Saturday, 04 December 2021 13:12

“ሸንጎ ተሰብስቦ ዕውነቱን ለሚስቱ የማይነግር ባል አይስጥሽ!” ታ ተረት

Written by 
Rate this item
(7 votes)

   የአይሁዶች ተረት ነው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ተፈላሳፊ ሰው በአንድ የገጠር ከተማ ይኖር ነበር።  እያነበበና እየተመራመረ ሳለ፣ የሰፈር ልጆች ይመጡና፤
“ምክር ስጠን… አስተምረን… አንድ ታሪክ ንገረን ወዘተ” እያሉ ያስቸግሩታል።
አንድ ቀን ፈላስፋው፤ “ለምን አንድ የውሸት ታሪክ ፈጥሬ አባርሬያቸው አላርፍም” ብሎ ያስብና፤
“ልጆቼ፤ ወደዚያ የዕምነት ቦታ ወደ ምኩራቡ ሂዱ። እዚያ አንድ ትልቅ የባሕር ጭራቅ ታያላችሁ። አምስት እግር፣ ሶስት ዓይንና እንደ ፍየል ዓይነት ፂም ያለው ሲሆን መልኩ አረንጓዴ ነው” አላቸው።
ልጆቹም ወደተባለው ቦታ በፍጥነት እየሮጡ ሄዱ። ፈላስፋውም ወደ ምርምሩ ተመልሶ ሥራውን ቀጠለ። በሆዱም “እነዚህን ደደብ ልጆች ተጫወትኩባቸው። የውሸት ጭራቅ ፈጥሬ አሞኘኋቸው” እያለ በደስታ ፈገግ አለ።
ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ የብዙ ሰዎች የእግር ኮቴ ሰማ። ወደ መስኮቱ ሄዶ ወደ ውጪ ተመለከተ። አያሌ አይሁዶች በብዛት ተሰብስበው ሲሮጡ አየና፤
“ወዴት ነው የምትሮጡት?” ሲል ጠየቃቸው።
አይሁዶቹም “ወደ አሮጌው የእምነት ቦታ ነዋ!” አሉት። “ከዕምነቱ ቦታ ምን ነገር ተፈጥሮ ነው ይሄ ሁሉ ህዝብ በመንጋ የሚተምመው?” ሲል ደግሞ ጠየቃቸው።
ከሰዎቹ አንደኛው ጥያቄውን በጥያቄ መለሰለት፡-
“አንተ ፈላስፋ አይደለህም እንዴ? ስለ ጭራቁ ምንም አላወቅህም?” አንድ እጅግ ግዙፍ የባሕር ጭራቅ ከዕምነቱ ቦታ ፊት ለፊት ታይቷል። እሱን ልንመለከት መሄዳችን ነው! ያዩት ሰዎች እንደነገሩን አሳር የሚያህል አስፈሪ ጭራቅ ነው። እንደ ፍየል አይነት ፂም ያለው፣ ደማቅ አረንጓዴ ጭራቅ ነው። በየደቂቃው እንደ እስስት መልኩን ይቀያይራል አሉ!”አሉት።
ፈላስፋው አሁንም፣ እየሳቀባቸው ነው! ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ዋናው አይሁዳዊ ቄስ፣ የዕምነቱ ቦታ ኃላፊ፤ ከህዝቡ ጋር ሲሮጡ አያቸው።
ከዚያም፤
“ኧረ የሰማያቱ ያለህ! ዋናው የዕምነት አባት ካሉበትማ አንድ የታየ ጭራቅ ቢኖር ነው!  “እሳት ከሌለ ጭስ አይኖርም” አለና ፈላስፋው፣ ካፖርታውን አጥልቆና ባርኔጣውን አድርጎ፣ከዘራውንም ይዞ “ማን ያውቃል የጭራቁ መታየት ዕውነት ቢሆንስ? መቼም ይሔ ሁሉ ህዝብ አይሳሳትም!” ብሎ ከህዝቡ ጋር መሮጥ ጀመረ፡፡
በልቡም፤
“ወይኔ መዐት ህዝብ ቀድሞኛልኮ!” እያለ መንገዱን ቀጠለ፤ ይባላል፡፡
***
 ኬንያውያን “አካፋን አካፋ ነው እንጂ ‘ትልቅ ማንኪያ ነው’ አንበል” ይላሉ፡፡ ይህን አባባል፣ ስለ ማንነታችንና ስለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን ስናወሳ ልብ እንበለው፡፡ ስለ ፓርቲያችን፣ስለ ድርጅታችንንና ስለ ሀገራችን ስናወሳም እናስበው ስለ መከላከያችንና ስለ ስልጣናችን ስለ ተቃዋሚዎቻችንና ጎረቤቶቻችን ስናወጋም እናስታውሰው፡፡ ስለ ዲሞክራሲና ስለ ልማት ስንወያይም ብሂሉን በጥሞና እናሰላስለው፡፡ ነገርን የማጋነንም ሆነ ከናካቴው የመዋሸት መጥፎነቱ ከላይ እንዳየነው ፈላስፋ፣ እኛኑ ተብትቦና አሞኝቶ ዕውነት እንዲመስለን ማድረጉ ነው፡፡ ጎብልስ የተባለው የሂትለል አማካሪ “አንድን ውሸት ደጋግሞ በመናገር ዕውነት ማስመሰል ይቻላል” ብሏል- ይባላል፡፡ ስለ ግልጽነት እያወራን ይበልጥ ሚስጢራዊ የምንሆን ከሆነ፣ ያው ከመዋሸት አንድ ነው! ያለ አቅማችን ጉልበተኛ መስለን ለመታየት መሞከርም ሆነ፣ጉልበተኛ ሆነን ምስኪን ደካማ መስለን መቅረብም ዞሮ ዞሮ መዋሸት ነው፡፡ እያየን አላየንም፤ እየሰማን አልሰማንም፣ እያጠፋን እንደ ጲላጦስ እጃችንን ታጥበን፣ ከደሙ ንፁህ ነን ማለትም፤ በጥፋተኝነት ከመፈረጅ አያድንም! የማታ ማታ ቅጥፈት መሆኑ ይጋለጣልና! የአብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክም ያው መዋሸት ነው፡፡ ከአፈርኩ አይመልሰኝም ያው የሐሰት ዝርያ ነው! አስገድደን የምንፈጽመውም ሆነ ዋሽተን የምናሳምነው ጉዳይ የአዘቦቱን ሰው ጭብጨባ ቢያተርፍልንንም፣የክቱን ሰው ያሳዝናል፡፡ “ቀድማ የበቀለች ማሽላም ቀድማ መቀጠፏን ነው የምትናገር የሚለውን አባባል እንዳንዘነጋ፡፡ የሞቅ ሞቅና የመንገኝነት ባህል (herdism) አደገኛ ነው፡፡ ዕምነተ -ሰብን (cultist) የመልመድ ፈሊጥና አካሄድም፣ አዋጭ አይደለም።
በሀገራችን አንድ የሁልጊዜ ስህተት በመሆን የሚታወቅ ነገር፣ የእድገት ሂደታችን እንቅፋት፣ የመጠራጠር አዝማሚያና ምክንያታዊነትን ማጣት /ማራቅ/ መሆኑ ነው! አመክንዮን ማምከን ነው! ከእንግዲህ፤ “መንገዶች ሁሉ ወደ ሮማ ያመራሉ” የሚለውን አባባል፣ “ብዙ አማራጭ መንገዶች እንዳሉ እንይ” በሚለው ለመቀየር መዘጋጀት ያስፈልጋል። ብዙ አጭር አቋራጭ መንገድም ሆነ ፣ ረዥምና ትዕግስትን የሚጠይቅ ጎዳና እንዳለ አበክሮ ማስተዋል ሀቀኛውን ፈር እንድንጨብጥ ያደርገናል። ማንኛውም ሹም ወይም ባለሥልጣን የየስብሰባዎቹን ዕውነተኛ ውጤት ወይም ጠቅላላ ሂደት ከህዝብ መሸሸግ የለበትም። “ሸንጎ ተሰብስቦ ዕውነቱን ለሚስቱ የማይነግር ባል አይስጥሽ” የሚለው የወላይታ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው! ለዚህም ብርታቱን ይስጠን!!

Read 12534 times