Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 15:27

“የታገደውን ጋዜጣ ለማስጀመር እስከመጨረሻው እንታገላለን”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ጋዜጣችሁ አሁንም እንደታገደ ነው?

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (የአንድነት ፓርቲ ሊ/መንበር)

ኢህአዴግ ጠ/ሚኒስትሩን ለመተካት ዘግይቷል፤ ጋና በሁለት ቀን ነው የተኩት

የጠ/ሚኒስትሩን ቦታ ማን ሊተካው እንደሚችል ይናገራሉ (አቶ ግርማ ብሩ አቶ አዲሱ ለገሰ አቶ ብርሃነ ገ/ክርስቶስ ወይምአቶ ስዩም)አዎ እንደታገደ ነው፡፡ ባለፈው አርብ ልዩ እትም ለማሳተም ሰዎች ልከን ክፍያ ለመፈፀም ስንል የብርሃንና ሠላም ማርኬቲንግ ሃላፊው ክፍያውን አልቀበልም አለ፡፡ ምክንያቱን ሲጠየቅ፤ በቁጥር 1 ልዩ እትማችሁ ያሳተማችሁት ነገር ቅሬታ ስላስነሳብንና የዚህን አይነት ጋዜጣ እንዴት ታወጣላችሁ ስለተባልን አናትምም ሲል መለሰ፡፡ ልዩ እትሙ የጠ/ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ የተፃፉ በርካታ ሃሳቦችን የያዘ ነበር፡፡ ከሃሳቦቹ መካከልም “ለፍርድ ሳይቀርቡ መሞታቸው” የሚልና እኔ የፃፍኩት “ህገመንግስቱና ጠ/ሚኒስትሩ”  የመሳሰሉ በርካታ በሳል ጽሑፎች አካትቷል፡፡

ሆኖም ግን ጋዜጣችሁን በተመለከተ በስልክ ቅሬታ ስለቀረበባችሁ፣ ማኔጅመንቱ ተወያይቶበት ጋዜጣው እንዳይታተም ወስነናል መባሉ ተነገረን፡፡ እኛም በማግስቱ ሃላፊ ለማነጋገር ሔድን፡፡ እኔ፣ አቶ ግርማ ሠይፉ እና አቶ አስራት ጣሴ ነበርን፡፡ ማርኬቲንግ ማናጀሩ ለኛም ያንኑ ደገመልን፡፡ ታዲያ ምን ይሻላል ብለን ስንጠይቀው ሃላፊዬን አነጋግሩ አለን፡፡ ዋናዋ ስላልነበረች ምክትሉ ቢሮ ገብተን ስናነጋግረው፣ ጋዜጣችን  አይታተምም የተባለው ማርኬቲንግ ሃላፊው እንዳለው ሳይሆን በሌላ ምክንያት መሆኑን ሰማን፡፡ “እኛ አቅም የለንም ነው ያልነው፤ ለኦሮሚያ ክልል የትምህርት መጽሐፍትን ለማተም ጨረታ አሸንፈናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለብዙ ጊዜ ደንበኞች የሆኑ የተወሰኑ ጋዜጦች ስላሉ የእነሱን ብቻ እናትማለን እንጂ የናንተን ለማተም አቅም የለንም፡፡ ማኔጅመንቱ ተወያይቶ የደረሰበት ውሳኔ ይሄ ነው፤ እናንተ አዲስ ስለሆናችሁ የናንተን ላለማተም ወስነናል” አለን፡፡ ይሄኔ በጣም ተናደድኩና “በምን መስፈርት ነው የእኛን አናትምም ብላችሁ የሌሎችን የምታትሙት?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡ “እነሱ የቆዩ ደንበኞች ስለሆኑ ነው፤ የፈለጋችሁትን ነገር አድርጉ፤ አናትምም” ብሎ ድርቅ አለብን፡፡

ሆኖም እኛ በደረሰን መረጃ መሠረት፤ እዚያ ማተምያ ቤት አንድ ሰው አለ፤ ጋዜጣው ሲመጣ ምን አይነት ይዘት እንዳለው ለደህንነቱ ሃላፊዎች ደውሎ የሚጠቁም፡፡ ከዛ ጉዳዩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል ጋር ይደርሳል፤ አቶ ሽመልስ ደግሞ ለም/ሥራ አስኪያጁ ደውሎ እንዳይታተም ያዛል፡፡ እንደዚያ ነው የሆነው፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ ከዚህ በፊት እንደነበረው ዓይነት የአፈናና የዲሞክራሲ መብቶች እረገጣ ነው፡፡ በመንግስት ላይ ተቃዋሚ አስተያየትና ሃሳብ የሚሰነዝሩ ግለሰቦችንና የህትመት ውጤቶችን ልሳን መዝጋት ነው፡

የጋዜጣችንን ሥርጭት ከ2500 ኮፒ ጀምረን ነበር 20ሺህ ኮፒ ያደረስነው፡፡ ግን ታገደ፡፡ ብርሃንና ሰላም አላትምም ሲለን እሱን ትተን ወደ ግል ማተምያ ድርጅቶች ሄደን ነበር፡፡ አንዳንዱ አቅም የለንም ይላል፤ ሌላው ደግሞ ለማተም ይቸግረናል ይለናል፡፡ ቦሌ ማተሚያ ፣ ሆራይዘን፣ ቅድስት ማርያም ማተምያ ቤቶች ሄደናል፤ ግን ለማሳተም አልቻልንም፡፡

የጋዜጣው አለመታተም ከገቢ አንፃር ፓርቲውን ይጐዳል?

ከጋዜጣው ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ የፓርቲው ገቢ የሆነው በቅርቡ ነው፡፡ ምናልባትም ያም ታስቦ ይመስለኛል እንዲቆም የተደረገው፡፡ ጋዜጣውን ስንጀምር እየደጐምነው ነበር የሚታተመው፡፡ አሁን ግን የጋዜጣው ዝግጅት ከፓርቲው ጽ/ቤት ግቢ ወጥቶ የራሱን ቢሮ እንዲከራይ፣ ተጨማሪ ጋዜጠኞች እንዲቀጠሩና ለጋዜጠኞች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ተሟልቶላቸው ስራቸውን እንዲሠሩ እየጣርን ነበር፡፡ ፓርቲውንም እንዲደጉም ሃሳብ ነበረን፡፡

ጋዜጣው ሊታገድ እንደሚችል ገምታችሁ ነበር?

እኛ የመንግስትን መልካምና ደካማ ጐን ነው የምንጽፈው፤ ጋዜጣው የህዝብ ልሳን እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ በጣም መጥፎና የከረሩ ነገሮች እንዲወጡ አናደርግም፤ ነገር ግን ተጨባጭ መረጃዎች ካሉ እንጽፋለን፡፡ ጋዜጣው በስራ አስፈፃሚው ስር አይደለም፤ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ስር ነው፤ ተጠያቂነቱም ለእሱ ነው፡፡ ስለዚህ  ጽሑፎች ከመውጣታቸው በፊት የተለያዩ አካላት አይተው አስተያየቶች የሚሠጡበት መንገድም አለ፡፡

አንዳንድ የመንግሥት ጋዜጦች ከውስጥ ምንጮች ያገኘነው በሚል የፓርቲውን ድክመትና ጉድለት ሲፅፉ ይስተዋላሉ፡፡ እናንተስ የኢህአዴግን የውስጥ ሚስጥር የሚነግራችሁ አለ?

አንዳንድ ነገሮች ይደርሱናል፤ ሆኖም ወደ ታች ወርደን እዚህ ስብሰባ ላይ እከሌ ይህንን ተናገረ፤ ያንን አደረገ እያልን ተራ ነገር መፃፍ አንፈልግም፡፡

ከጋዜጣውን መዘጋት ጋር ተያይዞ ፓርቲው ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚጠራ ገልጿል፡፡  የሠልፍ ፈቃድ ባታገኙም በሌላ መንገድ በመጥራት እናካሂዳለን ብላችኋል፡፡ እንዴት ነው ያሰባችሁት?

በመጀመሪያ የምናደርገው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት አላትምም ያለበትን ምክንያት በጽሑፍ እንዲገልጽልን ሲሆን ከዚያ በፊት ግን እንደገና አስቦበት እንዲያትምልን ደብዳቤ ልከናል፡፡ የመንግስትና የህዝብ ተቋም ስለሆነ መንግስትም ሃላፊነት አለበት፡፡ ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩም በጉዳዩ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ በተጨማሪ እኔ በራሴ የቦርዱ ሊቀመንበር ወ/ሮ ብስራት ጋሻው ጠና ጋር ደውዬ ልነግራቸው ሞክሬ ነበር፤ ሆኖም አሁን እሳቸው የብአዴን ሃላፊ ስለሆኑ ባህርዳር ናቸው፡፡ ጉዳዩን አላውቀውም፤ አጣርቼ መልስ እሠጣለሁ ብለውኛል፡፡ ያንን እየጠበቅሁ ነው፡፡ ስለዚህ ዝም ብለን አንቀመጥም፡፡ ከዛ በኋላ ነው ሠላማዊ ሠልፉን የምንጠራው፡፡ የሚያስፈልገውን ሁሉ እርምጃ እንወስዳለን፡፡ የታገደውን ጋዜጣ ለማስጀመር እስከመጨረሻው እንታገላለን፡፡

ህዝቡ በጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት የሀዘን ስሜቱን የገለፀው በግዳጅ እንደሆነ ገልፃችኋል፡፡ ምን ማስረጃ ይዛችሁ ነው እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሳችሁት?

የሚያዝን ሊኖር ይችላል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አገዛዝ ዘመን ጥቅማ ጥቅሞችን ያገኙ ብዙ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሰው በመሆናቸው ህልፈታቸው ሲሰማ ህዝቡ ላይ የመደንገጥ ስሜት ሊፈጥርም ይችላል፡፡ እኔ ለምሳሌ ከአውሮፕላን አስከሬናቸው ሲወርድ በማይበት ጊዜ ሀዘን ተሠምቶኛል፡፡ በቀብሩ ላይ ወ/ሮ አዜብ እየተወራጨች ሳያት እንዲሁም ስትናገር የሀዘን ስሜት ተሠምቶኛል፡፡ በሌላ በኩል ህዝቡ በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲወጣ የተበተነ ደብዳቤ አግኝተናል፡፡ በአንዳንድ ቀበሌዎች መንገድ ላይ ድንኳን ተክለው እሱን አቋርጦ ለመሄድ አስቸጋሪ ነበር፡፡ እኔንም የዛን አይነት ሁኔታ አጋጥሞኛል፡፡ ይሄ አስገዳጅ ነው፡፡ ጥሩ ሊሆን የሚችለው በአደባባይ ድንኳን ተተክሎ ሰው መጥቶ አስተያየት እንዲሠጥ ቢደረግ ነበር፡፡ እኔ በቀበሌዬ በገዛ ፈቃዴ የሃዘን መግለጫ መዝገቡ ላይ አስተያየቴን ጽፌአለሁ፡፡ እናም  ከተጨባጭ መረጃዎች በመነሳት ነው የምንናገረውና የምንጽፈው፡፡

ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?

የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሉ፡፡ የመገናኛ ብዙሀን አፈና አለ፡፡ የዋጋ ግሽበት አለ፡፡ ኢህአዴግ 21 አመት በነበረው የአገዛዝ ዘመን ያልተሳኩለትን ነገሮች መቀየር አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነ አገሪቱ ወደከፋ ነገር ትሄዳለች፤ ለእሱም ጥሩ ነገር አይመስለኝም፡፡

አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ቢሆኑ ብለው የሚያስቡት ወይም የሚመርጡት ሰው አለ?

ተመርጫለሁ የሚለው ኢህአዴግ ነው፤ ከዛ አንፃር የአገሪቱን ችግሮች ጠንቅቆ የሚያውቅና የሚፈታ ሰው ቢሾም ነው የሚሻለው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብቃት አላቸው ብዬ የማስባቸውና ድሮ ከማውቃቸው መካከል … (ስልጣን ከለቀቅሁ 11 አመታት ሊሆነኝ ነው)  አቶ ግርማ ብሩ ቢሆኑ ብዬ በ1993 ዓ.ም ሃሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ አሁን እድሜም ጨምሯል፤ ሆኖም እሱ ቢሆን ችሎታ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከህወሓት ብርሃኔ ገ/ክርስቶስ ቢሆን እላለሁ እድሜው ባይገፋ ኖሮ ስዩም መስፍንም ጐበዝ ነው፡፡ ከብአዴን ደግሞ አቶ አዲሱ ለገሠ፡፡ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች አርጅተዋል፤ መተካት አለባቸው፡፡  አዲሶቹን ወጣቶች ሊያደርጓቸው ይችሉ እንደሆነ አላውቅም፡፡ እኔ የምሻው ግን የስርአት ለውጥ መጥቶ ህዝቡ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ይመራኛል የሚለውን ቢመርጥ ነው፡፡

ጠ/ሚኒስትር በሚሞት ጊዜ የሚከናወኑ ስነ ስርዓቶችን በተመለከተ በህገ መንግስቱ ውስጥ የተደነገገ ህግ አለ?

ህገመንግስቱ ውስጥ የለም፡፡ ነገር ግን የሚደረጉ ነገሮች ከአገሪቱ አቅም ጋር ተገናዝቦ መሆን አለበት፡፡ የተንዛዛ ነገር መሆን የለበትም፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት በሚሞቱ ጊዜ ፕሮቶኮል አለ፡ ከዚያ አንፃር ከተመለከትነው የሚበልጠው የፕሬዚዳንቱ እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትር አይደለም፡፡ ለአንድ ጠ/ሚኒስትር እንዲህ ከተደረገ ለፕሬዚዳንቱ የዛን እጥፍ  መደረግ አለበት ማለት ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ይደረጋል ወይ ሰውን ማበላለጥ አይፈጠርም? የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ወ/ሮ አዜብም ተናግራለች፡፡ መለስ ቢኖር ኖሮ የዚህን አይነት ግርግር ይፈልጋል ወይ የሚለው ጥያቄ እኔም ውስጥ አለ፡፡ ለሰው ማዘን አለ፤ ክብር መስጠት አለ፤ ነገር ግን እንደ ሰሜን ኮርያ የማምለክ ዓይነት የተደረገ ይመስለኛል፡፡ በሌሎች አገሮች የዚህን አይነት ነገር ይደረጋል ወይ የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ ሌላው ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ ከታመሙ ጀምሮ ሌላ ወኪል ነበራቸው፡፡ ም/ጠሚኒስትሩ እያሉ ማለት ነው፡፡ በዚህም ህገመንግስቱ ተጥሷል፡፡ ሰኔ 30 ፓርላማ ተዘግቶ በጀት መጽደቅ ነበረበት ወይም ደግሞ ክረምት ላይ በይፋ ሰኔ 20 ዘግተናል ብለው በጀቱን ማጽደቅ እንጂ ሳይዘጉ ፓርላማ መቀጠል አልነበረባቸውም፡፡ አንቀጽ 58/2 በግልጽ ነው የተጣሰው፡፡ (ያን ጊዜ ምናልባት ታመው ሊሆን ይችላል፡፡) ሁለተኛ ደግሞ አንቀጽ 12፤ የመንግስት አሠራር ግልጽ መሆን አለበት ይላል፡፡ ሰው አሁንም እየጠየቀ ነው፤ ጠ/ሚኒስትሩ ምን አይነት ህመም ነበር የታመሙት? በትክክል ከመቼ ጀምሮ ነው የታመሙት? የሚሉትን ጥያቄዎች የሚያነሱ አሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ግልጽ ቢሆኑ ሰው ከሃሜትና ከአሉባልታ ይድን ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሞቱት ነሐሴ 15 ነበር፤ ወዲያው ተተኪ መሾም ነበረበት፡፡ የሞቱት የጋናው መሪ በሁለት ቀን ነው የተተኩት፡  ጠ/ሚኒስትሩ ከሞቱ በኋላ ማነው አገሪቱን እየመራ ያለው? በቀደም የጀኔራሎችን ሹመት ማነው የሰጠው? የምህረት ጉዳይ ማነው እያከናወነ ያለው ወዘተ … የሚሉት ለህዝብ ግልጽ መሆን አለባቸው ባይ ነኝ፡፡

የእግርዎ የጤንነት ሁኔታ እንዴት ነው?

አሁን በጣም ጤነኛ ነኝ፡፡ የእግሬን ጉዳይ በተመለከተ … የስኳር በሽታ አለብኝ፡፡  በሰውነቴ ውስጥ የተከማቸ ኮሌስትሮል አለ፡፡ ለብዙ አመታት ደግሞ ሲጋራ አጨስ ነበር፤ እነዚህ ነገሮች የእግር የደም ስርን የመዝጋት ሁኔታ ፈጥረው ነበር - በሁለት እግሮቼ ላይ፡ እረጅም መንገድ መሄድ አልችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ሳልታከም ብቆይ ኖሮ አደገኛ ችግር ማስከተሉ አይቀርም ነበር፡፡ አሁን የተዘጋውን የደም ሥር ከፍተውልኛል፡፡ በሙሉ ጤንነት ላይ ነኝ፡ አንዳንድ ሚዲያዎች አጋነውት ነው እንጂ እግሬ መቆረጥ ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡

 

 

Read 50761 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 15:45