Sunday, 23 January 2022 00:00

የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት ያላት አቋም መቼም ቢሆን አይለወጥም”

            ውድ አፍሪካዊ ወንድም እህቶቼ፡-
አፍሪካዊ ወንድማማችነታንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር በሚያስፈልገን በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ተስማምተው የኅብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ኢትዮጵያ- የአፍሪካዊነትን ጉዳይ እንደ መጀመሪያ አጀንዳዋ እንጂ እንደ ሁለተኛ አድርጋ ወስዳው እንደማታውቅ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ። ለአፍሪካ ነጻነት ያላት  አቋም አንድም ቀን ቀንሶ አያውቅም። ለፓን አፍሪካዊነት የምትሰጠው ቦታ ሁሌም ጉልህ ነው። ጥንትም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ “ኢትዮጵያ” ናት። በአፍካዊነት ላይ አትወላውልም። ይሄን የኢትዮጵያን አቋም ቀደምት የአፍሪካ መሪዎች እንደተገነዘቡት ሁሉ፣ የዚህ ዘመን መሪዎችም በሚገባ ተገንዝበው አጋርነታቸወን በሚያሳይ መልኩ የኅብረቱን ጉባኤ በአካል እዚህ ለማከናወን ያሳለፉትን ውሳኔ ኢትዮጵያ ታደንቃለች።
ወንድማዊ አጋርነታችሁን በምንሻበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የኮሮናን መስፋፋትንና ወቅታዊውን የጸጥታ ሁኔታ እንደ ምክንያት በማንሳት፣ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ አካላት ተግባራቸው ኢትዮጵያን አሳዝኖ ነበር።
በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚደረጉት የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤያት መካከል በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የመጀመሪያው ጉባኤ ከሶስት ዓመት በኋላ ዳግም በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራትና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ጋር በመሆን መንግስት ልዩ ልዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ጉባኤው እዚህ መካሄዱ የሚኖረውን ትርጉም የተገነዘቡና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም፣ ለአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እና የአፍሪካ ጉዳዮች በአፍሪካውያን እንዲታዩ ያላትን የጸና መርሕ ከፍ ያለ ዋጋ የሰጡ የአፍሪካ መሪዎች፤ ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱን መርጠዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ደስ ተሰኝታለች፤ እንኳን ደስ ያለን።
ውድ የሀገሬ ልጆች፤
በችግራችንም ሆነ በደስታችንም ጊዜ ቀድመው ከጎናችን የሚቆሙት አፍሪካዊ ወንድሞቻችን እንደሆኑ ይታወቃል፡፤ የምንጋራቸው ማንነቶች፣ የሚያስተሳስሩን ታሪኮች፣ የሚያመሳስሉን የጋራ ችግሮች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ኢትዮጵያ ለእነሱ ሁለተኛ ቤታቸው ናት። ሰው ወደ ቤቱ ሲመጣ እንደ ቤተኛ እንጂ እንደ ባዳ አይስተናገድም። እናም እጃችንንና ልባችንን ከፍተን ልንቀበላቸው፣ ለትዝታ የሚተርፍ ቆይታ እንዲኖራቸው አድርገን ልናስተናግዳቸው፣ በሰላም እንደመጡ በሰላምና በሐሴት አቆይተን  ልንሸኛቸው ይገባል።
አሁን ጉባኤውን ለማከናወን የቀረን ሁለት ሳምንት ብቻ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገን ጉባኤውን ማሳካት አለብን። የጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄድ ትርጉሙ ብዙ ነው። ሰላማችንና ደህንነታችንን የምናስመሰክርበት፣ ለአፍሪካ ጉዳዮች ያለንን አቋም በድጋሚ የምናስመሰክርበት፤ የኢትዮጵያን መልካም ሁኔታ ለአፍሪካውያን ወገኖቻችን በተግባር የምናሳይበት፤ ከዚያም አልፎ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የምናገኝበት ጉባኤ ነው። እናም ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ከሁላችንም ብዙ ይጠበቃል።
የጸጥታ አካላት፣ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች፣ እንዲሁም የመዝናኛና ቱሪዝም ስፍራዎች ከእናንተ ብርቱ ዝግጅት ይጠበቃል። የሚመጡትን እህትና ወንድሞቻችንን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተቀብለን፣ ምቾትና ደህንነታቸውን ጠብቀን ማስተናገድ አለብን። በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርና ህዝብ- ለአካባቢ ጽዳትና ጸጥታ ትኩረት ሰጥተው ከዛሬ ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ አደራ እላለሁ።
ታላቁ የነጻነት ታጋይና የይቅርታ አባት የሆኑት የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ስለ ሀገራችን ሲናገሩ “ኢትዮጵያ በምናቤ ውስጥ ሁሌም ልዩ ስፍራ አላት” ያሰኛቸው፣ ኢትዮጵያ ቅንነት በተሞላ ፊቷ ተቀብላ ስላስተናገደቻቸው እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም። ይህንን ሊናገሩ የቻሉት፣ የሀገራችንን ፍቅር ያልተለየው እቅፏን በማግኘታቸው ነው።
እናም ማንዴላን ባከበርንበት ልክ አሁንም የኅብረቱ አባላትን አክብረን እንድናስተናግዳቸው፣ በኩራት የምንጠቅሰው ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነትን ከነሙሉ ክብሩ ዳግም እንድንገለጥ አደራ እላለሁ።
ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆነው በሁሉም መስኮች አሸናፊ ከሆነች ነው። ከእነዚህ አንዱ ደግሞ ለአፍሪካ የገባነውን ቃል ጠብቀንና አጽንተን መቀጠላችን ነው። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት ያላት አቋም መቼም ቢሆን አይለወጥም። የገባችውን ቃልም በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ ሆና ማክበሯን ትቀጥላለች። ይሄንን አቋሟን ስለተገነዘቡ አፍሪካውያን ወገኖቻችንን በድጋሚ አመሰግናለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጥር 8 ቀን 2014 ዓ.ም



Read 931 times