Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 September 2012 12:21

“አድማጩ ‘ጥንቡሳሳም ለምን አለ?’

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ብሎ እንዲጠይቅ ፈልጌያለሁ”  ድምፃዊ ፀጋዬ ስሜ

በአሁኑ አልበሜ ላይ አንድ ሁለት ቦታ ላይ በጉሮሮ የምጠቀምባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ በኳየር የሚሰሩ ስራዎች ወደ መድረክ ለማምጣት ሲያስቸግር ይታያል፡፡ ለካሴቱ ስራ ኳየር ተጠቅመን ከሆነ በየሄድንበት መድረክ ሁሉ ኳየሩን ይዞ መሄድ የግድ ይሆናል፡፡ ያለበለዚያ ሰው በካሴት የሰማውን የሚመጥን ስራ ማቅረብ አንችልም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ባህሉን በጠበቀ መልኩ በከበሮ፣ በእጅ ጭብጨባና በድምፅ /በጉሮሮ ማጀብ ጭምር/ በመጫወት የሚታወቁና በጉራጌ ሰርግ ቤቶች የሚጫወቱ ጎበዝ ልጆች እየታዩ ነው፡፡

የአልበምህ ርዕስ “ጥንቡሳሳም” ለምን ተባለ? ምንድነው ትርጉሙ?

ርዕሱ ማንን፣ ምንን የሚል ጥያቄ ያስነሳል የክስታኔ ጉራጌ ቋንቋ ቃል ነው፡፡ “ጥንቡሳስ” ወደ አማርኛ ሲተረጐም “ጦስ” የሚለው ቃል አቻው ነው፡፡ “ጥንቡሳሳም” ደግሞ ጦሰኛ ማለት ይሆናል፡፡ የዘፈኑ ግጥም ውስጥ እንደሚደመጠው “ምካት ጥንቡሳሳም” የሚለው የሚያመለክተው መከራ፣ ድህነት፣ ችግር ጦሰኛ ስለሆኑ እንዲጠፉ እንጣር ለማለት ነው፡፡ ቃሉ አሉታዊ ይመስላል እንጂ አንድ ነገር ሆነን ወይም አንድ ችግር ገጥሞን ራሳችንን ጦሴን ይወሰድ ስንል፤ ሌሎችም “ጦስህን ይውሰድ” ሲሉን ተስፋ፣ ማበረታቻና ማጽናኛ ይሰጠናል፡፡

ግጥሙን ለመፃፍ መነሻህ ምን ነበር?

የአባይ ግድብ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ኢትዮጵያዊያን ግድቡን ለመገንባት ብንሞክር ግብፆች ጦርነት እንደሚከፍቱብን ሲወራ ብዙ ጊዜ እሰማ ነበር፡፡

በተደጋጋሚ የምሰማው ስጋት፤ በጨለማ ውስጥ ምን እንዳለ እንደማይታየው ሁሉ ግልጽ አልነበረም፡፡ ግድቡን መገንባት ከቻልን ደግሞ ብርሃን እናገኛለን፡፡ የልማት ሥራዎቻችን ይስፋፋሉ፡፡

ብርሃኑን ካገኘን በጨለማው ውስጥ ያለው ነገር ለምን ያስፈራናል የሚለውን መረዳቴ ነው “ጥንቡሳሳም” ግጥምን እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝ፡፡ በላያችን ላይ ለብዙ ዓመታት የኖረው፣ የምንሰደብበትና የምናፍርበት ድህነታችን ከላያችን ተነስ፤ ልቀቀን ነው የሚለው ዘፈኑ፡፡ ወደ ልማት ሥራ ተባብረን እንጓዝ ነው መልዕክቱ፡፡

በቅርቡ የወጡ የሙዚቃ ሲዲዎች ሰፋ ያለ የማስታወቂያ ሥራ ሊሰራላቸው ተሞክሯል፡፡ አንተ ደግሞ ማስታወቂያ ላይ ትኩረት ያደረግህ አይመስልም፡፡ አልበምህን “ጥንቡሳሳም” ያልከው ርዕሱ ትኩረት እንዲስብ፣ እንደማስታወቂያም ጭምር አስበህበት ነው?

ርዕሱን የመረጥኩት አሁን አይደለም፡፡ ከቴዲ ማክ ጋር እየሰራን በነበረበት ጊዜ ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ ሥራው አልቆ ያዘገየሁት በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው ከኮፒ ራይት ጋር በተያያዘ ሁሉም ድምፃዊ የተቸገረበትን ነገር እኔም ስለተጋራሁት ሲሆን ሁለተኛው በወቅቱ ብዙ የጉራጊኛ ዘፈኖች ስለወጡ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም እንዲደመጡ ዕድል ልስጥ በሚል ነው፡፡

አንድ ሥራ ሕዝብ ዘንድ እንዲደርስ አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ማስታወቂያ ነው፡፡ በጣም ጥሩው ማስታወቂያ ግን ጥሩ ሥራ መስራት ነው ብዬ በግሌ አምናለሁ፡፡ ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቶላቸው ብዙም ያልተደመጡ የሙዚቃ ሥራዎች አሉ፡፡ በተቃራኒው ጥሩ ሥራ በነጠላ ዜማ ለቀው በመላ አገሪቱ የሚደመጥላቸው አሉ፡፡ እኔ የአልበሜን መጠሪያ “ጥንቡሳሳም” ያልኩት ርዕሰ ጉዳዩ ወቅታዊ በመሆኑና ድህነትን ለማጥፋት ሁሉም ርብርብ የሚያደርግበት ጊዜ ስለሆነ፤ ለዚህ በጐ ዓላማ ሁላችንም እንተባበር ለማለት ነው፡፡ አድማጩም “ጥንቡሳሳም ምን አለ?” ብሎ ሲጠይቅ “ድህነትን እናስወግድ አለ” እንዲባልም ስለፈለግሁ ነው፡፡

አልበሙ ከወጣ በኋላ የአድማጩ ምላሽ ምን ይመስላል?

“መርካቶ” የሚለው ዘፈን ብቻውን በሸገር ሬዲዮ ከተደመጠ ጀምሮ፣ አሁን ሙሉ አልበሙ ወጥቶ የሰሙ ሰዎች “አነጋጋሪ ሥራ” መስራቴን ደውለው እየነገሩኝ ነው፡

“ጥንቡሳሳም” ከመውጣቱ በፊቱ ርዕሱን የሰሙ “አሁን ደግሞ ምን ይዞ ሊመጣ ነው?” በሚል ተነጋግረውበታል፡፡ አሁንም እየተነጋገሩበት እንደሆነ እሰማለሁ፡፡

እንደ ባህላዊ ዘፈን ተጫዋችነትህ ለሙዚቃ በምትሰራው ክሊፕ ላይ ባህላዊ ተወዛዋዦች እንድትጠቀም የሚጠብቁ ሰዎች አሉ፡፡ ሆኖም ለ”ጥንቡሳሳም” ዘፈን ማጀቢያ ይሄ አይታይም፡፡  ክሊፑን ወደ ተወላጆቹ መንደር ሄዶ መስራት የባህል ስራህን ይበልጥ የሚያሳካው አይመስልህም?

ለጉራጊኛ ዘፋኞች ውስጥ ክሊፕ ገጠር ድረስ ሄዶ በመስራት እኔ ጀማሪና ቀዳሚው ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ “ባላገር” የሚለውን ካሴቴን ስሰራ ክሊፑን ገጠር ሄጄ ነው የሰራሁት፡፡ ክሊፕ እንደየዘፈኑ ርዕሰ ጉዳይ ስለሚለዋወጥ ለሁሉም ተመሳሳይ ነገር አይሰራም፡፡ “መርካቶ” የሚለው ዘፈኔ፣ የገበያው ሴቶች ውበትና የስራ ጥረት እንዲያሳይ ተደርጎ ተሰርቷል፡፡ ጉራጌ በገጠር ብቻ ሳይሆን በከተሞችና በተለያዩ አገራት ስለሚኖር ክሊፕ ሲሰራ ያንን ታሳቢ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡

አልበም ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ሙዚቃዎች ቴዲ ማክ የሰራቸው ላይ ኢፌክቱ የተጋነነ ይመስላል፡፡ በግጥሙ ውስጥ ያለውን ሀሳብ እንዲዋጥ አያደርገውም ትላለህ?

ጊዜ ወስደን በጣም ተጠንቅቀን ለመስራት ሞክረናል በስራ ሂደት የተማርኩት አንድ ነገር አለ፡፡ ማስተር ካሴቱ ላይ ያልነበረ ኢፌክት ተባዝቶ በሚመጣው ውስጥ በቀጭኑ ይሰማል፡፡ እንዲህም ቢሆን በአንዱ ዘፈን ላይ ብቻ ነው ሳውንድ ኢፌክቱ ቀጠን ብሎ ጎልቶ የሚሰማው፡፡

በባህላዊው የጉራጊኛ ዘፈኖች ውስጥ ከበሮ፣ የእጅ ጭብጨባና ከጉሮሮ የሚወጣ ድምጽ ልዩ ድምቀት ሲሰጡት ይታያል፡፡ እነዚህ ነገሮች ባንተ ዘፈኖች ብዙም አይታዩም…

በአሁኑ አልበሜ ላይ አንድ ሁለት ቦታ ላይ በጉሮሮ የምጠቀምባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ በኳየር የሚሰሩ ስራዎች ወደ መድረክ ለማምጣት ሲያስቸግር ይታያል፡፡ ለካሴቱ ስራ ኳየር ተጠቅመን ከሆነ በየሄድንበት መድረክ ሁሉ ኳየሩን ይዞ መሄድ የግድ ይሆናል፡፡ ያለበለዚያ ሰው በካሴት የሰማውን የሚመጥን ስራ ማቅረብ አንችልም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ባህሉን በጠበቀ መልኩ በከበሮ፣ በእጅ ጭብጨባና በድምፅ /በጉሮሮ ማጀብ ጭምር/ በመጫወት የሚታወቁና በጉራጌ ሰርግ ቤቶች የሚጫወቱ ጎበዝ ልጆች እየታዩ ነው፡፡

ጉራጊኛ ሙዚቃ ሲባል ቶሎ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ሞቅ ያለ የሚያስጨፍር ሙዚቃ ነው፡፡

አንተ ከዚህ ወጣ ብለህ የትዝታ ቃና ያለው ዘፈን ተጫውተሀል፡፡ ምንድነው ምክንያትህ? እንዲህ ዓይነት ሙከራ ቀድሞ የጀመረ ነበረ?

ዘፈኖቼን በካሴት ማሳተም ከመጀመሬ በፊት ለስለስ ያሉ የጉራጊኛ ዘፈኖችን በ1992 ዓ.ም. በመድረኮች ላይ እጫወት ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አጨዋወት ካሴት አሳታሚዎቹን ስለማይስባቸው አልበሜ ውስጥ በማካተት ፈር ቀዳጅ መሆን አልቻልኩም፡፡ ለስለሳ ሙዚቃ በጉራጌ ባህል ውስጥ የነበረ ነው፡፡

ቅደመ አያቴ ምቱ በጣም ዝቅ ያለ ሊባል የሚችል ዘፈን በማንጎራጎር ሲጫወቱ ደርሼባቸዋለሁ፡፡ ጉራጊኛን በዚህም ቅኝት የመጫወት ፍላጎት ስለነበረኝ ከመድረክ አልፌ አሁን የአልበሜ አካል አድርጌዋለሁ፡፡ በጉራጌ ባህል ውስጥ ለጭፈራና ለመዝናኛ ብቻ ሳይሆን በሀዘንና በትካዜ ጊዜ የሚዜሙ ብዙ ዘፈኖች አሉ፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ከተማ ዕድሮች ለቅሶን ላለማበረታታት እንዲቆም ካደረጓቸው የለቅሶ ባህሎች አንዱ በመሆኑ አይታይም እንጂ ጉራጌዎች በለቅሶ ወቅት ሀዘናቸውን በዜማ የሚገልጹበት ልዩ ስነ ስርዓት ነበር፡፡ ይህ ልማድ በገጠር አልጠፋም፡፡

“ጊስት ና” የሚለው ዘፈንህን ነው በትዝታ ዜማ የተጫወትከው፤ ለዚህ ዘፈን የትዝታ ቅኝት ለምን መረጥክ?

እኔ ብዙ ጊዜ ሰርግ ላይ እየተጋበዝኩ እጫወታለሁ፡፡

በሁሉም መድረክ ማብቂያ “የሕይወቴ ሕይወት” እና “ሀይ ሎጋ” የግድ ይቀርባል፡፡ የእነዚህን ዜማዎች አገልግሎት በጉራጊኛም ለመድገም ነው የሞከርኩት፡፡

“ጊስት” በቀላል ትርጉሙ እመቤት ናት ለማለት ሲሆን ሰፍቶ ሲተነተን በእናትነቷ፣ በአገር ወዳድነቷ፣ ቤተሰብነቷ /ወልዳ የከበደች/፣ በማህበራዊ ተቀባይነትና ተከባሪነቷ… እንደ ንግስት የምትታይ አርአያ የሆነች ሙሉ ሴት ናት፡፡ እኔም “ጊስት ና” ብዬ የዘፈንኩት ለእንደዚህ ዓይነት ሴቶች አክብሮቴን ለመግለጽና ጋብቻ ወደ እመቤትነት መሸጋገሪያ አንዱ ድልድይ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡

አንጋፋው የጉራጊኛ ዘፈኖች አቀንቃኝ አርጋው በዳሶ የተጫወተውን “ዓለም ብሬ”ን ደግመህ ተጫውተኸዋል፡፡

ከቀድሞ ያንተ ዘፈኖች በዚህ አልበም ደግመህ የተጫወትከው አለ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ?

“ዓለምዬ ዓለመ” የሚለው ዘፈን በ1988 ዓ.ም በክስታኔ ባንድ እያለሁ የተጫወትኩት ነው፡፡ ሁለት ዜማ ብቻ ተጫውቼ ወደ ጭፈራ ነበር የምገባው፡፡ እንዲህም ሆኖ ሕዝብ በጣም ስለሚወደው አሁን ዜማ ጨምሬበት ነው በአልበሜ ያካተትኩት፡፡ “ዓለም ብሬ” እኔ ከጋሽ አርጋው በዳሶ የወሰድኩት ሳይሆን ሕዝባዊና በወለኔ፣ በክስታኔና በኦሮሞዎች ዘንድ የሚዘፈን ጥንታዊ ዜማ ነው፡፡ “ዓለም ብሬ” በድንበር የሚጎራበቱ ኦሮሞና ክስታኔዎች ሁለቱም በአንድነት የሚጨፍሩበት ዜማ ነው፡

ከባህልና ከሕዝብ ስንወስድ ግን መሰረቱን ሳንተው ለማዘመን መጣር አለብን፡፡ የምንሰራው ሙዚቃ ለባህሉ ባለቤት ተደራሽ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ተደማጭነት እንዲያገኝ መጣር ይኖርብናል፡፡ እዚያ ደረጃ ለመድረስ ግን ብዙ መስራትን ይጠይቃል፡፡

የጉራጊኛ ዘፈን ተጫዋቾች ልምድ የምትለዋወጡበት መንገድ አለ? ለምሳሌ ወጣቱ ከአንጋፋው…?

አጼ ቴዎድሮስ “የረገጥኩበት ቦታ ሁሉ አገሬ ናት” ይሉ ነበር እንደሚባለው ጉራጌም በሄደበት ሁሉ መድረሻውን አገሬ ነው ብሎ የሚያምንና ከማንም ጋር ተስማምቶ መኖር የሚችል ሕዝብ ነው፡፡

ስለዚህ ሰርቶ ለመኖር ይተጋል፡፡ በእኛ ሙያ ይህንን ለመግለጽ፣ ጋሽ አርጋው በዳሶና ጋሽ መሀሙድ አህመድ በድምጻዊነት የጉራጌ አምባሳደሮች ሆነዋል፡፡ እኛ እነሱን እየሰማን ወደ ሙያው መጣን እንጂ ልምድ በቅርብ ሆነን የተቀባበልንበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ዛሬ ያለው እውነትም ይኸው ነው፡፡ የእርስ በእርስ ግንኙነታችን ደካማ ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡

ነጋዴነትን ሞክረኸው ታውቃለህ?

አባቴ የከባድ መኪና ሹፌር ሲሆን እናቴ የቤት እመቤት ናት፡፡ በትምህርቴ ገፍቼ በጀኔራል መካኒክስ ከተመረቅሁ በኋላ በሙያው ሰርቼበታለሁ፡፡ የአገሬን ቋንቋ መናገር ያስደስተኝ ስለነበር የትምህርት ቤት ጓደኞቼ “ፀጋዬ ክስታኔ” ብለው ነበር የሚጠሩኝ፡፡ ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ የክስታኔ ባንድ አባል ሆንኩ፡ ከዚያ ተነስቼ በሙዚቃ ስራ እዚህ ደረስኩ፡፡ ከወደፊት ዕቅዶቼ አንዱ የንግድ ስራ እጀምራለሁ የሚል ነው፡፡

ለመስቀል በዓል አገር ቤት ትገባለህ?

የቀረህበት ጊዜ አለ ወይ? ብባል መልሱ ይቀለኝ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ደመራ ላይ መገኘቴን የማያስታውሰው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ደንጌሳት (የልጅ እሳት) ወይም ደንጋሳ (ክትፎ፣ አይቤና ጎመን ማቅረቢያ ጣባ) ከሚሉ ቃላት ስያሜውን ያገኘው የመስቀል በዓል ከሐምሌ መጨረሻ እስከ ጥቅምት 5 ቀን የሚዘልቅ ታላቅ በዓል ነው፡፡

አባወራ፣ የቤት እመቤት፣ ልጆች… ሁሉም የየራሱን ኃላፊነት በብቃት ተወጥቶ በስፋት የሚከበር ዓመታዊ በዓል ነው - መስቀል፡፡ ይህንን በዓል በአዲስ አበባም ለማስተዋወቅ ባለፉት ሶስት ዓመታት የደንጌሳት በዓል አቅርበናል፡፡ በቅርቡ በአገራችን ከተከሰተው ሀዘን ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴዎች ቀዝቀዝ ብለው ስለከረሙ ዘንድሮ የአዲስ አበባው ዝግጅት አይኖረንም፡፡

ሻማ የጉራጌ ባህላዊ ልብስ አይደለም በማለት የምታነሳቸው ሀሳቦች ከምን ደረሱ?

አሁን እግዚአብሔር ይመስገን ለውጥ እየመጣ ነው፡፡ ሻማን የጉራጌ ባህላዊ ልብስ ነው ብሎ ያወጀው ማን እንደሆነ እንኳን አይታወቅም፡፡ ነገሩ በቴአትር ቤቶች የጉራጊኛ ዘፈን ተወዛዋዦች ሻማ ለብሰው ከመጫወታቸው ጋር የተያያዘ ነው ይባላል እንጂ የሕዝቡ ባህላዊ ልብስ የሸማ ምርት ነው፡፡ በብዙ የጉራጌ እናቶች ወገብ ላይ የማይጠፋው ከሸማ የሚሰራው መቀነት /ደቆት/ ለዚህ እውነታ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

በመጨረሻ የምትለው ነገር ካለ…

በአዲሱ አልበሜ ላይ ታዋቂ አርቲስቶች ተሳትፈዋል፡ኃይሉ ፈረጃ፤ አንድ የሰባት ቤት ጉራጌ ግጥም፣ እንደሻው ጥላሁን የዶቢ ጉራጌ አንድ ዜማና ግጥም ሲሰጡኝ አለማየሁ ወልዴ ደግሞ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ሁሉም ጉራጌዎች እንዲሰሙት አድርጌ የተጫወትኩት ዘፈን ላይ ብዙ እገዛ አድርጎልኛል፡፡ ሁሉንም አመሰግናለሁ፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲሱ ዓመት የሰላምና የፍቅር እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ የመስቀል በዓል የምታከብሩ ሁሉ እንኳን አደረሳችሁ የሚል መልካም ምኞቴ ይድረሳችሁ፡፡

 

 

 

 

Read 2204 times Last modified on Saturday, 22 September 2012 12:27