Sunday, 26 December 2021 00:00

“በህዝብ የታቀፈ ሠራዊት ሁሌም አሸናፊ ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)


             ሻለቃ ታመነ አባተ ይባላሉ፡፡ የቀድሞ ሠራዊት አባል ናቸው፡፡ ከ2 ዓመት በፊት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍ እና የልማት ማህበርን ከመሰረቱና ካቋቋሙ የሰራዊቱ አባላት አንዱ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅትም ማህበሩን በስራ አስኪያጅነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ እኚሁ የቀድሞ መኮንን በሶማሊያ ወረራ ጊዜ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሰልፈው የተዋጉ ሲሆን በጦርነቱ ሶስት ጊዜ ቆስለዋል፡፡ በ1983 ከህወኃት ጋር የተደረገውን የመጨረሻውን ጦርነትም ከመሩ ወታደራዊ መኮንኖች አንዱ ነበሩ፡፡ በወቅቱም ኢህአዴግ ማሸነፉን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ውለው ለ10 ዓመት ያለ ምንም ፍርድ በእስር አሳልፈው ተለቀዋል፡፡ ሻለቃ ታመነ አባተ የህይወት ልምዳቸውን፣ ያሳለፉትን ውጣ ውረድ እንዲሁም አሁን ስላለው ጦርነት ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡

                 እስኪ ከትውልድዎና አስተዳደግዎ እንጀምር---
የተወለድኩት በቀድሞ ወለጋ ክፍለ ሀገር ሆረቱ በምትባል የገጠር መንደር ውስጥ ነው። ቤተሰቦቼ ወደ ተወለድኩበት ቦታ በስደት የመጡ አማራዎች ናቸው፡፡ እኔ እዚያው ተወልጄ ኦሮምኛ አፍ የፈታሁበት ቋንቋ ነው፡፡ የቄስ ትምህርት እዚያ ከጨረስኩ በኋላ አባቴ ትንሽ አልተማረም ግን ሃብታም ነበር፡፡ ገና ከልጅነቴ ጀምሮ አባቴ በቀለም ትምህርት ገፍቼ እንድማር ይፈልግ ነበር፡፡ እኔ ግን የልጅነቱ ሁኔታም ይዞኝ አሻፈረኝ ብዬ ገና በልጅነቴ ነው ከአባቴ ኪስ ብር ሰርቄ የጠፋሁት፡፡  እዚያው ወለጋ እኛው የነበርንበት ባኮ የሚባል ቦታ ነበር የቆየሁት። በወቅቱ እናትና አባቴ ተለያይተው ነበር። እናቴ ከአባቴ ከተለያዩ በኋላ ባኮ ነበር የምትኖረው፡፡ እኔም ከእናቴ ጋር ኑሮ ጀመርኩ፡፡ በዚያው በባኮ ከ1-4ኛ  ክፍል ተምሬ፣ ከ4-8 ደግሞ ኢሉባቡር የእናቴ ታናሽ እህት ነበረች፤ እሷ ጋ ሄጄ ተማርኩ። ከዚያ ከ9-12 ያለውን አምቦ ሃይስኩል ነው የተማርኩት፡፡ 12ኛ ክፍል ካጠናቀቅሁ በኋላ በፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ በምስራቅ በረኛ ምድብ (ሃረር) በስፖርተኛነት ተቀጥሬ ሄድኩኝ፡፡ እዚያ እንደደረስኩ የፈጥኖ ደራሽ ትምህርት ስልጠና በእስራኤል ሰልጥኜ ገና ሳላጠናቅቅ ሶማሊያ ውጊያ ስለተከፈተ በቀጥታ ወደ ውጊያው ገባሁ ማለት ነው፡፡ ያኔ በውጊያው መሃል ሶስት ጊዜ ቆስያለሁ፡፡
በዚያ ጦርነት ሙሉ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ ጦርነቱ ካበቃ በኋላም ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሲፈርስ ወደ የኢትዮጵያ ሠራዊት 3ኛ ክፍለ ጦር ተቀላቀልኩ። በኋላም 3ኛ ክፍለ ጦር ወደ ሰሜን ሲሄድ እኔ ሃረር አካዳሚ ለተጨማሪ ትምህርት ገባሁ፡፡ በኋላም ከሃረር አካዳሚ በም/መቶ አለቃነት ተመርቄ እንደወጣሁ ሁርሶ ማሰልጠኛ ማዕከልን በአሰልጣኝነት ተቀላቀልኩ፡፡ በዚያ አሠልጣኝነቴ በርካታ መኮንኖች አሰልጥኛለሁ፡፡ በ1978 ለተጨማሪ ትምህርትና ስልጠና ወደ ራሺያ ተላኩ። በዚያም ከፍተኛ የደህንነት ትምህርት ተምሬያለሁ፡፡ በ1980 ከራሺያ ወደ ሃገር ቤት እንደተመለስኩ በጥቂት ጊዜ በአሰልጣኝነት ቀጥዬ ነበር፡፡ ነገር ግን ኋላ ላይ ወደ ሰሜን ሄጄ አውደ ውጊያውን ተቀላቀልኩ። በወቅቱ ወደ ኤርትራ ነበር የሄድኩት፡፡ በ1980 ከራሺያ ስመለስ የሻለቃነት ማዕረግ ተሰጥቶኝ ስለነበር፣ በጦር መሪነት ነበር ወደ ኤርትራ የሄድኩት፡፡ በወቅቱ ኮ/ል መንግስቱ ወደ አስመራ በሚመጡበት ጊዜ ከእሳቸው ጋር ከሚሰበሰቡ 15 ሰዎች ውስጥ አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡ እንደውም በአንድ ወቅት ኮ/ል መንግስቱ መጥተው ሊሰበስቡን ስንቀመጥ አብዛኞቹ በእድሜ ጎልመስ ያሉ ጀነራሎች ነበሩ፤ እኔ በእድሜ አነስ ያልኩት ሻለቃ ነበርኩና አንድ ጥግ ላይ ነበር የተቀመጥኩት። ከዚያም ኮሎኔል መንግስቱ “አንተ ወጣት የእውነት ሻለቃ ነህ ወይስ አይኔ ነው” ብለው ነበር የጠየቁኝ፡፡ “አዎ! እንደውም እርስዎ ራሺያ በመጡ ወቅት የተማሪዎች ተወካይ ነበርኩ፤ ከዚያም ዴዴሳ ላይ የኮሪያን ም/ፕሬዝዳንት ይዘው ሲመጡ የደህንነት ሃላፊ ሆኜ ተቀብዬዎታለሁ” አልኳቸው፡፡ “የዚያን ጊዜ ማዕረግህ ምን ነበር” አሉኝ። እኔም “መቶ አለቃ ነበርኩ” አልኳቸው፡፡ በኋላም የኔ አመራሮች እነ ጀነራል ደምሴ ቡልቶ እንዴት የሻለቃነት ማዕረግ እንዳገኘሁ አስረዷቸው፡፡ በወቅቱ ያደረግነው ውይይት ወያኔ ወደ መሃል ሃገር እየመጣ ስለነበር እንዴት ግስጋሴውን እንግታው የሚል ነበር።
ይሄን ጉዳይ በስፋት ካነሱት አይቀር እስቲ ስለ መጨረሻዎቹ የጦርነት ሁኔታዎች እርስዎ ከነበሩበት አውደ ውጊያ አንጻር ይንገሩን?
እኛ ኤርትራ የነበረን ጦር 50 ሺህ ያህል ነበር በወቅቱ፡፡ ከፍተኛ ወታደራዊ መሳሪያዎቹ እኛ ጋር ነበሩ፡፡ በአራት ኮር የተደራጀ ነበር። ወታደራዊ ምክከሮችም ኮ/ል መንግስቱ እየተሳተፉበት ይካሄድ ነበር፡፡ በኋላ ግን ለስብሰባ ይመጣሉ ብለን ስንጠብቅ ነው፣ በሬዲዮ ወደ ዚምባቡዌ መኮብለላቸውን የሰማነው። በወቅቱ ኤርትራ አራቱን ኮር የሚመሩት ጀነራል ሁሴን ነበሩ፡፡ በቃ እኛ ጦርነቱን እንቀጥላለን። አራቱም ኮር በአንድ አቅጣጫ ወደ መቀሌ መገስገስ አለበት የሚል ውሳኔ ሰጡ፤ ጀነራል ሁሴን፡፡ በወቅቱ እኔ በጣም ተጠራጠርኩና “ለምንድን ነው አራቱም ኮር በአንድ አቅጣጫ እንዲሄድ የሚደረገው?” ብዬ  ስጠይቃቸው “ታመነ ጥያቄ አታብዛ፤ ትዕዛዝ ነው ትዕዛዝ ነው፤ እናንተ ደህንነቶች አንዳንዴ ዝም ብላችሁ ጥያቄ ታበዛላችሁ” አሉኝ፡፡ እኔም በውስጤ ጥርጣሬ ቢያድርብኝም የነበረኝ ምርጫ ትዕዛዙን መቀበል ብቻ ነበር፡፡ በኋላም ጉዞው ተጀመረ፤ በመጨረሻም ጀነራል ሁሴን ካሉበት ማዕከል ትዕዛዝ ተቋረጠብን። ብንደውል ምላሽ የለም፡፡ በኋላ እኔ አጃቢዎቼ ጋር ተመልሼ ወደ እዝ ማዕከሉ ስደርስ የእዝ ማዕከሉ በር ወለል ብሎ ተከፍቶ የቁስለኛ መዓት ጣር ያሰማል፤ በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ የሚያውቁኝ “እንዴ ሻለቃ እዚህ ምን ያደርጋሉ፣ እነ ጀነራል ሁሴን እኮ በሁለት ሔሊኮፕተር ተጭነው ሳውዲ አረቢያ ገብተዋል አሉኝ፡፡ በቃ በድንጋጤ ውሃ ነው የሆንኩት፡፡ ይሄን መርዶ ይዤ የኔን ምላሽ ወደሚጠብቁ ጓዶቼ ወደ ደቀ መሃሪ ተመለስኩ፡፡ መሪያችን የነበሩት ጀነራል አርአያን ብቻቸውን ጠርቼ “በቃ ጀነራል ሁሴን ወደ ሳውዲ ሸሽተዋል” አልኳቸው። በጣም ነበር የደነገጡት፡፡ “እኛ ታዲያ ምን እናደርጋለን? ይሄ  ሰራዊት እንዴት ነው  የሚያምነን? መንግስቱ ኃ/ማሪያም ትቶን ሄደ፤ አሁን ደግሞ ጀነራል ሁሴን አህመድ ትቶን ሄደ ታዲያ ይሄ ሠራዊት እንዴት ነው ከዚህ በኋላ የሚታዘዘን” አሉኝ፡፡ "ግድየሎትም ፈጣሪ ያለው ነው የሚሆነው” ብዬ አረጋጋኋቸው። የክፍለ ጦር አመራሮችን ሰብስበን ሁኔታውን ነገርናቸውና ቀጣይ እቅድ ማውጣት ጀመርን፡፡ በእነ ጀነራል ሁሴን የተቀመጠልንን መቀሌ የመግባት እቅድ ትተን ወደ ሱዳን መውጣትና ከማዕከላዊ መንግስት ጋር የተቋረጠውን ግንኙነት መቀጠል ነበር እቅዳችን። በዚህ መልኩ ጉዟችንን በከረን በኩል ጀመርን። በጉዞአችን መሃል ጀኔራል አርአያ ባሬንቱ ላይ ቆሰሉብን፤ እርሳቸውን እንዲያርፉ አድርገን ጀነራል ተስፋዬን መሪ አድርገን ጉዞአችንን ቀጠልን፡፡ ተሰናይ ላይ ምሽግ ያዝን፡፡ በወቅቱ እዚያ ቦታ ወያኔ ሻቢያና የሱዳን ወታደሮች  ሊወጉን እየጠበቁን ነበር። በወቅቱ አድፍጠው ይጠብቁን የነበረው እኛ ጋር ያለውን መሳሪያ ለመውሰድ ነበር። ታንኩ፣ ቢኤም ሁሉም እኛ እጅ ነበር። በወቅቱ የኛ ሰራዊት በጣም ተሰላችቶ ነበር፡፡ ደሞዝ አልተከፈለውም፤ በዚህ ቅሬታ ነበረው፡፡ በዚያ ላይ በማይክራፎን "ግዴላችሁም ምንም  አትዋጉ፤ እኛ እናንተን አንፈልግም" እያሉ ወያኔዎች እየቀሰቀሱብን ነበር፡፡ ሠራዊቱ ግን ከፍተኛ ዲስፕሊን የነበረው በመሆኑ ለነሱ ማግባባት ጆሮ አልሰጠም ነበር፡፡ በኋላ የውጊያውን እቅድ አወጣንና ውጊያ ገጠምናቸው። በዚያ ውጊያ የመረረ መስዋዕትነት ነበር የከፈልነው። በኋላ ያዙን፤ ወደ አዲስ አበባ አመጡን፤ መጀመሪያ ሰንዳፋ በኋላም ሆለታ ቀጥሎም ጦላይ ወሰዱን፡፡ በመጨረሻም ያለምንም ክስ ያለምንም የፍርድ ሂደት 10 ዓመት ያህል ታስሬ ቆየሁ፡፡ ከዚያም በራሳቸው ጊዜ ለቀቁኝ፡፡ በወቅቱ ሚሚ ስብሀት እስር ቤት መጥታ ያለ ፍርድ የታሰረው ከፍተኛ መኮንን ብላ ቪኦኤ ላይ ሰራችው። በኋላም ኢትዮጵ  መፅሄት ታሪኬን ሠርቶታል፡፡
ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ህይወት እንዴት ቀጠለ?
እኔ እስር ቤት እያለሁ ኦሮምኛ ቋንቋ ስለምችል ቁቤ ተምሬ ዲፕሎማ  ይዣለሁ። በቋንቋዎች አድቫንስድ ዲፕሎማ ነበረኝ። በኋላ ግን ስወጣ ወዲያው ታክሲ ነበር መንዳት የጀመርኩት፡፡ ከመገናኛ ገርጂ የሚጭን ታክሲ ነበር ለባለቤቱ የቀን ገቢ እያስገባሁ የምሰራው። በዚያ ስራ ላይ እያለሁ ከተሳፋሪ ጋር ተጋጨሁ፤ መኪናውን ለባለቤቱ መልሼ ስራውን ተውኩት። በኋላ የቀን ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡ በወቅቱ የተቀጠርኩበት መስሪያ ቤት ደግሞ እኔን የሚያውቁኝ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ነበሩ፡፡ በጣም ይንከባከቡኝ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ በኤርትራና ኢትዮጵያ መሃል የገባው የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ጦር (አንሚ) የቅጥር ማስታወቂያ አወጣ። ተወዳደርኩ፡፡ አለፍኩና እዚያ ረዳት የደህንነት ሃላፊ ሆኜ በ2400 ብር ደሞዝ ገባሁ፡፡ አራት ዓመት ያህል  ሠራሁ፡፡ እሱ ሲቋረጥ ደግሞ በሙያዬ በጥበቃ ድርጅት ውስጥ በስራ አስኪያጅነት ስራ ጀመርኩ። ከዚያም ኤቢሲ የሚባል ድርጅት ስራ አስኪያጅ ሆኜ ሰርቻለሁ። አሁን መጨረሻ ላይ ያለሁበት ቤዝሜክ የጥበቃና የፅዳት አገልግሎት ድርጅት በስራ አስኪያጅነት እየሰራሁ እገኛለሁ። በዚያው ልክ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና ልማት ማህበር ውስጥም አገለግላለሁ፡፡
ማህበራችሁ ከተመሰረተ በኋላ የፈፀማችኋቸው ጉልህ ተግባራት ምንድን ናቸው?
ማህበሩ የራሱ በጀትና ገቢ የለውም፡፡ ነገር ግን ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱ የሠራዊቱ አባላት እንደነ መቶ አለቃ በላይነህ ክንዴ፣ እንደነ ሻምበል እድሜ አለም እጅጉ የመሳሰሉትን ነበር የምናስቸግረው፡፡ እቅዳችን የነበረው ሜዳ ላይ የሚለምነውን ማንሳት ነበር። እነሱን ለማንሳት ስራ ለማስያዝ ህጋዊ ፍቃድ ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ይሄን ፈቃድ ለማውጣት እንዲህ ቀላል አልነበረም፤ ብዙ ውጣ ውረድና እንቅፋት ገጥሞናል፡፡ ኋላም ሰምሮልን ፍቃዱን ልናወጣ ችለናል፤ ነገር ግን ይሄን ሜዳ ላይ የወደቀ ሠራዊት አንስተን የት ነው የምናደርገው? የሚለው ለኛ አስጨናቂ ነበር፡፡ ለዚህ መፍትሔ አድርገን የተገበርነው የፈጥኖ ደራሽ የጥበቃ ደርጅትን ማቋቋም ነበር፡፡ እሱን አቋቁመን ህጋዊ ፈቃድ አውጥተን ሜዳ ላይ ያለውን ሠራዊት ሠብስበን፣ የሰራዊቱ አባላት ከ2 ሺ ብር በላይ በሆነ ደመወዝ በየቦታው በጥበቃ ስራ ላይ  እንዲሰማሩ አድርገናል፡፡ አሁን ሜዳ ላይ የሚለምን የሰራዊቱ አባል  አይገኝም፡፡
ምን ያህል ናቸው ያሰባሰባችኋቸው?
60 የሚሆኑ ናቸው ከሜዳ ላይ ያነሳናቸው።
አጠቃላይ አባሎቻችሁስ ምን ያህል ናቸው?
ከ1 ሚሊዮን በላይ ናቸው። በክልል ደረጃ ከ289 በላይ ማህበራት አሉን፡፡
መንግስት ለቀድሞ ሰራዊት አባላት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ምን ያህል አባሎቻችሁ ተሳተፉ? የተሳትፎውስ ሁኔታ ምን ይመስላል?
በጎልማሳነት እድሜ ደረጃ ላይ ያሉ በሙሉ ዘምተዋል፡፡ ስናደራጅ በስርዓቱ እግረኛ፣ ታንከኛ፣ ደህንነት እያልን ነው ያደራጀነው። መከላከያ ይሄን እፈልጋለሁ ሲለን በፍጥነት ለማቅረብ እንዲያመች፡፡ አኛ የጠበቅነው ተነስ ታጠቅ ዝመት የሚለውን ጥሪ ነበር። የሆነው ግን እንደሱ አልነበረም፤ የቀድሞ ሠራዊት እንዝመት ብሎ በጠየቀው መሰረት ቀጥሎ ያለውን መስፈርት የሚያሟሉ በሚል ነው ማስታወቂያው የወጣው። እኛ ፍላጎታችን የነበረው ተነሱ፣ ታጠቁ፣ ዝመቱ እንድንባል እንጂ በደመወዝ እንድንቀጠር አልነበረም፡፡ በመስፈርቱ ደግሞ ግፊት፣ ስኳር የሌለው ይላል። ይሄ እንዴት ይሆናል? ለ27 ዓመትና ከዚያ በላይ መከራውን ሲበላ የኖረ ሠራዊት ይሄ በሽታ አይደለም በአለም ላይ ያለ በሽታ ሁሉ እላዩ ላይ  ቢከመርበት ምን ያስደንቃል፡፡ መስፈርቱ በጣም የተለጠጠ ነበር፡፡ መንግስት በፈለግነው ሁኔታ ጥሪ ባያቀርብም፣ ባቀረበው መንገድ አባሎቻችን እንዲቀላቀሉ አድርገናል፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በሁሉም ክፍለ ከተማ ሠራዊቱ ከወጣቱ ጋር ተቀናጅቶ አካባቢውን በዘላቂነት በሚጠብቅበት ሁኔታ ላይ ከአስተዳደሩ ጋር እየተነጋገርን ነው ያለነው። የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር እነዚህን ስራዎች እየሰራ ነው ያለው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ሜዳ መዝመትና የተገኘውን ድል እንዴት ይገልፁታል?
ኮ/ል መንግስቱ ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው። ጠ/ሚኒስትር  ዐቢይ አህመድ ወደ ጦር ሜዳ መዝመት አዲስ ክስተት አይደለም። ኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም እኔ እዋጋበት የነበረው ጅግጅጋ ድረስ መጥተው ሠራዊቱን ሲያበረታቱ ነበር። አንዳንዴም ነሸጥ ሲያደርጋቸው ወደ ጦርነቱ ውስጥ የሚገቡበትም አጋጣሚ ነበር፡፡ ይሄ ሲሆን የሰራዊት ሞራል በጣም ከፍ ይላል፤ በወቅቱ ውጊያው ወደ ኋላ እያፈገፈገ መጥቶ ቆሬ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ በኋላ ነው ኮ/ል መንግስቱ በቦታው ተገኝተው በወሰዷቸው እርምጃዎች ድል የተገኘው፡፡ አሁንም ጠ/ሚር ዐቢይ ወደ ግንባር ባይሄዱ ኖሮ አሁን ያየነው ለውጥ አይኖርም ነበር፡፡ እሳቸው ብስለታቸውንና የአመራር ጥበባቸውን ያሳዩበት ነው፡፡ ሲአይኤ መንግስቱ ሃ/ማርያምን አወናብዶ አጭበርብሮ ከሃገር እንዲወጡ አድርጓል። ያንን ታሪክ ግን ጠ/ሚር ዐቢይ ላይ መድገም አልቻለም፡፡ ጄፈር ፊልትማን ሲመላለስ የነበረው ጠ/ሚኒስትሩ ለቆ እንዲወጣ ለማደራደር ነው፤ ግን ጠ/ሚኒስትሩ ጠንካራና ብቁ የአመራር ጥበብ ያለው ሰው ነው፡፡
በህዝብ የታቀፈ ሠራዊት ሁሌም አሸናፊ ነው። ያኔ በደርግ ጊዜ ህዝብና ሠራዊት ምን ያህል ይቀናጁ ነበር? አሁን ግን  ሠራዊቱና ህዝቡ በጣም ነው የተቀናጀው፡፡ ትኩስ ምግብ እየቀረበለት የታሸገ ውሃ እየቀረበለት በህዝብ ታቅፎ ተደግፎ ሠራዊቱ መቼም ቢሆን አሸናፊ ነው የሚሆነው፡፡ አንድነት ነው የማሸነፉ ሚስጥር፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መሄድ ደግሞ የበለጠ ሞራልና የማሸነፍ ስነ ልቦና ለሠራዊቱ አጎናፅፏል። ጦርነቱም በተናበበ መልኩ እንዲመራ አድርጓል፡፡


Read 12646 times