Saturday, 04 December 2021 13:10

አዲሱ የቻይና ነፃ ገበያ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(7 votes)

 በቀጣዮቹ 3 ዓመታት እስከ 300 ቢ. ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ከአፍሪካ መግዛት ትፈልጋለች
         ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሷ ለመፍታት ለምታደርገው ጥረት የበኩሌን ድጋፍ አደርጋለሁ - ቻይና
         ከቻይና የተሰጠን የነፃ ገበያ ዕድል ሊያዘናጋን አይገባም፤ ሌሎችንም አማራጮች ማየት ይገባናል -የኢኮኖሚ ባለሙያ
         አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ በማገዷ ወደፊት የምትጎዳው እራሷ ናት  - አሜሪካውያን ባለሃብቶች
                  
             ቻይና ለአፍሪካ የግብርና ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ ገበያን መፍቀዷን ያስታወቀች ሲሆን በቀጣዮቹ 3 ዓመታት 300 ቢሊዮን ዶላር  የሚያወጡ ምርቶችን ከአፍሪካ ገበያ ለመግዛት መወሰኗንም ገልጻለች፡፡
በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው የቻይና አፍሪካ 8ኛው የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ የቻይና  አፍሪካ 8ኛው የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ የቻይና ፕሬዚዳንት ሺን ጂንፒንግ ያሳለፉትን ውሳኔ ይፋ ያደረጉት በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች መምሪያ ዳይሬክተር ጀነራል ውፔንግ እንደተናገሩት፤ ቻይና የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን የበለጠ ለማጠናከርና የልማት አጋርነቷን ለማሳየት ለአዳጊ አገራት በምትሰጠው ነፃ የገበያ ዕድል  በሚቀጥሉት 3 ዓመታት ከአፍሪካ ወደ ቻይና የሚገቡት ምርቶች  300 ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ እቅድ ተይዟል፡፡
የቻይና አፍሪካ ትብበር ርዕይ 2013 ይፋ በተደረገበት በዚህ ጉባዔ ላይ እንደተገፀው በመጀመሪያዎቹ የርዕዩ 3 ዓመታት፣ የአፍሪካን የውጭ ንግድ ለማገዝ ድህነትን ለመቀነስና የግብርና ልማት መርሃ ግብርን ለማከናወን ቻይና ከአፍሪካ የምትሸምተውን ሸቀጥ ታሳድጋለች። ይህንኑ የአፍሪካን የግብርና ውጤቶች ለቻይና ገበያ የሚቀርቡበትን መንገድ የሚያፈጥንና የሚያቀላጥፍ ስርዓት ለመዘርጋት መታቀዱም ተገልጿል፡፡ አገሪቱ የአፍሪካ አገራትን እርስ በእርስ የሚያገናኝ አስር የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናውን ቃል ገብታለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካን መካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ፣ ለአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት የ10 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንደምትሰጥም ገልጻለች፡፡
ሰሞኑን በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ያደረጉት የይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በራሷ የመፍታት አቅም እንዳላት አገራቸው እንደምታምን ገልጸው፤ ለዚህም የበኩላችንን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ጥሪበማደረግ ላይ ያሉ አገራትን ቻይና እንደምትቃወም ሚኒስትሩ ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡
“ቻይና ለአፍሪካ አገራት የሠጠችው የግብርና ምርቶች የነፃ ገበያ ዕድል ኢትዮጵያ በአጎዋ ያጣቸውን የነፃ ገበያ ዕድል ለመተካት የሚችል ጥሩ ዕድል ቢሆንም የተሰጠን ዕድል ሊያዘናጋን አይገባም” ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ተስፋዬ ታምራት እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ በአጎዋ የተነጠቀችውን ዕድል ሊተካ የሚችል የነፃ ገበያ ዕድል ከቻይና አግኝታለች፤ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን ምርቶቻችንን ቻይና በምትፈልገው ብዛትና ጥራት እያመረትን ተወዳዳሪ ሆነን ማቅረብ መቻል አለብን፡፡ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን በብዛት በማምረት ለቻይና ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገራትም ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታን መፈለግ ይኖርብናል፤ ብለዋል። አያይዘውም እንደ ቻይና ሁሉ ሌሎች አገራትም ይህን አይነት ዕድል እንዲሰጡን ግፊት ማድረግ አለብን፤ በአንድ አገር ላይ የተመሰረተና ጥገኛ የሆነ ኢኮኖሚ የሚያስከትለውን ጉዳት አሁን በአጎዋ አይተነዋል ልንጠነቀቅ ይገባል” ሲሉ መክረዋል፡፡አጎዋ የበለፀጉ አገራት ለታዳጊ አገራት ከሚሰጧቸው የገበያ ዕድል አንዱ እንጂ ብቸኛው አይደለም ያሉት ዶ/ር ተስፋዬ፤ ሌሎች የገበያ አማራጮችን ማፈላለግ፣የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን ማድረግ፣ ዜጎች በአገራቸው ምርቶች እንዲጠቀሙ በማድረግ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን መቀነስ  በአጎዋ ያጣነውን የገበያ ዕድል ለማካከስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡በሌላ በኩል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንድትወጣ ለማድረግ ያስተላለፉት ውሳኔ በአሜሪካ ባለሃብቶች ተቃውሞ እንደገጠመው ፎርብስ መፅሔት ዘግቧል። መፅሔቱ አሜሪካ የኢትዮጵያን መንግስት እጅ ለመጠምዘዝና ጫና ለማሳደር በርካታ ስልቶችን እየተጠቀመች መሆኑን ገልፆ፤ ከእነዚህ መንገዶች መካከል አንዱ ከቀረጥ ነፃ ገበያ ዕድል ማስመጣት መሆኑንም አክሏል፡፡ መፅቱ ይህ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት የጠላላፊው ውሳኔ አገሪቱ በቀጥታ ከባለሃብቶች ጋር የሚያላትማት ውሳኔ መሆኑን ጠቅሶ፤ ውሳኔው ባለሃብቶችና አገራት የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈፀም የንግድ ግንኙነታቸውን በተናጥል እንዲያጠናክሩ ያስገድዳቸዋል ብሏል፡፡
የአሜሪካ መንግስት አጎዋን የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈፀሚያና መደራደሪያ ከማድረግ ሊቆጠብ እንደሚገባው ያመለከተው የፎርብስ መፅሄት፤ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯ ሲቀረፍ ባለሃብቶቹ ምርቶቻቸውን አስታማማኝ ወደ ሆኑና ወደተረጋጉ አገራት በጥሩ ዋጋ የሚሸጡ በመሆኑ የአሜሪካ ገበያ እንዳይረጋጋ ያደርጋል ብሏል፡፡

Read 11983 times