Thursday, 13 January 2022 06:25

“የማሽን ልጆች” ተወለዱ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

“የሜትሪክስ” አዲሱ ፊልም፣ ከተለመደው የፍልሚያ ጥበብና የተኩስ እሩምታ ያልተናነሰ፣ የወሬ እሩምታም የያዘ ነው፡፡
የፊልሙ ዋና ባለታሪክ፣ “በምርጥ የጌም ፈጠራ”፣ እጅግ ዝነኛ የኪነጥበብ ተሸላሚ ነው። ለአዲስ ዙር ፈጠራም፣ አዲስ ዝግጅት ተጀምሯል። በእርግጥ፣ ጎልማሳው ጥበበኛ፣ በሌሎች ሃሳቦች ተጠምዷል። በዚያ ላይ፣ በተፈጥሮው ቁጥብ ነው። ብዙ አይናገርም።
የስራ ባልደረቦቹ ግን ወጣቶች ናቸው - በአብዛኛውም ቅብጥብጥ። እናም፣ “ዓለምን ጉድ የሚያሰኝ ጌም” ለመስራት፣ ስለ ኪነ-ጥበብ ስለ መዝናኛ ያወራሉ - እየተሸቀዳደሙ።
…ዋናው የተወዳጅነት ሚስጥር፣ ሽጉጥ፣ ፍንዳታ፣ ተኩስ ነው… ትላለች አንዷ፡፡ “ዘመኑ፣ የሃሳብ ነው” ይላል ሁለተኛው። የፍልሚያ ጥበብና ቄንጠኛ እንቅስቃሴ በጣም ተወዳጅ የመዝናኛ ቅመሞች እንደሆኑ ይናገራል - ሌላኛው ወጣት።
ጎልማሳው በዝምታ ይብሰለሰላል። ወጣቱ እየተቁነጠነጠ ያወራል። ረዥም ገለፃና ማብራሪያ አይናገርም፤ በአጭር ባጭሩ ነው፡፡ የተቀነጫጨበ ቢሆንም ግን፣ ወሬው ብዙ ነው። ፋታ የማይሰጥ ወሬ…. መንጣጣት በሉት፡፡
በዚያ ላይ፣ በሌላ ሰው ጉዳይ ውስጥ ዘው ብሎ ይገባል፤ ሳይጠይቁት ያወራል። ሳይጋብዙት፤ በሌላ ሰው የግል ጉዳይ ላይ፣ ስለ ፍቅር ግንኙነት ሳይቀር፣ አስተያየት ይሰጣል፣ የምክር ሃሳብ ይደረድራል።
ከዚያም አልፎ፣ “ጉዳዩን ለኔ ተወው” ብሎ፣ ባልተላከበት ቦታ፣ የፍቅር መልዕክት አቀባይ ለመሆን ይወስናል። ተወካይ ለመሆን ራሱን ይሾማል - ለወሬ የሚቸኩል የሚንከወከው ወጣት።
ነገረ ስራው፣ በስነ ምግባር ያልተቀረፀ፣ በጨዋነት ያልተገራ፣ ከይሉኝታ ልጓም ያመለጠ እንደሆነ፣…. እሱ ራሱ ያውቃል፡፡ ግን፣ “አደብ ልግዛ” አይልም፡፡ በቃ፤ የልማድ ነገር፣ አያስችለውም፡፡ በዚያው ልማዱ፣ ያወራል፣ ይንጣጣል። አመል ሆነበት ይቅለበለባል፡፡
አመሉን ስለሚያውቅ፤ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ግን፤ ወሬውን ይቀጥላል፡፡
ይቅርታ፣…ምን ላድርግ? ማሽኖች ናቸው ያሳደጉኝ ብሎ ያመካኛል፡፡
ወላጆቹ ማሽኖች ናቸው? እደዚያ ባይልም፤ አሳዳጊዎቹ ማሽኖች እንደሆኑ ይናገራል፡፡
“I was raised by machines” ይላል፡፡
በአጭሩ ምንድነው? ንግግሩና አኳሃኑ፤ ቅጥ ያጣ፣ መረን የወጣ ቢሆን፣ አትፍረዱበት፡፡ “ማሽን ያሳደገው” ወጣት፣ እንዴት ብሎ፣ በስነ ምግባር ይታነጻል? ከየት ብሎስ፣ ጨዋነትን ይለምዳል? ትክክለኛ አነጋገር አስተምራችሁታል?
“እንዲህና አንዲያ አይባልም፡፡ እንዲህና እንዲያ አይደረግም” ብሎ እለት በእለት ከሚገስፅ አዋቂና ከሚያስተካክል ተቆርቋሪ ጋር አይደለም - አስተዳደጉ፡፡ ከአፍቃሪና ከአስተማሪ ወላጅ ጋር ሳይሆን፣ ከማሽኖች ጋር ነው በውሎና አዳሩ።
ገና በጨቅላነቱ፤ ገና አንድ ዓመት ሳይሞላው፤ “በማሽን ስክሪን” ላይ አይኖቹን ተክሎ ነው - ጡት የጠባው። “የማሽኖች ድምጽ” ላይ ጆሮዎቹን ደግኖ ነው፤ የመሳቅና የማልቀስ አይነቶችን የተለማመደው፣ መነጫነጭና እጆቹን ማወራጨት፣ መንፏቀቅና በዳዴ መራመድ የቻለው።
ዛሬ እንደድሮ አይደለም፡፡ በእርግጥ፤ የዛሬ 30 እና 20 ዓመትም ማሽኖች ነበሩ። ነገር ግን፣ የያኔ ቲቪ እና ቪዲዮ፣ የሕይወትን ሰዓት ሁሉ ጠቅልለው መውሰድ አይችሉም ነበር፡፡ በቲቪ ላይ ኮምፒውተር ሲታከልበት፤ በቪዲዮ ጌም ላይ የሞባይል ጌም ሲጨመርበትስ? ዩቱብ እና ፌስቡክ፣ ከዚያም የነዚሁ አምሳያዎችና መንትያዎች የተበራከቱበት ኢንተርኔት ዓለም ሲስፋፋስ?
ዛሬ፣ የማሽኖች ዓለም፣ ወደ ሁሉም ስፍራ፣ ከጓዳ እስከ ምድር ዋልታ ተንሰራፍቶ የከተመ፣ በሁሉም ሰዓት፣ ጥዋትና ማታ የማያንቀላፋ፣ ሁለገብና ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዓለም እየሆነ ነው - በሁሉም ቦታ ሁሌም የሚኖር፡፡ በማሽኖች ዓለም ውስጥ፣ ፀሐይ አትጠልቅም፡፡ ወሎና አዳሩ እዚህ ነው - የማሽን ልጅ።
በእዚህ ዓለም ውስጥ አስተዳደጉ፣ ምን አይነት ወሬ ሰምቶ፣ ምን አይነት አነጋገር ይለምዳል? ምን አይነት ድርጊትና አኗኗር አይቶ፣ ምን አይነት አመል ይይዛል?
በዚህ አይን ካየነው፣ በእርግጥም፣ የማሽን ልጆች ተወልደዋል ማለት እንችላለን፡፡
ሜትሪክስ ውስጥ፣ “ምን ላድርግ? የማሽን ልጅ ነኝ” የሚል ሃሳብ የያዘ አባባል ቢገባ አይገርምም - ከፊልሙ ርዕሰ ጉዳይም ይሄዳል፡፡
በእርግጥ፣ አዲስ አይነት አባባል አይደለም፡፡ “የማሽን ልጅ” ከማለታችን በፊት፣ ካሁን ቀደም፣ ከሌሎች ብዙ አባባሎች ጋር ኖረናል፡፡
አስተዳደግ፣ የግል ማንነትን ያግዛል፤ ወይም ይፈታተናል። እጣ ፈንታ ግን አይደለም።
“የቤት ልጅ”፣ “የጎዳና ልጅ”፣ “የባላባት ልጅ”፣ “የሰፈር ልጅ”፣ “የዱር ልጅ”፣ “የወንዝ - የአገር ልጅ”፣ “የቄስ፣ የሼህ ልጅ”፣ “የንጉሥ፣ የባርያ ልጅ”፣ “የማደጎ ልጅ”፣… “የስለት ልጅ”፣ “የእርግማን ልጅ”፣ “የበኩር ልጅ”፣… “የፈረንጅ ልጅ”፣ “የዘመድ የአርበኛ ልጅ”፣ “የባዳ የባንዳ ልጅ”፣ “የስደተኛ ልጅ”፣…. ብዙ የልጅ አይነት ሰምተናል።
አንዳንዱ ጥሬ ገለጻ ነው። አንዳንዱ የአዋቂ ወይም ያላዋቂ ፈርጅ ነው።
አንዳንዱ፣ ፍርጃ ወይም ሙገሳ፣ ንቀት ወይም አድናቆት፣ በላይነት ወይም የበታችነት፣ ውንጀላ ወይም ውዳሴ፣ ሽርደዳ ወይም ሽንገላ ነው። አንዳንዱ አባባል፣ በየዋነት ወይም በክፋት፣… በብልጠት ወይም በስህተት፣… በፈጣጣ ወይም በጭፍን የሚመጣና የሚዛመት ነው።
የጨርቆስና የቦሌ ልጅ፣ ወይም ከተሜና ገጠሬ፣… የሚሉ አባባሎችን በማየት ብቻ፣ ነገሩን በለዘብታ መረዳት ይቻላል።
በአንድ በኩል፣ የከተማና የገጠር ልጅ ስንል፤ የትውልድ ወይም የእድገት ቦታ፣ የመኖሪያ አድራሻ ወይንም የኑሮ ሁኔታ፣ የቅርብ ዓመታት ትረካ ወይም ወቅታዊ መረጃ ሊሆን ይችላል - ፍሬ ነገሩ። ጥሬ ገለጻ ነው።
ቢሆንም ግን፤ ጥሬ ገለፃ፣ በቀላሉ፣ ከዳኝነት ጋር ይምታታል፤ ይዳበላል። “አሪፍና ቀሽም፣ ማለፊያና ማፈሪያ፣ ጨዋና ባለጌ”፣ የሚል ጭፍን የዳኝነት መልዕክትን ለማራገብ ያገለግላል። አልያም፣ የአላዋቂ የስንፍና ስህተትን ለማናፈስ ይውላል (የትውልድ ቦታን፣ ከሰው መልካምትና መጥነት ጋር የማምታታት ስህተት)።
ምሳሌያዊ ትርጉም የያዙ ሌሎች ጥንታዊ ትረካዎችም አሉ።
ትንቢትን ወይም ጥቃትን የፈሩ ወላጆች፣ ጨቅላ ህጻን ልጃቸውን፣ በዘንቢል ሸፍነው፣ ዛፍ ላይ አንጠልጥለው ይሸሻሉ። ወይም ወንዝና ሀይቅ ላይ አንሳፍፈው ይሰወራሉ። ከዚያስ?
ያጋጣሚ ነገር ሆኖ፣ ጨቅላው በሕይወት ይተርፋል። እንደ እድል ሆኖ፣ ወደ ቤተመንግስት የመግባት፣ በአገሬው ንግስት ወይም በመልክ መልካሟ ልዕልት እቅፍ ውስጥ፣ በፍቅርና በእንክብካቤ የማደግ እድል ያገኛል።
አልያም፣ ተራ የገበሬ ቤተሰብ፣ ህጻኑን አግኝቶ፣ ያድነዋል። ባልና ሚስት፣ በግብርና አኗኗር፣ የአቅማቸውን ያህል በቅንነትና በፍቅር፣ ህፃኑን ያሳድጋሉ።
ወይም ደግሞ፣ የዱር አውሬ፣ ድኩላም ሆነ ነብር፣ ለጨቅላው ሕጻን በመራራት፣ እንደራሳቸው ልጅ፣ የነብር የድኩላ ጡታቸውን አጥብተው ያሳድጉታል።
ነብር ያሳደገው፣ ከአንበሳ ጋር እየተላፋና እየተፋለመ ያደገ ልጅ፣… በቤተ መንግስት እንዳደገ ልጅ ሊሆን አይችልም። ሕግና ስርዓትን አይተነትንም። የአነጋገር ለዛና የአረማመድ ሞገስ፣ የአለባበስና የትጥቅ ውበት፣ የአስተዳደርና የጦርነት ጥበብ፣ የታሪክና የኪነጥበብ ዕውቀት፣ ድሎትና ፌሽታ አያውቅም። ግን ማወቅ አይችልም ማለት አይደለም። ፈታኝ ይሆንበታል። ከጣረ ግን፣ ይችላል። የጥንቱ ባቢሎን፣ የኢንዲኩ ትረካም ይህን እውነት ይነግረናል። አጋዥ ሲኖረው ደግሞ፣ ስኬቱ ይሳለጣል። ኢንዲኩ፣ ጊልጋሜሽን የመሰለ ጀግና ጓደኛ፣ እንዲሁም ፍቅርን የምታውቅ “ሻሪምቱ” ሴት ማግኘቱ እድለኛ ነው። በልጅነት ያልተማረውን በጉርምስና ጊዜው እንዲያውቅ ረድተውታል።
የቤተመንግስት ልጅና የገበሬ ቤት ልጅስ?
በገበሬ ቤተሰብ ያደረገ ልጅ፣ የቤተመንግስት መውጫና መግቢያ አያውቅም። የጥበብ ማዕከላትንም ሳያይ ያድጋል። እውነት ነው። ነገር ግን፣ በጥረት፣ ሕግና ስርዓትን መተንተን፣ የረቀቀ ጥበብንና እውቀትን መማር ይችላል። እንዲያም ባይሆን፣ ተበድሏል ማለት አይደለም። ምድር የነካ የኑሮ ጥበብ፣ በገበሬ ቤተሰብ ውስጥ መማር ይችላል።
የገበሬ ቤተሰብ ኑሮና የእርሻ ስራን፣ ወተት ማለብና ምግብ ማብሰልን፤ ፈትልና ጥልፍን ብቻ አይደለም የሚማረው። የወላጅ ምክርና ፍቅር… ተግሳጽና ምርቃትንም በቅርበት ዘወትር ያገኛል። ብዙ ነው፣ የአስተዳደግ ጣጣውና ጣዕሙ።
“እንዲህ አይነት ተግባር እንዳይደገም፤ እንዲያ አይነት አነጋገር ሁለተኛ እንዳይወጣህ” የሚል ተግሳጽ፤ “ጎሽ የኔ ልጅ፤ አይዞህ በርታ”፤ “እስቲ ደግሞ፣ በዚህ በኩል ሞክረው”፤ “በዚህ በኩልም አስተውለው”፤ “ነገ ከነገ ወዲያ ስትለማመደው፤ ይታየኛል እንዴት እንደምትችለው” የሚል ማበረታቻ በየእለቱ ማግኘት መታደል ነው - ለልጅ እድገት።
…የወላጅ እክብካቤና ፍቅር፤ ትምህርትና ክትትል፣ የስነምግባር ምክርና ተግሳጽ፤ በሃሳብና በተግባር፣ ከጥዋት እስከ ማታ፣ በተገኘው ሰዓትና አጋጣሚ ሁሉ፤ እለት ተእለት አይቋረጥም። የእለት ተእለት ውጤቱ፤ በትንሽ በትንሽ ነው። የአእምሮና የስብእና እድገቱ፤ እንደ አካላዊ ለውጡ፤ በጥቂት በጥቂቱ ነው። ከዓመታት በኋላ ሲታይ ግን ድንቅ ይሆናል ውጤቱ። ለማመን የሚከብድ።
ቤተሰብን የሚያከበርና ታታሪ ባለሙያ፣ ጥንቁቅና ቁጥብ፣ አላስፈላጊ ጉዳይ ላይ ዘልሎ የማይገባ፣ የሰው ችግር ተረድቶ የሚራራ፤ ለማገዝ የማይሳሳ፣ ግን ደግሞ ኮስታራ፣… በአጠቃላይ በንግግሩና በተግባሩ፣ በስነምግባር የተቀረፀ፣… ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ፣ መረን ያልለቀቀ ጨዋነትን የጠበቀ ቁጥብ፣… የመሆን እድል አለው - “የቤት ልጅ። የወላጅ ጥበብና የልጅ ጥረት ተደማምሮ፣ ውጤቱ ይሰምራል።
የማሽን ልጅስ?

Read 1763 times