Tuesday, 21 December 2021 00:00

በአፍሪካ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር በሳምንቱ በ83 በመቶ ጨምሯል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  • ኦሚክሮን ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት በመዛመት 77 አገራትን አዳርሷል
   • ኦሚክሮን በአሜሪካ ካጠቃቸው 80 በመቶው ሙሉ ለሙሉ የተከተቡ ናቸው

           ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ አህጉር የተመዘገበው የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ካለፈው ሳምንት ጋር ሲነጻጸር በ83 በመቶ ያህል ጭማሪ ማሳየቱንና በሳምንቱ በአህጉሪቱ ከ196 ሺህ በላይ አዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውን የአለም የጤና ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን ኦሚክሮን የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ የቫይረሱ ዝርያ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ከፍተኛ ፍጥነት በመላው አለም በመሰራጨት 77 የአለም አገራትን ማዳረሱ ተነግሯል፡፡
ከ9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ በተጠቁባት አፍሪካ የአዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር በየ5 ቀኑ በእጥፍ ያህል እያደገ እንደሚገኝ ድርጅቱ ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ ማስታወቁን የዘገበው ሮይተርስ፤ በሳምንቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ምክንያት የሆኑት በስፋት በመሰራጨት ላይ የሚገኙት ዴልታ እና ኦሚክሮን የተባሉት የቫይረሱ ዝርያዎች ናቸው መባሉንም አስነብቧል፡፡
እስካለፈው ሰኞ ድረስ 10 በመቶ ያህል ዜጎቻቸውን መከተብ የቻሉት የአፍሪካ አገራት 20 ብቻ መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎንና ቻድን የመሳሰሉ አንዳንድ አገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን መስጠት የቻሉት ከአጠቃላይ ህዝባቸው ከ1 በመቶ በታች ለሚሆነው ብቻ መሆኑንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ ኦሚክሮን የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ የቫይረሱ ዝርያ ከሌሎች ዝርያዎች በተለየ ከፍተኛ ፍጥነት በመላው አለም መሰራጨት መቀጠሉንና እስካለፈው ሃሙስ ድረስ በ77 የአለማችን አገራት መግባቱ መረጋገጡን ቲአርቲ ዎርልድ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ህዳር ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ የተገኘው የቫይረሱ ዝርያ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ 77 አገራት መዛመቱ አለማችንን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደከተታት የጠቆመው ዘገባው፤ ቫይረሱ የገባባቸውና በምርመራ ያልታወቀባቸው ሌሎች ተጨማሪ አገራት ሊኖሩ እንደሚችሉ መነገሩንም አመልክቷል፡፡
ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ሞት የተከሰተባትና የሟቾች ቁጥር ሰሞኑን ከ800 ሺህ ባለፈባት አሜሪካ፤ ይሄው አዲስ የቫይረሱ ዝርያ ኦሚክሮን እስካለፈው ሳምንት ድረስ 43 ያህል ሰዎችን ማጥቃቱን ያስታወሰው ሮይተርስ በበኩሉ፣ ከእነዚህ ተጠቂዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ወይም ሰላሳ አራቱ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ሙሉ ለሙሉ የወሰዱ መሆናቸው መረጋገጡንና ይህም በስራ ላይ ያሉት ክትባቶች ኦሚክሮንን በመከላከል ረገድ ብቃት የላቸውም የሚለውን አስተሳሰብ እንዳጠናከረው ዘግቧል፡፡

Read 2880 times