Saturday, 22 September 2012 12:47

..እርግዝና እና የክብደት መጠን.....

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

..እርግዝና እና የክብደት መጠን.....

ሰዎች እርግዝናን እንደ አስቸጋሪነት የሚቆጥሩት ምናልባት ውፍረት ከመጠን በላይ ሲሆን ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የአንዲት ሴት የክብደት መጠን ከቁመትዋ ጋር ተዛምዶ በሚሰላው ስሌት ከመጠን በታች ከሆነም በእርግዝና ወቅት ሌላው አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ለዚህ እትም ማብራሪያቸውን የሰጡን ዶ/ር እስክንድር ከበደ ናቸው፡፡ ዶ/ር እስክንድር የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና ረዳት ፕሮፌሰር በጥቁር አንበሳ ሆስፒታልም የጽንስና ማህጸን ሕክምና ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡

ኢሶግ: በቅድሚያ ውፍረትና ቅጥነት ሲባል በምን አይነት መንገድ የሚለካ ነው?

ዶ/ር: አንድ ሰው ክብደቱ የሚለካው ከቁመቱ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ለምሳሌ አጭር የሆነ  ክብደቱ ትንሽ እንዲሁም ረጅም የሆነ ሰው ክብደቱ ብዙ ይሆናል፡፡ይህንን የምንለካበትልህ በእንግሊዝኛው ቄሳቨ ቂሮቋቋ ሽቃሳስቦ የሚባል የመለኪያ ዘዴ አለ፡፡ ክብደት ሲፈካል ...ለቁመት ተደርጎ የሚሰጠን ቁጥርልህ ይባላል፡፡ በአጠቃላይም በዚህ ስሌት መሰረት አንድ ሰው ትክክለኛ ክብደት መጠን ላይ ነው የሚባለው ተካፍሎ የሚገኘው ውጤት ከ18.5 እስከ 24.9 ሲሆን ነው፡፡

አንድ ሰው ከ18.5 በታች ከሆነ የክብደት ማነስ አለበት የሚባል ሲሆን ከ24.9 በላይ ሲሆን የክብደት መጠኑ ከፍተኛ ወይንም ወፍራም ነው ማለት ነው፡፡ የአንድ ሰው የክብደት ስሌት በልህ ከ30 በላይ ከሆነ እጅግ በጣም ወፍራም እንደሆነ የሚነገርለትና በከፍተኛ ሁኔታ ጥንቃቄን የሚሻ ነው፡፡ የክብደት ስሌታቸው ከትክክለኛው መጠን በታችም ሆነ ከዚያ በላይ ...በተቻለ መጠን ወደትክክለኛው የውፍረት ልክ እንዲመጡ ይመከራል፡፡ ለማንኛውም አንድ ሰው ያለው የክብደት መጠን ከቁመቱ ጋር ተመጣጥኖ በልህ ካልተሰላ በስተቀር እንደዚሁ የክብደቱን ኪሎ ግራም ቢናገር ወፍራም ነው ወይንም ቀጭን ነው ማለት አይቻልም፡፡

ኢሶግ: አንዲት ሴት ከማርገዝዋ በፊት ሊኖራት የሚገባት ትክክለኛ ክብደት ምን ያህል ነው?

ዶ/ር: ይህ ጥያቄ በጣም ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሴቶች በሚያረግዙበት ግዜ ይህንን ቢያስቡ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለማስወገድ አይቸገሩምና ነው፡፡ አንዲት ሴት ከማርገዝዋ በፊት ሊኖራት የሚገባው የክብደት መጠን ቀደም ብዬ  እንዳስረዳሁት ያላት የክብደት መጠንና የቁመት ርዝመት በ ቢኤም አይ ስሌት መሰረት ተሰልቶ ከ18.5 እስከ 24.9 ባለው ቁጥር ከሆነ ክብደትዋ ትክክለኛ ነው ይሰኛል፡፡ስለዚህም በትክክለኛው መንገድ የእርግዝናዋን ጊዜ ጨርሳ ልጅዋን በሰላም ለመውለድ ትችላለች ማለት ነው፡፡

ኢሶግ: አንዲት ሴት ክብደትዋ በጣም ዝቅተኛ ቢሆን በእርግዝና ወቅት ምን ይገጥማታል?

ዶ/ር: አንዲት ሴት እርግዝናዋን ከመጀመርዋ በፊት ክብደትዋ ዝቅተኛ ከሆነ በእርግዝናዋ ወቅት ከተገቢው ክብደት ላይ መድረስ ስለማትችል በምትወልደው ልጅ ላይ ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡ እነዚህም ችግሮች ለምሳሌ...ያለጊዜው ወይንም ከቀኑ በፊት መወለድ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቆ ካልተወለደ ልጁ ሆድ ውስጥ ከመሞት ጀምሮ ከተወለደም በሁዋላ ሕይወቱን ሊያጣ የሚችልበት አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል፡፡ ሁለተኛው ችግር ደግሞ ክብደቱ በጣም ያነሰ ልጅ ሊወለድ ይችላል፡፡ በእንደዚህ ያለው ሁኔታ ክብደታቸው የሚያንስ ልጆች ከሌሎች በትክክለኛው የክብደት መጠን ካሉ ሴቶች የተረገዙና ክብደታቸው አንሶ ከሚወለዱ ልጆች ጋር ሲነጻጸር ከሁለት እጥፍ በላይ በሆነ መልክ አንሶ የሚገኝ ሲሆን ይህም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታን ያስከትላል፡፡ ስለዚህ ሴቶች ክብደታቸው ከትክክለኛው መጠን በታች ከሆነ ከማርገዛቸው በፊት ቢያውቁትና ማስተካከል ቢሞክሩ ጠቃሚ ነው፡፡

ኢሶግ: አንዲት ሴት ክብደትዋ ከፍተኛ ከሆነ በእርግዝና ጊዜ ሊከሰት የሚችለው ችግር ምንድነው?

ዶ/ር: ክብደትዋ ከፍ ያለች ሴት ማለት በስሌቱ መሰረት ከ24.9ኪሎ በላይ ከሆነች ወይንም ደግሞ ከ30ኪሎ በላይ የሆነች ሴት ማለት ነች፡፡ ይሀች ሴት ክብደትዋን ሳታስተካክል ወደ እርግዝናው ብታመራ ሊያጋጥምዋት የሚችሉ የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ እንደስኩዋር በሽታ ወይ ንም ደግሞ የደም ግፊት እና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች በእርግዝናው ወቅት ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሚረገዘው ልጅም ክብደቱ ከሌላው ልጅ ጋር ሲተያይ ከፍተኛ የመሆን ማለትም ክብደቱ ከ4ኪሎ ግራም በላይ የሆነ ልታረግዝ እና በምትወልድበት ጊዜም ረጅም ጊዜን የሚጠይቅ ወይንም ከባድ የሆነ ምጥ ሊገጥማት ስለሚችል በወሊድ ጊዜም ሁኔታው በቀላሉ በተፈጥሮአዊ መንገድ የማይስተናገድ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ክብደታቸው ከፍተኛ የሆኑ ሴቶች በአርግዝና ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ የሚጨምሩት ክብደት ከሌላዋ ሴት ጋር ሲነጻጸር ከወለዱ በሁዋላ ወደ ትክክለኛው ክብደት ለመመለስ የሚፈጅባቸው ጊዜ በጣም ብዙና አድካሚ ይሆናል፡፡ በእርግዝናው በመጀመሪያ አከባቢ አስከ 20 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ክብደት የጨመረች ሴት ከወለደች በሁዋላ ያንን ክብደት ይዛ የመቅረቱ ሁኔታ ሰፊ እድል አለው፡፡

ኢሶግ: በእርግዝና ወቅት የሚጨመር ክብደት አለ ሲባል የእርግዝናውን አካል ጨምሮ ነው?ወይንስ?

ዶ/ር: በአርግዝና ወቅት የሚኖረውን የክብደት አጨማመር በወራት ከፋፍለን ልናየው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ሶስት ወር ላይ ክብደት አጨማመሩ ትንሽ ሲሆን በቀጣዮቹ ማለትም በስድስትና በዘጠኝ ወራት ጊዜ የሚጨምረው ክብደት ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡ በመጀመሪያው ሶስት ወር ውስጥ ወደ ሁለት ኪሎ አካባቢ ይጨምራል፡፡ በአማካይ አንዲት ሴት ትክክለኛ ክብደት አጨማመር አላት የምንለው በሳምንት ከአራት ኪሎ ግራም አስከ አምስት ኪሎ ግራም የሆነ ክብደት አጨማመር ሲኖራት ነው ፡፡ስለዚህ ከአራተኛው ወር ጀምሮ አስከ  ዘጠነኛ ወር ድረስ በየሳምንቱ ወደ አራት መቶ ግራም አከባቢ እየጨመረች እስክትወልድ ባለው ጊዜ ከ11-16 ኪሎ ግራም ክብደት ልትጨምር ትችላለች፡፡

ኢሶግ: አንዲት እርጉዝ ሴት ይህንን ያህል ኪሎ ልትጨምር ትችላለች ሲባል ምክንያቱ እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

ዶ/ር: እርጉዝዋ ሴት እስክትወልድ ባለው ጊዜ ከ11-16 ኪሎ ግራም ልትጨምር ትችላለች ሲባል ሊገለጽ የሚችለው በሚከተለው መንገድ ነው፡፡ የተረገዘው ልጅ ከ3-4 ኪሎ ግራም ሊከብድ ይችላል፡፡ ልጁን የሚሸከመው የማህጸን ክፍል  1/ኪሎ ይመዝናል፡፡ እንግዴ ልጁ አስከ 700/ግራም አከባቢ ይመዘናል ልጁ የሚዋኝበት የሽንት ውሃ ወደ 1/ኪሎ አከባቢ ይመዝናል፡፡ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ እናትየው በምታረግዝበት ወቅት በተፈጥሮ የደም መጠንዋ ስለሚጨምር አሱም ወደ 1.5/ ኪሎ ግራም አከባቢ ይሆናል፡፡ እንዲሁም ሰውነትዋ የሚይዘው ውሀ ወደ 1/ኪሎ ግራም የሚደርስ ሲሆን ጡትዋ ጡት ለማጥባት በሚያደርገው ዝግጅት ወደ 1/ኪሎ ግራም ይመዝናል፡፡ ባረገዘችው ሴት የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚጠራቀመው የስብ መጠን ወደ 3/ኪሎ ግራም የሚደርስ ሲሆን ይህ በአንድ ላይ ሲደመር ምንም እንኩዋን እንደሴቶቹ ሁኔታ የሚለያይ ቢሆንም ከ11-16 ኪሎ ግራም የሚደርስ ክብደት ይጨመራል፡፡ አንዲት እርጉዝ ሴት ከተጠቀሱት ምክንያቶች እና ልትጨምር ከሚገባት ክብደት መጠን ውጪ ኪሎ የምትጨምር ከሆነ በሰውነትዋ ውስጥ ብዙ ስብ አጠራቅማለች ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ አንዲት ሴት ከወለደች በሁዋላ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ

1/የደም መፍሰስ ይኖራል ፡፡

2/የደም መጠን የሚጨምረው ውሃው ስለሆነ በሽንት መልክ አየወጣ ከወለደች በስድስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሁሉም ነገር ወደ ቦታው ይመለሳል ፡፡

በሰውነትዋ የሚቀረው ያጠራቀመችው ስብ ብቻ ነው አሱም በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ወይም እንደ ሴትየዋ አንቅስቃሴ ወይንም እንደ ሴትየዋ አበላል በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ወደ ነበረበት ሊመለስ ወይም ላይመለስም ይችላል፡፡ይህንን የሚወስነው የሴትየዋ እርምጃ ነው፡፡

ኢሶግ: በእርግዝና ወቅት ክብደትን ለመቀነስ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይቻላልን?

ዶ/ር: አንዲት ሴት ክብደትዋ በጣም ከፍተኛ ከሆነ ክብደት መቀነስ ያለባት ካረገዘች በሁዋላ ሳይሆን ከማርገዝዋ በፊት ነው ፡፡ በእርግዝና ወቅት የክብደት መቀነሻ ፕሮግራም መያዝ አይቻልም፡፡ በዚያ ጊዜ ክብደት ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶች የሚያስከትሉት አሉታዊ ውጤቶች በልጁ ላይ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል ሴትየዋ ክብደት መቀነስ ካለባት ከማርገዝዋ በፊት መሆን ይገባዋል፡፡ በእርግዝና ወቅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ተገቢ ቢሆንም በባለሙያ እገዛ ሰውነትን ለማፍታታት እንጂ ክብደትን ለመቀነስ የሚያስችል አይደለም፡ ስለዚህ ማንኛዋም ሴት ከክብደት በታችም ሆነች ከክብደት በላይ እርግዝና ከመጀመርዋ በፊት ኪሎዋን ማስተካከል ይጠበቅባታል፡፡

ይቀጥላል

 

 

 

Read 2531 times Last modified on Saturday, 22 September 2012 12:50