Saturday, 25 December 2021 13:25

አንድ እንባ

Written by 
Rate this item
(5 votes)


              እንዴት ያደርጉታል የሆድን ህመም
ማጭድ አይገባበት በእጅ አይታረም፡፡
የሕዝብ ግጥም
“አንቺ ማኅሌት… ማኅሌት…” ትንፋሼ ቁርጥ ቁርጥ እያለ ደብተሬን ከጀርባዬ እየሸጎጥኩ ከዳግማዊ ምንሊክ ትምህርት ቤት ወደ ፓርላማ መንገድ ቁልቁል እከተላታለሁ፡፡ አንዴ ገልመጥ ብላ አይታኝ መንገዷን ቀጠለች፡፡
ሰሞኑን ደብሯታል፤ ምን አደረኳት?
ሮጥ ሮጥ ብዬ ፓርላማው አጥር ጋ ደረስኩባትና ከኋላዋ ሸሚዟን ይዜ አስቆምኳት፡፡ ያልተለመደ እርጋታቸው የሚረብሽ ዐይኖቿን ተከለችብኝ፡፡
“ምን ሆነሽ ነው?” ሳላስበው ተቆጣሁ፡፡
ሳትመልስልኝ አይኗን ሰበረች፡፡
ደሜ መፍላት ጀመረ፡፡ “ምን ሆነሻል?”
“ምንም”
 “ምንም ሳትሆኚ ነው ጠዋት ሳትጠብቂኝ ትምህርት ቤት የመጣሽው? ምንም ሳትሆኚ ነው አሁንም ጥለሺኝ ወደ ቤትሽ የምትሄጂው?”
“ባክህ ተወኝ አሁን ልሂድበት” ድንገት አራስ ነበር ሆና ትታኝ ሄደች፡፡
ተናደድኩ፡፡ “ጥርግ በይ እሺ ስታስጠላ” አልመለሰችልኝም፡፡ ጠደፍ ጠደፍ እያለች መንገዷን ቀጠለች፡፡ በጀርባዋ ካዘለችው የደብተር ቦርሳ ሌላ መጀመሪያ ልብ ያላልኩት አንድ መፅሐፍ ይዛለች፡፡
“ፍሬንድ አይዞሽ እሷ ብትሔድ ሌላዋ ትመጣለች” አለኝ፡፡ ቀና ብዬ አየሁ። የፓርላማው ጠባቂ ጠብ መንጃውን እንደወደረ ማማው ላይ ቁጭ ብሎ በግዴለሽነት ተናገረ፡፡
አንጋጥጬ ገላመጥኩትና ያገኘሁትን ጠጠር እየለጋሁ፣ በቅርብ ርቀት ከኋላዋ መራመድ ጀመርኩ፡፡ አንዳንዴ ስንኮራረፍ ፊትና ኋላ እንሄዳለን፡፡ ግን አያስችለንም፤ ዞር ብላ ታየኛለች ወይ ዞር ብዬ አያታለሁ፡፡
ባለወልድ ጋ ስትደርስ እንደ ሁሌው ቆም ብላ ልትሳለም ነው ብዬ ጠበቅኩ፡፡ አልተሳለመችም፡፡ ዞር ብላ ልታየኝ ነው ብዬ ጠበኩ አልዞረችም፡፡
ንዴቴ ጋብ እያለ ሲሄድ አሳዘነችኝ፡፡ ምን ሆና ነው? በእጇ የያዘችውን መጽሐፍ እየጠቀለለች እየፈታች ጠደፍ ጠደፍ ትላለች፡፡ እንደገና ሮጬ ደረስኩባትና እጇን ይዤ አስቆምኳት፡፡ “ማኂ” አልኩ፡፡ ቅድም የረጋው ያይኗ ውኃ አሁን መናወጥ ጀመረ፡፡ እኔ ያልገባኝ የሆነ ዑደት አለ ውስጧ፡፡
 “በእናትህ ቢኒ ምን ሆነሻል አትበለኝ” የውስጧ ማዕበል የገፋው ያይኗ ውሃ ዳርቻው ላይ ተንጠለጠለ፡፡ እጇን ለቅቄ በዝምታ የአዋሬን መንገድ ጎን ለጎን ሆነን ተያያዝነው፡፡
ነፍሴ ተጨነቀች፡፡ ማኂ እንዲህ ስትሆን አይቻት አላውቅም፡፡ አልፎ አልፎ በሸሚዟ እጅጌ ጉንጮቿንና አፍንጫዋን ትጠርጋለች። አቧሬ ገበያ እንደተዘጋጋን ስንደርስ ወደ እኔ ሳታይ “ቻው” አለችኝ፡፡
ሌላ ቀን ብዙ ለምናኝ ብዙ ጎትታኝ የምሸኛት ዛሬ አልፈለገችውም፡፡ ዝም ብዬ ቤቴን አለፍኩት፡፡ እሷ በር ላይ ስንደርስ አሁንም ዞር ብላ እንኳን ሳታየኝ “ቻው” አለች፡፡
የምናገረው ሳጣ “እሱን መፅሐፍ ላንብበው?” አልኳት፡፡
 “ልጨርስና እሰጥሃለሁ” ለአፍታ ዞር ብላ አይታኝ ፈጥና ወደ ቤቷ ገባች፡፡
የደፈረሱ ደም የለበሱ ዐይኖቿ ከፊት ከፊቴ እየቀደሙ እየታዩኝ እያሳዘኑኝ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡ ከቤተሰቦቿ ጋር እኛ ሰፈር ተከራይተው ከመጡ አራት ዐመት ይሆናቸዋል፡፡ ዘጠነኛ ክፍል አንድ ክፍል ስለደረሰን ተዋወቅን፡፡ አሁን አስራ ሁለተኛ ክፍል ነን፤ ወንበራችን አንድ ነው፡፡ ሁለታችንም በትምህርት ቀልድ አናውቅም። በዚህ ሉሁ ጊዜ ግን እንደ ዛሬው ስትሆን አይቻት አላውቅም፡፡
እንዲህ ሆነን ቀናት ተቆጠሩ፡፡ ቤት መጥታ ስለምትጠራኝ ቀድሜ ወጥቼ እጠብቃታለሁ፡፡ እንደነገሩ ሰላም ብላኝ አስሩን ስቀባጥር በይሉኝታ ፈገግ እያለች እንሄዳለን፡፡ የክፍላችን ልጆች በሙሉ በድንገተኛ ዝምታዋ ግራ ተጋብተዋል። ስንመለስ አትጠብቀኝም፤ እንዲሁ እከተላታለሁ፡፡ በፊት እጅጌ ሙሉው የደንብ ልብሷን ሸሚዝ እያስጠላት ክርኗ ድረስ ትሸበልለው የነበረውን ረስታዋለች፡፡ ሸሚዟ ብዙ ሰንበር አውጥቶ እጇን ያስዋኛል፡፡ እኔ ሰደርያዬን አውልቄ ትከሻዬ ላይ ሳደርግ ደስ ይላት ነበር፡፡ አሁን ለመንገዷ ባነጥፈው እንኳን አታየውም፡፡ ለምን? ይቺ ልጅ ምን ሆናለች?
አንብባ ጨርሳ በእጇ ይዛ የምታፍተለትለውን መፅሐፍ ተቀበልኳትና አነበብኩት፡፡ “አጥቢያ” ይላል ርእሱ፡፡ መጀመሪያ ስለ ሁለት ፍቅረኛሞች መስሎኝ ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ግን  ስለ አራት ኪሎ ኑሮ ነው፡፡ አሁን ፈራርሶ ሙጃ ስለበቀለበት አራት ኪሎ፤አሁን ህንጻ ስለተገነባበት አራት ኪሎ፣ አሁን እንደ ፈረስ መጋለቢያ ሜዳ ስለታጠረው አራት ኪሎ….
እና ይኼ መፅሐፍ ከሌላው በምን ተለየባት? አባቷ ማንበብ ስለሚወድ አልፎ አልፎ በተለይ ትምህርት ሳይኖር መፅሐፍ እየሰጠን እናነባለን፡፡ ፍቅር የሌለበት መፅሐፍ አንወድም፡፡ እዚህ ላይም ከእርጥባንና ከሙሴ ፍቅር ሌላ እኔን የመሰጠኝ ታሪክ የለም፡፡ እሷ እንዴት ይኼን ያህል ወደደችው?
መፅሐፉን አንብቤ ስመልስላት እንደ ወትሮው መፅሐፉ ውስጥ ያሉ ፍቅረኞችን እየጠራች “እንዲህ ሲላት አልሳቅህም? እንዲህ ብላ መለሰችለት ደስ አትልም?” አላለችም፡፡ ፍጹም ግራ ተጋባሁ፡፡
አንድ ቀን በብዙ ውትወታ ትምህርት ቤት ተጠርተናል ብለን ሲኒማ እንድንገባ አሳመንኳትና ፒያሳ ሲኒማ አምፒር ተገናኝተን አስቂኝ የፍቅር ታሪክ ለማየት ገባን፡፡ ሌላ ቀን ሲኒማ ስንገባ እንደምታደርገው እግሯን ወንበር ላይ አልሰቀለችም፡፡ አዳራሽ ሙሉ ሰው ሲስቅ እሷ አልሳቀችም፡፡ እኔም እሷን ስከታተል ሳቄ ተሰውሮብኛል፡፡ ምንድን ነው ነገሩ? ስለ እሷ እጅግ ተጨነቅኩ፡፡
ከሲኒማ ወጥተን መንገዱን ከሞላው ሕዝብ ጋር እየተጋፋን በዝምታ ወደ ሰፈራችን ስናዘግም እጄን ትከሻዋ ላይ ጣል አደረኩ፡፡ ዝም አለች፡፡ እንዴት ዝም አለች? ሌላ ጊዜ እኮ እንኳን አቅፊያት እጇን ለአፍታ ከያዝኩ “ልቀቀኝ እኔ ራሴን ችዬ መሄድ ነው ምፈልግ” ብላ ትጮኽብኝ ነበር፤ ዛሬ ያ ሁሉ የለም። አራት ኪሎ አደባባዩን አቋርጠን ፓርላማ ጋ ስንደርስ እንደምንም ራሴን አበረታትቼ “ማኂ” አልኩ፡፡
ቀና ብላ ፍፁም በረጉ አይኖቿ አየችኝ። ተሸበርኩ፡፡ ሰው ረጋ ብሎ እንዴት ያሸብራል? “እኔ ጥሩ ጓደኛሽ ነኝ ብዬ አስባለሁ፤ አንቺም ጥሩ ጓደኛዬ ነሽ” በዝምታ ራሷን በአዎንታ ነቀነቀች፡፡ ማኂ መጨነቄን ተረድታ ችግሯን እንድትነግረኝ እንዲያደርግልኝ ቀና ብዬ ፈጣሪዬን ላይ ስል የፓርላማው ጠባቂ ማማው ላይ ሆኖ ዐይኔን ቀለበ፡፡
“እኔ በሆነ ነገር ቢከፋኝና ለብዙ ቀን ባላወራሽ አይከፋሽም?” ስላት ራሷን ወደ ትከሻዬ ጠጋ አደረገች፡፡ አለሁልሽ እንደማለት ትከሻዋን እያሻሸሁ ቆምኩ፡፡ ፊት ለፊቴ ቆመች፡፡ ከእኛ በላይ ባለ ማማው ጠባቂ፤ ከእሱ በላይ ሰማይ፤ ከሰማይ በላይ እግዜር አለ፡፡
“ማኂ እወድሻለሁ እንዲህ ስትሆኝ  ማየት አልፈልግም፤ በጣም እየተጨነቅኩ ነው፤የግድ የሆንሺውን ልትነግሪኝ ይገባል። የ12ኛ ክፍል የመጨረሻው ፈተና ደግሞ እየደረሰ ነው፡፡” ዐይኖቿን በዐይኖቼ ፈጥርቄ ይዤ አስጨነቅኳት፡፡
ዕንባዋ ከየት እንደመጣ እንጃ ከንፈሮቿ እየተንቀጠቀጡ መላ ሰውነቷን የሚንጥ ለቅሶ፡፡ እንደቆምን ጥብቅ አድርጌ አቀፍኳት። ደረቴን የእንባዋ ትኩሳት ሲለበልበው ይታወቀኛል፡፡
“እናንተ ዞር በሉ፤ ከዚህ መቆም ክልክል ነው”! ከፍ ብሎ የተቀመጠው የፓርላማ ጠባቂ ድንገት ሲጮህ በድንጋጤ እንኳን የማኂ  ዕንባ ጣና ይደርቃል፡፡
ቤቷ ሳደርሳት ጭንቀቴ አሳዘናት መሰለኝ “ነገ ከትምህርት ቤት ስንመለስ ፅፌ እሰጥሀለሁ፤እንዲሁ ልነግርህ አልችልም እሺ” አለችኝና በቆምኩበት ጥላኝ ወደ ቤቷ ገባች፡፡ ስንት ደቂቃ በቆምኩበት እንደቆየሁ እንጃ! ቤቴ ስገባ በጣም መሽቶ ነበር፡፡
ምንድነው የምትጽፍልኝ? አፍቅሬሀለው ብትለኝስ ?ፈገግ አልኩ ሳላስበው…..
ከተኛሁ እንደ አቤሜሌክ ኢየሩሳሌም ጓደኛዬ ሌላ ሆና የምትጠብቀኝ መሰለኝ። የማሂ ሞትም ሆነ ሕይወት እንኳን ተኝቼ ዐይኔን ጨፍኜ እንዲያመልጠኝ አልፈለኩም። እንዲህ ስገላበጥ ነጋ፡፡ ቁርስ አላሰኘኝም፡፡ ማኂ የምትመጣበትን መንገድ በዐይኖቼ ደጅ እየጠናሁ እየተንጎራደድኩ ጠበቅኳት፡፡
ታናሽ ወንድሟ አቡሽ ከእኩዮቹ ጋር እየቦረቀ ሲመጣ አየሁት፡፡ ዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት የገባው ዘንድሮ ነው፡፡ ከዘጠነኛ ክፍል ተወዳዳሪ የሌለው ጎበዝ ተማሪ…..
እኔ የቆምኩበት ቦታ ሲደርስ ሰላም ብሎኝ ሊያልፍ ነው ስል ከቦርሳው አንዳች ነገር እየበረበረ ቀረበኝ፡፡
በድንጋጤ “ማኂ ቆየች” አልኩት፡፡
የማኂን የሂሳብ ደብተር እየሰጠኝ “ዛሬ አሞኛል አልመጣም፤ትናንት ያልኩህን ስታነብ ታገኘዋለህ” ብላሃለች” አለ፡፡
ግራ ገባኝ፡፡ ደብተሩን አበጠርኩት፡፡ ከቁጥር ውጪ ምንም የለውም፡፡ ወንድሟን ጠርቼ መጠየቅ ፈለግሁ፡፡ ግን ከጓደኞቹ ጋር እየቦረቀ ገና ድሮ ርቆኛል፡፡ ትቀልዳለች እንዴ?
እንዲሁ ደብተሩ ላይ እንዳፈጠጥኩ ጥቂት እንደቆየሁ አንድ ነገር ልብ አልኩ። የማኂ ደብተር ሂሳብ ደብተሯን ጨምሮ በጋዜጣ ወረቀት ተሸፍኖ አያውቅም፡፡ እጄ ላይ ያለው ደብተር ግን ባለ ለምድ ነው፡፡
በችኮላ ጋዜጣውን ስገነጣጥል የተጣጠፈ ወረቀት ዱብ አለ፡፡  
የፍቅር ደብዳቤ እንደሚሆን ተስፋ አደረኩ፡፡ ልቤ ስትዘል ስትፈርጥ መተንፈስ አቃተኝ፡፡ ፖስታውን እንደያዝኩ ዞር ዞር ብዬ አካባቢዬን አየሁ፡፡ ልብ የሚለኝ ሰው የለም። ትምህርት ቤት እስክደርስ አላስቻለኝም፡፡ እያዘገምኩ ፖስታውን ቀደድኩት፡፡ የማኂ የእጅ ፅሑፍ ….
“ቢኒዬ….ብሎ ይጀምራል፡፡ ዐይኔን ጨፍኜ በኃይል ተነፈስኩና እንደምንም ዝግ ብዬ እየተራመድኩ ማንበብ ጀመርኩ፡፡
“ቢኒዬ….” ሰሞኑን ስላስጨነኩህ በጣም አዝናለሁ፡፡ ለማንም የማልናገረው ግን ሕይወቴን ባዶ የሚያደርግ እውነት ዐውቄ ነው፡፡ ያን ያህል ስትጨነቅልኝ ሳይ ላንተ ብቻ ባወራህ እመኛለሁ፡፡ ግን ሁሉ ነገር ለማውራት ቀላል አይደለም፡፡ አሁን እንኳን ፅሑፉን እንዴት እንደምጀምረው ተጨንቄ ስንቴ ወረቀቴን ቀደድኩት፡፡….” እየተስገበገብኩ እንቅፋቱን እየቻልኩ ማንበብ ቀጠልኩ፡፡
“እናተ ሠፈር ከመምጣታችን በፊት ልደታ አካባቢ እንኖር እንደነበር ነግሬሃለሁ፡፡ የአባቴ እናት ቤት ሁለት ክፍል ሠርተን እንኖር ነበረ፡፡ ልደታ ያሉ የቀበሌ ቤቶች ከመፍረሳቸው በፊት አባዬ ከሚሰራበት መስሪያ ቤት በትምህርት ማነስ ተቀነሰ፡፡ ከአስራ ሁለተኛ ክፍል በላይ አልተማረም፡፡ በአስራ ሁለተኛ ክፍል ሥራ ካገኘ በኋላ ወንድሞቹን ማስተማር ነበረበት። ወንድሞቹ  ራሳቸውን ሲችሉ  ደግሞ እናቴን አግብቶ እኔና ወንድሜን ፈጠረ፡፡ ከእማዬ የፀሐፊ ደሞዝ ጋር እኛን ለማሳደግ ከባድ አልሆነበትም ነበር፡፡ እሱ ስራ ሲፈታ የእናቴ ደሞዝ ብቻ ቤታችንን ማስተዳደር ጀመረ፡፡ ቆይቶ ግን ለኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታ የቀበሌ ቤቶች መፍረስ ጀመሩ፡፡ እኛ ቤት ከባድ ጭንቀት ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሳለሁ። ለአያቴ ኮንዶሚኒየም ቤት ወይም የቀበሌ ቤት ምርጫ ቀረበለት፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤት ክፍያው ከባድ ስለነበር የቀበሌ ቤት መረጠች፡፡ ሁለት ክፍል ቤት ከአንድ ደባል ጋር ተሰጣት፡፡
ከዚህ በኋላ ከአያቴ ጋር መኖር ለእኛ ቤተሰብ ከባድ ሆነ፡፡ አባዬ አንድ የግል ድርጅት ውስጥ በጥበቃ ተቀጠረና ቤት ኪራዩን እችላለሁ አለ፡፡ እዚህ እናንተ ሠፈር መጣን። አንድ ክፍል ቤት 600 ብር ተከራየን። ያኔ የአባዬ ደሞዝ 500 ብር ስለነበር ቤት ኪራዩ እንዲሞላ እማዬ 100 ብር ትጨምርበት ነበር። ወላጆቼ እነሱ ምን ያህል ቢቸገሩ እንኳን ለእኔና ለወንድሜ አንዳች ነገር እንዳይጎድል በትምህርታችን እንዳንሰንፍ ይጥራሉ፡፡
በተለይ አባዬ በትምህርት ቀልድ አያውቅም። መፅሐፍ እንዳነብ ይፈልጋል። ዕረፍት በሆነ ቀን እኔና ወንድሜን ጭኖቹ ላይ አስቀምጦ ተምረን ወደፊት ሀገራችንን እንዴት ሳደግ እንዳለብን ይመክረናል፡፡ ከአደራው ብዛት ልክ እንደማሪያም ኢትዮጵያ ትውልድ   ሀገሬ ብቻ ሳትሆን የአስራት ሀገሬም ትመስለኛለች፡፡
አባቴ ሀገሩን በጣም ይወዳል፡፡ አንድ ዘፈን አለ ከአፉ የማይጠፋ፤
“ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፤ በአባቶቻችን ደም፤
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም የደፈረሽ ይውደም….”
ቤት ውስጥ ምኑንም ምኑንም እየጠጋገነ ወይ ሲያነብ ቆይቶ ሲደክመው ይዘፍናል። አንዳንዴ እየዘፈነ ያለቅሳል፡፡ ዘፈኑ አያስለቅሰኝም፤ እሱ ስላለቀሰ ብቻ ግን ዕንባዬ ይመጣል፡፡
“ግን ሀገራችንን  ክፉ ሚያስባትን ክፉ ሚያስብባትን
ቆራጥ ነን ልጆችሽ አንወድም ጥቃት
አንወድም ጥቃት….” ይልና አንዳንዴ ደግሞ መዝፈኑ አይዋጥለትም መሰለኝ “ኤዲያ” ይላል ጮክ ብሎ፤ ከዛ ረጅም ሰዓት ይተክዛል….ረጅም ሰዓት….
አባዬ ስላለቀሰ ብቻ ዕንባዬ ይመጣል፡፡ ግን አንድ ዕንባ እንዳልነበረኝ አሁን በቅርቡ ነው የተረዳሁት፡፡
…ሌላውን ነገር ልተውና ወደ ዋናው ጉዳይ ልግባልህ የተከራየነው ቤት በየጊዜው እየጨመረ 1500 ብር ደረሰ፡፡ የአባዬ ደሞዝ ግን የጨመረ አይመስለኝም። እማዬ ለቤት ኪራዩ አንድ ሺ ብር መጨመር ነበረባት። የእሷ ደሞዝ ለዓባይም ለኮንዶሚኒየም ቤትና ለሌሎች ጉዳዮች ተቆራርጦ 1500 ብር ቤት  ይመጣል፡፡ በአምስት መቶ ብር አራት ሰው ወር ሙሉ በቀን አንዴ ይበላል? በአምስት መቶ ብር እማዬ ከአቧሬ ሜክሲኮ በአውቶብስ እንኳን  መመላለስ ትችላለች? በአምስት መቶ ብር ለሁለት ልጅ ደብተር መፅሐፍ የደንብ ልብስ ይገዛል? ይኸ ሁሉ አይሆንም ግን በተዓምር ይሁን በሌላ ቤታችን ጎድሎ አያውቅም፡፡
በነገራችን ላይ አዋሬ ከመጣን ጀምሮ እኔና አቡሽ ከወላጆቻችን ጋር የምናመሸው አንዳንዴ ነው፡፡ የአባዬ ስራ የግድ ሌሊት ነው፡፡ እማዬ ደግሞ ቢሮ ስራ እየበዛ ብላ ታመሻለች፡፡ ራት በልተን በጊዜ እንድንተኛ አጥብቃ ስለምታስጠነቅቀን አንጠብቃትም፡፡
ባለፈው ሳምንት ግን በሊቢያ የታረዱትን ኢትዮጵያውያን የቪዲዮ ፊልም አይቼ ስለተረበሽኩኝ እንቅልፍ እምቢ ብሎኝ ስገላበጥ እማዬ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት መጣች፡፡ ስልክ እያወራች ነበር፡፡ ተነስቼ አብሪያት ልተኛ ሳመነታ አንድ አስደንጋጭ ቃል ስትናገር ሰማሁ፡፡
“ንጉሴ ሙት አሁንስ እኔንም ፍቅር አስይዘኸኛል …” ብላ ሳቀች፡፡ ደነገጥኩ። ንጉሴ ማነው? ቀጠለችና ደግሞ “እግዚአብሔር ይስጥልኝ የኔ ጌታ…” ስትል ሰማሁ፡፡ ለምኑ ነው?
ውስጤ ኃይለኛ ቁጣ ሲፈጠር ይታወቀኛል፡፡ እማዬን ልሰድባት ፈለኩ። ደግሞ ፈራኋት፡፡ እንደ አባዬ ምክር ባታበዛም አንዳንዴ ግን “የኔ ልጅ ሁሉ ነገር ይደርሳል እንዳትታለይ፤ አሁን መማር ብቻ እሺ…” ትለኛለች፡፡ የሰፈሩ ሰው ልጅሽ ጨዋ ናት አለኝ ብላ ትኮራለች፤ ጨዋ ያልሆነች እናት በልጇ መኩራት ይገባታል ቢኒ?
ጠዋት ያን ዘፈኑን እያፏጨ ብርድ እያንቀጠቀጠው  ሲመጣ አባዬ አሳዘነኝ፡፡
“ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም ባባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም የደፈረሽ ይውደም…”
“አባዬ ሚስትህ ተደፍራልሀለች…”ብዬ ማቃጠር አማረኝ፡፡
እናቴ ለአባቴና ለእኛ ለልጆቿ ቁርስ ለመስራት ትንደፋደፋለች፡፡ አቤት እንዴት እንደናቅኳት….
አባዬ እያፏጨ የእነሱ አልጋ ላይ ዘፍ አለ፡፡
“ምን ሆንክ ፊትህ እኮ ገርጥቷል” አለች እናቴ፤ የታወቀባት መስሎኝ ጆሮዬን አቆምኩ፡፡
“በሊቢያ የታረዱትን ልጆች ነገር ካየሁ ጀምሮ ላብድ ደርሻለሁ፡፡ እማዬም እባክህ የልጄን ድምጽ ከየትም ብለህ አሰማኝ እያለች ወጥራ ይዛኛለች፡፡” አላት፡፡ ከሶስት ወር በፊት በተመረቀበት ትምህርት ሥራ ስላጣ ወደ ሱዳን ስለሄደው ስለ አባ ታናሽ ወንድም እንደሚያወሩ ገብቶኛል፡፡
“እንግዲህ እሱ እግዚአብሔር መላ ያምጣ እንጂ ምን ማድረግ ይቻላል” ስትል  እናቴ ድምጿን ሁሉ ጠላሁት፡፡ በተኛሁበት ዝም ብዬ ሳደፍጥ “ነይ እስኪ የኔ አበባ ነይ…” አላት አባዬ
ሻይውን ጥዳ አጠገቡ ቁጭ አለች፡፡
“አሞሻል እንዴ ፊትሽ እኮ ልክ አይደለም” አላት፡፡
እሷ አትናገርም፡፡
 ቆይተው ቆይተው “እባክሽ አታልቅሺ” ሲላት ሰማሁ፡፡
ቀስ ብለው ተንሾካሾኩ፡፡ ሊሰማኝ አልቻለም፡፡ አንደምንም አጮልቄ ሳያቸው ደግሞ ተቃቅፈው ሁለቱም አለቀሱ፡፡
ግራ ገባኝ፡፡ እናቴ ተገዳ ተደፍራ ነው?
ቆይታ እናቴ ብር እየቆጠረች ይኼ ላስፔዛ …ይኼ ለቤት ኪራይ…
አባዬ እያለቀሰ ይሰማል፡፡
እናቴ ቆጥራ ስትጨርስ እንደምንም ፈገግ ብላ “አሁን እኮ ትንሽ ነው የቀረን ልጃችን እየደረሰች ነው፤ ወንድሟን  እሷ ትረዳለች፤ ለእኔና ለአንተ ሆድ ብንለምንስ መኖር ያቅተናል?” አለችው፡፡
አባዬ እጆቿን በሁለት መዳፎቹ ሸፍኖ ተንሰቀሰቀ፡፡
እማዬ አባቴን አቅፍ ራሱን እያሻሸች ግን ዕንባ  እያነቃት “ኧረ ተው ግፍ ነው ምነው የእኛ ተላላኪ ልጆቿን  ለማሳደግ ብላ ሌት ሌት መንገድ ላይ ትቆም የለ፤ እኔስ  አንድ ባለሀብት ጥሎልኝ እንደሷ አልሰቃይም” አለችው፡፡
 አየህ ቢኒ፤ በአንድ ቀን ሌሊት እንዴት እንደፈረስኩ? ይኼን ሰምቼ እንዴት ሳቅ ይመጣልኛል?
ይኼን ሰምቼ እንዴት እንደድሮው ልሁን…
ቢኒዬ “አጥቢያ” የሚለውን መፅሐፍ እንዳነበው አባዬ ሲሰጠኝ “ይኄ የድሆች የመከራ አጥቢያ ነው” ብሎኝ ነበር፡፡ ራስህን ሸጠህ ዳቦ መብላት እንኳን አሁን አይቻልም። በአጥቢያ ክብር ከፍለህ ዳቦ ትበላ ነበር፡፡ አሁን ሰፈሩ ታሪክ ሆኗል፡፡ ያ ሁሉ የአራት ኪሎ ተፈናቃይ በዚህ  አምስት ዓመት ውስጥ ሌላ ያልደረስንበት ከግምት  በላይ የሆነ ስንቱን መከራ ገፍቶ ይሆን? አላውቅም፡፡
እውነትም አጥቢያ …. ልንፈናቀል ነው  ብሎ  መጨነቅ   አጥቢያ ነው ተፈናቅሎ እንደ ውሻ በየታዛው ተልከስክሶ  መኖርስ ምንድን ነው?
ቢኒ ታምሜያለሁ እውነት አሞኛል፡፡ በሊቢ የታረዱት ሰዎች የኢትዮጵያ ህዝብ አለቀሰ ግን እንባችን እንድ ነው? የእማን ገላ አቆሽሾ የአባን ክብር እያጎደፈ ለእኛ ማሳደጊያ ገንዘብ የሚሰጣት ሰውዬና አባዬ አንድ እንባ ነው የሚያለቅሱት? እንኳን ሌላው እኔ ልጃቸው እንኳን ይሄን ጉድ ከመስማቴ በፊት  አንድ እንባ ነበረኝ?
ቢኒ…. መማር አልቻልኩም፡፡ ግን መማር አለብኝ፡፡ ያወቅሁትን እውነት ወላጆቼ አውቀው ሌላ እምባ ማየት አልፈልግም። ተምሬ ስራ ማግኘቴን አላውቅም፤ ግን ለእነባዬ ስል የግድ ማትሪክ ውጤት ማምጣት አለብኝ፤ የግድ…
…..
“ቢኒ በቃኝ አንብበህ ስትጨርስ ቅደደው እሺ….”
ንባቡ አለቀ፡፡ ብዙ እንባ ጠብታዎች ወረቀቱ ላይ አርፈዋል፡፡ ዛሬ ገና ከጓደኛዬ ጋር አንድ እንባ አነባሁኝ… ቁጭት፣ ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ ግራ መጋባት፣ ተስፋ ማድረግና ተስፋ መቁረጥ የሚነበብበት የእንባ ፅሑፍ….
“አንተ ምናባህ ይገትርኸል፤ ዞር ብል ከዚህ!” አስበርጋጊ ጩኸት፡፡ ሄጄ ሄጄ ወደ አራት ኪሎ መታጠፊያ ቦታ ላይ ቂሚያለሁ።
ቀና ብዬ እሳት በሚተፉ አይኖቼ፤ እሳቱን ለማጥፋት በሚጎርፉ እንባዎቼ ውስጥ ወደ ማማው አንጋጠጥኩ፡፡ ንቀት የተመሞላ አይንና “ዋ” የሚል አፈ ሙዝ ይታየኛል፡፡
(ምንጭ፡- “የባስሊቆስ እንባ”፤ ትዕግስት ታፈረ ሞላ)

Read 1396 times