Wednesday, 26 January 2022 00:00

በሊቢያ ከ12 ሺህ በላይ ስደተኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በ30 አመታት ውስጥ ከአለማችን ህዝብ ሩቡ አፍሪካዊ ይሆናል ተባለ

             በሊቢያ ከ12 ሺህ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ አገራት ስደተኞች በ27 እስር ቤቶች ውስጥ አስከፊ ህይወት እየገፉ እንደሚገኙ ተመድ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
እስረኞቹ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በሚገኙ የመንግስትና የታጣቂዎች እስር ቤቶች የድብደባና የጥቃት ድርጊቶች እየተፈጸሙባቸው እንደሚገኙ የገለጹት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ፣ በስውር እስር ቤቶችና ህገወጥ ማጎሪያዎች ውስጥ ተጨማሪ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በታጣቂዎች ታግተው ግፍ እየተፈጸመባቸው ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡
በተለይ ሴት እስረኞች የከፋ ጾታዊ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው የተናገሩት ጉቴሬስ፣ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በስደተኞች ላይ አስከፊ ጥቃቶችን እየፈጸሙ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
እስካለፈው ወር ድረስ በሊቢያ የሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ አገራት ለመሻገር ሲሞክሩ በድንበር ጠባቂዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ስደተኞች ቁጥር ወደ 40 ሺህ እንደሚደርስ የተነገረ ሲሆን፣ አብዛኞቹም ወደ አገራቸው ሳይመለሱ በእስር ቤቶች ውስጥ የከፋ ኑሮን በመግፋት ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የአፍሪካ የህዝብ ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝና እ.ኤ.አ እስከ 2050 ከአለማችን አጠቃላይ ህዝብ ሩብ ያህሉ በአፍሪካ ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙት 54 አገራት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የህዝብ ቁጥራቸው እስከ 2050 ድረስ በእጥፍ ያህል ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ በአፍሪካ እስከ ተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ተጨማሪ 1.2 ቢሊዮን ህጻናት ይወለዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል፡፡
በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2022 የአለማችን ህዝብ ቁጥር ከ8 ቢሊዮን ያልፋል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ዘገባው፣ ይህ ቁጥር እስከ 2050 ወደ 9.5 ቢሊዮን ከፍ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅና ከዚህ ውስጥም 25 በመቶ ያህሉ በአፍሪካ ውስጥ ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ መነገሩን አብራርቷል፡፡

Read 1055 times