Print this page
Sunday, 05 December 2021 00:00

አናሳንስ፣ አናብዛ፤ ፍጥረታችን የተመጠነች ናት፤ ከመጠኗም አንውጣ

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)

    “በጥበብህ ሚዛን” ተጠቀም። ሁሉም ነገር በልኩ ይሁን። ምትኩ (ወልደ ሕይወት) የተሰኘው ፈላስፋ፣ ይህን አስተምሯል። “ፍጥረታችን የተወሰነች ናት፤ ከወሰኗም ልንወጣ አይገባም” ይላል።
የሰዎችን ትምህርትና መጻሕፍት፣ ሳንመረምር በችኮላ አምነን ልንቀበላቸው አይገባንም። … በችኮላም ሐሰት ነው አንበል።
የታላላቆችህን ምክር ስማ። … ጥበባቸውንም አትናቅ። … ነገር ግን፣ ሁሉን እየመረመርክ… መልካሙን በልብህ ውስጥ አፅንተህ አኑር።
መፋቀራችንን በማፅናት እርስበርሳችን መረዳዳት ይገባናል። የተቸገሩትን ደግፍ። ሊሰሩ የማይወዱ ሰነፎችን ግን፣ “ሂዱ፣ የድካማችሁን ዋጋ ሰርታችሁ ብሉ” በላቸው። ለሰነፍ ገንዘብህን ከምትሰጥ ወደ ባህር መጣል ይሻላል።
መፅሐፉ ገና ሲጀምር፣ ይዘቱን ይናገራል። “የጥበብና የምርምር፣ የተግሳጽና የፍልስፍና መፅሐፍ” እንደሆነ ይገልፅልናል። ደራሲው፣ “ትልቅ የአገራችን መምህር፣ ስሙ ወልደ ሕይወት የተባለ ነው” በማለት ያስተዋውቀናል። ምትኩ በሚል ስምም ይታወቃል።
“በሕይወቴ ረዥም ጊዜ፣ በቅን ልቦናዬ የመረመርኩትን እፅፍ ዘንድ አሰብኩ” ይለናል ወልደ ሕይወት። ምክንያቱስ? የጸሃፊው አላማ፣ ከመፅሐፉ ምንነት ጋር የተዛመደ ነው።
ፍልስፍናው፣ በነባር እምነት ላይ ለማመፅ፣ እምነትን በጥርጣሬ ለመናድ ነው?
እውቀትና እውነተኛ ስርዓት፣ … “ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ፣ ከኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ ጋር ይኑር” በማለት ፈላስፋው ምኞቱን ገልጾ የለ? ነገር ግን፣  ፀሎትና ምኞት ብቻ አይደለም። የእውቀት መፅሐፍ ፅፎላቸዋል። መጽሐፉ፣ “ከእኛ በኋላ ለሚወጡ ልጆቻችን”፣ ይጠቅማል ይላል ጸሐፊው። “እውቀትና ምክር” ያገኙበታል።
ይህም ብቻ አይደለም።
ጠቢባን ጥያቄ እንዲያነሱ፣ መፅሐፉ መነሻ ምክንያት ይሆንላቸዋል በማለት ፈላስፋው አላማውን ያስረዳል።
 ጥያቄ ማንሳት ማለት ግን የሙግት ሱስ መፍጠር ማለት አይደለም። መጠየቅና መመርመር፣ የጥርጣሬ መንፈስን ለመንዛት አይደለም። በነባር እውቀት ሁሉ ላይ ለማመጽ፣ “ወደፊትም ምንም ነገር ማወቅ አይቻልም” ብሎ የሰውን አእምሮ ለማቃወስ አይደለም የጥያቄ ፋይዳ።
ይልቅስ፣ ሰዎች እንዲጠይቁ መፅሐፉ መነሻ የሚሆናቸው፤ “በጥበባቸውም ላይ ጥበበብን እንዲጨምሩ”ነው።
ከቀደምት መማር፣አዲስ እውቀት መጨመር ማስተማር፡፡
“መጠየቅና መመርመር”፣ እጅግ አስፈላጊና ቀዳሚ የስነምግባር መርህ ነው። ግን ለከንቱ አይደለም።  እውነትን ከሃሰት ለይቶ ለማወቅ፣ በቅጡ እውቀትን ለማካበት ነው።
“ጠቢብ፣ ጥበብ እንዲጨምር፣ ምክንያት ጨምርለት” የሚለውን ብሒል ጠቅሷል - ጸሐፊው። ከቀድሞ አዋቂዎች አንብቦ፣ መርምሮ፣ አጣርቶ እውቀትን ይገበያል።
ከዚህ በመነሳት፣ እሱም በፊናው፣ በአዲስ ምርመራ፣ አዲስ እውቀትን ያገኛል። በነባር ጥበብ ላይ አዲስ ጥበብ ይጨምራል።
 ከዚያ በኋላ በተራው፣ ሌሎች ሰዎችን ያስተምራል፤ መፅሀፍም ያዘጋጃል። ለሌሎች ሰዎች የጥበብ መነሻ ይሆናል - አዲስ እውቀትን እንዲጨምሩ።
ታላቁ የፊዚክስና የሂሳብ አዋቂ አይዛክ ኒውተን፣ ይህን ይመሰክራል። መቼም፣ በሳይንስ መስክ፣ እስከዛሬ፣ ኒውተንን የሚያክል ሊቅ አልተፈጠረም።  ይባላል እንደዚያም ሆኖ ለዚህ ሁሉ ስኬት እንደ መነሻና እንደ መንደርደሪያ የሆኑለት ሊቆችን አመስግኗል። በቀደምት አዋቂዎች ትከሻ ላይ ተደግፌ ነው ወደ ከፍታ የተሻገርኩት ብሏል ሊቁ ኒውተን።
እሱም በተራው ለእልፍ አእላፍ ጠቢባን መነሻ ምክንያት ሆኗል- የዓለምን ታሪክ ቀይሯል ብንል አይሻልም? እውቀትን አሰፍቷል፡፡ አርአያነቱ ብርሃን ሆኗል፡፡
እንዲህ ነው፣ እውቀት እየተስፋፋ፣ እየረቀቀና እየመጠቀ፤ ጥበብ እየበዛ፣ እየሰላና እየበረታ የሚቀጥለው። ከቀድሞ ሊቆች የሰማውን እየመረመረ ይማራል፤ ከመፅሐፍት ነባር እውቀትን እየመረመረ ይጨብጣል፤ አዲስ እውቀት እየጨመረ ይፅፋል፤ ያስተምራል።
ማንበብና መፃፍ፣ መስማትና መናገር፣ መማርና ማስተማር ብለን በሌጣው ካየነው ግን፤ ስህተት ላይ እንወድቃለን። ሁል ጊዜ፣ “መመርመር” የሚሉት የእውቀት ድልድይ መኖር አለበት። አለበለዚያ፣ ፅሁፉም፣ ትምህርቱም፣ ንግግሩም ሁሉ ከንቱ ልፋት ይሆናል፤ መክኖ ይቀራል፤ ወደ ስህተት ይመራል፤ ወደ ጥፋት ያስገባል። ፀሐፊውም ይህን ደጋግሞ ገልጿል። መርምሩ ብሏል።
“የመረመርኩትና መልካም መሆኑንም ያወቅኩት ካልሆነ በስተቀር፣ ከሰዎች አፍ የሰማሁትንና ከሰው ትምህርት የተቀበልኩትን ምንም አልጽፍም” ይላል ፈላስፋው ምትኩ (ወልደ ሕይወት)። የእውቀት መንገድን ከነ አቅጣጫውና ከነልኩ፣ ከነመነሻውና ከነጉዞው፣ ከነጥንቃቄውና ከነፍሬው ምን እንደሚመስል፤ ገና ከውጥኑ እየነገረን ነው። የጥበብ ሚዛኑን እያስጨበጠን እንደሆነ ልብ በሉ።
በአንድ በኩል፤ የትምህርትና የመፅሐፍ ጥቅምን ይነግረናል። ተማሩ፤አንብቡ፤ ነባር እውቀትን ለመገብየት ይበጃችኋል። እውቀትን ለማስፋትና ጥበብን ለመጨመር መነሻ ምክንያት ይሆናችኋል ብሎናል። ይህንም አስቦ፣ መጽሐፍ አዘጋጅቶ አበርክቶልናል።
ደግሞስ፣ የዘርዓ ያዕቆብ ተማሪ እንደነበረ በኩራት የሚተርክልን ሰው፤ ትምህርትን ቢያከብር ምን ይገርማል? መፅሐፍ የሚያዘጋጅልን ፈላስፋ፣ መፅሐፍን ቢያከብር ምን ይደንቃል?
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሰማችሁትን ሁሉ በጭፍን አትቀበሉ፤ የተማራችሁትን ወይ ያነበባችሁትን ነገር በዘፈቀደና በዘልማድ አትመኑ ይለናል።
“ምንም አትመኑ፣ ምንም አትቀበሉ” ማለት ግን አይደለም። ሁሉንም ነገር “እየመረመራችሁ” ይሁን በማለት የእውቀት መንገዱን ያመላክተናል። እውነትንና ሐሰትን ለመለየት መርምሩ፤ እወቁ። ይሄ፣ የእያንዳንዱ ሰው የግል ሃላፊነት ነው።
 ሰው፣ በተፈጥሮው፣ “የማወቅ አቅም” አለው፤ የተፈጥሮ ጸጋ ነው። አቅሙን መጠቀምና አለመጠቀም ግን የእያንዳንዱ ሰው ምርጫ ነው። የተፈጥሮ ፀጋውን በጥረት ለፍሬ ማብቃት፣ የእያንዳንዱ ሰው የግል ሃላፊነት ነው።
የፈላስፋው የጥበብ ሚዛኖች።
በአንድ በኩል፣ ሰው፣ “የማወቅ አቅም” አለው። “አዋቂ” ፍጥረት፣ … “ሊያውቅ የሚችል” ፍጥረት ነው። በተፈጥሮው፣ የአቅም ባለጸጋ ነው።
በሌላ በኩል ግን፣ እውቀት፣ በጥረት የሚገኝ ፍሬ ነው።
ሰው እውነትንና ሐሰትን ለመለየት መመርመር ይችላል። አቅም አለው። ለመመርመር በአግባቡ መጣር ግን፣ የግል ምርጫ፣ የግል ሃላፊነት ነው። እግርና እጅ የተፈጥሮ ፀጋ ናቸው- የመሮጥ አቅምና፣ የመጨበጥ አቅም ናቸው። መሮጥ ወይም ሯጭ መሆን፣ መጨበጥና የእጅ ባለሙያ መሆን ግን፣ በጥረት የሚገኝ፣ የምርጫና የሃላፊነት ጉዳይ ነው።
በአንድ በኩል፣ ሰውን ስማ፣ መፅሐፍ አንብብ፤ ተማር ይላል። በሌላ በኩል፣ ሐሰትና እውነትን እየመረመርክ እንጂ የሰማኸውን፣ ያነበብኸውን፣ ወይም የተማርከውን ሁሉ አትመን ይላል።
ሳይንስና ሃይማኖት፣ ፀሎትና ሃላፊነት ይታረቃሉ?
የግል አቅምንና የግል ሃላፊነትን፣ ተፈጥሯዊ ፀጋንና ጥረትን፣ የእውቀት ዘዴንና ጥንቃቄውን ሲዘረዝር፣… “ሁሉም ነገር በሰው እጅ ነው፤ ሁሉም ነገር በሰው ትከሻ ላይ ነው” የሚል መልዕክት ያስተላልፍልናል።
ግን ደግሞ፣ ለፈጣሪ መፀለይና ፈጣሪን መፍራት እንደሚያስፈልግም ይጠቅሳል። የእውቀት መንገድንና እውነትን እንዲያሳየው ለፈጣሪ ብዙ እንደጸለየ ይገልጻል - ፈላስፋው።
በእርግጥ፣ “ፀሎት” ማለት፣ ለፈላስፋው ለምትኩ፣ ሰፋ ያለ ትርጉም አለው። ጸሎት ማለት፣ ራስን ማዘጋጀት ማለት እንደሆነ ፈላስፋው ገልጿል።
ለማንበብ፣ በቅድሚያ መፅሐፍ ማግኘት ያስፈልጋል- የማንበብ ችሎታም ጭምር ሊኖርህ ይገባል። በዚያው ልክ፣ መፅሀፍን  ማግኘት ብቻ ሳይሆን አእምሮንም ማዘጋጀት ይገባል። የማንበብ ፍላጎትና ጥረት፣ የማንበብ ፍቅርና ልምድ፣ ከምር ከልብ የማንበብ ፅናትና ትኩረት… እነዚህ ሁሉ፣… በገፅታና በደረጃ ቢለያዩም፣ አእምሯዊ ዝግጅቶች ናቸው።
ፈላስፋውም እንዲሁ፣ ለምርምርና ለእውቀት ራሱን አዘጋጅቷል።
“የእውቀትን መንገድ እንዲገልጥልኝ፣ እውነትን እንዲሳየኝ…” በብዙ ፀሎት ጠየቅኩ… ሲል፣ ከምር ከልብ እውነትን ለማየትና በእውቀት መንገድ ለመጓዝ ራሱን እንዳዘጋጀ እየገለፀልን መሆኑን አትዘንጉ።
በፀሎት ጠይቄ አወቅኩ አይልም። የጸለይኩትን ነገር… ከመረመርኩና ካወቅኩት በኋላ እውነት ሆኖ የታየኝን እፅፋለሁ፣… ይላል ፈላስፋው። ፀሎት አእምሯዊ ዝግጅት ነው፣ የቅን ልቦና መንፈስን መላበስ ነው።
ለፈላስፋው ለምትኩ፣ “ፀሎት” ማለት፣ አቋራጭ የእውቀት ማግኛ መንገድ አይደለም። ከጥረትና ከግል ሃላፊነት የሚገላግል የማምለጫ ዘዴ አይደለም- ጸሎት። ይልቅስ፣ ለጥረትና ለምርመራ ከልብ የመዘጋጀት የፅናት ስንቅ ነው - ጸሎት።
ፈጣሪን እና እግዚአብሔርን መፍራት ሲልም፣ ለዘላለማዊ የተፈጥሮ ህግና ስርዓት መገዛት፣ ለእውኑ ተፈጥሮ መታመን ማለት  እንደሆነ ፈላስፋው ያስተምራል። “የተፈጥሮ ህግ” ማለት “ የፈጣሪ ፈቃድ” ማለት እንደሆነ ይጠቅሳል።ለዚያውም እጅግ እየደጋገመ ይነግረናል፡፡
ስለመፅሐፉ ለአንባቢው ሲናገር፣… “እዳልዋሽ በሚከለክለኝ በትልቅ የእግዚአብሔር ፍርሃት እንደጻፍኩት እወቅ” ይላል።
“ለእውነታ የመታመን ንፁህ መርህ ውሸትን ይከለክላል። ለእውነታ መታመን፣ ቀዳሚው የሥነ-ምግባር መርህ ነው፤ ትልቅም ሃላፊነት ነው” በሚል ትርጉሙ ልንገነዘበው እንችላለን።
“ፀሎትና ፈሪሃ እግዚአብሔር” ሲል፣ “ከልብ እና በእውነተኛ መርህ” ለእውቀት መጓጓትና መትጋት እንደ ማለት ነው፡፡ “በቅን ልቦናዬ የመረመርኩትን እፅፋለሁ” በማለትም ፈላስፋው ፍላጎቱንና ጥረቱን፣ የልቦና ዝግጁነቱንና የቅንነት መርሁን ይገልጽልናል።
ከዚህ ውጭ፣ “ሰውን አልፈራም።… ከንቱ ሐሰትን የሚያስተምሩና ከሚጽፉ ጋር፣ በማናቸውም ስራ አልተባበርም” ላይ ፈላስፋው ምትኩ።
ራስህ ሳትመረምር፤ እውነቱንም ከሐሰት ሳትለይ፣ ሰዎች የሚያስተምሩህን ምንም ነገር አትመን። ሰዎች ሊዋሹ ይችላሉና፤ ካልመረመርክ፣ እውነት ወይም ሐሰት ቢያስተምሩህ አታውቅም። እንደዚሁም ሁሉ፣ ካልመረመርካቸውና እውነት ሆነው ካላገኘሃቸው በስተቀር፣ በመጽሐፍት የተጻፉትንም ነገሮች አትመን። መፅሐፍትም በሐሰተኞች፣ ይጻፋሉና።…
ነገር ግን፣ ሊዋሹ ይችላሉ አልኩህ እንጂ፣ ሁሉም ሰዎችና ሁሉም መፅሐፍት፣ ዘወትር ይዋሻሉ አልልህም። ይህንም የምልህ፣ እንድትመረምር ነው። እውነት ወይም ሐሰት የሆነውን ነገር፣ ሳትመረምር ልታውቅ አይቻህም።
በመሆኑም፣ ሰዎች የሚያስተምሩትን የጻፉትንም መፅሐፍት ሁሉ ልንመረምራቸው ይገባል። ከእነርሱ ውስጥም እውነትን ስናገኛት በደስታ እንቀበላት። ሐሰትን ግን እንተዋት። ያለ ምህረት እናባራት። ይላል ጠቢቡ መምህር
በጭፍን ማፅደቅ፤ በጭፍን መቃረን
የወልደ ህይወት ትንታኔ፣ ጠንካራም ጠንቃቃም ነው።
መመርመር፣ ግዴታ ነው። በጭፍን ምንም አትመን ይላል- በፅናት።
 ነገር ግን፤ በጭፍን ላለመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በጭፍን ላለመቃረንም ነው።
ሐሰትን ለማባረር ብቻ ሳይሆን፣ እውነትን በደስታ ለመቀበል ነው። በጭፍን ላለማጽደቅ፤ በጭፍን ላለማፈንገጥ። ጠንካራና ጠንቃቃ አስተሳሰብ እንደዚህ ነው።
የሚዋሹ ሰዎች መኖራቸውን ይገልጻል። ግን ደግሞ ሁሉም ሰው ይዋሻል ማለት እንዳልሆነ ጠቅሳል።
የሚዋሹ ሰዎችም፣ ዘወትር ይዋሻሉ ማለት አይደለም በማለት፣ ወደ ጅምላ ፍረጃውና ወደ ድፍን ድምዳሜ እንዳንወርድ ያስጠነቅቀናል።
ለእውነት የፀና ነው፤ ግን ለውግዛት አልቸኩልም። የስነምግባር መርህና የነፃነት ሚዛን።
እውቀትን በደስታ እንቀበል፣ ሀሰትን ግን እንተዋት፤ ያለምህረትም ከኛ እናባርራት በማለት፤ ፅኑና ጥንቁቅ አስተሳሰቡን አሳይቶናል። ለእውነት የፀና ነው፤ ግን ለውግዘት አልቸኩልም። ለምን በሉ።
አንደኛ ነገር፣ እውነት ያልሆነ መረጃና ትምህርት፣ ከስህተት ወይም ከተንኮል ሊመጣ እንደሚችል ፈላስፋው አስተምሯል። ሳያውቁ ይሳሳታሉ አንዳንድ ሰዎች። ሌሎች ሰዎች ግን፣ ሆን ብለው ይዋሻሉ- ለሸፍጥ ለተንኮል። ሁሉም አይነት ስህተት እኩል አይደለም። እኩል ማውገዝ የለብንም።
ሁለተኛ ነገር፣ ማወቅ፣ ከሁሉም በፊት ለራስ ነው እንጂ፣ የሌሎችን ስህተት ለማውገዝ አይደለም።
 ሦስተኛ ነገር፣ በድፍን ውግዘት ወይም በጉልበት፣ ሰዎችን ከስህተትና ከውሸት ማላቀቅ እንደማይቻል ጠቢቡ ያስተምራል።
እውቀትና ትምህርት የጉልበት ሳይሆን የምርጫ ጉዳይ ነው።
መመርመርና ማወቅ፣ ቀዳሚና ፅኑ የስነ-ምግባር መርህ ነው።
 ነገር ግን በግል ምርጫና በነፃነት ነው፤ ስነ-ምግባር የሚከበረው።
 ታታሪነት የስነ-ምግባር መርህ ነው።
ነገር ግን ታታሪ ሁን የሚል ህግ ማወጅ፣ ነፃነትን ይንዳል። የስነ-ምግባር ስረ-መሰረትን ያፈርሳል።
ታታሪ እንዳይሆን አትከልክል፤ ሁከት አትፍጠር። የሚል ህግ ነው ትክክለኛው ህግ።
“የድካምህን ፍሬ ተመገብ” - የስራ፣ የጥበብና የደስታ ሚዛን።
“የድካምህን ፍሬ ተመገብ” የሚለው መርህ፤ የፈጣሪ ፈቃድ ወይም የተፈጥሮ  ህግ እንደሆነ ወልደ ህይወት ይገልፃል።
ሦስት ነገሮችን ያዋሃደ መርህ ነው።
አንደኛው፣  የስራ ፋይዳና ክብር ነው። ለሰው የሕልውና  ዋስትና ስራ ነው። ለሰው ክብር የሚመጥን ትልቅ የግል ሃላፊነትም ነው- ስራ። አለበለዚያ፤ የሰው ሰውነቱ የሰው ፍጥረቱ ይጠፋል፤ ኑሮው ሁሉ  ይፈርሳል ይላል- ፈላስፋው።
ታዲያ፣ “ጥረትና ድካም” ማለት፣ በዘፈቀደ ማጣጣር፣ በደመነፍስ መልፋት መባተል አይደለም። ልብ እንደሌለው እንስሳ አትድከም። ነገር ግን ጥረትህ፣ ጥቅም የሚያፈራ፣ ትርፍ የሚያመጣ መሆን አለበት።  እንደ ልበቢስ እንስሳ ሳይሆን፣ ለሰው ተፈጥሮ በሚመጥን ጥበብ ስራህን አከናውን ይላል - ጠቢቡ ወልደሕይወት። በልጅነትህ የእጀ ሙያ  ልመድ ሲልም ይመክራል።
ሁለተኛው ቁም ነገር ይሄ ነው። ስራህ በአላማ፣ ጥረትህ በጥበብ ይሁን። ጥረትህ ለጥፋት ሳይሆን ለልማት ነው- ለኪሳራ ሳይሆን ለስኬት። እና ደግሞ በትክክለኛ መንገድና በሙያ ብቃት ስራ፤ ትጋ።
ሥስተኛው ነጥብ፤… “ተመገብ” ከሚለው ቃል ጋር የተዛመደ ነው። የተፈጥሮ ስርዓትን ተገንዝበሃል። መስራት ከሰው ተፈጥሮ የሚመነጭ መርህ መሆኑን አውቀሃል፡፡ የግል ሃላፊነት ወስደህ ለጥረት ተነስተሃል። በጥበብ ተግተሃል። ይህ ሁሉ ለከንቱ አይደለም።  ፋይዳው ፍሬያማነትህ ላይ ነው። የፍሬያማነትህ ፋይዳ ደግሞ፣ ሕይወትን ማለምለሙ ነው። ሌላው ሁሉ ከዚህ የሚመነጭ ነው፡፡ ፍቅርና ቤተሰብ፣ ሽርክናና ግብይት፣ መተባበርና መደጋገፍ፣ ሌሎች መልካም ነገሮች ሁሉ የሚመጡት በዚህ መንገድ ነው።
እና፣ የስራ ፍሬህን ማጣጣም፣ ሕይወትህን ማለምለም፣…. የፈጥሯዊው መርህ ሦስተኛው ገጽታ ነው።
ከቤተሰብህ ጋር በደስታ ብላ፤ ጠጣ።
 የደስታና የድሎት በዓልም አድርግ በማለት ጽፏል - ወልደ ሕይወት።
ነገር ግን፣ “ከልክ አትለፍ። መጠንን ማለፍ ጤናን ያሳጣል፤ ደስታን ያጠፋል።” በማለት የስካርን መጥፎነት እንደ ምሳሌ ጠቅሶ ያስተምራል።
ሁሉም በልኩ ይሁን፡፡ ግን በቃኝ አትበል፡፡
“የበዓል ድግስ፣ በልኩ ይሁን” ሲባል፤  ሃብት በከንቱ አታባክን፤ አትስከር ማለት ብቻ አይደለም። “የስራ ሃላፊነትህና የጥበብ ጥረትህን አትዘንጋ” ለማለትም ነው። በፍሬ ላይ ፍሬ፣ በጥቅም ላይ ጥቅም እንዲጨምርልህ በስራህ ላይ ጠንክረህ ትጋ። ለኑሮዬ ጥቂት ይበቃኛል፤ ለምን እደክማለሁ” አትበል። ይህ ክፉ ነገር የስንፍና ነውና። ይላል- ጥበበኛው።
ትምህርትን ለመማር አትስነፍ። በህይወት ዘመን ሁሉ አትተዋት። “የሚያበቃንን ብዙ ትምህርት ተምሬያለሁ” አቶ አትበል። የሰዎችን ትምህርት ሁሉ ብትማር እንኳ፤ ገና የማታውቀው ይበዛል።
ንብ፣… በአንድ ቦታ፣ በአንድ አበባ ብቻ፣ የሚበቃኝን አግኝቻለሁ ብሎ አይኖርም። በንብትጋት፤ ማርና ሰም ይበረክታል። ጣፋጭ ምግብም የጧፍ ብርሃንም ይበዛል።
አንተም በትምህርት ብትተጋ ጥበብን ታካብታለህ፤ ሁለት ነገሮችንም ታገኛለህ። ጨለማን የሚያበራ እውቀት፤ ኑሮን የሚያጣፍጥ መልካም ምግባር።
የፅናት፣መርህ፣የመርህ፣የመልካም ማንነት ምክሮች፡፡
የድካምህ ፍሬ በጠፋና በፈረሰ ጊዜ፤ ልብህ ተስፋ አይቁረጥ። ነገር ግን በስራ ጸንተህ… የላብህን ፍሬ እንዲያበዛው…” ትጋ በማለት ይመክራል።
ከሰው ሁሉ ጋር፣ ከሃብታሙም ከድሃውም ጋር፣ ከትልቅና ከትንሹ ጋር ሁሉ ያለአድልዎ ትክክለኛ ሁን። በትክክል ፍረድ፤ የሰውን ፊት አትፍራ።
“ዛሬን እደሰታለሁ፤ ፍቃዴንም ሁሉ ፈጽሜያለሁና የሚመጣው ይምጣ” ከቶ አትበል።
መልካም ስራን ስራ። እሱ ይቆጥረዋል። ይሰፍረዋል፤ መዝግቦም ያኖረዋል። አንተ የሰራኸውን መልካም ስራ ትረሳለህ። እሱ ግን፤ ለዘላለም አይረሳውም።
ሦስቱ ክፍቶች፡፡
- ከእውነት የተጣላ ሀሳብ የለሽ ንግግር (ውሸትና ስድብ፤ ሃሜት- ክፋት)
- ከስራ የተፋታ ፍሬ አልባ እጅ (ስርቆትና ዝርፊያ፣ ሸፍጥና ጥፋት)
- ከፍቅር የሸፈተ ክብረ ቢስ ስሜት ( አስመሳይ፣ ምቀኛ፣ ሸንጋይ፣ አመለኛ ዝሙት)


Read 8041 times