Saturday, 11 December 2021 13:54

ልጅን ለመውለድ የሚያግዝ ተፈጥሮአዊ ዘዴ፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 ልጅን ላለመውለድ ምንም መከላከያ ሳይወስዱ ጥንቃቄ በማድረግ መከላከል ይቻላል፡፡ይህ ሲባል ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ቁምነገር ያስነበበው Health Line የተባለ ድረገጽ ነው፡፡ ልጅን ለመውለድ ወይንም ላለመውለድ ሲባል በተፈጥሮአዊ መንገድ መገደብም ሆነ መፍቀድ የሚቻለው በምን መንገድ እንደሆነ ሲያስረዳ ዋናው መንገድ የወር አበባ አመጣጥና አካሄድ ነው ይህም Fertility awareness method (FAM) በሚባለው ዘዴ ጥቅም ላይ መዋል ሲቻል ነው ይላል ፡፡  
የወር አበባ በመጣበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ከወሲባዊ ግንኙነት መታቀብ የጥንዶች ፍላጎትም ድርጊትም ነው፡፡ የወር አበባን አመጣጥና አካሄድ በመቆጣጠር ወይንም በመረዳት ልጅን ለመው ለድ መዘጋጀት ወይንም ላለመውለድ ማሰብ ለሁሉም ሰው በተመሳሳይ ይሰራል ለማለት ያስቸ ግራል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ሴቶች የወር አበባ አመጣጥ ጊዜው ስለሚዛባበቸው ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ነገር የሚገጥ ማቸው ሴቶች ወደሕክምናው በመሄድ እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
እርግዝናን ለመከላከልም ሆነ ላለመከላከል ከወር አበባ ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያውቁ ሴቶች ፕሮግራማቸውን በትክክል ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ልጅ ለመውለድም ሆነ ላለመውለድ የእርግዝና መከላከያን መውሰድ ወይንም አለመውሰድ ጥሩው አማራጭ መሆኑ አይካድም፡፡
አንዲት ሴት የወር አበባዋ ለመቋረጥ ያልደረሰች (premenopausal) ወይንም በመውለድ እድሜ ላይ ያለች ከሆነች እና ጥንቃቄ ሳይደረግ ወሲባዊ ግንኙነት ከፈጸመች እርግዝና የሚፈጠርበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ማህጸን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ጊዜ እንቁላልን ከማህጸን ይለቃል፡፡ ይህም የሚሆነው የወር አበባ ከመጣና ከሄድ በሁዋላ ከ12-16 ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ነው፡፡ ይህ ጊዜ መቼ ነው የሚለው የሚወሰነው በሴትየዋ የወር አበባ መምጫ ቀንና የሚቆይበት ጊዜ ምን ያህል ነው በሚለው ነው፡፡ ይህን ነገር በአብዛኛው የሚቆጣጠረው ያለው የሆርሞን ደረጃ ነው፡፡
አንዳንድ ሴቶች የወር አበባቸው አመጣጥና አካሄድ ከወር ወር ተመሳሳይ ሆኖ የሚቀጥልበት
አጋጣሚ ይስተዋላል፡፡ ሌሎች ደግሞ የወር አበባቸው መቼ እንደሚመጣ እና መቼ እንደሚሄድ በትክክል የማይታወቅበት ሁኔታ አለ፡፡ እርግዝና ሳይፈጠር እንቁላል ከተለቀቀ 14 ቀን በሁዋላ የወር አበባ ይመጣል፡፡
እንቁላል ከከረጢቱ አንዴ ከወጣ በህይወት የመቆየት እድሜው በጣም አጭር ነው፡፡ እንቁላል ከማህጸን ከተለቀቀ በሁዋላ ግንኙነት ከተደረገ እና ከ24-48 ሰአት ጊዜ ውስጥ መልማት ከጀመረ እርግዝና በመፈጠር ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የወንዶች የዘር ፍሬ (sperm) በማህጸን ውስጥ በህይወት እስከ አምስት ቀን ድረስ መቆየት ይችላል፡፡ ስለዚህም እስከ አምስት ቀን ባለው ጊዜ የግብረስጋ ግንኙነት በመፈጸምም እርግዝናን ማሳካት ይቻላል ይላል መረጃው፡፡
ይህ ተፈጥሮአዊ ሂደት ለአብዛኛዎቹ ሴቶች እርግዝናን ለማሳካት የሚያስችል ሲሆን ለእርግዝና የሚያበቃው ጊዜ ከአምስት ቀን እስከ ስምንት ቀን ድረስ ይገመታል፡፡ በአጠቃላይ ግን ብዙ ሴቶች በሚከተሉት ቀናት ውስጥ በአብዛኛው እርግዝናን ሊያሳኩ ይችላሉ፡፡
እንቁላል ከመለቀቁ አምስት ቀን ቀደም ብሎ፤
ልክ እንቁላል በሚለቀቅበት ቀን፤
እንቁላል ከተለቀቀ ከ12-24 ሰአት በሁዋላ፤
ሴቶች እንደየተፈጥሮአቸው ሁኔታ የወር አበባቸው ኡደት የተለያየ ነው፡፡ ስለዚህም ልጅን ለመውለድ የሚያስችላቸውን ተፈጥሮአዊ ሂደት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም በትክክል እንቁላል የሚለቀቅበትን ጊዜ መገመት ይጠቅማል፡፡ የወር አበባን ኡደት እና የእንቁላልን የመለቀቅ ሁኔታ ለማስተካከልና ለማወቅ የሚያግዙ ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ እነዚህ መንገዶቸም የሚከተሉት ሲሆኑ እነዚህን በመጠቀም በተሻለ ሁኔታ እርግዝናን መያዝ እንዲሁም እስከመጨረሻው ተንከባ ክቦ ማድረስ ይቻላል፡፡ እነዚህ መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
የቀን መቁጠሪያ ማዘጋጀት፤
ባለፈው ወር የወር አበባ የመጣበትን ጊዜ ማወቅ በየትኛው ቀናት እንቁላል ይለቀቃል የሚለውን ለመገመት ይረዳል፡፡ ይህንን በቀጥታ መጠቀም በመጠኑ እንደ ወሊድ መቆጣጠሪያ ያገለግላል፡፡ የወር አበባው አመጣጥ ከ26 ቀን በታች ከሆነና የቆየበት ጊዜም ከ32 ቀናት በላይ ከሆነ ለአገልግ ሎት ሊውል አይችልም፡፡
የሙቀት መጠን፤
የሰውነትን ሙቀት መጠን በሙቀት መለኪያ ሁልጊዜ መከታተል ይገባል፡፡ ይህም የሚደረገው ሁልጊዜ ጠዋት ከመኝታ ከመነሳት እና ከአልጋ ከመውጣት በፊት ነው፡፡ ለእርግዝና ዝግጁ ለመሆን እንቁላል በተለቀቀበት ወቅት የሙቀት መጠኑ ከፍ ይላል፡፡
በማህጸን በር በኩል የሚታይ ፈሳሽ፤
በማህጸን በር በኩል የሚታየው ፈሳሽ መልኩ፤ውፍረቱ እና ጠረኑ በእርግዝና ምክንያት ነው ወይንስ አይደለም የሚለውን ለማወቅ ይረዳል፡፡ በማህጸን በር በኩል የሚታየው ፈሳሽ መወፈርና የመጎተት ባህርይ ካለው እንቁላል ተለቆአል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ይህን ለመለየትና ለማወቅ የተወሰኑ ልምዶች እንዲኖሩ ያስፈልጋል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ሶስት ነጥቦችን በሰውነት ላይ ካገኙ ዘዴው ስለእርግዝና ለማወቅ ትክክለኛው መንገድ Fertility awareness method (FAM) ይሆናል፡፡ እነዚህን ነጥቦች በትክክል ለማወቅ ግን ቢያንስ ቢያንስ ከ6---12 የሚሆኑ የወር አበባ ኡደቶች ላይ ልምድን መቅሰም ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ እነዚህ ጊዜያት ወደ ወሊድ መቆጣጠሪያ ከመሄድ በፊት የሚፈለጉ ናቸው፡፡   
Fertility awareness method (FAM) የሚባለው ዘዴ ጠቀሚ ወይንም ውጤታማ እንዲሆን አስቀድሞ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ይገባል፡፡
እርግዝናን ለመከታተል የትኛውን ዘዴ ተጠቅመዋል?
የወር አበባው መምጫ ጊዜ ምን ያህል የተስተካከለ ወይንም ያልተዛባ ነው?
የወር አበባን መምጫና ማብቂያ የተቆጣጠሩበት ዘዴ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?
እንቁላል በሚለቀቅበት ሰሞን ለምን ያህል ጊዜ ግንኙነት ፈጽመዋል ወይንም ታቅበዋል ?
እርግዝናን ለመከታተል የሚረዳው ተፈጥሮአዊ ዘዴ ሁለቱም ማለትም ወንድየውም ሆነ ሴትየዋ ተባብረው በትክክለኛ እና በተከታታይ የሚከታተሉት ከሆነ ውጤታማ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ይህ ከባድ ሊመስል ይችላል፡፡ ይህንን ዘዴ ከሚጠቀሙ መቶ ሴቶች 24 ያህሉ በየአመቱ ያረግዛሉ፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፡፡ ይህ ዘዴ እጅግ ጠቃሚ ነው ሲባል ለምሳሌም፡-
በትንሽ ዋጋ፤
ለመጠቀም ደህንነቱ የተረጋገጠ፤
የሐኪም እርዳታ የማያስፈልገው፤
የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው፤
ምንጊዜም እርግዝናው ካልተፈለገ ወይም ከተፈለገ እንደአመቺነቱ Fertility awareness method (FAM) ሊደረግ ወይንም ሊቋረጥ ወይንም በቀላሉ ሊቆም የሚችል ነው፡፡
ይህንን ዘዴ ተአማኒ ለማድረግ ቢያንስ ቢያንስ ለ6 ወራት የወር አበባ አመጣጥና አካሄድን ማጥናት ይገባል፡፡
እርግዝናን በመፈለግ የሚደረገውን ግንኙነት ወይንም ባለመፈለግ የሚደረገውን መታቀብ ውጤታማ እንዲሆን Fertility awareness method (FAM)ን መጠቀም ይጠቅማል፡፡
ውጤታማ ለመሆኑ ሁለቱም ተጋቢዎች ወይንም ጉዋደኛሞች መተባበር አለባቸው፡፡
የወር አበባ መዛባት የሚገጥም ከሆነ ሐኪምን ማናገር ጠቃሚ ነው፡፡  

Read 12999 times