Saturday, 04 December 2021 13:05

በመላው አገሪቱ የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለአንድ ሳምንት ይዘጋሉ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

    መምህራንና ተማሪዎች አገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል
                         
                በአገሪቱ ሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከህዳር 27 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ለአንድ ሳምንት እንዲዘጉ ተወሰነ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ሴክተሩ እየተካሄደ ባለው አገርን የማዳን ዘመቻ ውስጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ በመታሰቡ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችን ለአንድ ሳምንት ዝግ በማድረግ፣ መምህራኑና ተማሪዎቹ እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ብለዋል።
ትምህርት ቤቶቹ ዝግ  በሚሆኑበት ወቅት ያልተሰበሰቡ የዘማች ሰብሎችን መሰብሰብ፣ የዘማች ቤተሰቦችን መርዳት በስፋት እንደሚከናወን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በከተሞች አካባቢ ያሉት ደግሞ በገቢ ማሰባሰብ፣ ደም በመለገስ፣ በስንቅ ዝግጅትና መሰል ተግባራት ላይ በስፋት እንዲሳተፉ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ ትምህርት ዝግ በሚሆኑባቸው ቀናት፣ አገራቸው ያለችበትንና ያሳለፈችውን ወቅታዊ ሁኔታ እያሰቡ ለወደፊት የዚህ አይነት ግጭት በየትኛውም መንገድ በአገራችን እንዳይደገም ለማድረግና አገራቸውን እንደገና ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩላቸውን አስዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል። የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶቹ የአንድ ሳምንቱን የትምህርት ጊዜ ወደፊት በሚያወጡት የማካካሻ መርሃ ግብር እንዲካካስ ያደርጋሉም ተብሏል።

Read 11629 times