Saturday, 11 December 2021 14:17

ነ ፃ ነ ቴ !

Written by  ነፃነት አምሳሉ
Rate this item
(5 votes)

   ነ ፃ ነ ቴ !
      
ወዲያ በል እያለ - እያገሳ ልቤ
በል ተነስ ይለኛል - ይሄ ቅዱስ ቀልቤ
ፍጠን በተራራ - ዝለል በባህሩ
እንደ ደረቅ ቅጠል
ይርገፉ በተራ - አንተን የሚደፍሩ !
-*-
የምን ብርድ ነው እቴ? - የምን ቁር እትት?
ጥላው ግፍፍ ይላል - ፍርሃት ቁርጥማት !
ሀዘን እንደ ጤዛ - ትንን ብሎ ጠፍቶ
መንፈስ ይታደሳል - አዲስ ስሜት ገዝቶ !
ውሽንፍር መብረቁ - ዶፍ ዝናብ ቢወርድም
ሀገር የለበሰ
በረደኝ እያለ - ፍም እሳት አይሞቅም!
-*-
ክንብንብ!
ሽፍንፍን! - እንደ ጠዋት ፍርፍር
ድምቅምቅ!
ፍክትክት! - እንደ ንጋት ጀምበር
ፍንድቅድቅ ሲያረገኝ - ጥርሴ ፊቴን ሞልቶ
አሁን በዚህ መንደር
እኔን መሳይ ንጉስ - ከወዴት ተገኝቶ ?
ድሮስ ከጥንታችን
ከአበው ትዝታችን
ሀገር የለበሰ
ሀገር የወረሰ
ድንገት እግር ጥሎት - ሲታይ በመንገዱ
እውነትና ታሪክ
ትከሻ እስኪነቀል - እስክስታ ወረዱ !
-*-
እሳት ከትከሻው የሚነድ አርበኛ
ሞገድ ከአንደበቱ ሚወጣ ዋናተኛ
ክንዱ ረመጥ አዝሎ ተራራ ሚወጣ
ቃሉ ባህር አልፎ አድማስ ላይ ሚቆጣ
እግሩ ባህር ዘልሎ ስሙ ምሽግ ሰብሮ
ድንበር ላይ ሚያፈራ
የበረሃ አበባ ጉድ አየሁ ዘንድሮ
-*-
ህብረ ቀለም ውህድ - ዓይን ማሳረፍያ
ደም አጥንት ያስገኘው - የህይወት ክፍያ
የሳጥን ውስጥ ወርቄ የእናት አባት ውርሴ
ተገምደሻል ውዴ - ከሥጋ ከነፍሴ !
-*-
ዘመን ያልበገረው - የአለት ላይ ቤቴ
የትናንት ቀለሜ
የነገ ውጥን ህልሜ
ማደርያ ሰላሜ
የፍቅር ህመሜ
ሥጋ ነፍስ እውነቴ - ሃቅ ማተብ እምነቴ
የዛሬ ብርታቴ
የነገ ትጋቴ
የልጅነት ሀብቴ
ገጸ-በረከቴ
የዘመን ላይ ጽሑፍ - የማትደርቅ ዥረቴ
የአበው ውርስ አደራ
ይቺ ናት ባንዲራ
አረንጓዴ ቢጫ - ቀይ ነፃነቴ !

Read 2062 times