Sunday, 23 January 2022 00:00

የካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር “ሀገር በቀል ዕፅዋት”

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ ሬዲዮ በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ ይቀርቡ ከነበሩ ዝግጅቶች በጣም ተደማጭ ከነበሩት ውስጥ አንዱ የእሑድ ጠዋት ፕሮግራም ነው፡፡ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር ደግሞ በዚህ ፕሮግራም ላይ  ዝግጅታቸውን ከሚያቀርቡ ተሳታፊዎች አንዱ ነበር። ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 25 ዓመታት በዚሁ የእሑድ ሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ተሳትፏል፡፡ ሽልማትም አግኝቶበታል። በሬዲዮ ብቻ ሳይወሰንም በአዲስ ዘመን፣ በሠርቶአደር፣ በዘኢትዮጵያን ሔራልድ፣ በዛሬይቱ ኢትየጵያ፣  በአፍሪካ ቀንድ፣ በኔሽን እና በሌሎች ጋዜጦችና መጽሔቶች በአምደኝነት ጽፏል፡፡ ከነዚሁ ሥራዎች በተጨማሪ ኅብረ ብዕር በሚል ርእስ በሦስት ቅጽ፣ #ምንኩስና በኢትዮጵያ ዛሬ እና ትናንት;፣ #ብጹአን እነማን ናቸው፣ ባሕል እና ክርስትያናዊ ትውፊት;፣ #ምስጢረ ፊደል ወትርጓሜ; የሚሉ መጻሕፍትም ለአንባብያን አበርክቷል፡፡ ከነዚህ መጻሕፍት አንዳንዱ በሺዎች የሚቆጠሩ አንባብያን እንዳፈሩለት ሁሉ በአንጻሩ  ለምን እንደዚህ ጻፍክ፣ ስለኛ እንዴት ትጽፋለህ፣  በሚል ጠላት ያፈራባቸውም ሆነዋል፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ካሕሳይ ገብረእግዚአብሔር ከዚህ ሁሉ በፊት በሰርቲፊኬት ከሐረር መምህራን ማሰልጠኛ፣ በዲፕሎማ ደግሞ ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ተመርቆ ትግራይ ውስጥ ለአንድ ዓመት ካስተማረ በኋላ ለሦስት ዓመታት ኢህአፓን በመቀላቀል በተዋጊነትና በሐኪምነት አገልግሏል፡፡ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ግን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን በምክትል መምርያ ኃላፊ ደረጃ የዜና ቤተ ክርስትያን ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ እንዲሁም የህዝብ ግንኙነት መምርያ ምክትል ኃላፊ  ሆኖ ሩብ ክፍለ ዘመን አገልግሏል፡፡
ካሕሳይ በርካታ የሥራ ጊዜውን በሥራ ያሳለፈባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ለሀገሪቱ በታሪክ፣ በትውፊት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በህክምና፣ በቋንቋና በሌሎችም ዐውዶች ታላላቅ አስተዋጽዖዎችን አበርክታለች፡፡ እነዚህን አስተዋጽዎች እንደ ፈጠራ ጽሑፍም ሆነ ኢ-ልቦለድ ከጻፉ ጸሐፍት መካከል ዶክተር አለማየሁ ዋሴ እሸቴ “እመጓ”፣ “ዝጎራ”፣ “መርበብት” እና “ሰበዝ” የተባሉ መጻሕፍትን አበርክተዋል፡፡
አሁን በሕይወት የሌለው ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔርም በሕይወት እያለ ካሳተማቸው በቤተ ክርስትያኒቱ ዙርያ ከሚያጠነጥኑ ሁለገብ ሥራዎቹ በተጨማሪ ያልታተሙ ሥራዎችንም ትቶልን አልፏል። ከነዚሁ ሥራዎች መካከል ባለቤቱ ወይዘሮ ጤናዬ ተስፋዬና ሴቶች ልጆቹ ነጻነት እና ስዬ ካሕሳይ ባለፈው ወር “ሀገር በቀል ዕፅዋት” በሚል ርእስ ባለ 207 ገጽ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ በ180 ብርም ለገበያ ቀርቧል። መጽሐፉ የተዘጋጀው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን እምነት፣ ከባህልና ከአየር ንብረት ለውጥ አንጻር ነው። መጽሐፉን ለማዘጋጀት አቶ ካሕሳይ ለ18 ዓመታት ጥናት አድርጓል፡፡
በአምስት ትልልቅ ምዕራፎች የተከፈለው ሀገር በቀል ዕፅዋት፤ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ሥር እያንዳንዳቸው ሰፋፊ አርእስት /ምዕራፎች/ በሚሆኑ በርካታ አርእስትም የበለጸገ ነው፡፡ ምዕራፍ አንድ ዕፅዋት እና ኢትዮጵያውያን፣ ምዕራፍ ሁለት ዕፅዋት በቅዱስ መጽሐፍ፣ ምዕራፍ ሦስት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ዕፅዋትን የምትንከባከበው ለምንድነው፣ ምዕራፍ ዐራት የሀገር በቀል ዕፅዋት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በመንፈሳዊና ማኅበራዊ ገጽታ እንዲሁም ምዕራፍ አምስት ዕፅዋት እና የአየር ንብረት ለውጥ በሚሉ ቁም ነገሮች ዙርያ ያጠነጥናሉ፡፡ ምዕራፎቹ በዝርው ጽሑፍ እና በግጥም እንዲሁም አልፎ አልፎ በአነስተኛ ፎቶግራፎች የተደገፉ ናቸው፡፡
በምዕራፍ አንድ ውስጥ ከተጠቀሱት አስገራሚ ቁምነገሮች መካከል የዛፎችን እድሜና ክብደትን የሚመለከተው ይገኝበታል፡፡ እንደ አዲሱ የካሕሳይ መጽሐፍ፤ አንዳንድ የዛፍ አይነቶች ከዐራት ሺህ ዓመታት በላይ እንደሚቆዩ በጥናት ተረጋግጧል፡፡
…ዕድሜአቸውን በትክክል ማወቅ ባይቻልም በሀገራችን ተመሳሳይና ከዛም በላይ ዕድሜ ያላቸው ዛፎች እንደሚኖሩ መገመት ይቻላል፡፡ ለአብነት አንድ ሁለት አንጋፋ ዛፎችን ላንሳ፡፡ መላዕክት ቅዱስ ያሬድን በሦስት አዕዋፍ ተመስለው (በአሮድዮን እና ዛሚር) ሰማያዊ ዜማን ያስተማሩት ዛሬ ድረስ “ሙራደ ቃል” እየተባለ በሚጠራው ዋርካ ሥር እንዳለ ነበር፡፡ (ፆመ ድጓ መግቢያ)
ስለ ክብደታቸው እና ቁመታቸው በጠቀሰበት አንቀጽም፤ በካሊፎርንያ የሚገኝ አንድ ዛፍ ከስድስት ግዙፍ አሳ ነባሪዎች በላይ እንደሚመዝንና የአንድ አሳ ነባሪ ክብደት የ2500 ሰዎች ክብደት እንደሚሆን ገልጧል፡፡ ስለዚህ አንድ ዛፍ 15 ሺህ ኪሎግራም ይከብዳል እንደማለት ነው፡፡ እንዲሁም አንድ  የአውስትራሊያ ባሕር ዛፍ ከ300 ጫማ በላይ ቁመት እንዳለው በዚሁ መጽሐፍ ካሕሳይ ጠቅሶታል፡፡
ይህን መጽሐፍ ሳነብ ዕፅዋት አጠገባችን ቢኖሩም ብዙም እንደማናውቃቸው አስገንዝቦኛል፡፡ ይህንኑ እውነታ የሚያጠናክሩልኝን  አንዳንድ መረጃዎች ከመጽሐፉ ልጥቀስና  ዳሰሳዬን ላጠቃልል፡፡
ዛፍ መንከባከብ እና ኢትዮጵያዊት ቤተ ክርስትያን( ገጽ 45)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ዕጽዋትን/ ተፈጥሮን በመንከባከብ በኩል የዕድሜዋን ያህል ረዥም ታሪክ ያላት ቤተ ክርስትያን ናት፡፡ የቤተ ክርስትያኗ ታሪክ ከቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ እና ትምህርት በእጅጉ የተገናኘ ነው፡፡ ይህም ማለት ቤተ ክርስትያኗ ዕጽዋትን በመንከባብ በኩል ከዘመነ አበው እና ከዘመነ ዖሪት ጀምሮ ያካበተችው ልምድ እና ዕውቀት በክርስትና ዘመን እንደ መሠረት ሆኗታል፡፡ ይህ ጠንካራ መሠረት ኢትዮጵያውያንን ከጅምሩ አንሥቶ ዕፅዋትን በተመለከተ ከወጡ ሕግጋተ እግዚአብሔር እንዲተዋወቁ ረድቷቸዋል፡፡
ዛፍ ቦርቦሮ ኑሮ
በ”ሀገር በቀል ዕፅዋት” ከተጠቀሱ ቁምነገሮች አንዱ ዛፍን በመቦርቦር ውስጡን ለመናንያን እንደ መኖርያ፣ ሲሞቱም እንደ መቀበርያ ማገልገላቸው ነው፡፡ መናንያኑ ሲሞቱ ክፍተቱ እየጠበበ እየጠበበ በመምጣት መግጠሙን እና ይህን አይነት ዛፎች ዋልድባ ገዳም አካባቢ እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡ (ገጽ 51-52)
ዛፎች ይረዳዳሉ
ዛፎች እርስ በርሳቸው ይነጋገራሉ፣ ይረዳዳሉ፣ መልዕክት ይለዋወጣሉ፡፡
ለምሳሌ በአንድ አካባቢ የተወሰኑ ዛፎች አሉ እንበል፤ እንደ አጋጣሚ አንድ ውሃ ካለበት አካባቢ የበቀለ ሆኖ ሌላኛው ግን ከዚሁ ራቅ ብሎ ይገኛል፡፡ ይህ ሁለተኛ ዛፍ ከአጠገቡ ውሃ ባይኖርም የበቀለበት ቦታ ለም አፈር ያለበት ነው፡፡ ሌላ ሦስተኛ ዛፍ ደግሞ ከነዚህ ሁለት ዛፎች ራቅ ብሎ በቂ አፈር እና ውሃ ባለበት የበቀለ ሆኖ ነገር ግን በቂ የፀሐይ ብርሃን በማይገኝበት ቦታ የሚገኝ ነው፡፡ እንዲህ በሚሆንበት አጋጣሚ ዛፎቹ በመሬት ውስጥ እርስ በርሳቸው የሚያገናኝ ድልድይ ይፈጥራሉ…አንዱ ዛፍ ያለውን ለሌለው በመስጠት ፍላጎታቸውን ያሟላሉ፡፡ (ገጽ 18-19)
ወንድ ቴምር እና ሴቷ
ዘንባባ (ሰሌን) ወንዴው ሲሆን ሴቴዋ ተምር ናት፡፡ ዘንባባ ፍሬ የሚያፈራ ቢሆንም ለመብል አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል ዘምባባ የወይናደጋ ተክል ሲሆን ተምር የቆላ (በረሐ) ተክል ነው፡፡
የካሕሳይ ሀገር በቀል ዕፅዋት መጽሐፍ በርካታ መረጃ ሰጪ ሳይንሳዊ፣ ታሪካዊ፣ ትውፊታዊና ሐይማኖታዊ መረጃዎችን የያዘ ነው፡፡ ሁሉንም በዚህ ጋዜጣ ላይ መዳሰስ አይቻልም፡፡ ገዝታችሁ ማንበብ ግን ትችላላችሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1059 times