Saturday, 15 January 2022 17:01

በቢሾፍቱ ከተማ የተገነባው ዘመናዊ ሞዴል ት/ቤት ነገ ይመረቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ፍሬገነት ኪዳን ለህፃናት”፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በቢሾፍቱ ከተማ በተሰጠው ቦታ ላይ ያስገነባውን ዘመናዊ ሞዴል ት/ቤት፣ ነገ ከጠዋቱ 3፡00-7፡00፣የትምህርት አመራሮች፣ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎችና የማህበረሰብ መሪዎች በተገኙበት እንደሚያስመርቅ ተገለፀ፡፡
ፍሬገነት ደንቢ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተብሎ የተሰየመው ይህ ዘመናዊ አፀደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት፤ ባለ አንድ ፎቅ ህንፃ ሲሆን በውስጡ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መፃህፍት፣ክሊኒክ፣ የኮምፒውተር ክፍል፣የህፃናት ማሸለቢያ ክፍል፣የመምህራን ማሰልጠኛ እንዲሁም የሥዕልና የሙዚቃ መለማመጃ ሁለገብ አዳራሽ በተጨማሪም የወጥ ቤትና የመመገቢያ አዳራሽ ይዟል ተብሏል፡፡
 “ፍሬገነት ኪዳን ለህጻናት” ለትምህርት ቤቱ ግንባታ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንና ግንባታውን ፍሊንትስቶን ኢንጂነሪንግ የስራ ተቋራጭ በጥራት ማከናወኑ ተጠቁሟል፡፡
“ፍሬገነት ኪዳን ለህጻናት” በ1997 ዓ.ም የተቋቋመ አገር በቀል የግብረ ሠናይ ድርጅት ሲሆን ዓላማውም ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚመጡ ህጻናት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ ነፃ ትምህርት እንዲያገኙ ማስቻል ነው ተብሏል፡፡ ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከተማ ለ17 ዓመታት በርካታ ህጻናትን ነፃ የምግብ፣የጤናና፣የአልባሳት ድጋፍ እያደረገ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በነፃ በመስጠት ህብረተሰቡን እያገለገለ መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 8550 times