Saturday, 18 December 2021 14:24

ጥቃትን ለመከላከል የወንዶች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 እ.ኤ.አ November 25 በኢትዮጵያ አቆጣጠር ህዳር 16/2014 በአለም አቀፍ ደረጃ የነጭ ሪቫን ቀን ተብሎ የተሰየመ ሲሆን አላማውም በተለያየ መንገድ በሴቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት ለማስወገድ ነው፡፡ ይህ ቀን በየአመቱ ሰዎች ስለችግሩ እውቀት እንዲኖራቸውና ንቃተህሊና  ቸውን አዳብረው ድርጊቱን እንዲከላከሉ የሚያግዝ እንዲሆን  የታሰበ ሲሆን በዚህም ቤተሰብ በሴቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠብ የሚያስችል ነው፡፡ የነጭ ሪቫን ቀን November 25 ጀምሮ በተከታታይ ለ16 ቀናት ያህል በተለይም ወንዶች በደረታቸው ላይ አድርገው በሴቶች ላይ የሚደርስን የተለያየ ጥቃት የማይፈጽሙበትና የሚቃወሙበት ነው፡፡ በተለያዩ መንገ ዶች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በአለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋልና መቀረፍ ያለበት ችግር ነው፡፡
በ2021 የዋለው የነጭ ሪቫን ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ በተለያየ ደረጃ ለ16 ቀናት ያህል በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ይቁም በሚል ስሜት ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው፤ በአካባቢያቸው፤ በስራ፤ በስፖርት፤ በትምህርት ቦታዎች እና በሚገናኙባቸው ቦታዎች ሁሉ ይህ ድርጊት በሴቶች ላይ ለምን ይፈጸማል የሚል ጥያቄ እንዲያቀርቡ እና በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት መኖር የለበ ትም እንዲሉ ይመክራል፡፡  
ከላይ የተገለጸውን ሀሳብ ለመግለጽ በምሳሌነት ወንዶች ቀድመው መገኘታቸው ለጾታ እኩልነት የሚሰጠውን ግምት ከፍ ስለሚያደርገው ለውጡን ያፋጥነዋል የሚል እምነት አለ፡፡ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ የየራሳቸውን ድርሻ በሁሉም ቦታ በመወጣት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለምን ይደርሳል ማለት አና በቃ ማለት ይገባል፡፡ ወንዶች ይህንን ችግር እንዲያበቃ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡   
የነጭ ሪቫን ቀንን የጀመሩት በካናዳ የሚኖሩ ወንዶች ናቸው፡፡ ወንዶች ሴቶችን መጉዳት አልፈልግም፤ ሲጎዱም ዝም ብዬ አላይም፤ በሚል ስሜት እንዲከበር የፈለጉት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማያውቁ ማሳወቅና ሴቶችን ከጉዳቱ መከላከል የሚቻልበትን እና በምን መንገድ መከላከል ይቻላል በሚለው ላይ ለመስራት ነው፡፡ ይህንን ሀሳብ የተረዱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶች በመጀመሪያው አመት November 25 ነጭ ሪቫንን በደረታቸው በማድረግ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ተቃወሙ፡፡ ይህ ጅምር እ.ኤ.አ በ1991 ሲሆን ይህ ቀን ከዚያ በሁዋላ ከካናዳ ውጭ በመስፋ ፋቱ ወደ አለም አቀፍ ደረጃ አድጎ በአለም አቀፍ ደረጃ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡
ለመሆኑ ሴቶች በምን መልክ ከጉዳት ላይ ይደርሳሉ የሚለውን በመጠኑ አንደሚከተለው ማስነበብ ወደድን፡፡
ሴቶች የጾታ እኩልነት ስለሚነፈጋቸው ማንኛውም የቤት ውስጥ አስተዳደር በወንዶች እንዲመራ እና እንዲወሰን በማድረግ ሴትዋ ለኑሮዋ ምንም አይነት ተሳትፎ እንዳታደርግ የሚኖሩት አጋጣሚዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይነት አለው፡፡ በዚህም ምክንያት በራስዋ ሕይወት በተለይም በስነተዋልዶ ጤና፤ በቤተሰብ እቅድ ዘዴ በመሳሰሉት የእስዋ ፍላጎት ሳይታይ በወንድየው ስሜት ብቻ የሚመራ ይሆናል፡፡
ሴቶች ብዙውን ጊዜ በልጆቻቸው ሕይወትም ሆነ በኢኮኖሚያቸው ላይ ምንም አቅም እንዳይኖ ራቸው ተደርጎ በወንዶች ተጽእኖ ስር የሚወድቁባቸው አጋጣሚዎች በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታይ ጾታዊ እኩልትን የነፈገ እውነታ ነው፡፡
ሴቶች በትምህርት ደረጃ ከፍ ወደ አለ ተቋም እንዳይደርሱ ብዙ ማእቀቦች ይደርሱባቸዋል። እሱም ተገዶ መደፈር፤ የልጅነት ጋብቻ፤ጠለፋ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
ሴቶች በትምህርታቸው ተፎካካሪ ቢሆኑም እንኩዋን ከወንዶች እኩል ቦታ ያለማግኘትና ቢያገኙም እንኩዋን ተገቢውን እድገት ወይንም ደረጃ እንዳያገኙ ማድረግ ሌላው በሴቶች ላይ የሚፈጸም በደል ነው፡፡
የአለም የጤና ድርጅት እንደሚገልጸው በአለም አቀፍ ደረጃ ከ3 ሴቶች አንድዋ ወይንም (30%) የሚሆኑት በህይወት ዘመናቸው አብረዋቸው በሚኖሩ ወይንም በፍቅር ተጋሪዎቻቸው ወይንም በሌሎች አማካኝነት የአካል ወይንም የሞራል ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በአካል፤ በስነልቡናና፤ ጾታዊ እንዲሁም ኤችአይቪን ጨምሮ  በስነተዋልዶ ጤናቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስባቸዋል፡፡ ጎጂ ልማዳዊ (ግርዛት)ድርጊቶችም ይፈጸሙባቸዋል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ሊከላከሉት የሚችሉት አደጋ ነው፡፡ ከምንም በላይ ችግን የመከ ላከያ ዘዴው ድርጊቱን አለመፈጸም ነው፡፡ ይህ የ16 ቀን የነጭ ሪቫን ቀናት ይህንን የሚመክር ነው፡፡ ወንዶች በደረታቸው ላይ ነጭ ሪቫንን በማድረግ እኔ ሴቶችን በማጥቃት ወይንም በመጉ ዳት ጉዳይ አልሳተፍም ወይንም ጥቃት ሲፈጸም ዝም አልልም የሚል ስሜት ያለው መልእክት በወንዶች ሲተላለፍ ወንዶች በሴቶች ላይ ጥቃት እንዳይፈጽሙ ለመከላከል ያስችላል፡፡
አለም አቀፉ ሪፖርት እንደሚመሰክረው በአለም ላይ እድሜአቸው ከ15-49 የሆኑ ከ1/4ኛ በላይ የሚሆኑ ሴቶች በአካል ወይንም በስነልቡናቸው ላይ ከተዘረዘሩት ጥቃቶች መካከል አብሮአቸው በሚኖር ወንድ ወይንም በሌላ ቢያንስ አንድ ጊዜ በህይወት ዘመናቸው ደርሶባቸዋል፡፡ ጥቃቱ ምን ያህል እንደሆነ የአለም የጤና ድርጅት እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡
አብረው በሚኖሩ ወንዶች ወይንም በሌሎች ወንዶች በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት፡-
በምእራብ ፓሲፊክ 20%
ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገራትና በአውሮፓ 22%
የአለም የጤና ድርጅት በሚከታተላቸው የአሜሪካ ግዛቶች ወደ 33%
የአለም የጤና ድርጅት በሚከታተላቸው የአፍሪካ አገራት 31%
የአለም የጤና ድርጅት በሚከታተላቸው ሜዲትሬንያን ዞን እና ደቡብ ምስራቅ ኤሽያ 31% ይሆናል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ከሚደርሱ የሞት መጠኖች ወደ 38% የሚሆኑት የሚደርሱ ባቸው አብረዋቸው በሚኖሩ ወይም ቅርብ በሆኑ ወንዶች አማካኝት በሚደርስ ጥቃት መነሻነት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ 6% የሚሆኑ ሴቶች ከባሎቻቸው ወይንም ፍቅረኞቻቸው ውጪ በሆኑ ሰዎች ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው መሆኑን ሪፖርት ማድረጋቸ ውን የአለም የጤና ድርጅት ገልጾአል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ በነበረው በቤት ውስጥ መቆየት ወይንም ከቤት ሆኖ መስራት እና ወደቢሮ ወይንም ወደውጭ አለመሄድ በመሳሰሉት እርምጃዎች ምክንያት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲጨምር አንድ ምክንያት ሆኖ እንደነበር ተስተውሎአል፡፡ ሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች ለአካላዊ ወይንም ሞራላዊ እንዲሁም ለስነልቡና ጥቃት መጋለጣቸው በተደጋጋሚ የተገለጸ ነው፡፡
ወንዶችና ወንድ ልጆች በየአመቱ November 25 ጀምሮ ለተከታታይ 16 ቀናት ነጭ ሪቫን በደረታቸው አድርገው መታየታቸው ወንዶች በሴቶች ላይ የሚያደርሱትን የተለያዩ ጥቃቶች ማስቀረት እንዲቻል ያለመ መሆኑ ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ነው፡፡
አለም አቀፉ የነጭ ሪቫን ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ ተከብሮአል፡፡ ኖቨምበር 2021 ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ከነጭርሱ እንዲወገድ የሚል አቋም የያዘ ነው ይላል በኢትዮጵያ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀውን ፓናል ውይይት የተሳተፈው ፕላን ኢንተርናሽናል ፡፡   
በአለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በእጅጉ አሳፋሪ ነው፡፡ የሚፈጸመውም በአብ ዛኛው በወንዶች ሲሆን ጾታዊ የበላይነትን ወይም እኩልነት ያለመኖሩን ማሳያ መንገድ ነው፡፡ ይህ የመብት ጥሰት በየአመቱ እንዲወገድ የተለያዩ ውይይቶች ቢደረጉም ሊወገድ ግን አልቻ ለም፡፡ የነጭ የሪቫን ቀን ይህንን ለመቅረፍ ያግዛል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ወንዶችና ወንድ ልጆች በየአመቱ November 25 ጀምሮ ለ16 ቀናት በደረታቸው ላይ ነጭ ሪቫንን ለ16 ቀናት በማድረግ በሴቶች ላይ ጥቃት አላደርስም፤ጥቀት ሲደርስም ዝም ብዬ አልመለከ ትም፤ይቅርታም አላደርግም የሚለውን መልእክት ስለሚያስተላልፉ ይህ ችግሩን ለማስቆም ጠቃሚ ቃልኪዳን ነው፡፡  

Read 10889 times