Saturday, 22 January 2022 00:00

“ተዋከበና!”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለቴዲ አፍሮ ዉበት ያምራል እንዴ? ቁ ንጅናስ ያምራል?

          አንዳንድ ጊዜ ሰዎች “I didn’t do nothing” ወይም “I didn’t say nothing” ሲሉ መስማት አዲስ አይደለም። እጅግ በጣም አልፎ አልፎ ቢሆንም፣ እንግሊዝኛ ያፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሆኑ ሰዎችም ሲሉት ይሰማሉ። በቋንቋው ህግ መሰረት ይህ ዓ.ነገር ጎደሎ ነው። “double negative” የሚፈጥረው  የ“positive” ትርጉም/ፍቺ ግድፈት ይመስለኛል። ሁለት ነጌቲቭ (“didn’t” እና “nothing”) ቃላት/ሃረጎች፣ አንዳንዴ ፖዚቲቭ ትርጉም የሚያስከትሉ መሆኑ ነው። “I didn’t do nothing” ወይም “I didn’t say nothing” በሚሉት ዓ.ነገሮች ውስጥ ለማለት የተፈለገው “ምንም አላደረግሁም”/“ምንም አልተናገርኩም” ሲሆን፣ ትርጉሙ ግን የተገላቢጦሹ ሊሆን እንኳን ባይችልም፣ በጣም ያደናግራል። እናም ጎደሎ ነው። እንዲህ አይነቱን ጎደሎ “ቋንቋ” (“ቋንቋ” እንደ አንድ የስነ-ጽሁፍ አላባ) አንዳንድ ጊዜ በስነ-ግጥም እና በዘፈን ግጥሞች ውስጥ ሰዎች ሊጠቀሙበት ቢችሉም እንኳን ጎደሎ ነው።
የቴዲ አፍሮ “ውበትሽ ያምራል”፣ “ቁንጅናሽ ያምራል” የሚሉትም ሃረጎች ጎደሎዎች ናቸው። ሲጀመር ቴዲ አፍሮ የልጂቱን “ውበትሽ” ሲል ማማሯንም ተናግሯል። “ውበትሽ ያስጠላል” እንደማይባለው ሁሉ፣ “ውበትሽ ያምራል”ም አይባልም። ምክንያት፦ ሁለት አፊርማቲቭ ቃላት አንድ ውበትን ለመግለጽ ተሰድረዋል። “አንድ ሰው የሴቲቱን ቁንጅናም ሲናገር “ማማሯንም’ ተናግሯል። በሌላ አነጋገር፤ ጸጉር፣ አይን፣ ዳሌ፣ ባት … ወዘተ ያምራል እንጂ ቁንጅና አያምርም። እንዲያውም በአንዳንድ ቋንቋዎች ህግ መሰረት፣ የሁለት “affirmative” ቃላት አንድ ላይ መሰደር በተቃራኒው “ኔጋቲቭ” የሆነ ፍቺ ይዞ ሊመጣ ይችላል። ስለዚህ ቴዲ በሃሳቡ ውስጥ የተከሰተችውን ልጅ … “ማስጠሎ ነሽ” ያላት ያህል ነው።
የ“ውበትሽ ያምራል” ግድፈት፣ የመለስተኛ/ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የተማርኩት እና “ጸያፍ አማርኛ/ቋንቋ” ውስጥ የሚመደብ ግድፈት ይመስለኛል። “ኢትዮጵያዊያኖች” የሚለው ቃል ጸያፍ ብዜት (plural) እንደሆነው ማለት ነው። “ኢትዮጵያዊያን” ብቻውን ብዙ (plural) ሆኖ ሳለ፣ የ“…ኖች” መደገም ጸያፍ ያደርገዋል። ያማርኛው ሊቅ  ሄኖክ የሺጥላ “ኤርትራዊያኖች” ሲል እንደሳተው ማለት ነው። “ቁንጅናሽ ያምራል”ም በጣም ጎደሎ ቋንቋ ነው።
ገጣሚ ሄኖክ የሺጥላ በቅኔ ዘረፋም አልተቻለም። በቅርቡ “ወልደማሪያም” ከሚለው ውስጥ የመጨረሻውን ፊደል በማንሳት፣ ሁለት ፍቺ ያለው ቅኔ ዘረፈልን።.. በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በላይ ዝርዝር ውስጥ መግባት በእውነት ራሴን በጣም ማውረድ ይሆንብኛል። “… እከተለዋለሁ ለሚለው ሃይማኖት እና አመልካታለሁ ለሚላት ማርያም እንኳን ትንሽ ክብር የለውም እንዴ?” የሚል የጅል ጥያቄም አልጠይቅ። … እንዲያው ለመሆኑ “ሰከን በል” የሚል ወዳጅ ዘመድ አጠገቡ የለውም?
“ተዋከበና!”
ኃያል ቃል ነው። ድምጻዊው ቴዎድሮስ በምናቡ፣ አጼው ሲሆን ያየውን ሁሉ እኔም በምናቤ አየሁ–በ”ተዋከበና” ውስጥ። ዋከባ፣ ግርታ፣ … የሼክስፔር “መሆን ወይም አለመሆን”… በአጼው ውስጥ… የእንግሊዝ ንግስት እንዳዘዘችው… አጼው በፊጥኝ ታስሮ እንደ እንሰሳ እየተነዱ ከመሄድ እና ካለመሄድ ጋር የህሊና ሙግቱ ሁሉ … ሲዋከብ … አንድ የሎሬት ጸጋዬ አማርኛ ግጥም ትዝ አለኝ … ሴባስቶቦልን በመቅደላ አፋፍ ላይ ለማድረስ ከፊሉ ሰራዊት ከመድፉ ኋላ ሆኖ ሲገፋ፣ ከፊሉ ደግሞ አፋፍ ላይ ሆኖ በመጫኛ ሲጎትት… እናም በስንት መከራ እና ጭንቅ አፋፍ ላይ የደረሰው ሴባስቶቦል ወደ ጠላት መተኮሱ ቀርቶ የኋሊት ፈንድቶ የፈጀውን የአጼውን ሰራዊት ብዛት… ለዚያ ሁሉ ሰራዊትም ሞት ምክንያት መሆን ራሱ ብቻውን የሚያስከትለው ፀፀት እና የጥፋተኝነት ስሜት በሞት እና በመኖር ላይ ጥልቅ ጥያቄ ያጭራል… የእንግሊዝ ወራሪዎች ተማርኮ መዘባበቻ እና መቀለጃ ከመሆን እና ካለመሆን፣ እናም እጁን ቢሰጥ ሊደርስበት የሚችለው የአካልም ሆነ የሞራል ጉዳት … ተዋከበና… እና ስጋት እና ጭንቀቱ፣ …ማን ነበር ጀግንነት የሚፈጠረው በፍርሃት እና በጭንቅ ውስጥ ነው ያለው? ጭንቀት እና ድፍረት… ፈሪ ሲፈራ ኖሮ፣ ኖሮ፣ ኖሮ እየፈራ የሞት ሞት ይሞታል። … ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ አባት ካሳሁን፣ ልጃቸውን “ቴዎድሮስ” የሚል ስም ሲያወጡለት… አጼውንም ሆነ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ያላቸውን እምነት ጭምር አውርሰውት ነው ያለፉት…  ያሰኛል…። ግን…
ግን ግን… አጼ ቴዎድሮስን ያህል ታላቅ፣ ጠላቶቹን እንግሊዞችንም ሳይቀር ያስደመመ እና ያስገረመ መሪ፣ በሜዲያ እንዳይቀርብ ብቻ ሳይሆን፣ ከታሪክ መጽሃፍቶችም ውስጥ እንዲጠፋ እየተደረገ ባለበት በህወሃት ዘመን፣ ቴዲ ሞክሼውን እንዲያ ባደነቀበት እና ባነገሰበት በዚያ ውብ ግጥሙ መሃል … “አናሳዝንም ወይ…?” … ምነው ቴዲ? ድንኳን ተክለን ሃዘን እንቀመጥ እንዴ? ካሳን ያህል ጀግና እና ቆራጥ መሪ የሚዘክር ዜማ እና ግጥም “ዘራፍ” “እምብኝ” የሚል እንድምታ ያለው፣ አገሪቱን ከገባችበት የጎሳ አገዛዝ እና ፖለቲካ ቅርቃር መንጥቆ የሚያወጣ፣ የሚያስቆጭ የጀግና ግጥም እንጂ … “አናሳዝንም ወይ” … አያስኬድም። ለማንኛውም ቴዲ ለወደፊት ግጥሞቹን በባለሙያ ቢያስፈትሽ ከዚህም በላይ ውብ ስራ ይዞልን እንደሚቀርብ ተስፋ አደርጋለሁ።
አማርኛ እየሞተ ነው። ቴዲ ድምጻዊ ነው። ቴዲ አፍሮ አማርኛን፣ የአማርኛ “ጋዜጠኛ” እና “ገጣሚ”የሆኑ አንዳንድ ሰዎች የገደሉትን ያህል አልገደለውም። አሁን አሁን ይናገር ይጽፈው ነገር ሁሉ ባይመቸኝም፣ የነውረኛነቱ እና “ምንችክ” የማለቱ ነገር ቢያስጠላኝም፣ ጥቂት ግጥሞቹን የምወድለት ሄኖክ የሺጥላ ባንድ ወቅት ያነበበውን ግጥም አድምጬ ገርሞኝ ገርሞኝ “በዚህስ ላይ መጻፍ አለብኝ… እንዲህ “አንቱ” የተባለ የአማርኛ ገጣሚ “በላክ”፣ “ጠጣክ”፣ “መጣክ” ሲል እያየሁ ዝም አልልም ብዬ ተነሳሁ። “ከመጻፍ ይልቅ በቪዲዮው ላይ አርትኦት ሰርቼ ለምን አላቀርብም?” … ብዬ፣ የአንድ ደቂቃ ቪዲዮ ለመስራት ከሳምንት በላይ ደክሜ፣ ለአንድ ወዳጄ በድረ-ገጹ ላይ እንዲያወጣው ላክሁለት።
ደውሎ “ምንድነው የላክኸው?” አለኝ።
“ሰምተኸዋል?” አልኩት። ሰምቶታል፣ አይቶትማል።
እየገረመኝ “ምንም ግድፈት አይታይህም?” አልኩት።
እንዳልታየው ነገረኝ። በአማርኛ “በላህ” “ጠጣህ”… እንጂ “በላክ”፣ “ጠጣክ”… እንደማይባል ተናግሬ ሳልጨርስ፣ “ይሄ እንኳን ኢምንት ነው….” አይነት መልስ ሰጠኝ። ከዚያ በላይ ለማስረዳት መሞከር ድካም መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ፈረንጆቹ አንድ ያልተለመደ/ህገ-ወጥ፣ ወይም ከዚህ በፊት እንደ ነውር ይታይ የነበረ ነገር መዘውተሩን ሲያዩ “the new normal” እንደሚሉት አይነት፣ ይሄም ነገር “the new normal ነው” ብዬ ዝም አልኩ። አሁን አሁን ሳስተውል፣ “መጣክ”፣ “በላክ” የሚለው (የሚጽፈውም) ሰው ብዛት መሳ ለመሳ ነው።
 በጥቅሉ ሌላ ምትክ ያልተበጀለት የአማርኛ ቋንቋ እና ስነ-ጽሁፍ እየሞተ ነው። ቋንቋ (ስነ-ጽሁፍ) የዕድገት ሁሉ መሰረት ነው፣ ስነ-ጽሁፍ በሞተበት ማህበረሰብ ሁሉ እድገት እና ስልጣኔም ሞቷል።
ዘ-ሃበሻም የአዲስ ሙዚቃ መውጣት “ሰበር ዜና” የመሆኑን እውቀት በየትኛው የጋዜጠኝነት ትምህርት እንዳገኘችው እግዜር ይወቅ። እንቶ ፈንቶውን ሁሉ “ሰበር ዜና” እያለ የሚያወጣው የፌስ ቡክ ጋዜጠኛና ታጋይ ሁሉ በዚህ አይነት ምን ይፈረድበታል? አሁን አሁን በ“ሰበር ዜናው” መብዛት ሳቢያ፣ “ሰበር ዜና” የሚል ሳይ ልቤ መደንገጡን አቁሟል።
 የአማርኛውን ነገር መተው ነው። “…ይዚት …” ስንቱን ነቅሼ እችላለሁ? የግድፈቱ ብዛት የ”ሽንፍላ …” ያህል ነው። ደሞስ የህወሃት “ድርድርን የማደናቀፍ…” ጉዳይ አዲስ ነው’ንዴ?፣ “አሳዛኝ” የሚያደርገውስ ምንድነው? … መቼም ጋዜጠኛ ተሁኖ ልብ ውልቅ ብሏል! ምናለ እንደ ብዙዎቹ እንዲሁ የተሰጣቸውን ብቻ ለጥፈው ቢያወጡ?… እነዚህ ጋዜጠኞች  ያልገባቸው ነገር ቢኖር፣ በሙያው ላይ ብቻ ሳይሆን በአገርም ላይ እያደረሱት ያለው ጉዳት… የእረኛውን እና የነብሩን አይነት ነው።
እረኛው አፋፍ ላይ ቆሞ “ነብር … ነብር መጣብኝ…” እያለ ሲጮህ የሰሙ መንደርተኞች እየተጠራሩ አንካሴና ጦራቸውን እየሰበቁ ካፋፉ ሲወጡ…”አይ ቀልዴን ነው” ይላቸዋል። “የልጅ ነገር..” ብለው ይመለሳሉ። እረኛው እንደገና በማግስቱ “ነብር መጣብኝ…” ሲል መንደርተኛው እንደገና ግልብጥ ብሎ እየተሯሯጠ ሲደርስ … “አይ ቀልዴን ነው…” ብሎ ይመልስላቸዋል። ለሶስተኛ ጊዜ እንደዚሁ “ነብር…” ሲል “አይ ልማዱ ነው! ተውት…” ብለው ዝም! ለካስ አያ ነብር የምር መጥቶ ኖሮ ልጁን አንጠልጥሎ ይዞ ጥርግ! የጋዜጠኝነትን ሙያ እየገደላችሁት ያላችሁት ይኼን ያህል ነው። ሙያን የመግደል፣ የሞራልም ወንጀል ነው።
አንድ ዜና “ሰበር ዜና” የሚሆነው የመደበኛውን ዜና ሂደት ለማቋረጥ የሚያደርስ ታላቅ እና አዲስ ክስተት ሲከሰት፣ እጅግ ጠቃሚ እና አንገብጋቢ መሆኑ በኢዲቶሪያል ቦርዱ ተመክሮበት መደበኛው ፕሮግራም ተቋርጦ የሚገባ ነው። የዘሃበሻ “ሰበር ዜና” ከመውጣቱ ከወራት በፊት ጀምሮ ዘፈኑ እንደሚለቀቅ ሲነገረን ነው የኖርነው፣ በራሱ በዘ-ሃበሻ እና በሌሎችም ሶሻል ሜዲያዎች አልበሙ ለገበያ እንደሚውል ሲነገረን ነው የከረምነው። ይሁን እንኳን ቢባል የቴዲ ዘፈን ሰበር ዜና ሊሆን የሚችለው በኢትዮጵያ ድምጻዊያን ታሪክ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በቢልቦርድ ላይ የመውጣቱ ጉዳይ ይመስለኛል። ቢልቦርድ ላይ የመውጣቱም ጉዳይ ቢሆን ከጀርባው የሚናገረው አያሌ ነገር አለ። መቼም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ህዝብ እንዲህ ለመቀናጣት የሚያስችል አቅም ኖሮት “አይቲዩን”ን አጣብቦ “ኦንላይን” ገብቶ በዶላር ለመግዛት አቅም ያለው አይመስለኝም። የገዛው ስደተኛው ነው። የተሰደደውንም ህዝብ ብዛት፣ በአገሩ መኖሪያ ያጣ ህልቆ መሳፍርት የሌለው ህዝብ መሆኑንም ይናገራል።
ሌላው በቴዲ ግጥሞች እና ዜማዎች ላይ ሲያከራክር የነበረው ባህላዊው የጎንደር ዜማው ነው። “የይርጋ ዱባለን ስራ ነው የደገመው…” “አይደለም…” አይነት ክርክሮች ያነበብሁ መሰለኝ። ዜማው የይርጋ ዱባለም የቴዲ አፍሮም ሊሆን ይገባ አይመስለኝም። እንደ ስነ-ቃል ሁሉ የህዝብ ሃብት ነው። በተለይ የዜማው ባለቤት ህዝብ ነው።
ቴዲ አገሩን ይወዳል። እዚህ ላይ ማንሳት ባያስፈልግም ስለ ግል ቤተሰቡ እና ልጆቹ የሰማሁት በጣም ገርሞኛል። እውነትም አገሩን ይወዳል። ለሃገሩ ሲል ዋጋ ከፍሏል። ወደፊትም ሊያስከፍለው ይችላል። ቴዲ ሽልማቱ ይገባዋል። ግሩም ድምጻዊ ነው። ለኔ ከድምጻዊነቱ በላይ የሚጎላብኝ ግን ጥሩ የህዝብ ግንኙነት (“የፐብሊክ ሪሌሽንስ”) ሰብዕናው ነው! የት? እንዴት? ለማን? እና ምን? መናገር እንዳለበት የሚያውቅ ብልህ ሰው ነው (“ብልጥ” አላልሁም)። “ብልህ” ለሚለው አማርኛ በጣም የሚቀርበው እንግሊዝኛ “Smart/Intelligent” ይመስለኛል።
("ጎልጉል" ከተሰኘው የድረ ገጽ ጋዜጣ የተወሰደ)



Read 1763 times