Thursday, 13 January 2022 06:27

ለሺዎች - የጥሪ ድምጽ ምላሽ መስጠት

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ የኢትዮጵያ ወጣት ክርስቲያናዊ ማህበር፣ የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር ወዘተ የሚባሉ ለበጎ ስራ የተቋቋሙ ማህበራት ነበሩ። እንደ ጉራጌ የመንገድ ስራ ማህበር ያሉም ለልማት የተቋቋሙ ማህበራት ነበሩ። ከእነዚህ ወይም ከውጭ ከተገኘ ልምድ በመነሳት ሊሆን ይችላል፣ የወታደር ሚስቶች “የኢትዮጵያ የወታደር ሚስቶች የበጎ አድራጎት ማህበራት” የሚባል ማህበር አቋቁመው ነበር። የማህበሩ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ደስታ ገብሩ ነበሩ። ወይዘሮ ደስታ፤ የወይዘሮ ስንዱ ገብሩ እህት የጀኔራል ከበደ ገብሬ ባለቤት ናቸው።
ማህበሩ እስከ  ንጉሠ ነገሥቱ መንግስት መውደቅ ድረስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ያለው በአንድ ወቅት የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ይዞት የነበረው ህንፃ፣ ማህበሩ ያሰራው ህንጻ ነው። በኤርትራ ይደረግ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት በተፈጠረው ችግር ምክንያት ሊሆን ይችላል ማህበሩ “እጓላማውታ” የተባለ የህጻናት ማሳደጊያ አቋቁሞ ያስተዳድርም ነበር። ደርግ ማህበሩ እንዲፈርስ ሲያደርግ  የህጻናት ማሳደጊያውን ግን እንዲቆይ አድርጎት ነበር።
የመቃዲሾው የጀኔራል ዚያድ ባሬ መንግስት በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፈተ። ድንበር ጥሶ 700 ኪ.ሜ ያህል ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት ሰፊ መሬት ተቆጣጠረ። መንግስትም የክተት አዋጅ አወጀ። ከመላው ኢትዮጵያ የተመለመሉ ሶስት መቶ ሺህ ሰዎች ለስልጠና ታጠቅ  ጦር ሰፈር ገቡ። ስልጣናቸውን እንደጨረሱ በሶማሌ ጦር ላይ ፈሰሱበት። በየካቲት 1970 ዓ.ም በካራማራ ላይ ድል ተገኘ። የዚያድ ባሬ ጦርም ተንደርድሮ እንደገባ እየበረረ ወጣ።
“የምስራቁ ድል በሰሜን ይደገማል” በሚል መርህ፣ በሰሜን የተከፈተውን አገር የመገንጠል እንቅስቃሴ ለመመከት መንግሥት ፊቱን ወደ ሰሜን አዞረ። “የቀይ ኮከብ ዘመቻ” ተጀመረ። ኤርትራን ለመቆጣጠር ተቃርቦ የነበረው ሻዕቢያ ወደ ኋላ እንዲመለስ ማድረግ ቢቻልም ጦርነቱን እንደታሰበው በድል ለማጠናቀቅ ሳይቻል ቀረ። ለዚያ ዘመቻ አለመሳካት የዛሬው አሸባሪ ትህነግ  የነበረው ሚና ሳይጠቀስ አይታለፍም።
ጦርነት  ብዙ ህይወት መቀማቱ ብዙ ሀብት ማውደሙ የታወቀ ነው። በጦር ሜዳ ተሰልፈው  ደማቸውን ለሀገራቸው አንድነት መከበር ላፈሰሱ ወገኖች ወረታው የሚከፈለው ልጆቻቸውን በመንከባከብ፣ በማሳደግ በመሆኑ፣ አለሁ የሚል መንግስት ያስፈልጋቸው ነበር። ይህን ኃላፊነት የተረዳው ደርግ፣ በ1973 ዓ.ም ከአዲስ አበባ 218 ኪ.ሜ ርቀት አላባ ቁሊቶ ወረዳ አላጌ በተባለ አካባቢ 105 ጋሻ ወይም 4200 ሄክታር መሬት ላይ በአንድ ጊዜ አምስት ሺህ አምስት መቶ ህጻናትን ተቀብሎ የሚንከባከብ “ህጻናት  አምባ” የተባለ የህጻናት ማሳደጊያ አቋቋመ።
ህጻናት አምባው፤ ሰብለ  አብዮት መስከረም ሁለት፣ ኦጋዴን፣ ዘርዓይ ደረሰና መንግሥቱ ሃይለ ማርያም የሚባሉ እራሳቸውን  የቻሉ መንደሮች ሲኖሩት ሁለት መዋዕለ ሕፃናት ሁለት የአንደኛ ደረጃና አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነበረው። ህጻናቱ በሙያና በአገር  ፍቅር ስሜት ተኮትኩተው እንዲያድጉም ለማድረግ ብዙ ተሰርቷል። አምባው ያፈራቸው ብዙ ወጣቶች በልዩ ልዩ ሙያ ተሰማርተው አገር እያገለገሉ መሆኑም የታወቀ ነው። የጦር ጉዳተኞችን ለመንከባከብ ደብረ ዘይት አካባቢ “የጀግኖች አምባ” የተባለም ተቋቁሞ እንደነበር  ይታወቃል።
ዛሬም አገር ጦርነት ላይ ናት። በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የመከላከያ፣ የክልል ልዩ ሃይል ሚሊሽያ እንዲሁም ፋኖ በግንባር ተሰልፈው አሁንም የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር እየተዋደቁ ነው። ብዙዎች እራሳቸውን ለአገራቸው አሳልፈው የሰጡት በቅርብ ጠባቂና ተንከባካቢ የሌላቸውን ልጆቻቸውን፣ በእነሱ ጥበቃ ስር የነበሩ እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድሞቻቸውን ወደ ኋላ ትተው ነው።
በተለይ ልጆቻቸው ጠባቂ ተንከባካቢ፣ መክሮና አስተምሮ የሚያሳድጋቸው ወገን ያስፈልጋቸዋል። እንደ ህጻን ቢኒያም ጌታቸው አይነት ድምጾች ከአሁኑ መሰማት ጀምረዋል። ብዙ ሺህ ድምጾች ለእኛስ ምን አዘጋጃችሁልን ብለው መጠየቃቸው አይቀርም። ሰሚ  ማግኘት ያለባቸው  ድምጾች መሆናቸውን ደግሞ መዘንጋት የለብንም።
ደርግ ህጻናት አምባን ሰርቶ ያጠናቀቀው በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ መንግስት ከአሁኑ መዘጋጀት አለበት። እስኪያለቅሱና እስኪላቀሱ ድረስ መጠበቅ የለበትም። መንግስት “ኑ አገራችሁን አድኑ” የሚል ጥሪ ለአባቶቻቸው እንዳቀረበው ሁሉ፣ ፈጥኖ ለልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው አለሁ ሊላቸው ያስፈልጋል። ይህንንም ሌላኛው የጦር ግንባር አውድ አድርጎ ማየት ይኖርበታል።
በነገራችን ላይ እንደሰማሁት ህጻናት አምባ በአሁኑ ጊዜ የኦሮሚያ ግብርና ኮሌጅ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው። ትህነግ ህጻናት አምባውን ያፈረሰው በ1990 ዓ.ም ሲሆን ያለምንም ማስጠንቀቂያና ዝግጅት ህጻናቱን አውጥቶ ዝዋይ ከተማ ላይ ያወጣ ያውጣችሁ ብሎ እንደበተናቸው ይታወቃል።


Read 12356 times