Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 22 September 2012 10:58

የእንግሊዝ አምባሳደር - ስለ ኢትዮጵያ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ግሪግ ዶሪ ከጠ/ሚኒስትር መለስ ህልፈት በኋላ ስላለው የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ስለበጀት ድጋፍ፣ ስለ ኢንቨስትመንት፣ ስለ ሰብዓዊ መብት አያያዝና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ እነሆ:-የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈትን ተከትሎ በአገሪቱ ውስጥ ችግር ይፈጠራል ብለው የገመቱ ሰዎች ነበሩ፡፡ እርስዎ ተመሳሳይ ግምት ነበርዎት?የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ድንገተኛ ሞት አሳዛኝ ነው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ማለት አንድ ሰው ማለት አይደለችም፡፡ ይሄ የታሪክ መጨረሻ አይመስለኝም፡፡ በአገሪቱ ብቃት ያለው መንግስት አለ፡፡ አገሪቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ጨምሮ በርካታ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች አሏት፡፡ ይህም ወደሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ያስጉዛችኋል፡፡ የወትሮ እንቅሥቃሴና ሥራ እንደተለመደው ይቀጥላል፡፡ ባለፉት ሳምንታትም ሆነ አሁን የፀጥታና ደህንነት ችግር አላየሁም፤ ደንብና ስርዓት እንደተጠበቀ ነው፡፡

ከመንግስት ጋር መወያየታችንን ቀጥለናል፡፡ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን በብዙ አጋጣሚዎች አግኝቼአቸዋለሁ፣ ከብሪታንያ ሚኒስትርና ከኔም ጋር ተወያይተናል፡፡ በሁለትዮሽ ግንኙነታችን ላይ ለውጥ አይኖርም፣ በብዙ ፈርጆች እንደነበረው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለቀጣይ ጥቂት ዓመታት እንዲሰሩ እንጠብቅ ነበር፡፡ ራሳቸውም እ.ኤ.አ በ2015 ሥልጣን እለቃለሁ ብለው ነበር፡፡ የስልጣን መተካካቱ ከገመትነው በላይ ፈጥኖ ተከናውኗል፡፡ በፖሊሲና በግንኙነት አንፃር ህልፈታቸው ያሳደረውን ተፅእኖ ማጋነን ተገቢ አይመስለኝም፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ህልፈታቸው በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል ይላሉ…

እውነቱን ለመናገር መለስ በጥልቅ በሳልነታቸው ልዩ መሪ ነበሩ፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች የመለስ አለመኖር ጉዳት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ድምፅ ነበሩ፡፡ ለምሣሌ በአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ ላይ የሰሩት ተጠቃሽ ነው፡፡ ከሁለቱም ሱዳኖች መሪዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ሀገራቱ ወደ ጦርነት እንዳያመሩ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አለመኖራቸው ክፍተት ይፈጥራል የሚለው ግን አይታየኝም፡፡ አቶ መለስ ሀገሪቱን ብቻቸውን አልነበረም የሚመሩት፡፡ መንግስትና የሥራ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም ብልህና ብቃት ያላቸው ኃላፊዎች ሀገሪቱን መምራትና ማስተዳደሩን ይቀጥላሉ፡፡ የአገሪቱን ሁኔታ ስቃኝ የእድገት መርሃ ግብሮችና ፖሊሲዎች መቀጠላቸውን እገነዘባለሁ፡፡ ትምህርት፣ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችና ስብሰባዎች ላይ ክፍተት አልተፈጠረም፡፡ በተወሠኑ ዘርፎች መለስን ማጣት በጣም ያሳዝናል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ግን ያለቀ ጉዳይ ነው ማለት አይቻልም፤ ሕይወት ይቀጥላል፡፡

እንግሊዝ በቀጥታ ለመንግሥት የበጀት ድጋፍ በመስጠት ትታወቅ ነበር፡፡ አሁንስ?

ለኢትዮጵያ መንግስት በቀጥታ የበጀት ድጋፍ አናደርግም፡፡ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ይኼን አላደረግንም፡፡

ከክልል መንግስት ጋር እንሰራለን፡፡ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲሟሉ የገንዘብ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ከሲቪል ማህበረሰብ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችም ጋር እንሠራለን፡፡

የዚህ ድጋፋችሁ መጠን ምን ያህል ነው?

በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ 1.3 ቢሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ ለመስጠት ነው ያቀድነው፡፡ ሠላሳ ሰባት ቢሊዮን ብር ገደማ ይሆናል፡፡ ሀቁን ለመናገር በአጠቃላይ እርዳታ የአሜሪካ መንግስት ይበልጣል እላለሁ፡፡ የእኛ መንግስት ሁለተኛው ሊሆን ይችላል፡፡ የእንግሊዝ መንግስት ለዓለም አገራት ከሚሰጣቸው ድጋፎች ሁሉ ትልቁ በእርግጠኝነት የኢትዮጵያ ነው፡፡ ለሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታትም በዚሁ ይቀጥላል፡፡ ይህ በየዓመቱ 330 ሚሊዮን ፓውንድ ማለት ስለሚሆን ብዙ ገንዘብ ነው፡፡

ከፍተኛ ድጋፍ የምትሰጡ ከመሆናችሁ አንፃር በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ምን እያደረጋችሁ ነው? አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስትን በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተደጋጋሚ እንደሚተቹ ይታወቃል…

ስለ የትኛው መብት ነው የምናወራው የሚለውን መለየት ያለብን ይመስለኛል፡፡ የምናወራው ስለሕብረተሰባዊና ኢኮኖሚያዊ መብት ከሆነ በአገሪቱ ላይ አዎንታዊ ለውጦች አሉ፡፡ ሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶችን በተመለከተ ግን የተባለው ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ እኛም የተወሠኑ ሥጋቶች አሉን፡፡ ይህንን በግል ከኢትዮጵያ መንግስት ኃላፊዎች ጋር እናወራለን፡፡ ሥጋቶቻችንንም እንገልፃለን፡፡ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሰብዓዊ መብቶች እንዲሻሻሉ ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም ለዚህ ቅድሚያ እንደሚሰጡ ነግረውን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ስንቀርፅም ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲካተቱ እናደርጋለን፡፡ ይሄም የሰብአዊ መብት ሌላው መልክ ነው፡፡

አንዳንድ ወገኖች ግን መንግስት ሰብዓዊ መብት እንዲያከብር የምታሳርፉት ተጽዕኖ እዚህ ግባ የማይባል ነው ይላሉ…

እኔ በበኩሌ የዚያን ያህል ተስፋ አልቆርጥም፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ መሥራታችንን እንቀጥላለን፡፡ እንዳልኩት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዕቅድ ረዥም ነበር፡፡ የተተኪው መንግስት እቅድም እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይህ ሂደት እንዲጠናከር ወይም ተጠናክሮ ማየት እንፈልጋለን፡፡ እንደሚመስለኝ ሀገሪቱ የበለጠ ባደገችና ሀብታም እየሆነች በሄደች ቁጥር የተማረ ወጣት የሥራ ኃይል ተጨማሪ መብቶችን ይጠይቃል፡፡ ብልህ መንግስት እነዚህን በቀናነት ይመለከታል፡፡

የእናንተን መንግስት ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን ቢመሰክሩም ዕድገቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድሀው የህብረተሰብ ክፍል ጋ አልደረሰም በሚል የሚከራከሩ አሉ…

ይሄ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከድህነት ተመንጥቀው ወጥተዋል፡፡ የምግብ ዋስትናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡ በቂ የእህል ምርት በማጣት የሚቸገሩት ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም፡፡ ችግሩን ለማቃለል የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር እየሰራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሁኔታ የዛሬ አስር ዓመት ገደማ ከነበረው እጅግ በጣም ተሻሽሏል፡፡ በመላ ሀገሪቱ ብዙ ልጆች ትምህርት ቤት ሲሄዱ ታያለህ፡፡ ብዙ ሰዎች ሕክምና ማግኘታቸውን ታያለህ፡፡ ጉልህና የሚለኩ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ ይህም በየጊዜው እየቀጠለ ነው፡፡ የሚሊኒየሙን የእድገት ግብ ለማሟላት የኢትዮጵያ መንግስት እየጣረ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለኢትዮጵያ በርካታ የልማት ድጋፎች እያደረግን ያለነው፡፡ ምክንያቱም ውጤቱን እናያለን፡፡ ስለዚህ የድሃው ሕይወት አልተለወጠም በሚለው አልስማማም፡፡

የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላትም እኮ ኢትዮጵያን የረሃብ ምሳሌ አድርጎ ነው የሚጠቅሳት…

የትኛውንና የመቼውን የመዝገበ ቃላት ሕትመት ነው የጠቀስከው? በየጊዜው በኢትዮጵያ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ በአንድ ወይ በሌላ በኩል መልኩ የምርት መቀነስና ድርቅ ሲከሰት በጣም ድሀ የሆኑ ሰዎች መቸገራቸው አይቀርም፡፡ ለእነዚህ እርዳታ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ግን እንደዚህ የሚቸገሩ ሰዎች ቁጥር ባለፉት አስር እና አስራ አምስት ዓመታት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከረድኤት ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሚያደርገው ጥረት ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ ለውጥና መሻሻሎችን ማየት ችያለሁ፡፡ ተንሰራፍቶ የነበረው ረሀብ ካለፉት ጊዜያት የበለጠ እየቀነሰ ነው፡፡

የሴፍቲ ኔት ፕሮግራምን እየደገፋችሁ ነው፡፡ እስካሁን ግን ህብረተሰቡ ከተረጂነት ወጥቶ ራሱን አልቻለም፡፡ ከዚህ አንፃር ፕሮግራሙ ስኬታማ አይደለም ለሚሉ ወገኖች  ምን ይላሉ?

ቁምነገሩ በችግር ውስጥ የሚኖሩ ወገኖችን መደገፍ ነው፡፡ በድርቅ ወይ በሌላ ምክንያት የምግብ ዋስትናቸው ተጓድሏል፡፡ ለተወሠነ ጊዜ የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ነው ሥራው፡፡ እንደዚያ አይነት ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም በአጠቃላይ የተጎዱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ በፍጥነት እያደገ ያለ የሕዝብ ቁጥርም አለ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለመቋቋም እገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የረዥም ጊዜ እቅዱ ግን የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖሩ ማስቻል ነው፣ የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጥ፡፡ የምግብ እርዳታ እያገኙ ቀስ በቀስ አካባቢውን የሚለውጥ ሥራም እየሰሩ ነው፡፡ ምርታማነቱን ያጣ መሬት ወደ ምርታማነት በማሻሻል ይንቀሳቀሳሉ፡፡

የኢትዮጵያና የእንግሊዝ የንግድ ግንኙነት በምን ደረጃ ላይ ነው?

ከጥቂት ዓመታት በፊት ከዝቅተኛ ደረጃ ነው የጀመርነው፡፡ ግን ያለፉትን አምስት ዓመታት ስትመለከት፣ በሁለቱም አቅጣጫ ትልቅ እርምጃና ለውጥ ታያለህ፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ እንግሊዝ የሚደረገውን ንግድ ያየህ እንደሆነ ከ50 ሚሊዮን ወደ 105 ሚሊዮን ፓውንድ ከእጥፍ በላይ አድጓል፡፡ ከብሪታንያ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገውም በተመሳሳይ ጊዜ ከ62 ሚሊዮን ወደ 148 ሚሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ አድጓል፡፡

ይሄ ትልቅ ጭማሪ ነው፡፡ የንግዱ መጠንም በጣም ጠንካራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኩባንያዎችን ኢንቨስትመንትም እያየን ነው፡፡ በሜታ ቢራ ፋብሪካ ኢንቨስት ያደረገው ዲያጆ 225 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መዋለ ንዋይ አፍስሷል - ዘንድሮ፡፡ ይህም በኢትዮጵያ እስካሁን የብሪታንያ ትልቁ ኢንቨስትመንት ነው፡፡

በጃሽን ቢራም የደየት ካምፓኒ ኢንቨስትመንት አለ፡፡ የብሪቲሽ ሚኒራል ውሃ ፍለጋ ካምፓኒም በዘንድሮው ዓመት በኢትዮጵያ ኢንቨስት አድርጓል፡፡ ሌሎች በርካታ ኩባንያዎችም አሉ፡፡

ወደኋላ ሄደን የታሪክ ጥያቄ እናንሳ…የጣልያን ፋሺስት መንግስት ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ እንግሊዝ ኢትዮጵያን ባትደግፍ ኖሮ በፋሺስቱ ቅኝ ግዛት ስር ትወድቅ ነበር ማለት ይቻላል?

ይኼን ለማለት አልደፍርም፡፡ ከ1886 ጀምሮ ጥሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት አለን፡፡ ከዚያም በፊት ብዙ ግንኙነቶች ነበሩ፡፡ ከሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ፡፡ በ1936 ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሲሰደዱ፣ እንግሊዝ ነው የሄዱት፡፡ ይህ ጥሩ ግንኙነት ያንፀባርቃል፡፡ በእርግጥ የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ወታደሮች ጣሊያኖቹን ለማባረር ጎን ለጎን ተሰልፈው ተዋግተዋል፤ በ1941 እ.ኤ.አ፡፡ ኢትዮጵያ እንግሊዝ ስላገዘቻት ነው ነፃ የወጣችው ግን አልልም፡፡ በጋራ ሰርተን ውጤታማ ሆነናል፡፡ አሁን በዘመናዊ የግንኙነት መረብ ውስጥ ነን፡፡ ኢጣሊያም አሁን ወዳጃችን ስለሆነች አብረን እንሠራለን፡፡ በንግድ፣ በልማትና በኢንቨስትመንት ላይ እናተኩራለን፡፡

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሃድ ወይም እንድትገነጠል የእንግሊዝ ሚና ምን ነበር?

የታሪክ ተማሪ ነበርኩ፡፡ ታሪክ በአጠቃላይ ይመስጠኛል፡፡ ማወቅ የምፈልገውን ያህል የአፍሪካ አካባቢያዊ ታሪክ አልተነገረኝም፡፡ ያንን ማስተካከል እፈልጋለሁ፡፡ እንግሊዝ ኤርትራን ከጣሊያን ነፃ ለማውጣትም ተዋግታለች፤ በ1941 እ.ኤ.አ፡፡ ቀጥሎ በመንግስታቱ ድርጅት ጥበቃ እንግሊዝ ኤርትራን አስተዳድራለች፡፡ በአሜሪካ ድጋፍ የመንግስታት ድርጅቱ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሀድ አድርጓል፡፡ ብሪታንያም ይህንን ውሳኔ አስፈፅማለች፡፡ እንደሚገባኝ ያንን እኛ አልመራንም፡፡ ግን ተቀብለነዋል፡፡ የቅርብ ጊዜ ታሪክን በተመለከተ ሪፈረንደሙን ደግፈን ውጤቱን እንደማንኛውም የዓለማችን ሀገር ተቀብለናል፡፡ ይህን ተከትሎም የኤርትራ ነፃ መንግስትነት ታውጇል፡፡

ሪፈረንደሙ ነፃ አልነበረም በሚል ቅሬታ ያላቸው ወገኖች አሉ…

ትክክል ልትሆን ትችላለህ፡፡ አንዳንዶች በሂደቱ ደስተኛ እንዳልነበሩ ማሰብ ምክንያታዊ ነው፡፡ በትክክል ታሪኩን ስለማላውቅ ዝርዝር ነገሮች አላወራም፡፡ በሆነ መልኩ የታሪክ ጉዳይ ነው፡፡ በጣም አስፈላጊው አሁን በተግባር ምን አለ የሚለው ነው፡፡ አሁን ጥሩ ያልሆነውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሻሻል መሞከሩ ነው ተገቢው፡፡ ልዩነታቸውን ለመፍታት ሁለቱ ሀገራት በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ አለመወያየታቸው ይፀፅተኛል፡፡ ምክንያቱም ያለው ሁኔታ ከፍተኛ ኢኮኖሚን ያስከፍላል፡፡ የሁለቱም አገራት ሕዝቦች ድንበር አልፈው በነፃነት እንዲዘዋወሩ ከመግባባት ላይ ተደርሶ የንግድ ልውውጥና ጤናማ ግንኙነት ቢኖር ጥሩ ነው፡፡

በኤርትራ አምባሳደር አላችሁ…

አዎ አለን፡፡

የሁለቱን ሀገራት ግንኙት ለማሻሻል ትወያያላችሁ?

እንግሊዝ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሻሻል የምትችልበት መንገድ መኖሩን መነጋገራችን ግልፅ ነው፡፡ መነጋገር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የዳበረ ንግግር አለን፡፡ ከኤርትራ መንግስት ጋርም ንግግር አለን፡፡ ሁለቱ ወገኖች እንዲነጋገሩ ለማበረታታትና ወደ ጦርነት እንዳይሄዱ ለማደራደር ጊዜ ሰጥተን እንሰራለን፡፡ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ጉብኝት ሲኖር እኔም አስመራ ያለችው አምባሳደራችንም በቂ ማብራርያ መስጠታችንንና ድርድር ማበረታታችንንን እናረጋግጣለን፡፡

አሁንም ወደኋላ ልመልስዎ… በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጊዜ ከመጣው የጀነራል ናፒየር ጦር ወዲህ በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ እንግሊዝ ተወስደው የአብያተ መዘክር ፈርጦች ሆነዋል ይባላል፡፡ በእርግጥ ጥቂቶቹ ተመልሰዋል፡፡ ያልተመለሱት እዚያ መቆየታቸው አግባብ ነው?

ጀነራል ናፒየር በዘመተባት ፓኪስታንም ሥራ ነበረኝ፡፡ ሲንድ የሚባል ክፍለሀገር አለ፡፡ ጀነራሉ ያን አካባቢ ሲይዝ ወደ እንግሊዝ የላከው ቴሌግራም፣ በላቲን ‘ፔካቪ’ /I have sinned/ (ሀጢአት ሰርቻለሁ) ይላል፡፡ ሁለት ትርጉም አለው - “ሀጢአት ሠርቻለሁ” እና “ሲንድን ይዣለሁ” የሚሉ ሲሆን አሁን እንደ አካዳሚክ ቀልድ የሚነገር ነው፡፡ የመቅደላ ቅርሶችን ጥያቄ ለመመለስ አልችልም፡፡ ቅርሶቹን በባለቤትነት የያዘው የብሪቲሽ ሙዚየም ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ለመናገር ሕጋዊ መሠረት የለኝም፡፡ ሆኖም በጀነራል ናፒየር ወደ እንግሊዝ የተላኩ በርካታ ቅርሶች በብሪቲሽ ሙዚየም አሏችሁ፡፡ በለንደን በጥንቃቄ ተይዘውና መለያ ተሰጥቷቸው ተጠንተዋል፡፡ ስለነዚህ ለማወቅና ለማጥናት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ክፍት ነው፡፡ ቅርሶቹ እንዲመለሱ እንቅስቃሴ መኖሩን አውቃለሁ፡፡ በ1965 እ.ኤ.አ በተደረገ መንግስታዊ ጉብኝት የአፄ ቴዎድሮስን ማህተም ጨምሮ የተወሠኑ ቅርሶች ተመልሰዋል፡፡ ሌሎችም ቅርሶች ከዚያ ወዲህ ተመልሰዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ቤተመዘክር የአንድ ውስን አካባቢ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ቅርሶችን መያዝ አለባቸው የሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡ በግሌ ዓለምአቀፍ ቤተመዘክር ዓለም አቀፍ ስብስቦች ሊኖሩት ይገባል እላለሁ፡፡ የሆኖ ሆኖ ጉዳዩ የብሪቲሽ ሙዚየም እንጂ የእኔ አይደለም፡፡

በሃንጋሪ የእንግሊዝ አምባሳደር ሳሉ ውክልናዎ ለሀንጋሪ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ፣ የሶማሊላንድ፣ የጅቡቲና የአፍሪካ ሕብረት አምባሳደር ነዎት? የስራ መደራረቡ እንዴት ነው?

ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ሁሌም መባተል ነው፡፡ በአዲስ አበባ አምባሳደር ነኝ፡፡ በጅቡቲም አምባሳደር ነኝ፡፡ ግን እዚያ ነዋሪ አይደለሁም፡፡ በተቻለኝ መጠን ግን እሄዳለሁ፡፡ በአፍሪካ ሕብረት እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የብሪታንያ ቋሚ ተጠሪም ነኝ፡፡ አሁን በናይሮቢ አምባሳደር አሉን፡፡ ወደ ሞቃዲሾ ሄደው ሶማሊያንም ሶማሌላንድንም እንዲወክሉ ታቅዷል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን በሶማሌላንድ ያሉ ሥራዎችን እዚህ ያሉ ባልደረቦቼ እየሰሩ ናቸው፡፡ ለምሣሌ የሀገሪቱ ፀጥታ እንዲሻሻል እየሰራን ነው፡፡ ሀርጌሳ የሚሄዱ ሰዎች ናይሮቢ ከሚሄዱ ይልቅ ከዚህ በቀላሉ እንዲሄዱ ማድረግ ተችሏል፡፡ የልማት ፕሮግራሞችም እንደዚሁ እየተካሄዱ ነው፡፡ እስከማውቀው ድረስ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ናቸው ሁለት ሁለት አምባሳደሮች ያሏቸው፡፡ አንዲት ሌላ ሀገርም ሁለት አምባሳደሮች ለመመደብ እንዳቀደች አውቃለሁ፡፡ ቁምነገሩ ግን ለየትኛው ቅድሚያ እሰጣለሁ የማለት ነው፡፡ ደግሞ ብቻዬን አልሠራውም፤ ጠንካራ ባልደረቦቼ ያግዙኛል፡፡

ከእርስዎ በፊት የነበሩት አምባሳደሮች እንደእርስዎ ስራ ይበዛባቸው ነበር?

በተመሳሳይ የሃላፊነት ደረጃ ቢሰሩም ምን ያህል ስራ በዝቶባቸው እንደነበር አላውቅም፡፡  አሁን ግን በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ላይ የሚከናወኑ ስራዎች በዝተዋል፡፡ እየጨመረ በመጣው የንግድ ኢንቨስትመንት ግንኙነት እና በሌሎች የጋራ አጀንዳዎች ለምሳሌ እ.ኤ.አ በፌብሩዋሪ 2012 በለንደን የተካሄደው የሶማሊያ ጉባዔ የጋራ አጀንዳችን ነበር፡፡ በሁለቱ ሱዳኖች ጉዳይም አብረን እንሰራለን፡፡ በአፍሪካ ሕብረት የአቅም ግንባታ ፕሮጀክቶችም እንሳተፋለን፡፡ በተለይ በፀጥታና ደህንነት፣ በነፃ የንግድ ቀጣና ወዘተ፡፡ በቅርብ ጊዜ በርካታ የእንግሊዝ ሚኒስትሮች ወደዚህ መጥተዋል፡፡ ምክንያቱም ያለውን ግንኙነት ማጥበቅ በማስፈለጉ ነው፡፡ አሁን ካለፉት አመታት በበለጠ በርካታ የሁለትዮሽ ስራዎች አሉ፡፡ ከእኔ በፊት የነበሩት ባተሌ አልነበሩም ሳይሆን በሥራው እየጨመረ መሄድ የተነሳ አሁን የስራ መደራረቦች አሉ፡፡

አዲስ አበባ ያለ የእንግሊዝ አምባሳደር እያንዳንዷን ቀን እንዴት ያሳልፋል?

የተለየ ቀን የለኝም፡፡ ለምሳሌ ዛሬ ጠዋትን የጀመርኩት በአማርኛ ትምህርት ነው፤ ሕልም ቢሆንብኝም እየታገልኩ ነው፡፡ አንዳንዴ በአፍሪካ ሕብረት ሥብሰባ ይኖረናል፡፡ በሌላ ጊዜ ተቃዋሚዎችን ላነጋግር እችላለሁ፡፡ የሀገሪቱን የተለያዩ ክፍሎች እጎበኛለሁ ወይም በከፍተኛ ባለሥልጣን ደረጃ ከሚኒስትሮች ጋር ሥብሰባ ይኖረኛል፡፡ ባለፈው ሳምንት አዲሱ የDFID ባልደረባዬን ለማስተዋወቅ ከተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡ የሪሰፕሽን ግብዣዎችን ጨምሮ የምሽት ፕሮግራሞችም አሉ፡፡ ባህላዊ ዝግጅቶችም ይኖራሉ፡፡ ሁሉንም ማዳረስ ስለማይቻል መምረጥ አለብህ፡፡ በጣም አስፈላጊዎቹ ጋር ትሄዳለህ፡፡

የአምባሳደር ዋነኛ ሥራ ከቢሮ ይልቅ ሕዝቡ ውስጥ ነው የሚሉ የዲፕሎማሲ ባለሙያዎች አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ይስማማሉ?

በእርግጥ በኢትዮጵያ የብሪታንያ ተወካይ ነኝ፡፡ እዚህ ያሉ የእንግሊዝ ጉዳዮች ሁሉ ይመለከቱኛል፡፡ ከማንኛውም በኢትዮጵያ ከሚኖር እንግሊዛዊ የበለጠ የእንግሊዝ ምልክት እኔ ነኝ፡፡ በአዲስ አበባና በክልሎች ወጣ ብሎ መጎብኘትና ከሕዝብ ጋር መነጋገር አስፈላጊ ነው፡፡ ለእኔ ብቻ የተጣሉ ኃላፊነቶችና ሥራዎች አሉ፡፡ ለምሣሌ አንተ ቃለ ምልልስ ለማድረግ የጠየከው እኔን እንጂ ሌሎች የኤምባሲ አባላትን አይደለም፡፡ ክልሎችን ለመጎብኘት ስታልም ከማላዊ ወደ ኢትዮጵያ የተዛወረው ዓይነት የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ይገጥምሀል፡፡ ያልታሰቡ ድንገተኛ ጉዳዮች የሚያጋጥሙበት ጊዜ አለ፡፡ በጣም አሳዛኙ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሕልፈት የተጠበቀ አልነበረም፡፡ አስደንጋጭ ነው፡፡ ከዚህ ጋር የተያያዘ ሥራም አለ፡፡ ተገቢዎቹ ሰዎች ሃዘናቸውን መግለፃቸውን ማረጋገጥም አለብኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ  ካሜሮን እና ንግሥት ኤልሳቤጥ ዳግማዊት ይህን አድርገዋል፡፡ የብሪታንያ ሚኒስትርም ተገኝተዋል፡፡ እንዲሁ ሌሎች ያልተጠበቁ ጉዳዮችም ያጋጥማሉ፡፡

አብዛኛዎቹ ሥራዎችዎ ከውጭ ይልቅ የቢሮ ናቸው ማለት ይቻላል?

የለም፡፡ ያ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ከቢሮ ይልቅ ከቢሮ ውጭ የምሆንበት ሥራ ይበዛል፡፡ በዘመናዊ ዓለም እንደሚደረገው የኢሜል ጫናም አለብኝ፡፡ የፅሁፍ ሥራ መኖሩ ግልፅ ነው፡፡ ባልደረቦቼን በማስተባበር ስለምንሠራቸው ሥራዎች መወያየትም አለ፡፡ በዲፕሎማቲክ ሕይወት የተለያዩ ሰዎችን ማግኘትና መወያየትም ከቢሮ ውጪ ሊሆን የሚችል የየእለቱ ሥራ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ስትነሳ ወደ አዕምሮዎ የሚመጣው ምንድነው?

ከየእለት ሕይወቴ ጋር የሚያያዘው የአፍሪካ ዲፕሎማቲክ መዲና መሆኗ ነው፡፡ ጥንታዊነትና ብቸኛዋ በነፃነት የቆየች የአፍሪካ ሀገርም ነች፡፡ ልብ የሚመነጥቅ ውበት ያላትና ሕብረ ብዙ አገር ነች፡፡ ከፍተኛ የቱሪዝም አቅምም አላት፡፡ በሰፊው የምጣኔ ዘርፍ ረገድ ቀደም ሲል እንደ ተነጋገርነው ድሃ ሀገር ብትሆንም በፍጥነት እያደገች መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍሎች ስጎበኝ ብዙ ኩሩና የሚያስደንቁ ሕዝቦች እንዳሏትም አይቻለሁ፡፡ እዚህ ዘመዶች ስለነበሩኝም ልዩ ባህላዊ ታሪክ እንዳላት አውቅ ነበር፡፡ እዚህ ከመጣሁ በኋላ ደግሞ የበለጠ አውቄአለሁ፡፡

የኢትዮጵያ አገልግሎትዎን ሲፈፅሙ የት የሚመደቡ ይመስልዎታል?

በኢትዮጵያ ገና ብዙ አመት እንደማገለግል ተስፋ አለኝ፡፡ ስለዚህ የት እመደብ ይሆን ብዬ ከወዲሁ አልጨነቅም፡፡

 

 

Read 3767 times Last modified on Saturday, 22 September 2012 11:15

Latest from