Sunday, 26 December 2021 17:46

የ"ሩብ ጉዳይ ለሀገር ጉዳይ" - ድንቅ ስኬት ያኮራል - ያነቃቃል!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

"ይህ የሁላችንም ታሪክ ነው፤ ማን ከማን የማይባል፡፡ እንደዋዛ የተጀመረው የ"ሩብ ጉዳይ ለሀገር ጉዳይ" ዘመቻ ገና ቲኬቱ ሳይታተም እንዲሁ በእምነት ብቻ 500 ሺህ ብርን ተሻግሯል፡፡ ይህ የሁላችንም ውጤት ነው፡፡ ከአንድ ቤት 20ሺህ እና 25ሺህ ብር ካወጡት ጀምሮ፣ ማድረግ ፈልጋችሁ እጅ አጥሯችሁ ዝም እስካላችሁት ድረስ፣ ይህ ውጤት የሁላችንም ነው፡፡ ሌላ ቀርቶ ፖስት በሚደረጉት ላይ አስተያየት በመጻፍ ወይም በማጋራት ሌሎች እንዲያዩ ያደረጋችሁ ሁሉ፣ይህ ውጤት የእናንተም ነው፡፡"
በጋዜጠኛና ጸሃፌ ተውኔት ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ፌስቡክ ገጽ ላይ፣ከዚህ በላይ የሰፈረውን ጽሁፍ ከተመለከትኩኝ ከሁለት ቀን በኋላ ነበር ወዳጄን ቴዎድሮስን በስልክ አግኝቼው በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርኩት፡፡
"ሩብ ጉዳይ ለሀገር ጉዳይ" በሚል እሱና ጓደኞቹ በጀመሩት ዘመቻ፣ የ500ሺህ ብር ገቢ ማሰባሰብ መቻላቸውን አድንቄ ስነግረው፣ የገንዘቡ መጠን ወደ 700 ሺህ ብር መመንደጉን በመግለጽ ማረምያ ሰጠኝ፤ ቴዲ፡፡ ቀጥዬ ያቀረብኩለት ጥያቄ፤ "ሩብ ጉዳይ ለሀገር ጉዳይ" እንዴት ታሰበ የሚል ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡-
በቅርቡ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይን ጨምሮ ሌሎች አርቲስቶችና ጋዜጠኞች፣ በጦርነቱ ከፍተኛ ውድመት ወደደረሰባት አጣዬ ተጉዘው ነበር፡፡ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ነዋሪዎች ያሰባሰቡትን የተለያዩ የእርዳታ ቁሳቁሶች በአካል ተገኝቶ ለማድረስ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ጦርነቱ አጣዬን ምን ያህል እንዳወደማት ትክክለኛ ግንዛቤ ያገኙት፡፡ በነዋሪዎች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠንና ጥልቀት ተዘዋውረው ማየታቸውንም ቴዎድሮስ በሃዘን ድምጸት ነግሮኛል፡፡
"የሆነ ከተማ ወድሟል ተብለህ በሬዲዮና ቴሌቪዥን ሲነገርህና ራስህ በአካል ሄደህ የደረሰውን ውድመትና ጥፋት መመልከት ፍጹም ይለያያል፤የሚጋባ ነገር አለው" ብሏል - ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ፡፡
ከዚህ ጉዞ መልስ ነው ከዓመታት በፊት በራሱ በቴዎድሮስ ተ/አረጋይ የተደረሰውን "ሩብ ጉዳይ" የተሰኘ ተወዳጅ ቲያትር በተለያዩ የመግቢያ ዋጋዎች ለተመልካች በማሳየት፣ለተፈናቀሉ ወገኖች ገቢ የማሰባሰብ ሃሳቡ የፈለቀው፡፡ ደራሲው ተዋንያኑ፣ ዳይሬክተሩና ፕሮዱዩሰሩ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሃሳቡ ዙሪያ ውይይትና ምክክር አደረጉበት፡፡ የተለያዩ የትኬት ዋጋ ተመኖች አወጡ፤ ከ2000 ብር እስከ 100 ሺ ብር፡፡ ዘመቻው በማህበራዊ ድረ ገጽ ተጧጧፈ፡፡ የመጀመሪያ ዕቅዳቸው በአጠቃላይ 300ሺ ብር ማሰባሰብ ነበር፡፡ አሁን ግን ከዕቅዳቸው ከእጥፍ በላይ ልቆ 700ሺ ብር ደርሷል፡፡ ቲያትሩ ለተመልካች የሚቀርበው ታህሳስ 26 ቀን 2014 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ ገቢው ከ1 ሚሊዮን ብር እንደሚበልጥ ወዳጄ ቴዲ ነግሮኛል፡፡ ቅንጣት አልተጠራጠርኩትም፡፡ ለምን ቢሉ ቲያትሩን ወደ አገር አሳድገውታል፡፡ "ሩብ ጉዳይ ለሀገር ጉዳይ" አይደል  የሚለው፣የዘመቻው መሪ ቃል፡፡

ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ዘመቻውን አስመልክቶ በፌስ ቡክ ገጹ ካሰፈረው መረጃ በጥቂቱ እነሆ፡-
"ለዚህ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሃሳብ ሜላት ዳዊት ናት፡፡ የኋላሸት ዘሪሁን ደግሞ ሃሳቡን አዳበረው፡፡ እኛ ሁላችን ከሁለቱ በኋላ ነው የመጣነው፡፡ ጥናት ቢያስፈልገውም በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካም ይሁን በዓለም ትያትር ታሪክ ውስጥ ሊመዘገብ የሚችል ታሪክ ተሰርቷል፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ ሁሉ ብር የተሰበሰበው በመላው ዓለም ከሚገኙ የእኛ ጓደኞች መሆኑ ለእኛ ድላችን ነው፡፡ ሙያን መስጠት ብቻ ሳይሆን ትያትር ገንዘብ አምጪም ጭምር እንደሆነ አሳይተንበታል፡፡ ከመንግስት ምንም ዓይነት ድጋፍ የሌለውና በተደጋጋሚ ታክስና ቢሮክራሲ መከራውን የሚያይ ጥበብ ነው፡፡ አሁን በጥቂት በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪነት ተአምር እየተሰራ ነው። ይህ ትያትር ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ እንዲውል የፈቀደው ዳይሬክተሩና ፕሮዲዩሰሩ ተፈራ ወርቁ፣ከመፍቀድ አልፎ የ10ሺህ ብር ቲኬት ቆርጧል። በትያትር ታሪክ ውስጥ ከሸዊት ከበደ እና ከሳምሶን ታደሰ (ቤቢ) ውጭ ትያትር ለማየት ሳይሆን ለማሳየት 10 ሺህ ብር የከፈለ መኖሩን የምታውቁ ንገሩን።--"

ጥቂት ጠቃሚ መረጃዎች

*እስካሁን ለአንድ ትኬት የተከፈለው ከፍተኛ ገንዘብ - 60ሺ ብር
*ዳያስፖራ የትያትር አፍቃሪዎችና አገር ወዳዶች፣ ከ10ሺ ብር እስከ 25ሺ ብር ለአንድ ትኬት ከፍለዋል
*ዝነኛ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ለአንድ ትኬት 10ሺ ብር ከፍለዋል
*ብቸኛውን ባለ 100 ሺህ ብር አንድ የመግቢያ ትኬት የሚቆርጠው ማን ይሆን?

እኛም በመጨረሻ እንዲህ አልን፡- ኢትዮጵያን መውደድ ማለት በተግባር ሲገለጽ እንዲህ ነው! ለወገን መድረስ ማለትም ይኸው ነው!

Read 1195 times