Sunday, 09 January 2022 00:00

“የኢትዮጵያ ቀን ሊነጋ ፅልመቱን ሰንጥቆ ጉዞ ጀምሯል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የዘንድሮውን የልደት በዓል የምናከብረው የመከራችን ዘመን እያከተመ፣ የችግራችን ቋጠሮ እየተፈታ፣ የሰቆቃችን ምንጭ ላይመለስ እየደረቀ ባለበት ወቅት ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ መከራችንን ከኋላችን ጥለን ተስፋችንን አሻግረን እያየን የምናከብረው በዓል ነው ብለዋል- ከትናንት በስቲያ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት።
“ጠላታችን ዲያብሎስ በማይታክት ተንኮሉ አዳምን እስከመጨረሻው ከፈጣሪው አቆራርጦ ለማኖር ከፅንሰቱ እስከ ስቅለቱ ያልፈነቀለው ድንጋይ፣ ያልፈጸመው ሴራ አልነበረም። ጭፍራዎቹን አሰማርቶ ብዙዎች ከእውነት ጋር እንዳይቆሙ አድርጓል። ሐሰትን እየፈበረከ የክርስቶስን ስምን እንዲያጠፋ አድርጓል፡፡ ብዙዎች ወደ ክርስቶስ እንዳይሄዱ ተከታዮቹን አስፈራርተዋል።  ወደ ክርስቶስ የመጡትን ትታችሁ  ውጡ ብለዋል። ሃዋርያትን ጭምር በገንዘብ አስክደዋል። የውጭ ጠላቶች ሮማውያን፣ ከውስጥ ባንዳዎች አይሁድ ጋር አንድ ሆነው ክርስቶስን አሳድደዋል” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ሃይማኖታዊውን ታሪክ ጠቅሰዋል- በመልዕክታቸው።
ጠ/ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት የልደት በዓል መልዕክት ሲቀጥሉም፤
“የኢትዮጵያ ጠላቶችም ሊወለድ ያለውን ተስፋችንን ሊያጨነግፉ ለዓመታት ታግለዋል። ሲፀነስ ሊያጨናግፉት ሞክረው ነበር። መወለዱን ሲያውቁ ያልፈጸሙት የግፍ ዓይነት የለም። ግጭቶችን እየጠመቁ ህዝብን ከህዝብ ሲያጋጩ፣ በየደረሱበት ንፁሃንን ሲያፈናቅሉና ከህጻናት እስከ አዛውንት ያገኙትን ሲያሰቃዩና በጭካኔ ሲገድሉ ነበር። የሃገራችን የመዳንዋ ጊዜ የማይመጣ እስኪመስል ድረስ መከራችን በዝቶ ታይቷል። እንደ ሄሮድስ ያሉ አበጋዞች ብሩህ ተስፋችንን ሊያጨልሙ ባለ በሌለ ጉልበታቸው ታግለዋል። አንድነታችንን ሊንዱ ተባብረዋል፤ ሀገራችንን ሊያፈርሱ እስከ ሲኦል ለመውረድ ምለዋል። ኢትዮጵያ በዚያ ሁሉ መከራ  ውስጥ አልፋ  እዚህ ደርሳለች። የተረገዘው የለውጥ ፅንስ ተወልዶ እያደገ ነው። ኢትዮጵያም በሚወረወሩባት ፍላጻዎች ድልድዮችን እየገነባች፣ ተስፋዋን ለመፈጸም ከመጓዝ ያገዳት የለም” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ ቀን ሊነጋ ፅልመቱን ሰንጥቆ ጉዞ ጀምሯል፤ ጀንበሯ ደምቃ ልትወጣ ከጨለማው ጋር ትግል ላይ ናት። በዚህ ወሳኝ ወቅት ሁላችንም አቅማችን የፈቀደውን መስራት ከቻልን፣ ያለጥርጥር የኢትዮጵያ ነገ ብሩህ ይሆናል፤ የመከራ ዘመንዋ እስከ ወዲያኛው ይሸኛል። ኢትዮጵያም የማትደፈር፣ የምትታፈር ሀገር ሆና በአለት ላይ ትቆማለች” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መልካም የልደት በዓል በመመኘት ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እነሆ።

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ
የዘንድሮውን የልደት በዓል የምናከብረው የመከራችን ዘመን እያከተመ፤ የችግራችን ቋጠሮ እየተፈታ፣ የሰቆቃችን ምንጭ ላይመለስ እየደረቀ ባለበት ወቅት ነው፡፡ መከራችንን ከኋላችን ጥለን ተስፋችን አሻግረን እያየን የምናከብረው በዓል ነው፡፡
የክርስቶስ ልደት የአዲስ ተስፋ ጅማሬ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ ነው፡፡ የጭንቁ ጊዜ እያለፈ መሆኑ የመከራው ዘመን እየተገባደደ መምጣቱ፣ ጨለማው በብርሃን መሸነፉ፣ የኃጢአት እስር አብቅቶ ነፃነት መቅረቡ የተበሰረበት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት የነበረው ዘመን ዓመተ ፍዳ ነበር፡፡ ሰው የፈጣሪውን መመሪያ ተላልፎ የተከለከለውን በመፈፀሙ ምክንያት ርግማን ወርዶበት ከገነት ተባርሮ የኖራቸው እነዚያ ዘመናት በድቅድቅ ጨለማ የተሞሉ ነበሩ። ጊዜው ደርሶ ክርስቶስ በቤተልሔም ሲወለድ፣የኩነኔው ዘመን በሥርየት ተለውጦ የምህረት ዘመን ተብሏል፡፡
የሰው ልጅ ድኅነት በፅንሰት ተጀመረ፣ በልደት ተበሰረ፣ በስቅለት ተፈፀመ በትንሳኤ ተደመደመ፡፡ እያንዳንዱ ምእራፍ በፈተናና በደስታ ነበር የታለፈው፡፡ የክርስቶስ ልደት የምህረት ጊዜ መቅረቡን እንጂ ሁሉም ነገር መጠናቀቁን አላበሰረንም፡፡ ዕለተ ስቅለቱ ደርሶ አዳም ከዲያቢሎስ ባርነት፣ ከኃጢአት ቀንበር ነፃ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ፣ በመንገዱ ብዙ ውጣ ውረዶች አጋጥመዋል። የሄሮድስ ሞት አዋጅ፣ስደት፣ እንግልት፣ ረሃብ ጥማት፣ ነበረ፡፡
ጠላታችን ዲያቢሎስ በማይታክት ተንኮሉ አዳምን እስከ መጨረሻው ከፈጣሪው አቆራርጦ  ለማኖር ከፅንሰቱ እስከ ስቅለቱ ያልፈለቀለው ድንጋይ፣ ያልፈፀመው ሴራ አልነበረም፡፡ ጭፍራዎቹን አሰማርቶ ብዙዎች ከእውነት ጋር እንዳይቆሙ አድርጓል፡፡ ሐሰትን እየፈበረከ የክርስቶስን ስም እንዲያጠፉ አድርጓል፡፡ ብዙዎች ወደ ክርስቶስ እንዳይሄዱ ተከታዮቹን አስፈራርተዋል፡፡ ወደ ክርስቶስ የመጡትን ትታችሁ ውጡ ብለዋል፡፡ ሐዋርያትን ጭምር በገንዘብ አስክደዋል፡፡ የውጭ ጠላቶች ሮማውያን፣ ከውስጥ ባንዳዎች አይሁድ ጋር አንድ ሆነው ክርስቶስን አሳድደዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠላቶችም ሊወለድ ያለውን ተስፋችንን ሊያጨነግፉ ለዓመታት ታግለዋል። ሲፀነስ ሊያጨናግፉት ሞክረው ነበር። መወለዱን ሲያውቁ ያልፈፀሙት የግፍ ዓይነት የለም፡፡ ግጭቶቼን እየጠመቁ ሕዝብን ከህዝብ ሲያጋጩ ፣በየደረሱበት ንፁሐንን ሲያፈናቅሉ ከሕፃናት እስከ አዛውንት ያገኙትን ሲያሰቃዩና በጭካኔ ሲገድሉ ነበር፡፡ የሀገራችን የመዳንዋ ጊዜ የማይመጣ እስኪመለስ ድረስ መከራችን በዝቶ ታይቷል፡፡ እንደ ሄሮድስ ያሉ አበጋዞች ብሩህ ተስፋችንን ሲያጨልሙ ባለ በሌለ ጉልበታቸው ታግለዋል፡፡ አንድነታችንን ሊንዱ ተባብረዋል፤ ሀገራችንን ሊያፈርሱ አስከ ሲኦል ለመውረድ ምለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ አልፋ እዚህ ደርሳለች። የተረረገዘው የለውጥ ፅንስ ተወልዶ እያደገ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በሚወረወሩባት ፍላፃዎች ድልድዮች እየገነባች፣ተስፋዋን ለመፈፀም ከመጓዝ ያገዳት የለም፡፡
ውድ ወገኖቼ፡
ሰው በሕይወቱ እጅግ ወሳኝ ከሆኑ ቀናት መካከል ሁለቱ፤ የተወለደበትና ለምን እንደተወለደ ያወቀበት ቀናት ናቸው ይባላል። ሁላችንም ያለ አንድ ዓላማ አልተፈጠርንም። አንቱ የምንላቸው ቀደምቶች  ቀደምትነታች አንቱ ያስባላቸው ጉዳይ ለምን እንደተወለዱ ማወቃቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆነን መወለዳችን ያለ ምክንያት እንዳልሆነ አስበን ሀገራችንን ከጥገኝነት የሚያላቅቅ፣ ወገናችንን ከድህነት ዙሪት የሚገላግል፣ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ጎዳና የሚያስገባ፤ ኢትዮጵያ ራሷን በሁሉም ነገር ችላ እንድትቆም የሚያደርግ አንድ ቁም ነገር ሠርተን ማለፍ አለበን። ለዚህ ደግሞ ከአሁን የተሻለ ጊዜ የለም። አሁን የምንገኝበነት ወቅት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊሸጋገር የሚችል አንፀባራቂ ገድል የሚሠራበት፣በኩራት የሚነገር ታሪክ የሚፃፍበት ወሳኝ ወቅት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ቀን ሊነጋ ፅልመቱን ሰንጥቆ ጉዞ ጀምሯል፣ ጀንበሯ  ደምቃ ልትወጣ ከጨለማው ጋር ትግል ላይ ናት፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት ሁላችንም ዐቅማችን የፈቀደው መሥራት ከቻልን ያለ ጥርጥር የኢትዮጵያ ነገ ብሩህ ይሆናል፤ የመከራ ዘመንዋ እስከ ወዲያኛው ይሸኛል፡፡ ኢትዮጵያም የማትደፈር፣ የማትታፈር ሀገር ሆና በዐለት ላይ ትቆማለች፡፡
ኢትዮጵያን ለማገልገል ስንነሳ ልብ ማለት የሚገባን ነገር አለ። የሰነቅነው ዓላማ የቱንም ያህል የገዘፈና የተቀደሰ ቢሆን ትኅትና ካልታከለበት ትርጉም የለውም። ታላላቅ ግቦች ፍጻሜያቸው ብቻ ሳይሆን አፈጻጸማቸውም ታላቅና አስደናቂ ነው። የክርስቶስ ልደትም የሚያስተምረን ይሄው ነው። ዓለምን ለማዳን እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ለታላቅ ዓላማ ሲልከው፣ ከታላላቅ ሰዎች ይልቅ እረኞች፣ ከታዋቂዎች ይልቅ ከብቶችን፣ በጌጣጌጥ ከተንቆጠቆጡ እልፍኞችና ቤተመንግስቶች ይልቅ በረትን መረጠ። ዓለምን ማዳንን ያህል ታላቅ ሥራ በትህትና ነው የተፈጸመው። ታላላቅ ግቦች በትህትና ተጀምረው፣ በትህትና የሚጠናቀቁ መሆናቸውን መድኃኔዓለም ክርስቶስ አስተምሮናል።
ዛሬ በኃይልና በትዕቢት ተወጥረው የምንጀምራቸውና “በእኔ አውቅልሃለሁ” ስሜት ተኮፍሰን የምንሰራቸው ስራዎች ዘላቂ እድሜ ሊኖራቸው አይችልም። ከድሃው ሕዝብ ርቀን፣ በጌጣጌጥ በተንቆጠቆጡ ቢሮዎች ውስጥ ተቆልፈን፣ በዘመናዊ መኮኖች ተንፈላስሰን የምንወጥናቸው ዕቅዶች ቢተገበሩም ቆይተው ይፈርሳሉ። በተቃራኒው ወደ ታች ወርደን ከሕዝቡ ጋር የነደፍናቸው ግቦች፣ ጀምረን ባንጨርሳቸው እንኳን፣ ትውልድ ተረክቦ ከዳር ያደርሳቸዋል።
ሌላው የልደት በዓል በህዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የእርቅ ምልክት ተደርጎም ይታሰባል። በፈጣሪና በአዳም መካከል የጸብ ግድግዳ የፈረሰው መጀመሪያ በቃሉ ነበር፤ “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚል ቃል። የክርስቶስ መወለድ ቃሉ ወደ ተግባር መለወጡን፣ የእርቁን አይቀሬነት አሳይቷል። በዲያቢሎስ ገፋፊነት ሕግ የጣሰው በደል የፈጸመው አዳም ሆኖ ሳለ ለእርቅ ልጁን አሳልፎ የሰጠው ግን ፈጣሪ ነው። አዳምን ለማዳን፣ ከሐጥያት ቀንበር ለማላቀቅ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በሥጋ በመወለዱ ክብሩ ጨመረ እንጂ አልቀነሰም።
በየዘመናቱ በሚነሱ የዲያቢሎስ ጭፍሮች አሳሳችነት በሀገራችን ግጭቶች ተፈጥረው ያውቃሉ። ግጭቱን ተከትሎ የሚወረወረው የበደል ሥለት አብረው የሚኖሩ እሴቶቻችን ሊበጥስ ታግሏል። ነገር ግን ጨርሶ አልቆረጣቸውም። ማህበራዊ እሴቶቻችን በይቅርታ እየታሹ፣ በእርቀ ሰላም ተጠግነው ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ። እስከ አሁንም ሀገር አድርጎ ያቆየን ይሄ ሂደት ነው።
ጁንታው መከላከያ ሠራዊታችን ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የተፈጠረውን ግጭት ጨምሮ በሌሎች ምክንያቶች በሀገራችን የተፈጸሙ መበዳደሎችን ለመሻር በዚህ ሰዓት ሀገራዊ እርቀ ሰላሙ ያስፈልገናል። አንድነታችንን ለማስጠበቅ ስለሚያስችለን፣ በእርቀ ሰለም ኢትዮጵያ አትራፊ እንደምትሆን እሙን ነው። በሰውና በፈጣሪ እርቅ ምክንያት የከሠረው አሳሳቹ ዲያቢሎስ እንደሆነው ሁሉ፣ በሀገራችን እርቀ ሰላሙ ምክንያት የሽብር ቡድኖቹ የሕወሃትና የሸኔ እኩይ ዓላማ፣ እንዲሁም የታሪካዊ ጠላቶቻችን ሕልም ይከሽፋል።
በድጋሚ መልካም የልደት በዓል ይሁንልን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ታኅሣሥ 28 ቀን 2014 ዓ.ም

Read 7816 times