Saturday, 11 December 2021 13:49

“የሚያብለጨልጨው ሁሉ ወርቅ አልሆን እያለኝ...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ እንዴት ነህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡- ዛሬ ምን ሆነሃል! አሻንጉሊት ያሳዩት ህጻን መሰልክ እኮ! ለአንተ ከሰው የተለየ ስድሳ አራት ጥርስ የሰጠሁህ ነው እኮ ያስመሰልከው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ምን መሰለህ እንዲህ ደስ በሚል ድምጽ ስታናግረኝ በቃ ምን ልበልህ፣ ሁለመናዬ…
አንድዬ፡- ቆይ…ቆየኝ! እንደዚህ ማለት ከዚህ በፊት አንተን የማናግርበት ድምጼ መጥፎ ነበር ማለት ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡- እንደሱ ለማለት ፈልጌ አይደለም፣ አንድዬ!
አንድዬ፡- ሲያሰኛችሁ እኮ እዛ ታች ሆናችሁ የምትሉትን ሁሉ እሰማለሁ፡፡ ለምን አንደኛውን ክፉ ነህ አትለኝም!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ! እንዴት እንደሱ እላለሁ! ምን ቆርጦኝ ነው እንደዛ የምለው!
አንድዬ፡- አንተ ብቻ ሳትሆን ብዙዎቻችሁ ግርም ትሉኛላችሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜማ የምትሉኝን ላለመስማት ጆሮዎቼን ግጥም አድርጌ ልይዝ ምንም አይቀረኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ! በእርግጥ አንዳንዴ አፍ እላፊ እናበዛለን፡፡ ግን እኮ፣ አንድዬ፣ ለክፋት ብለን አይደለም፡፡ የረሳኸን እየመሰለን ሆድ ሲብሰን እኮ ነው!
አንድዬ፡- አይደለም፣ አይደለም! እናንተ እኮ ራሳችሁ ምኑንም፣ ምናኑንም አደበላልቃችሁ ካበለሻሻችሁ በኋላ ነው ወደ እኔ ጣት የምትቀስሩት!
ምስኪን ሀበሻ፡- አን…
አንድዬ፡- …ቆይ ጣልቃ አትግባ ልጨርስ፡፡ ምን አደረግንህ፣ ምን በደልንህ ምናምን ስትሉኝ ሁልጊዜ እነግራችኋለሁ። እኔን ራሳችሁ ካበለሻሻችኋቸው ነገሮች ውስጥ አውጡኝ፣ ባልዋልኩበት አታውሉኝ  እላለሁ፣ አልልም?
ምስኪን ሀበሻ፡- እሱማ…እሱማ ትላለህ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- እና፣ የእኔ እጅ በሌለበት ጉዳይ ለምን ስሜን እያነሳችሁ የአቤቱታ መአት ታወርዱብኛላችሁ! እንደውም ልንገርህና ነገራችሁ ሲበዛብኝ አንዳንዴ ሁላችሁንም እጠረጥራችኋለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- በምን አንድዬ! በምንድነው የምትጠረጥረን?
አንድዬ፡- እኔ ላይ ግልበጣ ለማካሄድ የምታስቡ እየመሰለኝ ነዋ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ! አን…
አንድዬ፡- ረጋ በላ! ደግሞ ቀስ ብለህ ተናገር፡፡ ለአንድ ከተማ ህዝብ የምታወራ ነው እኮ የምትመስለው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ ምን አድርገን! በየትኛው ሀጢአታችን ነው ግልበጣ ያስባሉ ብለህ ያሰብከው?
አንድዬ፡- ያልኩት ታስባላችሁ ብዬ እጠረጥራለሁ ነው እንጂ ታስባላችሁ አይደለም፡፡ አየህ ከዚህ በፊትም ነግሬሃለሁ፣ ምድር ላይ ትልቁ ችግራችሁን እዚህ ይዘህ መጣህ፡፡ የምትሰሙት ለመስማት የምትፈልጉትን ነው እንጂ የተባለውን አይደለም፡፡ እሱን ነገር አልተው ብላችኋል፡፡ አሁን እሱን እርሳውና አንተም እኮ ስትመጣ ፊትህ ከሌላው ጊዜ ይልቅ በራ ብሎ ነበር፡፡ አዲስ ነገር አለ እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ሆነ ብለህ ነው አይደል እንዲህ የምትለኝ! አሁን ሳታውቅ ቀርተህ ነው! እዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ የአንተ እጅ ሳይኖርበት ቀርቶ ነው?
አንድዬ፡- ጎሽ! እንዲህ ማመስገን ስትለምዱ ጥሩ ነው፡፡ ሲመቻችሁና ጥሩ ነገር ስታገኙ ማመስገን እኮ ብዙም አልለመደባችሁም፡፡ ችግር ሲመጣ ደግሞ የማትሉኝ ነገር የለም። እንደውም ልንገርህ አይደል፣ አንዳንድ የምትናገሯቸውን ነገሮች ስሰማ ነው እነዚህ ሰዎች ምን አስበውብኝ ነው የምለው!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፤ እስከዚህ የሚያስከፋ ነገር ተናግረን!
አንድዬ፡- የሚያስከፋ! የሚያስከፋ ብቻ ቢሆንማ ምንም አልነበረም፡፡ ጭራሽ ወይ ውረድ፣ ወይ ፍረድ እያላችሁ ታስጠነቅቁኝ የለ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፤ እሱ እኮ ልመና ነው እንጂ ማስጠንቀቅ አይደለም! ስንበሳጭ፣ ግራ ሲገባን እኮ ነው እንደዛ የምንለው፡፡
አንድዬ፡- እሺ ፍረድ ማለታችሁ ይሁን ልበል፡፡ ወይ ውረድ ማለትን ምን አመጣው?....እኮ መልስልኛ፣ ምነው ዝም አልክ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ...እኔ በዛ መልኩ አስቤበት ስለማላውቅ ምን እንደምል ግራ ገብቶኝ እኮ ነው፡፡
አንድዬ፡- በል እኔም ለቀልድ ያህል ነው። ደግሞ ምድር ላይ ስንት ሥራ እያለብህ ትቀልዳለህ ወይ እንዳትለኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- አንተ ሰው ደግሞ ይሄ በትንሽ ትልቁ የምትደነግጠውን ነገር ተወኝ፡፡ እሺ፣ ዛሬ መቼም ያለ አንድ ምክንያት  አልመጣህም፡፡ መቼም መወፈር መቅጠኔን ልታይ አይደለም፣ ነው እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ እን...እንደሱ ስትል ይከ…
አንድዬ፡- እንደሱ ስል ይከፋሃል፡፡ በል አሁን ልትነግረኝ የምትፈልግው ነገር ካለ ንገረኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ መቼም እየሆነ የነበረውን ያን ሁሉ ጉድ ስትታዘብ ቆይተሀል። አንድዬ፣ ቢከፋ ቢከፋ የሰው ልጅ እንዲህ ይከፋል! ጭካኔስ ቢሆን ልክ የለውም?...አንድዬ ምነው ዝም አልከኝ?
አንድዬ፡- ዝም አልኩህ፣ አይደል?
ምስኪን ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ፣ ተለዋወጥክብኝ እኮ! አስከፋሁህ እንዴ!
አንድዬ፡- አንተ ይሄ አስከፋሁህ፣ ምን አልኩህ የምትለውን ንግግር ተወኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ምን መሰለህ ምስኪኑ ሀበሻ፣ መቼም እንዲህ ስልህ ግራ ይገባህ ይሆናል። በአጭሩ እኔም ግራ ገብቶኛል ልልህ ነው፡፡ እኔም እንዲህ አይነት ጥፋት የመጣው በእኔ ስህተት ነው ወይ እያልኩ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ኧረ አንድዬ፣ እንደሱ ብሎ ነገር የለም፡፡ ሁላችንን እኩል አድርገህ አይደል እንዴ የፈጠርከው!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ አሁን ያልከውን እውነት ከልብህ ታምንበታለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- ምኑን አንድዬ?
አንድዬ፡- ሁላችንንም እኩል ነው የፈጠርከን ያልከውን...
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እሱን ያላመንኩ ምን ላምን ነው!
አንድዬ፡- ግን ደግሞ ምድር ላይ እኩል እንደፈጠርኳችሁ የማታምኑ ብዙዎች እንዳላችሁ አውቃለሁ፡፡ ገሚሶቻችሁ እኔ የተለየ ዙፋን የሰጠኋችሁ ይመስል በሌላው ላይ ስትኮፈሱ ሳይ አዝናለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደእሱ የሚያደርጉት እኮ እነኚህ ዘረኞቹ ፈረንጆች ናቸው...
አንድዬ፡- ወዴት፣ ወዴት! እኔ እያወራሁ ያለሁት ስለፈረንጅ አይደለም፡፡ ፈረንጅን ከእኛ አስበልጠህ እያላችሁ የምትከሱኝማ ሁልጊዜ ነው፡፡ አሁን እያወራሁት ያለሁት ስለ እናንተ፣ ስለ እያንዳንዳችሁ ነው፡፡ ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ በየጓዳችሁ የምትባባሉትን አልሰማ መሰለህ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ያስቆጣህ ገብቶኛል፡፡ ግን እኮ ስንበሳጭ...
አንድዬ፡- ስንበሳጭ! ስንበሳጭ! ስንበሳጭ! በቃ የእናንተ ብስጭት አያልቅምና ሁላችሁም ራሳችሁን ምርጦቹ የእኔ ፍጡራን አድርጋችሁ ሌላውን ረግሜ የፈጠርኩት እያስመሰላችሁ ማናችሁስ የምትሉኝን እንዴት አድርጌ ነው የምሰማው!
ምስኪን ሀበሻ፡- አን... አንድዬ፣ ተቆጣህ እንዴ!
አንድዬ፡- ስማኝ...ይሄ ስለጭካኔ ያልከው ነገር እኔንም ግራ የገባኝ ነገር ስለሆነ ሌላ ጊዜ ስትመጣ አንሳብኝና ያኔ ምናልባት የምለው ነገር ይኖረኝ ይሆናል፡፡ የሚያብለጨልጨው ሁሉ ወርቅ አልሆን እያለኝ ነው እኮ ግራ የገባኝ፡፡ በል ደህና ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!Read 1015 times