Tuesday, 07 December 2021 05:30

ከ“ኬሬዳሽ” እስከ “ኋሳፕ፣”...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)


             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“የእኛ ሙሽሪት ኩሪባቸው በእንግሊዝ አናግሪያቸው፣” ይባል ነበር፡፡ በ‘እንግሊዝ’ መናገር የኩራት ምንጭ ነበር፡፡ እኔ እንደውም ምን ይመስለኛል መሰላችሁ...አለ አይደል... ሚስተር ባል ‘ሲፕ’ ላይ ከወዳጆቹ ጋር ሲጨዋወት በሆነ ነገር ነቆር ያደርጉት የለ፣ ምን የሚል ይመስለኛል መሰላችሁ...
“አዳሜ ሁሉ እንዲህ የምትለፈልፊው ቅናት ይዞሽ ነው”
“ለምንድነው ቅናት የሚይዘን?”
“በ‘እንግሊዝ’ የምትናገር ሚስት ስላለችኝ ነዋ!” (ቂ...ቂ...ቂ...)
እኔ የምለው፣ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...እንደዚህ አይነት ግጥም አሁንም አለ እንዴ?! አሀ…አገር ሁሉ “ኋሳፕ” እና “አት ሊስት” የሚል ሆነና ማን ለማን በ“እንግሊዝ አናግሪያቸው” ብሎ ይዘፍናል ብለን ነዋ! ለነገሩ እኮ የበፊት የእኛ ‘እንግሊዝ’ እኮ እንደ “ኋሳፕ” ይሄ ‘ከት ፔስት’ ምናምን የሚሉት ነገር አይነት አልነበረችም፡፡
“እትየ እከሊት፣ ያቺ ማናት፣ ጎንሽ እንኳን ያለችው ጎረቤትሽ…”
“ደግሞ ምን ሆነች?”
“ዛሬ  ጠዋት ስላንቺ ስታወራኝ ነበር”
     “ደግሞ ምን አለችሽ!”
  “ጓደኛሽ ከፍ ዝቅ አድርጋ ሰደበችኝ ነው የምትለው፡፡”
“ሲያንሳት ነው፡፡”
“አንቺ ደግሞ ጀመረሽ! ረጋ በይና እንነጋገር፡፡”
“እንደውም እንደገና ባገኘኋት፣ ገና  እስከ ዶቃ ማሰሪያዋ ነግሬያት ልብሷን አስጥዬ ባላስኬዳት ምን አለች በዪኝ!”
“ኧረ እባክሽ አደብ ግዢ! ቀበሌ እከሳታለሁ እያለች እኮ ነው፡፡”
“አይደለም ቀበሌ ለምን ከፈለገች እላይ ድረስ አትሄድም፣ እኔ ልጅት ግድ አለኝ ብለሽ ነው! “ኬሬዳሽ!”
አለቀ፡፡ “ኬሬዳሽ!” ከተባለ በኋላ “እንመካከር...” ብሎ ነገር የለ፣ “እንገማገም...” ብሎ ነገር የለ...ፋይል ይዘጋል፡፡ አሁን “ኬሬዳሽ!” የምትለውን ቃል... አይደለም ዌብስተር፣ አይደለም  ሼክስፒር...የትኛው ‘እንግሊዝ’ አፍ መፍቻ ቋንቋው የሆነችው ሰው ሲላት ሰምተን እናውቃለን! ፈጠራ ማለት ይሄ አይደል! ደግሞ ምን መሰላችሁ፣ ግን ‘እንደ አማራኪኖቹ እራቀቃለሁ’ ብሎ ነገር የለ፣ የራስን ጉሮሮ ‘ማነቅ’ የለ፣ ቃላቶቹን አኝኮ የመዋጥ ሙከራ የለ! እንደወረደች “ኬሬዳሽ!” ትባላለች፣ እዛ ላይ ያልቃል፡፡
ስሙኝማ... አሁን በ‘ፈረንጅ አፍ’ ሚዲያዎች የ‘እንግሊዝ’ ዜና፣ ሀተታ የምታነቡ አንዳንድ ወገኖቻችንን...እንደራስ ሆኖ ከማንበብ የበለጠ ነገር አይኖርም፡፡ አሀ...በገዛ እጅ በራስ ሰውነት ላይ የኦክሲጅን ማእቀብ ማድረግ ምን የሚሉት ሳይንስ ነው! ለዚህ ነው በፊት ጊዜ “ኬሬዳሽ!” የምትለውን እንዳለች ከእነ ምናምኗ ይሏት የነበሩ ወገኖቻችን “ኬፍ!” ሊባሉ የሚገባቸው፡፡ (አውራ ጣትን ከፍ አድርጎ “ኬፍ” የሚሏት ነገር ነበረች አይደል!)
እኔ የምለው…ወደ ራሳችን ሰውነት የሚገባውን ኦክሲጅን መገደብ እኮ ይሄ ኳሰኞቹ ‘ኦውን ጎል’ እንደሚሉት አይነት ነው፡፡ የኦክሲጅን ነገር ካነሳን አይቀር... እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እነኛ በቀደም ስለ አየር ንብረት የተሰበሰቡት ቱባ፣ ቱባ ሰዎች ‘እንደ አማሪካን’ ለመናገር ሲሞክሩ ትንፋሽ ስለሚያጥራቸው ሰዎቻችን ምንም ያሉት ነገር የለም? አሀ...ማን ያውቃል፣ ሌሎቹ “ቀጫጭኖቹ ሀበሾች እንዲህ የሚያደርጉት ጥሩ ነገር ቢሆን ነው...” ብለው ይቀላቀሉና ደግሞ ሌላ የዓለም አቀፍ ቀውስ ምናምን የሚባል ነገር ሊፈጠር ይችላላ!  
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡
“ደስ ብሎኛል፤ ይኸው ፈጣሪ የስንት ዘመን ጸሎቴን ሰምቶልኝ ልጄ አማሪካን ሆነልኝ!”
“እልልል!”
ልከ ነዋ! ’አማሪካን‘ ስለምትባለዋ ምድር ስንገነባ የኖርነው ምስል መንግሥተ ሰማያትን ሊስተካከል ምንም ያህል አልቀረውም ነበራ፡፡ እናማ ማንም ሰው ልክ ‘አማሪካን’ ሆነ ሲባል ሁሉም የመንግሥተ ሰማያት በሮች ወለል ብለው የተከፈቱለት ይመስለናላ! ኑሮ ‘ሁሉ በእጁ፣ ሁሉ በደጁ’ የሚሆንለት ይመስለናላ! በእርግጥ እዛ ነጭ ቤተ መንግሥት ምናምን የተሰበሰቡት አሁን ክህደት እየፈጸሙብን ነው ብለን ሁሉንም ነገር ማጣጣል ‘ፌይር’ አይደለም! ብዙ በጎ ነገሮች አሉ፣ ብዙ መጥፎ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ ማለት ነው፡፡ ደግሞላችሁ...ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሀገር ፓስፖርት መውሰድ ግለሰባዊ ምርጫ ነው፡፡ ግን መቼም ቢሆን ብዙዎቹ ወገኖቻችን የፈለገው የዓለም ክፍል ይሂዱ፣ የፈለገውን ሀገር ፓስፖርት ይያዙ፣ ከፈለገው ሀገር እንትና ወይም እንትናዬ ጋር በአንድ ጣራ ስር ይኑሩ፤ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን ከውስጣቸው እንደማትወጣ ከሰሞኑ ሰልፎች የተሻለ ማሳያ የለም፡፡
ግን ደግሞ ለሁሉም ህይወት አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው ነው ማለት አይደለም፡፡ ልጄ...እዛ፣ እዛ ካልሠራህ አትበላም ነው ነገሩ፡፡ በቀን አስራ ስድስት ሰዓት ድረስ የሚለፉት ለሀብታምነት ሳይሆን የእነሱና የቤተሰቦቻቸውን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ነው፡፡
እነ እንትና...እንደው እዛ ያሉትን ዘመድም፣ የሰፈር ልጅም፣ የድሮ የትምህርት ቤት ጓደኛም...አለ አይደል... “ዶላር! ዶላር!” እያላችሁ መከራ የምታበሉት፤ እነሱ ከዛፍ ላይ እንደ ቅጠል የሚበጥሱት መሰላችሁ እንዴ! የምር እኮ አንዳንዱ ነገር ኮሚክ ነው፡፡ እነሱ እዛ ባልና ሚስት አስርና አስራ አምስት ቀን ሳይተያዩ እየከረሙ፣ ልጆቻቸው ቤታቸው ውስጥ ሆነው እየናፈቋቸውም፣ አንዱን ‘ቢል’ ሲሉት ሌላው እየመጣ...መከራ በልተው በሚልኩት ‘ዶላሬ’ እዚህ እኮ ቅንጡ ኑሮ የሚኖር፣ ውድ ሆቴሎችና ሬስቱራንቶች የሚያጨናንቅ፣ የሚያብለጨልጭ መኪና እያሽከረከር የእኛን ‘ብለድ’ ሁለት መቶ ምናምን ዲግሪ ፋሬንሀይት ለማንተክተክ የሚሞክር መአት ነው፡፡ ምቁነት እንዳይመስል እሺ ይሁን... ቢያንስ፣ ቢያንስ በነጋ በጠባ “አነሰ ጨምሩ፣” ከማለት “በወጣ ይተካ...” ብሎ መመረቅ ምን ክፋት አለው! የእኛን ሆድ ላለማባባት ጭጭ እያሉ ነው እንጂ ብዙዎቹ እያንዳንዷን ዶላር እንዴት ለፍተው እንደሚያገኟት ፈጣሪና ራሳቸው ነው የሚያውቁት!
አንድ ወዳጅ ነበረን፡፡ አማሪካን ሄዶ እንደ እድል በሙያው የሆነ ቦታ ሥራ ያገኛል፡፡ (በነገራችን ላይ በሙያቸው የሥራ እድል የሚያገኙ በጣም ጥቂት፣ እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡) እናላችሁ ይህ ወዳጃችን በገባበት መሥሪያ ቤት የተወሰኑ ጥቁሮች ቢኖሩም ከቆዳ ቀለማቸው በስተቀር እንደ ‘ፈረንጅ’ የሚያደርጋቸው በጣት የሚቆጠሩ አፍሪካ አሜሪካውያን ብቻ ነበሩ፡፡ አለቆች ሁሉ ነጮች ሆነው ጥቁሮቹ ማድረግ የሚጠበቅባቸውን ስለሚያውቁ ሰልፋቸውን አስተካክለዋል፡፡ ይኸ የእኛው ቀጭኑ ሀበሻ ግን የማያምንበትን ወይም “ትክክል አይደለም...” ብሎ የሚያስበውን ነገር ሥራ ሲባል ወይ “ኤቲክሱ አይፈቅድም፣” ወይ ደግሞ “ከአሠራር ውጪ ስለሆነ ሊያስጠይቅ ይችላል...” እያለ ለፈረንጆቹ ‘ሽቅብ’ ምላሽ መስጠት አበዛ፡፡ በሥራው አንዳችም ጉድለት ባያገኙበትም መንፈቅ ሳይደፍን አስወጡታ፡፡ ከዛ በኋላ በሙያው የሚቀጥረው ማግኘት ስላልቻለ እንደ አብዛኛዎቹ ወገኖቹ ያገኘውን መሥራት ጀመረ! እናማ፣ ነገሮች እኛ እዚህ ሆነን “በአስቸኳይ ላክ...” “ትንሽ ጨምሪበት እንጂ...” እንደምንለው ሳይሆን ነገሮች ከባድ ናቸው፡፡ ደግሞ እዛ ያላችሁ አንዳንዶቻችሁ...ይህን ይህል ‘ቋጣሪ’ አትሁኑዋ!“ያቺ ትልቀኛዋ ልጅ እኮ ‘እንግሊዝ’ ሆነችልኝ!”
“እሰይ! እሰይ! እንኳን ደስ አለሽ!”
በቃ እንዲህ ነው፡፡ ለዘመናት ከጠፈነገን ችግራችንም የተነሳ፣ ዘለዓለም ዓለም እላያችን ላይ ሰፍሮ አልወርድ ካለው ድህነት የተነሳ፣ በጊዜው በሚፈጠሩ የፖለቲካ ቀውሶች የተነሳ ውጪ፣ ውጪ ብንል አይገርም፡፡ እናም ልጅትየው ‘እንግሊዝ ሆነች’ ማለት አንድ ቀንም የሆነ በብርን ደጃፍ ሳይረግጡ “እሰይ ስለቴ ሰመረ” የሚያሰኝ ነው፡፡ (ምድር ላይ “መቼና ምን ብለህ እንደተሳልክ ማስረጃ አምጣ፣” የሚል የለ!)
ስሙኝማ...‘አማሪካን፣’ ‘እንግሊዝ’ ይባላል እንጂ...አለ አይደል... “ልጄ ሩስያዊ ሆነልኝ!” “ልጄ ኬንያዊት ሆነችልኝ!” ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ! በቃ አማሪካንና እንግሊዝ የሁሉም ነገር ቁንጮ ናቸዋ! ለነገሩ ለምን ይዋሻል…በብዙ ነገር ቁንጮ ናቸው፡ በተለይ በተንኮል! ቂ...ቂ...ቂ...እንግሊዝን እንኳን ያው ድሮም ጀምረን እናውቃታለን፡፡ “እሱ እኮ ሆዱ የእንግሊዝ  ነው!” ከመባል “ሆዱ የሰይጣን ነው፣” ቢባል ይሻል ነበር፡፡ ብቻ ከ“ኬሬዳሽ” እስከ “ኋሳፕ” የእኛ የፈረንጆች ታሪክ ገና ብዙ የሚጻፍ ነገር ሳይኖረው አይቀርም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1739 times