Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 22 September 2012 11:16

መስቀል እና “ጣባ”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በመርካቶ ቆጮ ተራ በዛጎል የተጌጡ ጣባዎችን የሚሸጡ ሰዎች አሉ፡፡ የሶዶ ጉራጌ ሴቶች በየቤታቸው የሚሰሩትና ጣባን በዛጎል በማስጌጥ የሚታወቁበት ሥራም አለ፡፡ የቤት እመቤቶች ይህንን ችሎታቸውን በግል ከመጠቀም ውጭ ለገበያ ሲያቀርቡት አይታይም፡፡

እስቲ ራስሽን አስተዋውቂ…

ኢሲያ ሆሣ እባላለሁ፡፡ ትውልድና ዕድገቴ አዲስ አበባ መርካቶ ውስጥ ሸክላ ተራ ተብሎ በሚጠራው መንደር ውስጥ ነው፡፡ “ትምህርቴን በዕድገት በሥራ ትምህርት ቤት” እስከ 6ኛ ክፍል ተከታትያለሁ፡፡ በሸክላ ተራ ንግድ ከጀመርኩ 13 ዓመት ሆኖኛል፡፡

በሸክላ ተራ ምን ያህል ነጋዴዎች አላችሁ?

በፊት ብዙ ነበርን፡፡ አሁን ቁጥራችን እየቀነሰ 15 ያህል ነው ያለነው፡፡

ስንት ዓይነት የሸክላ ምርቶች አሉ?

የሽሮ ድስቶች በተለያየ ዓይነትና መጠን አለ፡፡ የቡና ጀበና ለቤት፣ ለሆቴልና ለ “ኑ የጀበና ቡና ጠጡ” የሚያገለግል አለ፡፡ ለተጋቢኖ፣ ለፍም ጥብስ ማቅረቢያ የሚሆን፣ የተለያየ መጠን ያለው የአበባ ማስቀመጫ፤ ከሰል ማንደጃ፣ የዕጣን ማጨሻ ፤ የአበባ መትከያ … ብዙ ዓይነት የሸክላ ምርት አለ፡፡ ጣባም በዓይነት፣ በመጠኑና በሚሰጠው አገልግሎት ብዙ ዓይነት አለ፡፡

ምርቱን ከየት ነው የምታገኙት?

እዚሁ አዲስ አበባ በዋነኛነት ከቀጨኔ አካባቢ ነው የሚመጣው፡፡ በኤሌክትሪክና በማገዶ የሚጋገርበት የሸክላ ምጣድ ከኦሮሚያ መንደሮች ነው በብዛት የሚመጣው፡ የጣባ ምርት ደግሞ በዋነኛነት ከወሊሶና አገና ከሚባል የጉራጌ አገር ነው የሚመጣው፡፡ ጣባ የሚለው ስያሜም ከጉራጌዎች የመነጨ ስለሆነ ይመስለኛል ከሌሎች የሸክላ ምርቶች የተለየ ስያሜ የተሰጠው፡፡

የቀጨኔ ሸክላ ሥራ ባለሙያዎች ጣባ አይሰሩም?

ይሰራሉ፡፡ ግን እኛ ከወሊሶ ወይም ከአገና የሚመጣውን ሰጥተናቸው፣ ያንን አስመስለው ይሰሩልናል እንጂ በዋነኛነት ጣባ አያመርቱም፡፡ ከወሊሶና ከአገና የሚመጣው ጣባ እንደ መስታወት የሚያበራ ልዩ ምርት ነው፡፡

ስንት ዓይነት ጣባ አለ?

እንደ ሌሎቹ የሸክላ ምርቶች ሁሉ ጣባም ብዙ ዓይነት አለው፡፡ ሆቴሎች አዋዜ፣ ዱለት፣ ክትፎ፣ ጎመን በሥጋ፣ ቡላ፣ ገንፎ … የሚያቀርቡባቸው የተለየ መጠንና ዓይነት ያላቸው ጣባዎች አሉ፡፡ በየቤቱም ለተለያዩ አገልግሎቶች ከሚውሉ ጣባዎች መካከል የጎመን፣ የአይብ (ወይም ሁለቱም ተቀላቅለው የሚቀርቡበት) እንዲሁም ሥጋ፣ አይብ፣ ወይም ጎመን ማዘጋጃና መቀላቀያ ሆኖ የሚያገለግል “ሴራ” የሚባሉ የጣባ ዓይነቶች አሉ፡፡ ክትፎ የሚዘጋጀው ብዙ ጊዜ በሴራ ነው፡፡

ለጣባዎች ክዳን የሚያዘጋጀው ማንና የት ነው?

ለክትፎ፣ ለአይብ ወይም ለጎመን ማቅረቢያነት የሚያገለግሉት ጣባዎች በስንደዶና በቅል እጀታ የሚሰራ የሚያማምሩ ክዳን አላቸው፡፡ ይህንን በመሥራት በመርካቶ መሶብ ተራ የሚታወቁ ሰዎች አሉ፡፡ ከወሊሶና ከጉራጌ አገር የሚመጣ የጣባ ክዳንም አለ፡፡ በይበልጥ የሚያምረው ግን ከገጠር የሚመጣው ነው፡፡ የመሶብ ተራ ባለሙያዎች ትዕዛዝ ሲያገኙ እንጂ ሥራዬ ብለው አይሰሩትም፡፡

ጣባዎችን በዛጎል የሚያስጌጠውስ ማን ነው?

በመርካቶ ቆጮ ተራ በዛጎል የተጌጡ ጣባዎችን የሚሸጡ ሰዎች አሉ፡፡ የሶዶ ጉራጌ ሴቶች በየቤታቸው የሚሰሩትና ጣባን በዛጎል በማስጌጥ የሚታወቁበት ሥራም አለ፡፡ የቤት እመቤቶች ይህንን ችሎታቸውን በግል ከመጠቀም ውጭ ለገበያ ሲያቀርቡት አይታይም፡፡

የሸክላ ምርቶች ገበያ ሞቅና ቀዝቀዝ የሚልበት ጊዜ አለ?

ምርቱ ክረምት ላይ ይቀንሳል፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በክረምት ብዙ ፀሐይ ስለሌለ ባለሙያዎቹ በማምረቱም በማድረቁም ይቸገራሉ፡፡ በክረምት ወቅት በሁለት ሣምንት ወይም በወር አንድ ጊዜ ነው ምርታቸውን የሚያመጡልን፡፡ በበጋ ግን በሣምንት ሁለት ቀን ያመጣሉ፡፡ ረቡዕና ቅዳሜ ዋነኛው የገበያ ቀን ነው፡፡

ከመስቀል በዓል ጋር በተያያዘስ ገበያው ምን ይመስላል?

የመስቀል በዓል የሚያከብረው ክርስቲያኑም ሙስሊሙም የከተማ ነዋሪ በአብዛኛው ወደ ትውልድ መንደሩ ስለሚሄድ የመስቀል በዓልን ምክንያት አድርጎ የሸክላ ምርቶችን ለመግዛት የሚመጣ ብዙ ሰው አለ ማለት አይቻልም፡፡

ከኑሮ መወደድ ጋር የሸክላ ምርቶች የመሸጫ ዋጋስ ምን ይመስላል?

በሥራው ላይ በቆየሁበት ባለፉት 13 ዓመታት  የሁሉም ምርት ዋጋ በእጥፍና ከዚያም በላይ ጨምሯል፡፡ የ10 ብር የቡና ጀበና 35 ብር፣ የ50 ሣንቲም አዋዜ ማቅረቢያ 3 ብር፣ የ2 ብር ክትፎ ማቅረቢያ 5 ብር፣ የ15 ብር ከሰል ማንደጃ 35 ብር … ደርሰዋል፡፡

ቤተሰባዊ ሕይወትሽ ….

ባለትዳርና የ3 ልጆች እናት ነኝ፡፡

 

 

Read 2751 times Last modified on Saturday, 22 September 2012 11:28

Latest from