ህዳር 23 ቀን 2014 አዲስ አበባ)

Read 11033 times