Tuesday, 25 January 2022 10:21

ከአውሎነፋስ ጋር መደነስ...

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

  በ1954 እ.ኤ.አ ከተጻፈው ከኦስትሪያ ቬና ተነስቶ የሳውዲ በረሃዎችን ለስድስት ዓመታት የበረበረው በኋላ ሕይወቱ እስክታልፍ ሐይማኖቱን ወደ እስልምና እምነት ቀይሮ ሙስሊም ሆኖ የኖረው የመሐመድ አሳድ የሕይወት ልምድና የጉዞ ማስታወሻ እጅግ አስደናቂ መጽሐፍ ‹‹The Road to Mecca›› ውስጥ ጥቂት ገጾች ለቅምሻ እነሆ...
ጥም
- አንድ -
 ***
ሁለት ሰዎች በሁለት የበረሃ ግመሎች ላይ ተቀምጠን ፈጣን ግልቢያ ላይ ነን... ፀሐይዋ በአናታችን ላይ የእሳት ነበልባሏን ለቃዋለች፡፡  ሁሉም ነገር በሚያብረቀርቅ፣ የሚያጥበረብር የብርሃን ንኝት ተሞልቷል፡፡ የተቅላላ፣ ብርቱካናማነትን የተላበሰ የአሸዋ ክምር ንብርብር... ከአሸዋው ክምር ባሻገር፣ ከአሸዋው ክምር ጀርባ፣ ንጡልነት ብቻነት፣ የሚፋጅ አርምሞ ብቻ...
ሁለት ግለሰቦች በሁለት ግመሎች ጀርባ ላይ... በግመሎቹ የሚንገላወድ እርምጃ ምክንያት ድባቴ የሚጥልብዎት በዚህም ሰበብ ቀኑን፣ ፀሐይዋን፣ ነዲዱን ነፋስና ረጂሙን ጉዞ የሚያስረሳዎት ዓይነት ግስጋሴ፡፡
እጅግ አልፎ አልፎ በአሸዋው ክምር አናት ላይ ጉች ጉች ያሉ የበረሃ ሳሮች፣ ጠመዝማዛ የተንጨፈረሩ የበረሃ ቁጥቋጦዎች፣ በአሸዋው ቁልል ላይ ሁሉ እንደ ዘንዶ የሚጥመለመል ጠሮ ይታያል፡፡ ስሜትዎ ተደብቷል። ኮርቻው ውስጥ ሆነው ይንገላጀጃሉ፡፡ የግመሎቹ እግር ከአሸዋው ጋር ከሚፈጥረው መንሿሿት እንዲሁም የኮርቻዎ የእርካብ ገመድ ከታጠፈ እግርዎ ጋር ከሚፈጥረው ፍትጊያ ውጪ ምንም የሚያስተውሉት ነገር የለም፡፡ ራስዎን ከነፋስና ከአሸዋ ለመከላከል ባደረጉት ክንብንብ ፊትዎ ተሸፍኗል፡፡ እና ደግሞ ንጡልነትዎን እንደ ሆነ ግዑዝ ነገር የተሸከሙት ዓይነት ይሰማዎታል፡፡
ድንገት ግን በቀኝ በኩል፣ ልክ በቀኝ በኩል ... የታይማ የጉድጓድ ውኃ...  ለራሱ ለጥም ለጥማት ውኃን የሚቸር ጭለማማ የምንጭ ውኃ ...
‹‹...ከኑፉድ (በታይማ ከተማ አጠገብ የሚገኝ በሳውዲ አረቢያ ትልቁ ሦስት ሺህ ዘመናትን ያስቆጠረ ጥንታዊ የጉድጓድ ውኃ)  በቀኝ በኩል በቀጥታ ወደ ታይማ...›› ድምጽ ሰማሁ፡፡ ግን ደግሞ ውልብታ ነገር ይሁን የጉዞ ጓዴ ማወቅ አልቻልኩም፡፡
‹‹የሆነ ነገር አልክ እንዴ ዛይድ?››
‹‹አልኩ እንጂ...›› አብሮኝ የሚጓዘው ሰው መለሰ፡፡
‹‹የታይማን የጉድጓድ ውኃ ለማየት በኑፉድ በኩል ማቋረጥ ብዙ ሰዎች የማይደፍሩት ጉዞ ነው ነበር ያልኩት››
***
እኔ እና ዛይድ በንጉስ ኢብን ሳውድ ጥያቄ ከተጓዝኩበት ናጂድ የኢራቅ አዋሳኝ ግዛት እየተመለስን ነበር፡፡ በንጉሡ የተሰጠኝን ተልዕኮ በአግባቡ ከፈጸምኩ በኋላ በተረፈኝ ሰፊ ነጻ ጊዜ ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ከሁለት መቶ ማይል (322 ኪሎሜትሮች ያህል) በላይ የሚርቀውን ጥንታዊ የታይማ የበረሃ የምንጭ ውኃ ለመጎብኘት ፈለኩ። ለቴማ ምድር የብሉይ ኪዳኑ ኢሳያስ በትንቢቱ ‹‹በቴማን የምትኖሩ ሆይ ወደ ተጠሙት ሰዎች ውኃ አምጡ›› ብሎላታል። ታይማ በውኃዋ በረከት እና በምንጭዋ ጥልቀት በአረቢያ ምድር መሰል ያልነበራት፣ በቅድመ እስልምና ዘመን ዋነኛ የንግድ መነሃሪያና የአረብ የባህል ማዕከል የነበረች ሥፍራ ናት፡፡ ይህችን የምንጭ ውኃ ለማየት ከተመኘሁ ቆይቻለሁ፡፡
በጉዟችንም ዙሪያ ጥምጥሙን የጥንታዊያን ነጋዴዎች መንገድ ችላ ብለን ከቃስር አታይሚን ተነስተን በቀጥታ ተቅላልቶ  በመካከለኛው አረቢያ ተራራማ ግዛቶች እና በሶሪያ ሐሩራማ አካባቢዎች መካከል ወደተዘረጋው ፍጹማዊ ኃያል በረሀ ተንደረደርን፡፡ ወደዚህ ጠፍ በረሀ የሚያገባም ሆነ ለጉዞ አመልካች የሚሆን ምንም ጠቋሚ የእግር መንገድ የለም፡፡ ቁጡው ነፋስ የእንስሳትም ይሁን የሰዎችን የእግር ዳና እያነፈነፈ አሸዋ በማልበስ ማንኛውም እግር የጣለው መንገደኛ ለጉዞው የሚከተለው አንዳችስ እንኳ ምልክት እንዳያገኝ እያሳደደ ይደመስሳል፡፡ የነፋሱ ፋታየለሽ ውሽንፍርን የታከበለበት ግልቢያ እንኳን የእግር አሻራን የአሸዋማውን ግዛት ቅርጽ ሳይቀር በፍጥነት ይቀያይራል፡፡ ኮረብታ ይመስል የነበረው በድንገት ሸለቆ፣ ሸለቆው በቅጽበት ሜዳ ይሆናል፡፡ በነፋሱ ጥፊ የሚንሿሹ በድን የበረሃ ሳሮች ሳይቀር ለግመሎቹ ምላስ የእሬት ያህል መራራ ናቸው፡፡
ይሄን በረሃ ለበርካታ ጊዜያት ያህል ባቋርጠውም ቅሉ አቅጣጫ እንዳልስት ስለምሰጋ  ዘወትር ያለ ረዳት ብቻዬን መጓዝን አልሞክረውም፡፡ ስለሆነም ዛይድ ከጎኔ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡ ይህ ምድር ለዛይድ የትውልድ ቦታው እርሱ የተገኘባቸው የሻማር ጎሳዎች መኖሪያ ነው፡፡ ሻማሪያዊያን የታላቁን የኑፉድ በረሀ ደቡብና ምስራቃዊ ዳርቻ ታክከው ኑሮአቸውን ይገፋሉ፡፡ በክረምቱ ወቅት ውሽንፍርን የለበሰ ዝናብ በድንገት  የአሸዋውን ክምር ወደ አረጓዴ መስክነት ሲቀይረው ሻማራዊያን ለጥቂት ወራት ወደ በረሃው ግመሎቻቸውን ያሰማራሉ፡፡ ለዛይድ የበረሃው ቀለም፣ ቅጥ፣ ይትብሃል ከደሙ፣ ከልብ ምቱ ጋር ተዋህዷል፡፡
ዛይድ ምናልባትም ከማውቃቸው ወንዶች ሁሉ ቆንጆው ሳይሆን አይቀርም። ሰፋ ያለ ግንባር እና ሰልከክ ያለ ገላ፣ መካከለኛ ቁመትና ጠንካራ አጥንት ያለው ቀጭን ሆኖ እንደብረት የጠነከረ ሰው ነው። ጠባብ ፊቱ ላይ ወጣ ብለው ከሚታዩ ጠንካራ የፊት ገጽ አጥንቶቹ  እንዲሁም ጠባብ መግነጢሳዊ የሆኑ ከናፍሮቹ ጋር ሲታይ በአረቢያ በረሃ በሚኖሩ ህዝቦች ዘንድ ግርማና ተወዳጅነት የሚያላብስ ሞገስ እንደተሰጠው ያስታውቃል፡፡ ይህ ሰው የበዶይን (በአረብ የባህር ሰላጤ የሚኖሩ ጥንታዊ ዘላን ጎሳዎች) የአረብ ዘላን ጎሳዎችን አኗኗር ከናጂዲ የአረባዊያን የቀለጠ የከተማ ሕይወት አጣምሮ የተካነ ልዩ ሰው ነው፡፡ በአንድ በኩል ስሜት ላይ ጥገኛ መሆንን አስወግዶ የበዶይኖያዊያን ደመነፍሳዊ ስልነት(sureness of instinict) ተቀዳጅቷል፡፡ በሌላ በኩል ያልተወሳሰበ ገር የከተማ የአኗኗር ስልትንና የተግባር ዕውቀትን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
ይህ ሰው ልክ እንደኔ ሁሉ የለየለት ጀብደኛ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ሕይወቱ በገጠመኞችና አስደሳች ክስተቶች የተሞላች ናት፡፡ ገና በለጋነቱ ለታላቁ ጦርነት የቱርክ መንግስት ወደ ሲናይ ባህር ወሽመጥ ባዘመተው ሰራዊት ኢ-መደበኛ የግመል ጓድ አባል ሆኖ ዘምቷል፡፡ ከንጉሥ ሳውድ ሠራዊት ጋር የጎሳዎቹ የሻማራዊያን ደጀን ሆኖ ተፋልሟል፡፡ በፋርስ ባህረ ሰላጤ የህገወጥ መሳሪያ አዘዋዋሪ ሆኖ ሰርቷል፡፡ በአረቢያ ምድር ከበርካታ ሴቶች ጋር እፍፍፍ ያለ ፍቅር ይዞት ለቁጥር የሚያታክቱ ሴቶችን በህጋዊ መንገድ እያገባ ፈትቷል፡፡ በግብጽ ሀገር ፈረስ ነጋዴ ነበር፡፡ በኢራቅ የቅጥር ወታደር ሆኖ አገልግሏል፡፡ በመጨረሻ ደግሞ አምስት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የእኔ አጃቢ ሆኖ እየሰራ ይገኛል፡፡
ይሄው አሁን ደግሞ በ1932 እ.ኤ.አ የበጋ ሐሩር ወቅት አብረን እየጋለብን ነው። ልክ እንደዛሬው ሁሉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይሄን ጀብደኛ ጉዞ ስንከውን አሳልፈናል። ለብቻችን ንጡል ሆነን በአሸዋ ክምሮች መካከል ስንጓዝ ውለን በምናገኛቸው የትኞቹም የውኃ ጉድጓዶች አጠገብ እያረፍን፣ ሜዳ ላይ ከከዋክብት ጋር እየተኛን፣ ዘለዓለማዊ የሆነው የአራዊቱ የነዲድ አሸዋ ላይ ሸብረብ የጉዞ ዳና ድምጽ፣ አንዳንድ ጊዜ ምናልባትም በይበልጥ በዘመቻዎች ላይ ከግመሎቹ ሶምሶማ ጋር በተናበበ ሁኔታ የዛይድ እንጉርጉሮ፣ የበረሃ ውስጥ የአዳር ሰፈራችን ሁኔታ፣ ቡና ማፍላቱም ሆነ ሩዝ መቀቀሉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንግዳ የሆኑ ጨዋታዎቻችን (ግጥሚያዎቻችን)፣ በውድቅት ሌሊት ሜዳ ላይ ተዘርግተን የእኩለ ሌሊቱ ቁጡ ብርዳም ነፋስ አሸዋ ሲያለብሰን፣ እንደገና ማለዳ ሆኖ ፀሐይ በአሸዋ ክምሮቹ አናት እሳት፣ ነበልባል የመሰሉ ጨረሮቿን ስትፈነጥቅ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ልክ እንደዛሬው [እንደታይማ የምንጭ ውኃ] የዕድል መዳፍ በውኃ እርጥባን የዳሰሳት የፈካች ሕይወት ሐሩር መሀል ብቅ ስትል... [እነዚህ ሁሉ የዓመታት የጉዟችን ሽርፍራፊ ትውስታዎች ናቸው፡፡]
ለእኩለ ቀን ጸሎት ጉዟችንን ገታን። እጆቼን፣ ፊቴንና እግሮቼን በውኃ በማረጥብበት ጊዜ ጥቂት የውኃ ጠብታዎች ከእጆቼ አምልጠው በፀሐይዋ ቃጠሎ የጠወለገች፣ የገረጣች አሳዛኝ የሰርዶ የሳር ተክል ላይ አረፉ፡፡ የውኃ ጠብታዎች ቅጠሎቿ ላይ ባረፉ ቅጽበት ቅጠሎቿ ቀስ በቀስ እየተንቀጠቀጡ ለእርጥበቱ እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ አየሁ፡፡ ጥቂት ተጨማሪ የውኃ ጠብታዎች ሲደርሷት ሁሉም ቅጠሎቿ እያመነቱ፣ እየተንቀጠቀጡ ቀስ በቀስ ስትር ብለው ቆሙ፡፡
ትንፋሼን ሰብስቤ ተጨማሪ ውኃ በአናቷ ላይ አፈሰስኩባት፡፡ በድንገት የሆነ ስውር ረቂቅ ኃይል ከሞት አፋፍ የመለሳት፣ ከቅዠት ያነቃት ዓይነት ቁጡ ሆና በፍጥነት ተንቀሳቀሰች፡፡ በዚያች ቅጽበት የዚህችን ተክል ቅጠሎች ማየት እንዴት ያስደንቃል! ከቅዠት የባነነች ያህል፣ ቅልጥ ባለ ነውር የታከለበት ድግስ የታደመች ያህል፣ ተቅበጥብጣ የኮከብ ቅርጽ ያለው ዓሳ(Starfish) እግሮቹን እንደሚያንቀሳቅሰው ዓይነት የሳር ቅጠሎቿን በፍጥነት ሰብስባ ዘረጋች፡፡ ወዲያው ከሞት ወደ ሕይወት በአሸናፊነት ተመለሰች፡፡ ከቅጽበታት በፊት በሞት አፋፍ ላይ ተንጠልጥላ ስትቃትት የነበረችው ዕጽ በጉልህ ግርማ ወደ ሕይወት፣ ወደ ህልውና ዛቢያ ተመለሰች፡፡
የሕይወትን ዋጋ፣ ግርማና ሞገስ በቅጡ የሚገባህ በረሀ ውስጥ ነው፡፡ በበረሃ መካከል ሕይወትን ማስቀጠል ምንጊዜም ፈታኝ፣ አዳጋች፣ አንዳንዴ ዕድለኝነት የሚፈልግ ትግል ነው፡፡ እያንዳንዷ ሽርፍራፊ ሕይወት እሴት፣ ድብቅ ሀብት፣ ድንገቴ ክስተት ነች። ለምንም ያህል ዓመት ብታውቀው በረሃ ምንጊዜም የማይለመድ ዘወትር እንግዳ አስበርጋጊ ቦታ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በኦናነቱና በመገርጣቱ ውስጥ አገኘሁት ስትል በረሃው ከጥልቅ እንቅልፉ በድንገት ነቅቶ ትንፋሹን ያሰማራል፡፡ እናም በቀደመው ዕለት ምንም ያልነበረበት የአሸዋ ክምር ላይ በሚቀጥለው ቀን የገረጣ አረንጓዴ ሳር አካባቢውን አልብሶት ይገኛል፡፡ ወይም ደግሞ መነሻቸው ያልታወቁ ሞጋጋ፣ ረጃጅም ክንፎች፣ ነጣ ያለ አረንጓዴ ቀለም ያላቸው መንጋ ወፎች ድንገት በሰማዩ ላይ ሲርመሰመሱ ልታይ ትችላለህ፡፡ ከየት መጡ? ወዴት ይቀዝፋሉ? ማን ሊያውቀው ይችላል፡፡ አሊያም አሁንም በድንገት ከየት መጣ ያልተባለ እንደ አረመኔ፣ መደዴ ወራሪ፣ ዘራፊ፣ ጨካኝ ሠራዊት ስፍር ቁጥር የለሽ ሆኖ ከመሬት ከፍ ብሎ የሚተም የአንበጣ መንጋ ሊያጋጥምህ ይችላል...
ሕይወት እስከ ግርማ ሞገሷ፣ እስከ በማናለብኝነት የተዘረጋ ክፍት፣ ገበርባራ ገጽዋ፣ እስከ ዘለዓለማዊ አስበርጋጊነቷ፣ የትም እስከተናኘ ስም ያጣ፣ ስያሜ ያልተሰጠው የአረቢያ ጠረኗ በዚህና በሌሎችም የአረቢያ ምድር በረሃዎች አድፍጣለች፡፡                                    


Read 1047 times