Tuesday, 07 December 2021 05:15

አሜሪካኖቹ በወሳኝ ሰዓት ለምን ይክዱናል?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ክፍል ፩
የኢትዮ-አሜሪካ ወዳጅነት ከ፻(መቶ) ዓመታት የዘለለና ዘለግ ያለ የንግድና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካላቸው ሀገራት ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ከዐድዋ ድል ማግስት በ፲፰፻፺፮ ዓ.ም ገደማ በንግድ ትሥሥር ተጀምሮ እስከ አብሮ መዝመት የደረሰውና “የልብ” የሚባል ወዳጅነት ላይ የተመሠረተው የሁለቱ ሀገራት ዝምድና መከዳትም (አንድ ወገን) የተጠናወተው ነው፡፡ ቅርርቡ ጎልብቶ ጫፍ ደርሶ ነበር በሚባልበት በንጉሱ ዘመን’ኳ “ሸርተት፣ ሸርተቱ” አልቀረም፡፡
በእኔ ምልከታ አሜሪካኖቹ (መንግስታቸው ሊባል ይችላል) እኛ   ብናምናቸውም እነሱ ግን የልብ
እንዳልሆኑ ያስመሰከሩበት ብዬ የማስባቸውን ልጥቀስ (የራሳችን ዲፕሎማሲያዊ ድክመትም ሳይረሳ ነው
ታዲያ)፡፡ ሃሳቤ ክዳቶቹን ጠቅሼ፣ ለምን? የሚለውን መልስ መፈለግ ነው፡፡ ከዚያስ? የሚለውን
በትንሹ እንጀምረውና ትውልድ ይሞላዋል ግዴለም፡፡
በቅድሚያ ግን ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋምና፣ በሳትኩ ለማረም ባጎደልኩ ለመሙላት የታመንሁ ነኝ፡፡
ክዳት_፩፡- ጀኔቫ ላይ
የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት “ንፋስም አይገባበት” በሚባልበትና ኢትዮጵያም በወዳጇ ጋባዥነት በቃኘው ሻለቃ አማካኝነት ኮሪያ ድረስ ዘምታ አመርቂ ድል አስመዝግባ ተመልሳለች፡፡ ከዚያ ትንሽ ቀደም ብሎ ታዲያ ፋሽስት ጣሊያን ለ ፵(አርባ ዓመታት) የተዘጋጀችበትን የበቀል በትር ኢትዮጵያ ላይ ለማሳረፍ የመርዝ ጋዝና ዘመናዊ መሣሪያዋን ሰድራ ስትመጣ “አቤት” ለማለት ጄኔቫ የተገኙት ንጉሱ፣ ጆሮ እንኳን የሚያውሳቸው ጠፍቶ ተራግመውና እንደ ሣራ እንባቸውን ወደ ላይ ረጭተው ሲወጡ፣ አሜሪካኖቹ እንዳሁኑም ባይሆን ከነተሻለ ተጽዕኗቸው እዚያው አዳራሽ ውስጥ ቁልጭ ቁልጭ ይሉ ነበር፡፡
ሊረዱን ግን አልፈቀዱም፡፡ ነሐሴ 18፣ 1935 እ.ኤ.አ ጌታው ሩዝቬልትና የውጭ ጉዳይ ከዋኛቸው
ሁል /C.Hull/ የግብር ይውጣ ዓይነት “ተው ወደ ተኩስ አትግቡ፣ ባይሆን ጥላችሁን በንግግር ፍቱ” የምትል የተለመደች ጥርስ አልባ መልዕክት ወደ ሞሶሎኒ አቻቸው ላኩ፡፡ ቤኒቶ ሞሶሎኒም የምር እንዳልሆነ በሚያሳብቅ መልኩ ጉራም አክሎ፤ “ሚሊዮኖችን አንቀሳቅሰናል፣ ፪(ሁለት) ቢሊዮን ሊሬም ያፈሰስኩበት የሞት (በኋላ የውርደት ሆኗል) ድግስ ልታስቀር አይቻልህም” ዓይነት መልስ ሰጠ፡፡ በቃ!.... የሆነብን ሁሉ ሆነብን፡፡ እድሜ ለአርበኞቻችን፣ ለንጉሱ በሳል ዲፕሎማሲ፣ ለንግስት ኤልዛቤጥ ፪ኛ (በአጠቃላይ እንግሊዞች በተለይ ለእነ ጀ/ል ዊንጌትና ኮ/ል ፒንክ...)፣ እንዲሁም ለዘመኑ የቅርምት Ego ይሁንና ነጻ ወጣን፡፡ አሜሪካኖቹ እየቻሉ ስላልረዱን (እንዲያውም ገሸሽ ስላደረጉን)ከክዳት ቆጥሬባቸዋለሁ፡፡ አንድ በሉ…
    ክዳት_፪፡-
የታኅሳሱ_ግርግር_መነሾ
“የታኅሳሱ ግርግር” (ታኅሳስ ፬-፯/፲፱፻፶፫ ዓ.ም) የሚባለው ብዙ ጊዜ በተራማጅነት የሚሞካሹት ወንድም
አማቾቹ ገርማሜና መንግስቱ ንዋይ ለውጥ ፈላጊነት የመጣና የተፈጠረ ብቻ ተደርጎ ነው፡፡ ለእኔ ግን “በኋላ” የገባኝ፣ የ“ግርርግሩ” ዐቢይ ምክንያት ድኅነታቸው እንዳስጠቃቸው ገብቷቸው ያንን ለመለወጥ ከነበረ ፍላጎት ብድርና ሥጦታ ቢያማትሩ ያጡት ንጉሱ፣ ለእርሻ ሥራ ግብዓት መግዣ ብለው ከአባት ሀገር ሶቭዬት ኅብረት ያገኙት ፬፻ (አራት መቶ) ሚሊዮን ሩብልስ ነው ባይ ነኝ፡፡ በዚያን ወቅት በዓባይ ወንዝ ላይ ፬ ፕሮጀክቶች (የአሁኑ ሕዳሴ ግድብ ያለበትን ጨምሮ) እና ሌሎች የሚያስጎመዡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተነድፈውና የ፭ ዓመት መሪ እቅድ ተነድፎ፣ ኢትዮጵያን የ“እህል ጎተራ” የማድረግ ውጥን ለማሳካት የሚፍጨረጨሩበትና ይሄው ሕልምም የጨነገፈበት ወቅት ነው፡፡ ዋናዋ የቲያትሩ ጸሐፊ ደግሞ ይችው በወሳኝ ጊዜ የምትከዳው “ወዳጅ” ናት፡፡ ምን ዋጋ አለው “ግርግሩ”ም ግቡን ሳይመታ በነ በጋው መብረቅ ጃገማ ኬሎ ቢከሽፍም፣ ምን ምን የመሰሉ ለሀገር አሳቢ ሊቆችን (እነ ራስ አበበ አረጋይ…) እና ጦር ጠበብቶችን (እነ ጀነራል ሙሉጌታ ቡሊ…) ቀጥፎ ንጉሱንም ከተራማጅ አስተሳሰባቸው ተጠራጣሪና
ወደ ተንኮል ያደላ አድራጎት እንዲጠናወታቸው አድርጎ አለፈ፡፡ በማን መዘዝ? በዚችው አሜሪካ፣ ለምን?
ከሩሲያ አምጥታችሁ/ትለማላችሁ በሚል! ሆ ሆ...
    ክዳት_፫፡-
ባዕዱ የኤርትራ ፌዴሬሽን
እነ አይደክሜው ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድና ኤርትራን ከእናት ሀገሯ መቀላቀልን አጥብቀው
የሚሹት ኤርትራውያኑ የአንድነት አቀንቃኖች እነ ቢተወደድ አስፍሓ እና ተድላ ባይሩ ከበቂ በላይ የሰውና
ሰነድ ማስረጃ ቢያቀርቡም ሲንሻፈፍ ሲንሻፈፍ ኖሮ አሜሪካኖቹ (ከአራቱ ኃያላን አንዱና ዋናው ነበሩ)
በቀረበው ማስረጃ ላይ የነበረንን ወዳጅነት ተጠቅመው በቀላሉ ማለቅና የተሻለ ውሳኔ ማግኘት የሚችለውን እሰጥ_አገባ፣ እጅግ ውስብስብ የሆነና በወቅቱ ለትግበራ አዳጋች የሆነ “ፌዴሬሽን” ጽንሰ ሀሳብ ወለዱና “ተግብሩት” አሉ፡፡ ንጉሱም የሆነው ነገር ቢያበሳጫቸውና ለመረዳትም ትንሽ ቢጸንናቸውም፣ ወዳጅ ናቸውና ክፉ አያስቡም፣ “ለእኛው ብለው ነው” በሚል ስሜት (ከዚህ ውጭ ምንስ ማድረግ ይችሉ ነበር በውነቱ) እየጎረበጣቸው ተቀበሉት፡፡ ችኮላም ታክሎበት ቢሆን መዘዙ አልቀረልንም፡፡ የኋላው ዐብዮተኛ ትውልድ ስህተት በአናቱ ታክሎበት፣ ከአንድ ሀገርነት ወደ ባላንጣ ጎረቤት፣ ከዚያም ወደ አስከፊ መተላለቅ የደረሰ መዘዝ አመጣ፡፡ ምን ይሄ ብቻ ሀገሬንም Landlocked (መቶ አሥር ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ወደብ አልባ ብቸኛ ሀገር) አድርጎ አለፈ፡፡ በተከፈለ ልብ ነው እንዴ የልብ ወዳጅ የሆኑን? እላለሁ፡፡ እስቲ እንቀጥል፡፡
ክዳት_፬፡- ቀፍሎ መካድ በዘውርዋራው ዚያድ ባሬን መደገፍ
በጓድ መንግስቱ ዘመን በእርግጥ በመስመር ተለያይተው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጥል አልፎ አንዱ
በአንዱ ላይ የሚያሴርበት መሆኑ እሙን ቢሆንም፣ የልዕለ ኃያልነቱን መንበር እየተቆናጠጠች ለመጣች ሀገር ያውም ደግሞ በውለታ ጭምር የታሠረ መልካም ግንኙነት ላላቸው ሁለቱ ሀገሮች በጭንቅ_ጊዜ መክዳትን የሚያስብ ካለ እሱ ጠንቋይ መሆን አለበት፡፡ ግን እንዲህ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የጦር መሣሪያ ለመግዛት ተዋውላ አልፎ ተርፎም ተበድራ ተለቅታ ብር ከፍላለች፤ በንጉሱ ዘመን የሆነ ነው፤ በውልም የታሰረ ነበር፣ ነበር! ወዲህ የእነ ተፈሪ በንቲ መገደል ወዲህ በኢራቅና ሦሪያ በገፍ የሚደገፉት የኤርትራ ተገንጣዮች ግራ ቀኝ እያጣደፉት ያለው የኮሎኔል መንግስቱ አስተዳደር፣ ድንገት ዚያድ ባሬ ከታላቋ_ሶማሊያ ፉከራና ቀረርቶ ወደ ማጥቃት ተራምዶና ግስጋሴውን አፋጥኖ ወደ አዋሽ ገሰገሰ፡፡ ይኸኔ እነ ኃይሌ ፊዳ፣ ሰናይ ልኬና ኮሎኔል ፍሰሓ ደስታ ሀገር ላገር ዞረው ሰባራ መሣሪያ እንኳን የሚሰጥ/የሚሸጥ ባጡበት ሰዓት ጭራሽ ረብጣ ዶላር (፻ ሚሊዮን የኢት. ብር) የተከለፈለበትን የመሣሪያ ግዢ አሜሪካ  ካደች፡፡ ጭራሽ የካርተር አስተዳደር ሰበባ ሰበብ ፈልጎ ከሐምሌ 1969 ዓ.ም ጀምሮ የመሣሪያ ግዥ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ ጣለ፡፡
በሌላ አባባል ይህን እርምጃ በግሌ በሶሻሊስትነቱ የሚመጻደቀውን ዚያድ ባሬን የመደገፍ አድርጌ
እቆጥረዋለሁ፡፡ እድሜ ጥይት ለማያባክኑትና በአንድ ጥይት ሦስት አራቱን ጀሌ በሚያጋድሙት ዓላሚዎቹ
አሊ_በርኬና...ሌሎች፣ እንደ አሞራ ክንፋቸው የሚቀላቸው ሚግና F5 አብራሪዎቹ ኮ/ል በዛብህ፣ ኮ/ል
መንግስቱ ካሳዬ፣ ጀ/ል ለገሰ ተፈራ እና ሌሎች ጀግኖች፣ የክፉ ቀኖቻችን ኩባና ሶቪዬት ተዋጊዎች ይሁንና
እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ዚያድ ባሬን አስተነፈሱት፡፡ ይሄው ድሬዳዋና ኦጋዴንም የእኛው ሆኖ፣ ቀና
እንዳልን አለን፡፡ የአሜሪካኖቹ ሥር የሰደደ የክህደት ጥግ ግን ከፍ እያለ እንጂ ዝቅ አላለም፡፡ “ወይ
አሜሪካ…!” አለ ሸምሱ፤ ይሄን አስተውሎ ይሆን ክበበው ሲጽፍ? እንጃ!
ክዳት_፭፡- በጠነዛ አበባ ላይ አካሉ በእሾክ የተተበተበ ትሕነግን እንደ_ሥጦታ
… ( ይህንና የካርተርና የኦባማ ሽምጠጣ፣ የትራምፕ ቦምብ፣ ከአጎዋ መሰረዝ በክፍል ፪ እንመለስበት)
ለክፍል ፩ ማሳረጊያ ግን ይችን መውጫ ልጨምር፡-
“የአሜሪካን ወዳጅ መሆን ለም አፈር ካለው ትልቅ የወንዝ ዳርቻ ከመኖር ጋር ይመሳሰላል፡፡ ነገር ግን በየ፬
ና ፭ ዓመቱ ወንዙ አቅጣጫውን ሲለውጥ ብቻህን ምድረ በዳ ላይ ትቀራለህ፡፡”
(አንድ የአፍጋኒስታን ባለስልጣን ያለውን ጠቅሶ ኮ/ል ፍስሓ ደስታ እንደጻፈው፡፡)

    ክፍል_፪
    በክፍል_፩ የልብ ወዳጃችን ያደረሰችብንን አራት ወሳኝ_ክዳቶች ተመልክተናል፡፡ በክፍል_፪ ደግሞ ቀሪዎቹን
፬ ወሳኝ ክዳቶች እናያለን፡፡
ክዳት_፭፡- በጠነዛ_አበባ_ላይ_አካሉ_በእሾክ_የተተበተበ_ትሕነግን_እንደ_ሥጦታ
ከኮሎኔል መንግስቱ ጋር በአንድ በኩል በብልጠት መያዝ ይችል የነበረ የጎራ ልዩነት አለፍ ሲልም የፈረጠመን ክንድ ፍርኃት ታክሎበት ወደ መሠሪነት ያደላውና የኋላ ኋላ በ”የጠላቴ ጠላት” የሚታወቁት አሜሪካኖቹ፣ ከዚያድ ባሬ መተንፈስ በኋላ ሲያስሱ ሲያስሱ “ትሕነግ” የተባለ መርዘኛ ድርጅት አገኙ፤ ወደዱትም፤ ረዱትም፤ ኧረ ተሸከሙትም ማለት ይቀላል፡፡ አንዴ በእርቅ ሰበብ፣ ሌላ ጊዜ በእርዳታ፣… ብቻ ኳትነው ኳትነው የሥርዓቱ (ደርግ) የራሱም ሰው በላነት (የራሱን ምርጥ ጀነራሎች ጨምሮ)፣ የምሥራቁ ጎራ መንኮታኮትና ሌሎችም ችግሮችና ምክንያቶች ታክሎበት ምኒልክ ቤተ መንግስትን አስከድተው ለአዲሱ ወሮ በላ ቡድን አረካከቡ፡፡ እዚህ ላይ ግን እነ ሓየሎም አርዓያን የመሰሉ ሞትን ፊት ለፊት እየገጠሙ ደጋግመው ያሸነፉ፣ የተጋጠሚያቸውን ስስ ብልት እያዩ የሚመቱ፣ ተዋጊዎቻቸውን ለዓላማ እንጂ ለጥቃቅኑና ርካሹ ጉዳይ እንዳይታለል በሥነምግባርም በሳይንስም የሚያንጹ ድንቅ ድንቅ የተፈጥሮ ጦር ጠበብቶች ብቃት ሳይረሳ ነው፡፡
አንድ በደንብ መነሳት ያለበት ጉዳይ ያኔ (፸ዎቹ መጨረሻና ፹ዎቹ መጀመሪያ) USSR’ዊነትና የምሥራቁ ጎራ እየተናደ (በተለይ ሶቪዬት ከፈራረሰች በኋላ) ምዕራቡ ኮረብታ እያበጠ በመጣበት ወቅት ኢትዮጵያን
የምታህል የ”ልብ” ወዳጅ ሀገር ታሳቢ በማድረግ፣ የመንግስቱን አስተዳደር በተለያዩ ማማለያዎችም ቢሆን
በመያዝ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ወይስ እሱን አግባብቶ ወደ ዚምባቡዬ ሸኝቶ፣ ትሕነግን መትከል
ይቀል/ይሻል ነበር? የሚለውን ጥያቄ መላልሶ መጠየቅና መልስ ማግኘት ይፈልጋል፡፡ እዚች ጋ ሁለት ነገሮችን ማንሳት ለወቀሳም ለክርክርም ሳይረዳ አይቀርም፡፡ በጎራ ከሆነ እድሜ ለተገለባባጭና ፖለቲካዊ ዘማ ጠባይዋ ይሁንና ትሕነግም ቅልጥ ያለች ምሥራቃዊ ነበረች፡፡ እንዲያውም “ማን ነው የበለጠ ሶሻሊስት፣ መለስ እኮ የአልባኒያው የመጨረሻው ደረጃ ሶሻሊዝም የገባው ነው” እየተባለ ይሞካሽ ነበር፣ ከነሚያቦኑት ሲጋራ ጭምርም ነው የወረሱት ያውም፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ትሕነግ ዴሞክራሲን ያሰፍናል እንዳይባል እርዳታን እንደ ጦር መሣሪያ የመጠቀም የካበተ ልምድና ምርጥ ምርጥ ጓዶቹንና አጋር ኃይሎችን (ኦነግን ያስታውሷል) ጭምር በድቅድቅ ጭለማ የምትቀረጥፍ ጉደኛ ድርጅት ናት፡፡ በነገራችን ላይ መቸም ሁሉም የእጁን ሲያገኝ ጥሩ ነው፡፡ የኋላ ኋላ የትሕነግ ነጭ አባት ኸርማን ኮኸንም “እንዲህ እንደሚሆኑ ብናውቅ ኖሮ መጀመሪያውኑም ባልረዳናቸው/ባላመጣናቸው” ብሎ በመፍጠሩ እስኪጸጸት አባት አሜሪካን አንገብግበዋታል፡፡ በእውቀትና ንባብ የማይታሙት አልፎ ተርፎም The Prince የተሰኘው የማኪያቪሊ መጽሐፍ የአመራር መጽሐፍ ቅዱሳቸው ነው የሚባሉት አቶ መለስ በእንግሊዝኛ “እሺ፣ በጄ” እያሉ በአማርኛ ይዘልፏቸው/ይንቋቸው አልፎ አልፎ እንዲያውም እንደ ፉከራም ይዳዳቸው ነበር፡፡ አቶ መለስ ግን በእኔ አተያይ አሜሪካንቹን (ምዕራቡን እንደአጠቃላይ) በፍቅር “ወጥሮ” የሚይዙበት አንድ ልዩ መስተፋቅር ነበራቸው፡፡ ጉልበት! የራሳቸው ቡድን /ፓርቲ/ ላይ፣ ሀገሬው ላይ፣ ምሥራቅ አፍሪቃ ላይ፣ አለፍ ሲልም አፍሪቃ ላይ፡፡ ሌላው ግን ሳይጠቀስ የማይታለፈው የመጣን አጀንዳ በተፈጥሯዊ ጉብዝናው አፈፍ አድርጎ ከፍ ላለና ለራስ ጥቅም የማዋል ብቃት ነው፡፡ የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ በመላ አፍሪካ አከባበር፣ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ክርክር፣ የካርበን ልቀት/አረንጓዴ ኢኮኖሚ/ ጥብቅና፣ የምዕተ ዓመቱ ልማት ግብ/MDG/ እና በቀላሉ የሚታዩ ተግባራት/አስፋልትና የትምህርት ቤት መስፋፋት/ የመሳሰሉትን በማሳየትና በማማለል፣ ከዚህ ቀደም የተጣባቸውን ልክፍት በመቀስቀስ ጭምር “እንዲያውም አፍሪካ ልማት(ዳቦ ጥያቄ) እንጂ ዴሞክራሲ ምን ሲያደርግላት!” ወደሚል ከባድ ድምዳሜ እንዲደርሱና ዐይናቸው እንዲታወር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን ግን ከላይ የተጠቀሱትና ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በ፺፯ ዓ.ም ለምርጫው ያሳዩት ተነሳሽነት ውለታቸው አለብን ብዬም በጽኑ አምናለሁ፡፡ ይሄ ነገር ባህር ነው፡፡ ለጊዜው እዚህ ላይ እንግታውና ወደቀደመ ነገራችን እንመለስ፡፡ ከመደምደሜ በፊት ግን ከዚህ ቀጥሎ በማቀርባቸው ኹለት ተጨማሪ ሀሳቦች የ”ልብ” ወዳጃችንን ሁኔታ ገምግመን ግለ ሂሷን እንድታወርድ እናደርጋለን፡፡
ክዳት_፮፡- የካርተርና_የኦባማ_ሽምጠጣ
የቀድሞው አሜሪካ ፕሬዝዳንት፣ ጂሚ ካርተር፣ በእርጅ ዘመናቸው የካርተር ማእከልን አቋቁመው ምርጫን ይታዘባሉ፡፡ የእኛንም የ፺፯ ዓ.ም ምርጫ ታዝበዋል፡፡ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር እንደ ትልቅ ምዕራፍ የሚቆጠረው ምርጫ ቀድሞ እንደተከፈተው ወለል ያለ በር አልዘልቅ ብሎ የኋላ ኋላ መጠፋፊያ ሆኖ አረፈው፡፡ አዛውንቱም ያዩትን ሁሉ ዐይተው የደረሰውንና የሆነውን በወረቀት ላይ ለግብር ይውጣ ከትበው ሲያበቁ ተጽዕኗቸውን ተጠቅመው፣ ለመንግስታቸው አስረድተው፣ ይህን መርዘኛና በካርዳችን የቀጣነውን ድርጅት ይገላግሉናል ስንል “ምርጫው መሥፈርቱን ባያሟላም ችግራችሁን በጠረጴዛ ዙሪያ ፍቱ” ዓይነት የተድበሰበሰ ምክር አዘል ቁንጠጣ አክለው፣ ወደሞቀ ሀገራቸው ገቡ፡፡ እኛም በልብ ወዳጃችን እንዳዘንን ቀጠልን፡፡ ለንጽጽር እንዲመች ከአውሮፓ “ኅብረት” ምርጫ ታዛቢ ቡድን የተወከሉትና ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለመረዳት አፍታም ታክል ያልወሰደባቸው አና ጎሜዝ፣ የጠ.ሚ መለስን አስተዳደር እንዴት እንዳብጠለጠለችው ማስታወስ በቂ ይመስለኛል፡፡ አይ ግዴለም ካረጁ አይበጁ ነው፣ ምን አልባት እድሜ ተጫጭኗቸው ነው ብለን በደላችንን ሳንረሳ ቀጠልን፡፡ በአምባሳደሯ በኩል ለማሸማገልና የሞተን ማስነሳት ጥረትም በአናቱ ጨምሩበት፡፡
የኋላ ኋላ በምላሱ ጤፍ የሚቆላውና በንግግር ክህሎቱ የሚታወቀው፣ የእሱን ወደፊት መምጣት አብዝተን
ተስፋ ስናደርገው የነበረው ወጣቱና እዚህ ጎረቤታችን ኬንያ ዘር ሀረግ የሚመዘው ባ.ሁ.ኦባማ በብዙ
አማላጅነት ኢትዮጵያ መጣ፡፡ ቻይና በችሮታ ባሠራችው አዲሱ አፍሪካ ኅብረት ሕንጻ መድረክም ላይ ጊዜ
ተሰጥቶት ያንን የሚያማልል ንግግሩን አስተጋባ፡፡ “ቻይና ባልተገባ ሁኔታ ከአፍሪካ ጥቅም እያጋበሰች ነው፤
በብድር ሰበብ አህጉሩን ቅኝ ተገዥ ልታደርገው ነው” አለ፡፡ አፍሪካውያን መሪዎችን ደግሞ የራሱን ለሦስተኛ ዙር ሰልሦ ያለመመረጥ የሕግ ገደብ ጠቅሶ፤ “ዙፋናችሁን ከሕግ በላይ አታድርጉ፣ ከወጣችሁ በኋላ ለምን መውረድ ያቅታችኋል?” ዓይነት አሽሙር ሸነቆጣቸው፡፡ በሙት መንፈስ ይመራል የሚባለውንና በጨካኞቹ አጋዚ ኮማንዶና ፌደራል ፖሊሶቹ አማካኝነት ሰዎችን ደመ ከልብ እያደረገ ያለውንና መጨረሻው ያላማረውን የኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት፣ “ተግሳጽ ብጤ ሊሰጡት” ነው ስንል ጭራሽ ወደ ኤርትራ በረኻዎች አንጋጠው “በዴሞክራሲ የተመረጠን መንግስት ለመጣል የሚደረግን የትኛውንም ትግል አንደግፍም/እናወግዛለን” ብለው ቡናቸውን ጠጥተው፣ የ”ልብ”ነታቸውንም አስመስክረው፣ የሶማሊያ ዘመቻን “ዋ ትወጡና” ዓይነት ማስፈራሪያ አስተላልፈውና እሳት ላይ ጥደውን ወደ ሞቀ ቤታቸው ሽው አሉ፡፡
ለንጽጽር እንዲረዳ ጌታው ኦባማ ከእኛ ቀደም ብለው በምርጫ ማግስት ስትተራመስ የከረመችው
የአባታቸውን ሀገር ኬንያ ጎብኝተው በአንድ ስታዲዬም ውስጥም በአብዛኛው ዩኒቨርስቲ ተማሪ ለሆኑ ሰዎች ንግግር አድርገው ነበር፡፡ በጣም አንጀታቸውን የበላቸውና የአፍሪካ ዋና የራስ ምታት ችግር ስለሆነ አንድ ጉዳይ አነሱ፡፡ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ¡¡ በየሴኮንዱ ጭብጨባ ሲቸራቸው የነበረው ታዳሚ ትንሽ
እንደ ማጉረምረም ቃጣው፡፡ በመጨረሻም ኬንያታ ወደ አትሮኑሱ ሄዱና “ክቡርነትዎ፤ ይሄ ጉዳይ የኬንያውያን ብሎም የአፍሪካውያን ጭንቀት አይደለም፤ በባህላችንም ነውር ነው” በሚል ዓይነት ንግግር ኮረኮሟቸው፡፡ የጄሞ ኬንያታ ልጅ ናቸዋ! እሳት እሳትን ይወልዳል’ኮ፣ አመድን ብቻ አይደለም፡፡ ተመልከቱ የእኛን (100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብና የልብ ወዳጅ ሀገር) ጉዳይ ከነውረኞች ጋብቻ በታች ቆጥረውት መሆኑ ነው እንግዲህ!
በግሌ የአዛውንቱንና ወጣቱን ጥቁር የነጩ ቤተ መንግስት ሰዎች ተግባር በዋና ዋና ምዕራፎች ወቅት የነበረ
ከባድ ክህደት አድርጌ ቆጥሬዋለሁ፡፡
ክዳት_፯፡- የትራምፕ_ቦምብ
ብዙም “ንግግር አይመቻቸውም” ወዲህም “በነጭ አክራሪነት ያምናሉ ይደገፋሉ” የሚባሉት ቱጃሩ ዶ.ጄ.
ትራምፕ ነጩን ቤተ መንግስት እንደረገጡ፣ አፍሪካን በስድብ ጥፊ ለማጮል የቀደማቸው የለም፡፡ ከቻይና ጋር በነበራቸው “እኔ እቀድም፣ እኔ እቀድም” ፉክክር፣ አፍሪካን መራኮቻ ሜዳ አድርገውት ነበር ማለት ይቀላል፡፡ ግን ደግሞ ተጠቃሚነቱም የዚያኑ ያህል ነው፡፡ “አቅለ ቢሱ” ሰው ቆያይተው የእኛንም በር ማንኳኳታቸው አልቀረም፡፡ በ“ለውጡ” ሰሞን ዐቢይ አሕመድን ወደፊት በማምጣት በኩል የማይናቅ ሚና እንደነበራቸው አዛውንቱ አቦይ ስብሓት ጠቆም አድርገውናል፡፡ በጄ! በኋላ ለሰላም ኖቤል ሽልማት ግብ ግብ ሲጦፍ እሳቸውም ከተሸላሚ ተፎካካሪዎቹ ዝርዝር ገቡ፡፡ “I saved a big war. I’ve saved a couple of them,” (ከደም መቃባት ያወጣኋቸው ደካሞች ይሄው ቀድመውኝ ተሸለሙ) እያሉ ሲብሰለሰሉ የከረሙት ወፈፌው ሰው፤ የግድቡን ውዝግብ ለመፍታት መጀመሪያ በታዛቢነት፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ሚናዋን ወደ አድራጊ ፈጣሪነት ከፍ ያደረገችው የ“ልብ” ወዳጅ ሀገር፣ እንደ ቩቩዜላ ያለ እረፍት የሚያናፋው የእነ ጌታቸው ረዳ “ዐቢይ ግድቡን ሸጦታል” ፉጨት ጋር ተዳምሮ፣ አሜሪካ ግምጃ ቤት ድረስ የሄዱት እነ ገዱ ትኩሳቱን ለክተው ሹልክ ብለው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው፣ “አፍንጫሽን ላሽ” አሏት፡፡ ጌታው ትራምፕም ቦምባቸውን መዘዙና፤ “Egypt might ‘blow up’ the Ethiopian-built dam” አሉ፡፡ ሁሉም እንደምነቱ ለፈጣሪው፣ ለሚወደው ታቦት ተሳለ፡፡ ጥቅምት “ታፈነዳዋለች” ብለው ጥር ላይ በብዙ ጣርና ጋር ከነጩ ቤተ መንግስት ተሸኙ፡፡
የማይታይ ተዋጊ እንዳለን አላወቁም! ቁምነገሩ ግን በታኅሳሱ ግርግር፣ ውጥኑ ባልታወቀና በረቀቀ መንገድ
የተደናቀፈው የግድቡና “የእህል ጎተራ” ፕሮጀክት በእኛም ዘመን ሊደናቀፍ ሩብ ጉዳይ ሲቀረው፣ በነ ዶ/ር
ዐቢይና ኢ/ር ሥለሺ፣ በነታዬ አጽቀ ሥላሴ ያለቀ ሰዓት ጥረትና በጌትዮው ፈቃድ ሁለተኛ ዙር ሙሌት
አከናውኖ ራሱን አስከበረ፡፡ ይህን ሁሉ ሽኩቻ ላየና አንገት ላለው ሰው ግን ጠ/ሚ መለስ ፕሮጀክቱን
ያስጀመሩበትን ሰዓት /timing/ አለማድነቅ ኃጢያት ነው ባይ ነኝ፡፡ ቢቀድምም ቢዘገይም የራሱ መዘዞች
ነበሩት፡፡ እዚች ላይ “ምሥጋና ለአረብ ነውጥ ይሁን” ማለትም ሳይገባ አይቀርም፡፡
የሆነው ሆኖ አሜሪካ በወሳኝ ወሳኝ ምእራፎች ወቅት ሀገሬን መክዳቷንና መንሸራተቷን ተያይዛዋለች፡፡ ይባስ ብላ “ቦምብ ጣሉባትም” እስከ ማለት እንደደረሰች ልብ በሉ፡፡
ክዳት_፰፡- ከአጎዋ_መሰረዝ
የመጨረሻ ያልሆነ ከህደት ደግሞ AGOA ነው፡፡ ይህ እድል እንደ ሀገር ተጠቅመንበታል ባይባልም ከ ፳ ፰(ሃያ ስምንት) ሚሊዮን ዶላር ተነስቶ እስከ ፫፻ (ሦስት መቶ) ሚሊዮን ዶላር ግብይት እያደገ ያለ፣ ወዲህም በአብዛኛው ሴት የሆኑ ከ፹ (ሰማኒያ ሺህ) በላይ ወጣቶች ሥራ እድል የፈጠረ ጥሩ እድል ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ ኬንያ፣ ትንሿ ሀገር ሌሶቶን ጨምሮ ፴፪ አካባቢ የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ የሆኑበት እድል፤ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ  አሜሪካ የልብ ወዳጇን በዚህ ፍጥነት ትቀጣለች ብሎ ያሰበ ካለ፣ ይህ ሰው ጠንቋይ ነውና አገናኙን፤ ሌላም ሌላም ነገር እንጠይቀው ዘንድ አለንና! በነገራችን ላይ ዴሞክራቲክ ኮንጎ እንዲሁ ተቀጥታ  በቅርቡ ነው የተመለሰችው፡፡ ወዳጃችን በቅርቡም በአምባሳደሯ በኩል የዘንዘልማ ችግረኞችን ተመልክተው፣ ወደ ሀዋሳ በአጭሩ አቅንተው የጎበኙት አምባሳደር ጊታ ፓሲ፤ “አጎዋ ለብዙ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩን ተመልክቻለሁ” በዘወርዋራው “ኢትዮጵያ ከዚህ እድል መሰረዝ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን፣ በኢንቨስትመንት የተሠማሩ ሰዎችን እንደሚጎዳ ተመልክቻለሁ፤ የባይደን አስተዳደር ተቻኩሎ ወደ ስረዛ እንዳገባ እሠራለሁ” ዓይነት ንግግር አድርገን ቆጥረነው ነበር፡፡ እነማን? እኛ የዋሆቹ ነና! ታዲያሳ? ታዲያማ የልብ ወዳጅነትን በእድሜና አፍ፣ ክዳትን በተደጋጋሚ ምግባሯ የምናውቃት/እያወቅናት ያለ ቢባል ይሻላል/ ወዳጃችን እመት አሜሪካ አምባሳደሯ እግራቸው ከሀዋሳ ሳይወጣ አንደ_ድሮን_ሚሳይሏ_የቅጣት_ቦምቡን_ንጹሓን_ላይ_ጣለችው፡፡ ጉዳቱን ገና እያጣራን ነው፡፡
ቀድሞውንም በሰሜኑ ጦርነት በገለልተኝነት የምትታማው የ”ልብ” ወዳጃችን፣ የተሻለና አዋጭ መፍትሔ
አፈላላጊ መሆን ሲችሉ በወሳኝ ሰዓት ሸርተት አሉ፡፡ የሚዲያ ሠራዊታቸውን አዝምተው በተቀናበረ ምሥል ወድምጽ ጭምር ይከሱን፣ ያብጠለጥሉን ይባስ ብሎ በሕልም ዓለም የሚኖሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ድኩማንን ሰብስበው ዋሽንግተን ዲሲ ላይ “ጥምረት ፈጠሩ፣ ከእንግዲህ የዐቢይን መንግስት አናውቅም” አሉን፡፡ በእኔ ትዝብት እንኳን ሬውተርስ ፭፣ ሲኤንኤን ፭ (በላይ)፣ ዘ ኢኮኖሚስት እንዲሁ ከ፭ ያላነሱ፣ ቢቢሲ ፭ የሚደርሱ የተዛቡና ከእውነት የራቁ መረጃዎችን ፸፪ (ሰባ ሁለት) ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አሠራጭተዋል፡፡ እንዲያውም እነ አልጀዚራና ኤፍፒን ጨምሮ ፸፪ የተሳሳቱ መረጃዎችን እንደለቀቁ የቆጠሩም አሉ፡፡ ምን ይሄ ብቻ ሰኞ ጥቅምት ፳፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም በእኛው አቆጣጠር ሌሊቱን ለ፲፪ኛ ጊዜ የተሰበሰበውና ኦ.ኦባሳንጆን ከአዲስ አበባ በቀጥታ አስገብቶ የእኛኑ ጉዳይ ሲያቦካ የነበረው UN Security Council አሜሪካ በቋሚ መልዕክተኛዋ ሊ. ቶማስ አማካኝነት “ወንጀለኞች ናችሁ፣ ጦርነት ቆሞ የማትደራደሩና ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ፣ ዜጎቻችንን ለመጠበቅ የትኛውንም ነገር ልንጠቀም እንችላለን” ብለው ድብቁን አጀንዳ ዘርግፈውልናል፡፡ እናያለና!
ይባስ ብሎ እመቤት ሊንዳ የተፉት ምራቅ ሳይደርቅ በሳምንቱ ሐሙስ ሕዳር ፳፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም ደግሞ
Bloomberg Opinion ላይ አንድ ጀምስ ሰታቨርድስ (U.S. Navy admiral and former supreme allied commander of NATO) የተባለ አምደኛና የወዳጃችን ምሥጢር አዋቂ ሁነኛ ሰው፣ የኢትዮጵያን አስፈላጊነት በምክንያት ካጠናከረ በኋላ፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ብዙ ፍላጎቶች ስላሏት በዚያች ሀገር ላይ ከማዕቀብ በተጨማሪ ራሷ የምትመራው ሰላም_አስከባሪ ታዝምት አለ፡
እርግጥ ነው፣ ይሄ ጦርነት በተራዘመ ቁጥር ከዚህ በላይ መዘዞችን እንደሚያመጣ ቢታመንም፣ አሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ትሞክራለች ብሎ ማሰብ ግን “ይህች ወዳጅ ሀገር አናውቃትም እንጂ ጠላታችን ኖራለች” ያሰኛል፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋል አሉ፡፡ ሐምሌ ወር መጀመሪያ አካባቢ አንድ ወዳጄ የሰሜን ሰው ጋር እንዲሁ “ምን
ይሻላል?” በሚለው ላይ እያወራን፣ ድንገት እንደቀልድ “ያው እንደምታውቀው አሜሪካም ጦሯን ለማዝመት ጫፍ ላይ ናት” አለኝ፡፡
የእሱ ሀሳብ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነበርኩ፣ ስለማውቀው፡፡ ኦው የሆነች ነገር እየተቦካች ነው ማለት ነው ብዬ ገርሞኝም ወዲህም ንቄም ተውኩት፡፡ ከዚያም ሰሞኑን አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ቀንጨብ አድርጎ ያጋራውን ጽሑፍ ወደ ምንጩ ገብቼ አየሁት፤ ከወዳጄ ምኞት ጋር ገጠመልኝ፡፡ አጃኢብ፣ ወይ አሜሪካ! እናንተዬ! የክሕደት ሽቅበት እንበለው ይሆን?
(ይቀጥላል)


Read 8009 times