Tuesday, 07 December 2021 06:29

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በገና ወዳገርቤት!!


          ዘማቹ የአትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በዓለም ላይ ተበትነው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን /diaspora/ እና ለኢትዮጵያውያን ወዳጆች ቢያንስ 1 ሚሊዮን ሞልታችሁ፣ እዚህ በሃገር ቤት የገና በአልን ታህሳስ 29 ቀን 2014 አብረን እናክብር ሲሉ በፌስ ቡክ ገፃቸው ተጣሩ! ዐቢይ ከጦር ግምባር ሆነው በሀገሩ ጉዳይ የግምባር ስጋ ሆኖ በያለበት የዓለም ከተማ፣ ለእማማ ለእናቱ፣ ለመተኪያ- የለሽ ዞሮ-መግቢያ ቤቱ አገሩ ሳያቋርጥ አደባባይ የተፋለመላት ዲያስፖራ ያቀረቡት ይህ ጥሪአቸው፣ ከጠበቁት በላይ ምላሽ እንደሚያገኝ ይጠበቃል::
በገና ወደ ሀገር ቤት ውርርድ /challenge / አዲስ አበባ ተኩላና ተሞሽራ ስትጠብቅ፣ ቦሌ አየር ማረፊያ በመንግስታዊ በግለሰባዊና በኪነታዊ ልዩ አቀባበል ራሱን የቻለ አውዳመት ትሆናለች::  የአፍሪካ “አድራሽ መላሽ “ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለዚህ #ወደ ሃገርቤት ዘመቻ ዝግጁነቱን በቅርቡ ያስታውቃል ተብሎ ይጠበቃል:: ቅድስቲቱ የዓለም የቅርስ ከተማ  ላሊበላ እንሆ፣ የነፃነት አየር መተንፈስ ጀምራለች! ለታወቀው የገና ቅዳሴና ዝማሬዋ፡፡ አየር ማረፊያው ዝግጁ ነው!
ከዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ በጦርነቱ የተፈናቀሉና ለአስቸኳይ እርዳታ የተጋለጡ ወገኖቻችን ይጠቀማሉ!
ለበዓሉ በየደረሱበት ቡናው ይቆላል! ፈንድሻው ይበተናል! ሽንጥና ዳቢት ለቁርጥና ጥብስ በዝነኛ ስጋ ቤቶቻችን ሜንጦዎች ላይ ይንጠለጠላል--ከኢትዮጵያ በስተቀር ሌላ የትም ዓለም ከማይገኘው የአዋዜ የሰናፍጭ የሚጥሚጣና የወላይታ ዳጣ ጋር! ጥሬ ስጋ ያለ ሃሞት በስተቀር አይዋጠንም ለምትሉ ያነጋገርኳ ቸው ስጋ ቤቶች በቀኝ እጆቻቸው የያዙትን ቢላ ወደላይ እያወናጨፉ፣ “ምን ችግር አለ?!” ብለውኛል:: የባህል አዳራሾች ከወዲሁ በዕለቱ ከልዩ የባህል ጭፈራዎች ጋር ለሚበላ ቡፌ፣ ክትፎውን ቀይና አልጫ ወጡን፤ ምንቸት አብሹን ጎረድ ጎረዱን፤ ቦዘና ሽሮውን ወዘተ ለማዘጋጀት ከወዲሁ የገበያ ዝግጅት ላይ ናቸው:: አንድ ለመሬት ሳይሉ በፊት ዉሃ እንደምትውጥ ዶሮ አንገታችሁን ሽቅብ አቅንታችሁ፣ ቁልቁል ወደ ጉሮሮአችሁ የምታንቆረቁሩት ጠጅ፣ በሹርቤ ብርሌና በጠርሙስ ይጠብቃችኋል!
የዛን እለት ቅዳሴው ወረቡ ከነከበሮውና ፀናፅሉ ጋር ያምማል! ከዝማሜው ስልትና ከከበሮው ድምፀት ጋር የእጣኑ ማእዛ ወደ ውጭ እየተረጨ ቀዬውን ያውዳል! እግዛብሄር መድሃኒያለም ይወደሳል! እንደ ኦርቶዶክስና ካቶሊኮች ቤተ ክርስትያናት ሁሉ የፕሮቴስታንት የፀሎት አዳራሾች በዝማሬ በእልልታ በዕምባ በታጠበ የአምልኮት ስርዓት ይናወጣሉ! እየሱስ ክርስቶስ ስሙ ይከብራል! ዕለቱ ለሙስሊም ወገኖቻችን አውዳመት ባይሆንም፣ በየለቱ በማይዛናፈው ስግደት አዛኑ ምእመናንን ከሩቅ ይጣራል! አላህ ስሙ ይባረካል!
ኑ ሀገር ቤት በገና!!! 1 ሚሊዮን በገና!!
ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሆይ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የውጭ ምንዛሪ ምንጭና የጦርነቷ ኑክሌር ቦምብ መሆናችሁን በተግባር አሳይታችኋል!!! ክበሩ! ሰላም፣ ጤና ደስታ - ገንዘባችሁ ይሁን!

===================================================

                              የጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ ቅስቀሳ ከሥነልቦናዊ ፕሮፓጋንዳ አንፃር ሲታይ
                                     (ጌታሁን ሔራሞ)


            የውትድርና ጠበብት በውጊያ ወቅት ጥቅም ላይ የሚያውሏቸው ልዩ ልዩ የፕሮፓጋንዳ ስልቶች አሉ። ከነዚህም አንዱ የጠላትን ሰብዕናውን ገፎ “Dehumanize” ማድረግ ነው። የጦር ፕሮፓጋንዲስቶች ጠላትን “dehumanize” የሚያደርጉበት ምክንያት አንድም ከሰው ተፈጥሮ ጋር የሚገናኝ ነው። ይህን በተመለከተም የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሳይኮሎጂ ፕሮፈሰርና የ”The Age of Propganda” ደራሲ አንቶኒ ፒራክታኒስ፤ “Dehumanization” ያስፈለገው አብዛኛው ሰው ሌላውን ሰው ለመግደል ስለሚሳቀቅ ነው ይላል።
“For most human beings, it takes an awful lot to allow them to kill another human being”
ለምሣሌ የፕሮፓጋንዳ ፊልም አጥኚው ጄምስ ፎርሼር ጠላትን ማሰይጠን (demonization) የ”dehumanization” አንዱ ዘዴ ነው ይለናል። እንደ ጄምስ ፎርሼር ዕሳቤ፤ የአንድ ወታደር አዕምሮ ጠላቱን እንደ ሰይጣን መቁጠር በጀመረበት ቅፅበት እርምጃ ለመውሰድ ያለው ውሳኔ በዚያው ልክ ይጠነክራል። እርምጃውን መውሰዱንም እንደ ጥፋት ሳይሆን እንደ ፅድቅ መቁጠር ይጀምራል።
“When you dehumanize, it allows you to kill your enemy and no longer feel guilty about it.”
“Dehumanization” በመጀመሪያውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጥቅም ላይ ከዋሉ የፕሮፓጋንዳ ስልቶች አንዱ ነው፤ ስልቱ ዛሬም ድረስ ጥቅም ላይ ይውላል። ለምሣሌ በሀገራችን የቀድሞው ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ በቅርቡ ወደ ሸዋ ግንባር ሄደው፣ ሚሊሻዎቹንና ፋኖዎቹን ሲቀሰቅሱ እንደዚህ ነበር ያሉት፦ ...ክርስቲያን የሆናችሁ በስመዓብ ብላችሁ ተኩሱ፣ ሙስሊም የሆናቸው ቢስሚላሂ ብላችሁ ተኩሱ፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰይጣኖች ናቸው፤ ይህ ሰይጣን ፊታችሁ ድርሽ አይልም
እንግዲህ ጄኔራሉ ታዳሚያቸውን (ሚሊሻዎችና ፋኖዎች) መነሻ በማድረግ ሕወሓትን በማሰይጠን “dehumanize” አድርገውታል። ይህ ከላይ እንደጠቀስኩት በውጊያ ወቅት የሚተገበር የፕሮፓጋንዳ ስልት ነው። (በእርግጥ አንዳንዶች ሰይጣን ራሱ ክፋትን የሚኮርጀው ከሕወሓት ነው በማለት ሕወሓትን ከማሰይጠንም የዘለለ ማጠቃለያ ላይ ይደርሳሉ።)
ከውጊያ ፕሮፓጋንዳ አንፃር “Dehumanization” ምን ሊመስል እንደሚችል በጥቂቱ ያካፈልኳችሁ ያለ ምክንያት አይደለም። የሕወሓት ወጣቶች (ፕሮፈሰር ክንድየን ጨምሮ) ሰሞኑን የጄኔራል ካሳዬ ጨመዳን ቅስቃሳ በሶሻል ሚዲያቸው እየለቀቁ ሲሳለቁባቸው አይቼአቸው፣ እነዚህ ሰዎች ቢያንስ ጄኔራሉ ምን እያደረጉ እንደሆነ ያለማስተዋላቸው ገርሞኝ ነበር። They didn’t even grasp that the general is injecting dehumanization into the minds of the militia by demonizing TPLF. They didn’t know this is one form of psychological operation...psychological warfare!
በሌላ አነጋገር፣ የሕወሓት ወጣቶች ቧልት፣ ልክ አንድ ሕፃን ልጅ የቦንብ ምንነቱን ሳያውቀው እንደ ኳስ ሊጫወተው እንደሚሞክረው ዓይነት ነው ማለት ይቻላል። ጄኔራሉ ለሚሊሻዎቹና ፋኖዎች እያስታጠቁ የነበረው ሥነ ልቦናዊ ቦንብ እንደሆነ ገና አልተረዱትም ነበር። የምር ያሳዝናሉ።

=================================================

                            ኢትዮጵያ እንደ ልማዷ ታሸንፋለች
                                  (አንዱአለም ቡኬቶ ገዳ)


          ኢትዮጵያኖች ከሰሞኑ ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ ከውጭ ሃገር እስከ ሃገር ውስጥ አስደማሚ አንድነት ፈጥረው ከውስጥም ከውጭም ለተነሳባቸው ጠላት ራስ ምታት ሆነዋል። ጠላት ለክፉ ቀን ስንቅ ይሆነኛል ያለው ‘ልዩነታችን’ የጥንካሬያችን ምንጭ ሆኗል።
አፋር፣ ሶማሌ፣ ኦሮሞ፣ አማራ ደቡብ ወዘተ-- በኢትዮጵያ ስም ምለው፣ ሃገር ሊያፈርስ የተነሳውን ባንዳ አይቀጡ ቅጣት እየቀጡት ይገኛሉ! አሁን ላይ በዚህ ሁኔታ የትም መድረስ እንደማይችል የተረዳው ጠላት፤ ለክፉ ቀን ያስቀመጣትን አጀንዳ በቅጥረኞቹ አማካኝነት መዟል! ለሶማሌና ለአፋር የቅኝ ግዛት ትርክት ለማቀበል እየተሞከረ ነው። የኦሮሞን ልብ ለማሸፈት የተለመደው የሚኒሊክ ካርታ ተመዟል።
ይሄን ከፋፋይ አጀንዳ ማን እንዳቀነባበረው፣ በዚህ ሰዓት ማንሳቱም ለምን እንዳስፈለገ እንኳንስ እኛ ጡጦ የጣለ ህጻን ልጅ እንኳን አይጠፋውም!!
በጦር ሜዳው ድል እየቀናን ሲመጣ እንደዚህ አይነትና ከዚህም በላይ ሴራ በጠላት እንደሚጎነጎን በበኩሌ ስጠብቀው የነበረ አካሄድ ስለሆነ አልገረመኝም! እኛም ይህን አውቀን የጠላትን አጀንዳ ተከትለን አንትመም!!
ይህንን የሚያራግቡት እነማን እንደሆነ አስተውለን፣ በአንድነት ሃገር ወደ ማዳን ተልእኮኣችን ብቻ እናተኩር!!
ኢትዮጵያ እንደ ልማዷ ታሸንፋለች!!

==============================================

                           ኢትዮጵያ ክቡር ስም!
                                  («ዘውዳለም ታደሰ»)

ስሟ ቃልኪዳን ነው የአንድነት ማህተም
ድንገት ከፋን ብለን፥
ቀደን የማንጥለው ነፍስ ላይ ሚታተም!
የጥላቻ ነፋስ ጠርጎ እንዳይወስደው
ከደም ካጥንታችን ፥ ታሪክ ያዋሃደው!
ልክ እንደከንአን፥
ማር ባይሞላ ደጇ ፥ ወተት ባታፈልቅም
ይሄን ስም አንለቅም!

=============================================

                    ኢኮኖሚ ሁለተኛው የጦር ግንባር ነው
                            (ሙሼ ሰሙ)


          በመጀመርያ ሰራዊታችን ከክልል ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ላጎናጸፈን ድል አክብሮቴን እገልጻለሁ።
ጦርነትን በስኬት ለማጠናቀቅ ኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ነው፡፡ በጥንቃቄ የማይታቀድና በአግባቡ የማይመራ ኢኮኖሚ፣ ጦርነቱን በማራዘም እጥረትና የደጀን መሰላቸት አስከትሎ፣ የጦርነቱን ውጤት ፈታኝ ስለሚያደርገው፣ ጦርነቱን ለማሸነፍ ኢኮኖሚውን ማሸነፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
ማንኛውም ጦርነት ፋይናንስ የሚደረገው በሶስት መንገዶች ነው፡፡ አንደኛው፤ ከዜጎች በሚሰበሰብ ግብር ነው፡፡ ሁለተኛው፤ በብድር ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ግሽበት (Inflation Financing) ነው፡፡
 ጦርነቱ በብድር፣ በከፍተኛ የግብር ጫናና “መዋጮ”ብቻ ፋይናንስ የሚደረግ ከሆነ፣ ጫናው ሲበዛ ልማቱና እድገቱን በማኮማተር፣ ኢኮኖሚውን ሊያናጋው ይችላል፡፡ ኢኮኖሚያዊ መናጋቱም ማህበራዊ ቀውስን በመፍጠር ሰላማዊ ሕይወትን መምራትም ሆነ ጦርነቱን ማካሄድን ፈታኝ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ኢኮኖሚ ሁለተኛው የጦር ግንባር ነው የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
የጦርነት ኢኮኖሚ እንደ ሃይማኖት ቀኖና የለውም፤ የትርፍ ሰዓት ስራም አይደለም፡፡ ከጦርነቱ እኩል ልዩ ትኩረትን ይሻል፡፡ ጦርነቱን ለማሸነፍም ሆነ ጦርነት የሚያስከትለውን ዘለቄታ ያለው ጠባሳ ለመጠገን አቅምህን አስተባብረህና አሟጠህ ከመጠቀም ባሻገር ከርዕየተ ዓለም አሰላለፍ አኳያ ረድፍህን ማስተካከል የግድ ሊልህ ይችላል፡፡ አሜሪካ የምታወግዘውንና የምታሳድደውን “ሶሻሊዝም”፤ በ1940ዎቹ፣ በ2ኛው የዓለም ጦርነት፣ በ1950ዎቹ በኮርያ ጦርነት ወቅት ለመቀበል ተገዳ ነበር፡፡
አሜሪካ በ2ኛው የዓለም ጦርነት 2.2 ቋሚና 34 ሚሊዮን በጎ ፈቃደኛ ወታደሮችን መልምላለች፡፡ ይህን ሃይል ለማደራጀት ለማስታጠቅና ለማዝመት መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ እድገትና ሽግግርን ጠይቋታል፡፡ ስንቅና ትጥቆችን ለማምረት ነባር ኢንዱስትሪዎችን ወደ ጦር መሳርያ ማምረቻነት መለወጥ፣ አዳዲስ የጦር መሳርያ ማምረቻ ፋብሪካዎችን መትክል፣ ለሲቪል የፍጆታ አጠቃቀም ስርዓት ማበጀት፣ አላስፈላጊ የቅንጦት እቃዎችን ከምርት ሰንሰለት ማስወገድን ጨምሮ ከውጭ ማስመጣትንም አግዳ ነበር፡፡
ደጀኑ (Home Front) እንደ “ቪክትሪ ጋርደን” ባሉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች አማካኝነት በጓሮውና በይዞታው ላይ የራሱን ምርት በማምረት መደበኛውን ምርት እንዲያግዛና ቁጠባን ባህል እንዲያደርግ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል፡፡ ውሳኔዎቹ እስከ 20 ሚሊዮን (10 ሚሊዮኑ ሴቶች ናቸው) የሚደርሱ የስራ እድሎችን ከመፍጠራቸውም በላይ ከጦርነቱ በኋላ ኢኮኖሚው ከደረሰበት ጉዳት በአጭር ጊዜ ውስጥ አንሰራርቶና ጠንክሮ እንዲወጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ከእኛስ ምን ይጠበቃል? ለጊዜው ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን ብቻ ላንሳ። አንደኛው ከመንግስት በኩል የሚጠበቅ ነው፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ላይ ሆነን በተለመደ መንገድ (Business as usual) ስራን መከወን አይቻልም፡፡ በእለት ከእለት ስራ በተጠመዱ የሚኒስቴር መስርያ ቤቶች አማካኝነት ስራን መከወን ውጤቱ እዘጭ እንገጭ ከመሆን አይዘልም፡፡ የእለት ከእለት ስራቸው የሚያንገዳግዳቸው ተቋማትን የሚያግዙ አዳዲስ አደረጃጀቶችንና አወቃቀሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በጦርነቱ ወቅት አሜሪካ (Office of Price Administration “ዋጋ ተማኝና ተቆጣጣሪ ቢሮ”፣ Office of Economic Warfare “የጦርነት ኢኮኖሚ ቢሮ”፣ Office of War Mobilization and Reconversion “ለጦርነት ሀብት አሰባሳቢና የማምረቻ ተቋማት ለውጥ ቢሮ “) የመሳሰሉ ተቋማት አቋቁማ ነበር፡፡
ሌላው መንግስት ተቋሞቹ በጥብቅ የቁጠባ ዲሲፕሊንና ፖሊሲ እንዲመሩ፣ ኃላፊዎቹም በሀገሪቱ አቅም ልክ ቢሮዎቻቸውን እንዲመሩ ማድረግ ያስፈልገዋል፡፡ የስራ ሰዓትን ማክበር፣ መስተንግዶን ማቀላጠፍና ዘመቻ ባህል እንዳይሆን ተጠንቅቆ ጦርነቱ የሚነጥቀንን የጊዜ፣ የሰው ኃይልና የሀብት ብክነትን ለመሻማት፤ በተጨማሪ የስራ ሰዓት አማካኝነት በጎ ፈቃደኞች ያለ ክፍያ በዘመቻ የሚያግዙበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ በምርት አቅርቦትና ግብይት መካከል ያለውን የተዛባና የተራዘመ ሰንሰለት በመበጣጠስ የዋጋ ንረትና እጥረት መቋቋም ይገባል።
ሁለተኛው ከሕዝብ የሚጠበቀው ነው ( Home Front)፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ የሚያባክነውና የሚያድፋፋው ሀገራዊ ሀብት ኮሮና፣ ጦርነትና የተፈጥሮ ችግር በተፈታተነው ኢኮኖሚ ላይ የሚጥለው ተጨማሪ ጠባሳ መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ እንደ ብክነት፣ ዝርክርክነት፣ ስግብግብነትና አለመቆጠብ ያሉ ኋላ ቀር ባህሎች በኢኮኖሚው ላይ የሚስከትሉት መዘዝ ዘላቂና ተቀጣጣይነት ያለው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ኃላፊነት መሰማትና ተቆርቋሪነት ባህል መሆን አለበት፡፡ ገንዘብ ስላለን ብቻ ያላመረትነውንና ያሻንን ትርኪ ምርኪ ሁላ በውጭ ምንዛሪ እየሸመትን ያለገደብ ማግበስበስና መቀራመትን ጋብ ማድረግ አለብን፡፡ ለእጥረትና ለንረት መንግስትን በማማረር ብቻ መፍትሔ አይገኝም፡፡
መብራት፣ ውሃ፣ የነዳጅ ውጤቶችን፣ ስፔር ፓርቶችን፣ ጎማና ሌሎች ወሳኝ የፍጆታ አቅርቦቶችን እንቆጥብ፡፡ ከሚያስፈልገን በላይ በመግዛትም (Horde) ሆነ በመጠቀም (Wastage) ኢኮኖሚው ላይ ተጽእኖ ከመፍጠር እንቆጠብ፡፡ ሀገር በጦርነት ላይ ነች፡፡ የሀገራችን ልጆች በባዶ ሆድ፣ በሀሩርና በጥም እየተቃጠሉ መስዋእትነት እየከፈሉ ነው፡፡ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት ዋጋ በመጫንም ሆነ አቅርቦትን በመሰወር የምንፈጽመው ሕገ ወጥ የስግብግብነት ተግባር በዘማች ቤተሰቦችና ወገኖች ላይ የሚሰራ የግፍ ግፍ መሆኑንም አንርሳ፡፡

================================_

                 ኢትዮጵያ ትቅደም!Ethiopia flag: its meaning, history and design – Lonely Planet


            በላቲን አሜሪካና አፍሪካ አሜሪካ ከተገበረችው የአሻንጉሊት መንግስት ምሥረታ ጣልቃ ገብነት ታሪክ ብዙ መማር ይቻላል። ከሁሉም በላይ አሜሪካ በሕዝብ በተመረጠ መንግስትና በሕዝቡ መካከል መቃቀርን በመፍጠር የአሻንጉሊት መንግስቷን ከጫካ እስከ ቤተመንግስት ለማምጣት የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም። የሕዝቡን አንድነት መሸርሸር፣ አማፂያንን ማደራጀት፣ የፕሮፓጋንዳና ሥነ ልቦናዊ ጦርነትን መክፈት ከተሳካላትም ተናጠላዊ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን እስከ መተግበር ትዘልቃለች። በተለይም ለአሜሪካኖቹ መሬትን ከመቆጣጠር ይልቅ አዕምሮን መቆጣጠር ከፍተኛ ግምት ይሰጠዋል። ይህን በተመለከተም ማንዋሎችን በማዘጋጀት ለአማፂያን ልዩ ሥልጠና ይሰጣሉ። ለምሣሌ በ1980ዎቹ ኒካራጓ ውስጥ ለሚደግፏቸው አማፂያን፣ የሲአይኤ ኃላፊዎች “PSYCHOLOGICAL OPERATIONS IN GUERRILLA WARFARE” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ማንዋል አዘጋጅተው ሥልጠና ሰጥተው ነበር። መቼም በዚህ ማንዋል ውስጥ አሜሪካኖቹ፣ በሕዝብ የተመረጠውን መንግስት፣ ከሕዝቡ ለመነጠል ያልሸረቡት ሴራ፣ ያላቀናበሩት ሥነ ልቦናዊ ታክቲክ የለም። የተለመደ ትችት አይሁንብኝ እንጂ ሰይጣን እራሱ በነርሱ ልክ ሴራ የሚጎነጉን አይመስለኝም። ማንዋሉን ለማንበብ ለምትፈልጉ ጎግል ውስጥ በፒዲኤፍ ፎርማት አለላችሁ።
ወደ ዋናው መልዕክቴ ልመለስ፦ አሜሪካኖቹ በሌሎቹ ሀገራት የተጠቀሙትን ሥነ ልቦናዊ ኦፕሬሽን፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በቀጥታም በተዘዋዋሪም በሀገራችንም እየተጠቀመች ነው። በተለይም ሰላም በሰፈነባት መዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ በቀጥታ በሽብር ተግባር እየተሳተፈች ትገኛለች። ከራሷ ዜጎች አልፋም የሌላ ሀገር ዜጎችንም በማሸበር ድርጊት ላይ ተጠምዳለች። በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ብቸኛ በሽታዋ የአሜሪካ ሥነ ልቦናዊ ኦፕሬሽን እንጂ ሌላ ሚሊተሪ ኦፕሬሽን አይደለም። በነገራችን ላይ አሁን እራሱ ይህን ልጥፍ እየፃፍኩ ያለሁት ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ካልዲስ ካፌ ቡናዬን ፉት እያልኩ ነው። አሁን ባለው ነባራዊ እውነታ አሜሪካ በእጅጉ እየተሸወደች ነው፤ ሌሎች ሀገራት ውስጥ ውጤታማ ያደረጋት ስትራቴጂ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ሲመጣ ፉርሽ እየሆነ ስለመምጣቱ እራሳቸውም እየተረዱት የመጡ ይመስላል። በውሸት ላይ የተመሠረተ ሥነ ልቦናዊ ሽብርም ሆነ ዜና በጊዜ ሂደት እርቃኑን ቀርቶ የወሬውን አመንጪም ማዋረዱ አይቀሬ ነው።
አሜሪካ በሀገራችን ያቀደችው ሥነ ልቦናዊ ሽብር በፈለገችው ፍጥነት ላለመሄዱ በዋናነት የሚጠቀስ አንድ ምክንያት አለ ፦ ይኸውም ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ላይ አደጋ በሚያንዣብብበት በማንኛውም ወቅት የፖለቲካ ፣ የብሔር፣ የመደብና የሃይማኖት ልዩነቶቻቸውን “Switch off” አድርገው ለሀገራቸው ሕልውና ቅድሚያ ይሰጣሉ (ባንዳዎች እዚህና እዚያ ሊኖሩ ቢችሉም)። ኢትዮጵያዊያን ችግርና ድህነት ውስጥ ሆነውም ሀገራቸውን ያስቀድማሉ። ለዚህም ነው ባለፈው ከተፈናቃዮች ውስጥ አንዷ ሚዲያ ላይ ቀርባ “አሜሪካ” የሚባል ሀገር ሳይሆን ቃሉን እንኳን መስማት አልፈልግም ያለችው። ትናንትና አንድ አሜሪካዊ ወዳጄም ከዚያው ከአሜሪካ ደውሎልኝ ያረጋገጠልኝ ይህንኑ ነበር፦ “ አሜሪካኖቹ የኢትዮጵያዊያንን ሥነ ልቦና እስከአሁን ያለማወቃቸው ይገርመኛል፣ በሌሎቹ ሀገራት የተጠቀሙትን ዘዴ በቀጥታ እየተጠቀሙ ቅሌት ውስጥ እየገቡ ነው” በማለት ነበር ያጫወተኝ። በኢትዮጵያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶም በአንድ ወቅት፤ “ኢትዮጵያዊያን ሲጫኗቸው አይወዱም፣ ኩሩዎች ናቸው” ስለማለቱም ይነገራል። ያማማቶ ከላይ የተቀመጠውን ቢልም ባይልም መሬት ያለው እውነት ከተባለው የተለየ አይደለም፤ እስቲ አስተውሉ፤ ጫናው በበረታ ቁጥር ትስስራችን እየጠነከረ ነው የሄደው! እንኳን እኛ ተስፋ ቆርጠን ሸብረክ ማለት ይቅርና ሸብረክ ያሉ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በእኛ ምክንያት እየነቁ፣ ንቅናቄው አህጉራዊ ቅርፅ እየያዘ ነው። በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ የዲያስፖራ ወገኖቻችን ሌሎች ልዩነቶቻቸውን ትተው በአንድ ድምፅ እንደዚህ እያሉ ነው፦ ኢትዮጵያ ትቅደም! አዎን ለአሜሪካኖች መርዝ ማርከሻ መድኃኒቱ ያለው እኛው እጅ ላይ ነው፦ ኢትዮጵያን አስቀድመን በአንድነት መቆም!



Read 1897 times