Saturday, 11 December 2021 13:19

በነዳጅ ዋጋ ላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ8 ብር በላይ ጭማሪ ተደርጓል

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(0 votes)

  በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማሻሻያ እስከሚደረግ ባለበት ይቀጥላል ተብሏል
                         
   -የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ አዲስ የዋጋ ማስተካከያ መደረጉንና በአንድ ሊትር የነዳጅ ዘይት ላይ 5.88 ብር ጭማሪ መደረጉን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል። ይህ ጭማሪ በአንድ ዓመት ብቻ የተደረገውን ከስምንት ብር በላይ እንደሚያደርሰውም ታውቋል። ይህ ዋጋም እስዛሬ ድረስ በነዳጅ ዋጋ ላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ከተደረጉ ጭማሪዎች ከፍተኛው ነው ተብሏል።
 የዓለም አቀፍ ነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑንና ነዳጅ ዘይት ከአገራችን በተለያዩ  ህገ-ወጥ መንገዶች እየወጣ በጎረቤት አገራት እየተሸጠ መሆኑ ስለተደረሰበት የዋጋ ማስተካከያ እንዲደረግ መወሰኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል። በዚህ መሰረት አንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ ቀደም ሲል ይሸጥ ከነበረበት 25.85 ሳንቲም የ5 ብር ከ 89 ሳንቲም ጭማሪ በማድረግ ወደ 31.74 ሳንቲም ከፍ እንዲል ተደርጓል። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ሲያሳይ መቆየቱን ያመለከተው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ላለፉት 2 ዓመታት 24.05 ቢሊዮን ብር የዋጋ ጭማሪውን መንግስት እየደጎመ መቆየቱን አመልክቷል። ይህ ጭማሪም በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረገ መሆኑም ተመልክቷል።በተያያዘ ዜና አዲስ የታሪፍ ማሻሻያ ተጠንቶ ይፋ እስሚያደረግ ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ቀደም ሲል ይሰጥ በነበረበት ታሪፍ  እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደር ቢሮው በህዝብ ትራንስርት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ጥናት እያከናወነ ሲሆን ጥናቱ ተጠናቆ በቀጣይ ቀናት ይፋ ይደረጋልም ተብሏል።
በከተማዋ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ አሽከርካሪዎች የታሪፍ መጠኑ ይፋ ሳይደረግ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉም ተገልጿል።
ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ በየዕለቱ 2.5 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚንና 8 ሚሊዮን ሊትር ናፍታ ጥቅም ላይ ይውላል።


Read 1978 times