Saturday, 22 January 2022 00:00

ስም እና ተግባሩ- (የስሞች እኩልነትና መበላለጥ)።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

  ስም፣ የ”ማንነት” ታፔላ ነው - የሃሳብና የባሕርይ ገላጭ? ወይስ፣ እንደ ታርጋ ቁጥር ትርጉም አልባ፣ መለያ ምልክት ይሆን? “ስሞች ሁሉ እኩል ናቸው” ያስብላል።
ከአቶ እስከ ፊልድ ማርሻል፣ ከወይዘሮ እስከ ፕሬዚዳንት ድረስ፣ የሰው ስያሜ፣ እንደ ማዕረግ፣ ማንነትን የሚጠቁም፣ የሹመት ማረጋገጫ ነው?
የንጉሦች ስም ይቀየራል። በንግስ በዓላቸው፣ ከአዲስ ስልጣን ጋር፣ አዲስ መጠሪያ ስም ይይዛሉ። እንደገና እንደመወለድ፣ ወደ አዲስ ማንነት እንደመሻገር ስለሚቆጠር ይሆን? “ተፈሪ መኮንን” የሚለው ስያሜ ቀሪ ሆኖ፣ “ኃይለሥላሴ” ተብለው ተሰይመዋል። በነጠላ ነው፣ የአባት ስም ሳይጨመርበት። ለምን? መቼም ትርጉም ቢኖረው ነው።
ቢሊዮነርዋን ደራሲ ደግሞ አስታውሱ። የመጀመሪያውን የ”ሃሪ ፖተር” ልብወለድ ድርሰት ለማሳተም፣ ስሟን በከፊል ለመደበቅ ተገድዳለች። ለምን? “መፅሐፍሽ ገበያ እንዲያገኝና እንዲነበብ” የሚል ምክንያት ነው ያቀረቡላት። ለምን? ስሟ፣ የወንጀለኛ ስም አይደል! “እሺ” ብላ የተስማማችውስ ለምን ይሆን? የመጠሪያ ስም፣ የማንነት መግለጫ ስላልሆነ? ሌላ የስም ለውጥም አጋጥሟታል። የለውጦቹን  ሚስጥር ስንመለከት፣ በእርግጥም፣ የመጠሪያ ስም፣ “ማንነትን የሚገልፅ ትርጉም” የለውም ያሰኛል።
እና፣ የመጠሪያ ስም፣ እንደ እለታዊ የወረፋ ቁጥር፣ እንደ ጊዜያዊ የማሊያ ልብስ ይሆን? ምንም ትርጉም የሌለው፣ አውልቀው የሚቀይሩት፣ በማግስቱ እንደ እጣ የሚያነሱት ቁጥር ነው? በተቃራኒው፣…
“በስሙ ይነግዳል፤ በስሙ ይፈውሳል፤ በስሟ ይምላል”፤ የሚሉ አባባሎች ደግሞ አሉ። “በስሟ ስለት ገብቼ” ብሏል - ታላቁ ባለቅኔ። ስም፣ ትልቅ ትርጉም ቢኖረው ነው። መቼም፣ “ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት” የሚለው ስያሜ፣ ያለአንዳች ትርጉም የመጣ አይደለም። “ቦይንግ” ወይም “አፕል” የሚሉ የኩባንያ ስሞች፣ “ምንም ትርጉም አያስተላልፉም” ማለት አይቻልም።
የስም ትርጉም፣… ማንነትን የሚቀርፅና የሚገልፅ?
“ስምን፣ ያወጣዋል መልዐክ” ይባላል። ስም፣ “የሰውን ማንነት ይገልጻል” ለማለት ነው። ስም፣ “የሰው ማንነትን ይቀርጻል” ለማለት ታስቦም ሊሆን ይችላል። ለዚህም ይሆናል፣ “ምስራቅ” የሚል እንጂ፣ “ምዕራብ” የሚል የሰው ስም የማያጋጥመን። ጥበቡ እንጂ ገልቱ የሚል ስም አለ? በእርግጥ፣ “ከደስታና ከሰላሙ” ጎን ለጎን፣ “አዘነ ወይም አሸብር” የሚሉ ስሞች ያጋጥማሉ።
ቢሆንም ግን፣ “አሸናፊ፣ ልዑል፣ ገነነ፣ እልልታ፣ ገነት፣ ንግስት” ብሎ ልጆቹን የሚሰይም ወላጅ ይበዛል። “ተሸናፊ፣ ሎሌ፣ ሟሸሸ፣ እሪታ፣ ገሃነም፣ ባሪያ” የሚሉ ስሞችን ለልጆቹ የሚያወጣ ወላጅ የለም። ወይም መኖር የለበትም። እና፣ የሰው ስም፣ ማንነትን የሚገልፅና የሚቀርፅ ትርጉም ይይዛል? የስያሜ ትርጉም፣ የሰውን ማንነት የሚገልፅ ሳይሆን፣ የወላጆችን ምኞት የሚጠቁም ነው ቢባል ይሻላል።
“በላቸው” የሚለውን ስም፣ ምን ተብሎ ይተርጎም?
“ስም፣ ትርጉም የለውም” የሚሉ አሉ። “ስም አይተረጎምም” ይባል የለ? “ደምሴ አለሙ” የሚለውን ስም፣ ምን ብለን ወደ እንግሊዝኛ እንደምንተረጉመው ይታያችሁ።
“በላቸው” የሚለው ስምስ፣ “ንገራቸው” ማለት ነው? ወይስ “ምታቸው”? ወላጆቹን መጠየቅ ሊኖርብን ነው። ደግነቱ፣ “መጠሪያ ስም”፣ የወላጆችን ወይም የአሳዳጊዎችን ምኞት ቢጠቁምም እንኳ፣ የሰውን ማንነት የሚገልፅ ትርጉም የለውም።
“አበበ” ማለት፣ ከአበባ ጋር ግንኙነት የለውም። “ከበደ” ወይም “ከበደች” ስንል፣ ከክብደትና ከኪሎግራም፣ ከክብርና ከሃብት፣ ወይም ከእርግዝና ጋር አይዛመድም። “በቀለ”፣ ከችግኝ አልያም ከብቅል ጋር አይመሳሰልም።
ስም፣ ትርጉም ከሌለው፣ ከታርጋ ቁጥር አይለይም? “ያንቺ ቁጥር፣ ካንተ ቁጥር ይበልጣል” ብለን ታርጋዎችን ወይስ የስልክ ቁጥሮችን አናወዳድርም። ምክንያቱም፣ እንደ መጠሪያ ስም ናቸው።
ስሞች፣ ቃላት ቢሆኑም፣ ማንነትን (የባሕርይ ወይም የብቃት ማንነትን) የሚገልፁ አይደሉም። የስልክ ቁጥሮችም፣… ቁጥር ቢሆኑም፣ ብዛትን ወይም መጠንን የሚገልፅ ትርጉም የላቸውም።
የገቢ የወጪ፣ የትርፍ የኪሳራ፣ የብዛት የመጠን ቁጥሮች አይደሉም - የታርጋና የስልክ ቁጥሮች። “ብዙዬ” እና “ትርፌ” የሚሉ ስሞችም እንደዚያው ናቸው። አለበለዚያማ፣ “ዋጋዬ” ከሚለው ስም ጋር፣ የቫት ደረሰኝ፣… ከ”ትርፌ” ጋር ደግሞ፣ “ግብር ክፈል” የሚል ጣጣ ይመጣ ነበር።
ስም ክብር አለው - ትርጉም ባይኖረውም።
ስም፣  ትርጉም የሌለው፣ የግል መጠሪያ፣ የግል መለያ ታርጋ ነው። ታዲያ ለማጣጣል አይደለም። የግል ስም፣ ክብር አለው። ለእያንዳንዷ ጠጠር ወይም ሚስማር፣ ለእያንዳንዷ ዛፍና ወፍ፣ የግል መጠሪያ ስም አናወጣም። የግል ስያሜ የሚመጣው፣ ለግል ህልውና ተገቢውን እውቅናና ተገቢውን ዋጋ ከመስጠት ጋር ተያይዞ ነው።
ቢሆንም ግን፣ ማንነትን የሚገልጽ ትርጉም ወይም ማንነትን የሚቀርጽ ሃይል የለውም። አባይ፣ የወንዝ አልያም የሰው ስም ሊሆን ይችላል። የቦታ የከተማ፣ የተራራ የኩሬ ስም ቢሆንም ችግር አያመጣም። የግል ስያሜ ዋና ቁምነገር፣ የግል ቋሚ መጠሪያ፣ የዘወትር መለዮ መሆኑ ላይ ነው። የግል… እና ቋሚ! አለበለዚያማ ምኑን ስያሜ ሆነው! እለታዊ የወረፋ ቁጥር ሆኖ ያርፈዋል።
ስሞች  ሁሉ እኩል ናቸው- ትርጉም የሌላቸው።
ለሰሚ  የማይከብድና የማያስነውር እስከሆነ ድረስ፣ ቋሚ የግል መጠሪያ ሆኖ ማገልገሉ ነው- የስያሜ ፋይዳው። ከዚያ ውጭ ፣ ሁሉም ስም እኩል ነው? እኩልነታቸውም፣ ስሞች ሁሉ ትርጉም አልባ መሆናቸው ላይ ነው? ይመስላል። ነገር ግን፣…
“የሚስተር ባይደን የስዕል ስራዎች፣ ለሽያጭ ቀርበዋል” የሚል ዜና ስትሰሙም፣ በስም እኩልነት ታምናላችሁ? ስም፣ ትርጉም የለውም ትላላችሁ? ታዲያ የባይደን ጉዳይ፣ የትልልቅ ጋዜጦች ትልቅ የመወዛገቢያ ርዕሰ ጉዳይ የሆነው ለምን ይሆን?
ሰዓሊ ሆኛለሁ ብለው የመጡት ሚስተር ባይደን፣ የፕሬዚዳንት ባይደን ልጅ ናቸው። የአባታቸው ስም እና ታዋቂነት የስዕል ማሻሻጫ ቢሆንላቸው አይገርምም። ስሞች ሁሉ እኩል ባይሆኑ ነው። ምን ይሄ ብቻ!
 ከፕሬዚዳንት ባይደን ውለታ ለማግኘት የሚመኝ ሃብታም ድርጅት የልጃቸውን ስዕል በመግዛ ውለታ ለማስመዝገብ መሞከሩ አይቀርም የሚል ነበር ውዝግቡ።
በአጭሩ፣ ነገሩ የሙስና ጉዳይ ሆነ ማለት ነው። የስም እኩልነትና ትርጉም አልባነት ላይ እንደገና መነጋገር ሳይኖርብን አይቀርም።
ቢሆንም ግን፣ መጠሪያ መለዮ ስም፣ ሁለት ነገሮችን እንደሚያሟላ ግልጽ ነው። ቋሚ መሆን አለበት። የግል መጠሪያም ነው። “ተራራ” የግል ስም አይደለም። ሁሉንም ተራሮች ያዋሃደ ግንዛቤ ወይም ፍሬ ሃሳብ ነው። ራስ ዳሽን ግን የግል ስያሜ ነው- የአንድ ትልቅ ተራራ ስም። ግን ቋሚም መሆን አለበት። የግል… እና ቋሚ! አለበለዚያማ ምኑን ስያሜ ሆነው!
“ከማንነት ለውጥ” ጋር የሚመጣ ቅያሬ ስምስ? እንደገና እንደመወለድ።
አዎ፣ ስም፣ ቋሚ ሆኖ ላይዘልቅ ይችላል። ስያሜ ይቀየራል። በንግሥ ጊዜ፣ ስም ይለወጣል። የንግሥ በዓል፣ “በአዲስ መልክ የመወለድ” ባሕርይ አለው።
ከንግሥ በዓሉ በኋላ፣ ንጉሡ፣ እንደ ተራ ሰው ለመሆን ይቅርና፣ እንደ ሌላ ባለስልጣን ለመሆንም አይችልም። የትናንት አኗኗሩ፣ ተግባሩና ንግግሩ፣ ወደ ነገ አይሸጋገርም። ትናንት የማይችላቸው ነገሮች ደግሞ፣ ዛሬ፣ በስልጣኑ ስር ናቸው። ሃላፊነትና ግዴታ ጭምር ይሆኑበታል።
ነገረሥራው ሁሉ፣ በሹመቱ ቅኝት ስር ይገባል። የቀድሞ ፍላጎቶቹንና ልምዶቹን መከተል፣ እንደቀድሞ መደበኛ ኑሮውን መምራት አይችልም። መልክና አዋዋሉ ሁሉ ይቀየራል። የንግሥ ሥርዓትን ተከትሎ፣ ልብስ መቀየር፣ በትረ መንግስት መጨበጥ፣ ዘውድ መድፋት ይኖራል።
አድራሻውም ይለወጣል። መኖሪያው በቤተ መንግስት፣ መንበሩም ዙፋን ላይ ይሆናል።… ወራሽ ነኝ ይላል - መወለድን በመጥቀስ። ነገር ግን፣ የድሮ ስያሜውን መለወጥ የተለመደ ነው። ለዚያውም፣ የአባት ስም ቅጥያ አይኖረውም። ነጠላ ስም ይወጣለታል።
በቅድሚያ፣ አልጋ ወራሽነትን ለማረጋገጥ፣ “የእገሌ ተወላጅ” ብሎ ማሳመን የግድ ነው። “ከንግሥ” በኋላ ግን፣ “የእገሌ ልጅ” ብሎ ነገር አይኖርም። “የእገሌ ልጅነት” የቀድሞ ታሪክ ይሆናል። ንጉሡ፣ በበዓለ ንግሥ፣ የቀድሞ ታሪኩን አልፎ ይሻገራል፤ ከወላጆቹ በላይ ልቆ ይሄዳል። ከንግሥ በኋላ፣ ወላጆቹም ታዛዦቹ ናቸው። ይህም ብቻ አይደለም።
የቀድሞ ሕይወቱና ማንነቱ የተቀየረ ያህል ነው የሚታሰበው። በበዓለ ንግሥ፣ እንደ አዲስ የተወለደና አዲስ ስም የወጣለት፣ አዲስ ማንነትን የተሸከመ ወይም የተጎናፀፈ ያህል ቁጠሩት። ከምድራዊው ቤተሰብ ባሻገር፣ በመለኮታዊ ሃይል የተመረጠና የተሰየመ ያህል ነው - ለውጡ። በወላጅ የተሰየመ ሳይሆን፣ “በፈጣሪ የተሰየመ” እንደማለት መሆኑን አስቡት። አዲስ ልደትና አዲስ ስም እንደማለት።
በምንኩስና ወቅት፣ የቀድሞ አለማዊ ሕይወት ሞቶ፣ አዲስ መንፈሳዊ ሕይወት ይወለዳል ይባል የለ! እንደገና እንደመወለድ ስለሚቆጠርም፣ አዲስ የመጠሪያ ስም ያስፈልጋል። “የዚህ አካባቢ ወይም የዚያ አካባቢ ተወላጅ ነኝ” ብሎ ማሰብና መናገር ይቀራል። በመነኩሴ ዘንድ፣ “የእገሌ ወይም የእከሌ ልጅ ነኝ” ማለትም አይኖርም። የንጉሥም፣ እንደዚያ አይነት መንፈስ አለው።
“በፈጣሪ የተሰየመ” እንጂ፣ “የእገሌ ልጅ” አይባልም። በዚያ ላይ፣ “የአገር ሆኛለሁ፣ የሁሉም ሕዝብ ሆኛለሁ” የሚል ትርጉምም ይኖረዋል። በዚህም ተባለ በዚያ፣ “ተሰይሜያለሁ” ይላል። አዲስ ስያሜውንና ማዕረጉን ያውጃል። የስልጣን ምልክቶቹንም ያሳያል - በዘውድና በዙፋን፣ በአልባሳትና በበትረ መንግስት።
በርካታ የአገራችን ነገሥታትን መጥቀስ ይቻላል። “ካሳ ኃይሉ” እና “ካሳ ምርጫ”፣ ከንግሥ በኋላ በተሰየሙበት መጠሪያ ነው በሰፊው የሚታወቁት - አፄ ቴዎድሮስ እና አፄ ዮሐንስ በሚል ስያሜ።
እና፣ በዚህ መነፅር ስናየው፣ የመጠሪያ ሥም፣ የግል ማንነትን የሚገልፅ አንዳች ትርጉም የተላበሰ አይመስልም?
የደራሲዋ ማንነትና ዝና፣ በሥም ለውጦች የሚገለፅ ወይስ በድርሰት ስራዎቿ?
የመጠሪያ ሥም፣ በንግሥ ወይ በምንኩስና ብቻ ሳይሆን፣ ለሌላ ምክንያትም ይቀየራል። ከዓለማችን የኪነጥበብ ደራሲዎች ሁሉ በሃብት የላቀችው ደራሲ፣ ሁለቴ የስያሜ ለውጥ አጋጥሟታል- አንዴ በትንሹ አንዴ በትልቁ፣ አንዴ በተጽዕኖ፣ አንዴ በራሷ ፍላጎት። በድህነት ነበር ኑሮዋ። አንዳንዴም ጾም እያደረች ነበር ድርሰቷን የምትጽፈው። ከዚያስ?
የመጀመሪያ መጽሐፏን  ለአንባቢዎች ለማድረስ፣ በርካታ አሳታሚዎችን አጠያይቃለች - ግን ቶሎ አልተሳካም።
12 አሳታሚዎች፣ “አንፈልግም” ብለው ድርሰቷን በመጣበት ተመላሽ አድርገውባታል። ከወቅቱ ጊዜዊ ፋሽን ጋር አይሄድም የሚል ምክንያትም አጋጥሟታል። በመጨረሻ፣… በአምስት መቶ ቅጂ አሳትመን እንሞክረው የሚል ድርጅት አገኘች። ግን፣ ስምሽ ችግር ያመጣል አሏት። በሴት ደራሲ ስም የታተሙ መጻህፍት፣ ብዙ ገዢና አንባቢ አያገኙም። ስለዚህ የሆነ መላ እንፍጠር አሏት።  
ያደረገችበትን ስም መቀየር አለባት? ሙሉ ለሙሉ ሳይቀየር፣ በከፊል መሸፈንና የሴት ስም መሆኑ እንዳያስታውቅ ማድረግ ይቻላል። ጆአና የሚለው ስም ቀረ። ጄ.ኬ.ሮውሊን በሚል ስያሜ መጽሐፏ ታተመ። እንዲያም ሆኖ፣ ለጊዜው ብዙ አልተሸጠም።
እየዋለ ሲያድር ግን፣ መጽሐፏን ያነበቡ ጥቂት ሰዎች፣ በአድናቆት ለሌሎች እየነገሩ፣ በሰው በሰው ተወዳጅነት እያገኘ፣ በተደጋጋሚ በብዛት እየታተመ፣ የመጽሐፏ ዝና ተስፋፋ። የሚታተመውና የሚቸበቸበው የመጽሐፍ ቁጥር በሚሊዮኖች ሆነች።
ከመነሻውም በሰባት ክፍል ለመጻፍ ወጥና የጀመረችው ድርሰት፣ ሰመረላት። ሁለተኛው፣ ከዚያም ሦስተኛው እያለ በተከታታይ ሲታተም፤ በይዘትም በተወዳጅነትም እየላቀ፣ ደራሲዋ፣ ቢሊዮነር ሆነ።
ከዚያስ ምን ትስራ? ሰባቱ መጻህፍት፣ በፊልም ተሰርተው ስኬታማ ሆነዋል። ለተወሰነ ጊዜ እዚህ ላይ ሰርታለች። ግን ከዚያስ? መቼም፣ በሷ ስም የሚታተም ድርሰት፣ በሚሊዮኖች መታተሙ አይቀሬ ነው-ምንም ሆነ ምን። ስሟ፣ የገበያ እንቅፋት ሳይሆን፣ አጓጊ የገበያ ማሻሻጫ እንደሚሆን ቅንጣት አያከራክርም።
 ስሟ ከብሯል፤ ተወዳጅና፣ ተፈላጊ ሆኗል። ስሟ በመላው ዓለም ነግሷል። ግን ለበርካታ ዓመታት ድምጿ አልተሰማም። ዓለምን የሚነቀንቅ ድርሰት በሷ ስም አልታተመም።
ደግነቱ ሌላ ደራሲ አልጠፋም።  እዚያው እንግሊዝ ውስጥ፣ ልክ እንደሷ ሌላ ድንቅ ደራሲ በሌላ የልብወለድ ዘርፍ ተወዳጅነት አግኝቷል- ወንጀል ምርመራ ላይ ባጠነጠነ የልብ ወለድ ድርሰት። መቼስ እንግሊዝ፣ በወንጀል የምርመራ ድርሰት፣ ለገናና ጸሃፊዎች እንግዳ አይደለችም። አሁንም ሌላ ታላቅ ደራሲ ተፈጠረ። ድርሰቱ  በብዛት ተሸጠ። ሁለተኛው መፅሐፍ ሲታተም  ደግሞ ከመጀመሪያው የሚበልጥ ሆነ። በተለይ ደግሞ ሶስተኛው መፅሐፍ…
እንዲህ እንዲህ እየተባለ በሚሊዮኖች የተሸጡ አምስት ድንቅ ድርሰቶች ታትመዋል።  ድርሰቶቹ፣ በሌላ ስም የታተሙ ቢሆኑም፣ የጄኬ ሮውሊን ድርሰቶች ናቸው።
እና፣ ዋናው ነገር፣ ስያሜ ነው? ወይስ ነገረ ስራ?
የማንነቷ መፍቻ ቁልፍ፣ ስሞቿ ናቸው ወይስ የጥበብ ስራዎቿ?
ዋናው ነገር፣ የሰው ስያሜው ሳይሆን፣ “ነገረ ስራው” ነው ብለው የሚያስተምሩ አሉ። “ስልቻ ቀልቀሎ፤ ቀልቀሎ ስልቻ” የሚል ብሂል ጠቅሳሉ።
ዋናው ቁልፍ፣ የሚስጥር ሁሉ መፍቻ፣ “ስም” ነው የሚሉም ሞልተዋል። እውን ነገሮችን ማየት፣ ተፈጥሯዊውን ዓለምም መዳሰስ፣ ትልቅ ቁምነገር አይደለም ይላሉ። ለዚህ ለዚህማ፣ ብዙ እንስሳትም ያያሉ፤ ይዳስሳሉ። የነገሮችን ስም ማወቅ ነው፤ እውቀት ማለት። ስም ማወቅ፣ አንዳች ምትሃተኛ ሃይል እንደመጨበጥ ነው ብለውም ያምናሉ።
ስም ከማወቅ ይልቅ ደግሞ፣ ስም ማውጣት ይበልጣል። ስም መስጠት፣ ልሕቀትን፣ የበላይነትንና ስልጣንን ይመሰክራል። ከተሰየመ የሰየመ ይልቃል። ከተሿሚ ሿሚ ይበልጣል እንዲሉ።
መሰየም (ስም ማውጣት ወይም ሹመት መስጠት) ቀላል ነገር ባይሆንም፤ የአንድ ነገር ስያሜ፣ እውኑን ነገር መተካት ይችላል? የነገር ስም፣ ከእውኑ ነገር የላቀ ትርጉምና ዋጋ መያዝ አለበት? “የለበትም” ብለው የሚስተምሩ አዋቂዎች ቢኖሩ አይርምም።
ስያሜን ለማቃለል ሳይሆን፤ ልኩን እንዳንስተው አስበው ይሆናል። ስያሜ ዋጋ አለው፤ ግን እውኑን ነገር ለመሸፈንና ለመሸወድ የሚገለግል የማታለያ መሳሪያ ይሆናል- ልኩን ከሳትነው።
“መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” ይላል አንዱ ብሂል። በእርግጥም፣ ስያሜ፣ ትንሽ ትንሽ “ይደግፍ” ይሆናል። ነገር ግን፣ እውኑን ዓለም፣ የምኞት ተገዢና ታዛዥ እንዲሆንልን የሚያገለግል መሳሪያ አይደለም- ስያሜ።
አስማተኞች ነን ካልተባለ በቀር፤  ስሞችን ወይ ቃላትን በመናገር ብቻ፣ “በጎ ምኞትን”፣ ወደ “በጎ ክስተት” መቀየር አይቻልም። እንደዚያ ከተቻለ፣ አስማት ተሰራ ማለት ነው።
ነገር ግን ለእልልታ አትቸኩሉ። አስማት ወይም ምትሃት፣  ለበጎ ምኞት ከሰራልን፣ ለክፉ ምኞትም እንደሚያገለግል አንርሳ።
“በስም ይደግፉ” ከሚለው አባባል ጎን ለጎን፣ “በስም ያጠፉ” የሚልም ይመጣል። “ሊበሏት ያሰቧትን ጅግራ፣ ቆቅ ይሏታል” ተብሎ የለ? ቆቅ ብለው ሲሰይሟት፣ ቆቅ ትሆናለች! “ተባለች!” ከማለት ልቅ፤ “ተበላች” ብንል ይሻላል እንጂ።
ስያሜ፣ ምንነትና ማንነት የሚወስንና የሚቀርጽ ከሆነ፣ “ሆረር” ነው።
 በአጭሩ፣ ስያሜዎች ዋጋ አላቸው። ፋይዳቸው ግን፣ ልካቸውን እስከጠበቅን ድረስ ነው። ልካቸውን ከሳትን፣… ፋይዳቸው ወደ ፍርጃ ይዞርብናል።
ግን፣ ከምር ስታስቡት፣ ስሞች ማንነትን አይገልጹም? የሆነ አይነት መልዕክትና ትርጉም አያስተላልፋሉም? ጄ.ኬ ሮውሊን ወይም ያሬድ የሚሉ ስሞች፤ አፕል ወይም ዊንዶውስ የሚሉ ስያሜዎች ትርጉም የላቸውም?
“ትርጉም አላቸው” ያስብላል- የአንዳንዶቹ ዝና።
 ነገር ግን ከየት የመጣ ይሆን ዝናቸው? መቼም የደራሲዋ ዝና፣ ከስሟ የፈለቀ አይደለም።
በሃሳቦቿና በስራዎቿ፣ በብቃቷና በሙያ ፍቅሯ፣… በአጠቃላይ… በግል ማንነቷ አማካኝነት ነው፤ የሷ ስም በመላው ዓለም የናኘው፤ በክብር የገነነው። በድንቅ ስራዎቿ፣ ስመጥር ሆናለች። በክቡር ጥበቧ ነው ስሟ የተከበረው።
በሌላ አነጋገር፣ ስሟ አይደለም፣ ክብርን ያመጣላት። ሞገስን የፈጠረላት። ከስራዎቿ በፊት፣ የደራሲዋ ስም፣ ከሌሎች ሚሊዮን ስሞች የተለየ ዋጋ አልነበረውም። የተለየ ትርጉም ይዞ አልመጣም።
በዚህ በዚህ ካየነው፤ በእርግጥም፤ ስሞች ሁሉ፣ መጠሪያ መለያ ሆነው እስካገለገሉ ድረስ፣ እኩል ናቸው፤ ትርጉም አልባ ናቸው ማለት ይቻላል።
ነገር ግን፣ ከጊዜ በኋላ፣ በጥሩም ሆነ በመጥፎ ስራ አማካኝነት፣ ስመ ጥሩነት እና ስመ ጥፉነት ይመጣል። በመልካም ስራ፣ መልካም ስምን ያተርፋሉ- አንዳንድ ሰዎች። በመጥፎ ስራ ደግሞ ስማቸውን ያጎድፋሉ- አንዳንድ ቀሽሞች።
ከዚህ አንጻር ስናያቸው ደግሞ፣ ስሞች፣ በጭራሽ እኩል አይደሉም ማለት ይቻላል። ትርጉም የለሽ ወይም ትርጉም ያጡ ናቸው የሚስብሉም አይደሉም።
ያሬድ የሚለው ስያሜ፣ ከሙዚቃ ጥበብ ጋር የተዛመደ መልዕክት ያዘለ አይደል? ስለሆነም ነው በስሙ የሙዚቃ የትምህርት ተቋም የተመሰረተው። አፕልና ዊንዶውስ የሚሉ ስያሜዎችንም አስታውሱ። አንዱ፣ በዓለማችን የአብዛኞቹ ኮምፒውተሮች የውስጥ  “ነፍስ” ነው- ዊንዶውስ። በጣም ተፈላጊና ዝነኛ። ሌላኛው ደግሞ፣ የዝነኛ ኩባንያ ስም ነው። በእነ አይፎን ምርቶቹ ይታወቃል። የአፕል ኩባንያ አክስዮኖች፣ ወይም 3 ትሪሊዮን የተጠጋ ዋጋ አላቸው። የአለማችን  ውድ ኩባንያ ነው- ዛሬ። ታዲያ ምን ይጠየቃል?
እነዚህ ስሞች፣ ከወርቅ ከእንቁ የከበረ መልእክት የያዙ ናቸው። ትርጉም አላቸው።
ነገር ግን የተከበረና የተወደደ ትርጉም የመጣው፤ ከስራ ብቃትና ከምርታማ ስኬት እንጂ፣ ከስያሜ አይደለም።
በስያሜ ትርጉም ቢሆንማ፣ ከ”ፓም” እና ከ”መስኮቶች” ያለፈ ትርጉም አይኖራቸውም ነበር- አፕል እና ዊንያውስ።
ምን ለማለት ነው?
ዞረን ዞረን ስናየው፤ የግል መጠሪያ ስያሜዎች፣ ትርጉም አልባ  በመሆን እኩል ናቸው ወደሚለው ሃሳብ ተመለስን ማለት ነው።
ወይም ደግሞ፣ መጠሪያ ስም፣ “ትርጉም” አያስፈልገውም፤ እናም አይተረጎምም።
መጠሪያ ስሞች፣ ከመነሻቸው እኩል ናቸው-በስራ አማካኝነት፣ መልካም ወይም መጥ ፎ ዝና እስኪላበሱ ድረስ።

Read 4729 times