Tuesday, 11 January 2022 07:13

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

በአባቴ ደጃፍ ፊት - በዓይኑ ስር ተኝቼ
ምን እንደሆነ እንጃ ...............
እንዲያው ብትት ብዬ - ከእንቅልፌ ነቅቼ
ዓይኔን ገለጥ ሳደርግ - ገዝፈሽ ከተራራ
ሳገኝሽ በግርማ ..................
ከቶ ይህን ተአምር ...........
ማን ያምነኛል ብዬ - አፍ አውጥቼ ላውራ?!

በፍጥረቴ ሀ ሁ - በዚያ ቅዱስ ጫካ
በብርሃን ገላዬ - ደምቄ ስፈካ
ከአውሬ ከአራዊት ጋር - እያልኩ ሰበር-ሰካ
ፍጥረት በሚያሸብር - ግዙፍ ሳቅ ሳውካካ
ሳስመስል ነው እንጂ - ነፍሴ ሳትረካ
ግንጥል ጌጥ የሆንኩኝ - ጉደሎ ነኝ ለካ ?!

ሃቅና እውነታው
በጠራራ ፀሀይ - ፍም መስሎ ሀገሩ
ጨለማ ነው ውስጤ - ያላንቺ መኖሩ !
ሳቅ ፈስሶ በሜዳ - ፍጥረቱ ሲያውካካ
ያላንቺ ጠውልጌ ~ እንዴት ብዬ ልፍካ ?!

እይልኝ ጉልበቴን - ታዘቢው ሀሞቴን
የነፍሴን ኩነኔ - አጽድቂው መሞቴን
በችሎት መዝገቡ - እውነቴን መዝኚ
ሙግት የወጣሁ ቀን - ጠበቃዬ ሁኚ !

ጎጆ እንዳጣች ርግብ - ዛፍ ማረፍያ ሳጣ
ደግሞ ገላዬ በገላሽ
አጥንቴሸ በአጥንቴ
ጭቃ አፈር ለብሶ - እያበራ መጣ !
ጎኔ ተነድሎልሽ - ያለምንም ስቃይ
ቀለምሽ ተጋብቶኝ - ፈስሶ በላዬ ላይ
... ስለት የማይቆርጠን
... ጊዜ ማይለውጠን
... ሁለት አንድ አካሎች
... ሁለት አንድ ነፍሶች
በትንፋሽ ጉሮሮ - በልብ ውስጥ ምታችን
አንድ ነን ካንቺ ጋር - ውዴ ለፍቅራችን !

መቋሚያ ደስቄ - ከበሮ ባልመታ
በምን ላወድስሽ - በየቱ እልልታ
በጽፋት አድምቄሽ - ባላወርድ ሆይሆይታ
ስምሽን አዜማለሁ- ሆኜ መሪጌታ!
ደግሞ መሪጌታ - የተቀኘ ለታ
ምድር እጅ ሰጥታ .................
ቆማ ታደምጣለች - መሸከርከሯን ትታ!

የነፍሴ ላይ ንጋት - የማለዳ ወፌ
የአርምሞ ጸሎቴ - የንባብ ምእራፌ
የዘመን መስፈርያ - የጥበብ ዋሻዬ
ክፉ ቀን ማለፍያ - ንጽህ መኝታዬ
የጽናት ምርኩዜ - ማረፍያ መልህቄ
እንኳን ከአንቺ ጋር - ሆነ አወዳደቄ!

በዚህ መሀል ታዲያ
ዝናብና ነፋስ - ብናኝና አፈሩ
ውርጭና ውሽንፍር - በላዬ ሲያጓሩ
እንደ ቀትር ጥላ - በዚህ ምድረ በዳ
ያለፈራጅ ዳኛ ........................
ሲከሰኝ ለብቻ - የሰው መሆን እዳ
ከራስ ጋር ጦርነት ......................
ገጥሜ ስላፋ - በእሾኃማ ሜዳ
.... ባንቺ ጸጋ ደምቆ
.... ባንቺ ውበት ልቆ
.... ባንቺ ፍቅር ረቅቆ
.... ባንቺ መዳፍ ጸድቆ
.... ባንቺ ቃላት ታጥቆ
.... ባንቺ መንፈስ ረቅቆ
ይገርመኛል ሔዋን .....
በአንድ አጥንት ስትደፍኚው - ይህን ሁሉ ቀዳዳ!
(ነፃነት አምሳሉ አፈወርቅ)


Read 1755 times