Tuesday, 25 January 2022 10:32

ለዲያስፖራው ማህበረሰብ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ያደርጋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በኤግዚቢሽን፣ ኑ ቡና ጠጡ፤ የጎዳና ላይ ሩጫና የሙዚቃ ኮንሰርት


             የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ወደ ሀገር ቤት የመጡ የዲያስፖራ ማህበረሰብን በልዩ የመዝናኛና የባህል ልውውጥ መድረኮች ለማስተናገድ መዘጋጀቱን አስታውቋል። የሚኒስትር መ/ቤቱ ከኢስት አፍሪካን ቢዝነስ ግሩፕ እና ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ጋር በመተባበር ከጥር 20-22 በባህል፣ በኪነጥበብና በስፖርት ዘርፎች  ልዩ ሁነቶችና ትዕይንቶችን እንዳሰናዳ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ ገልጿል።
“በታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት መርሃግብር” የመጡትን ኢትዮጵያውያን፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ዘመድ ወዳጆቻቸውን በአንድ ላይ ለማሰባሰብ የታቀደ ሲሆን፤የሀገራቸውን ባህላዊ እና  ኪነጥበባዊ እንዲሁም እደጥበባዊ እሴቶችን  የሚጎበኙበትና እርስ በራስ የሚተዋወቁባቸው የመዝናኛ መርሐ ግብሮችም ተዘጋጅቶላቸው። በባህልና ስፖርት ሚኒስቴሩ ይፋ በሆኑት መርሐ ግብሮች መሰረት ጥር 20 ላይ በሸራተን አዲስ የመክፈቻ ሲምፖዚየም የሚካሄድ ሲሆን በወዳጅነት ፓርክ ደግሞ ሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የሚሳተፉበት የባህል ኤግዚቢሽን ይኖራል።
 በተመሳሳይ ዕለት ልዩ የቡና ጠጡ ፕሮግራም የተዘጋጀ ሲሆን በኤግዚብሽኑ የዕደ ጥበብ ምርቶች፤ አልባሳትና ባህላዊ ምግቦች እንዲሁም የስ-ጽሁፍ ቅርሶች እንደ ሚቀርቡና  በብሔር ብሔረሰቦች የደመቀ ሙዚቃ ተሰናድቷል። ቅዳሜ ጥር 21  ላይ በወዳጅነት ፓርክ ሙሉ ቀን ኤግዚቢሽንና ከልዩ ባዛር ጋር በሙዚቃ ዝግጅቶች ተዋህዶ መስተንግዶው የሚቀጥል ይሆናል። በወዳጅነት ፓርክ በሚካሄደው ኤግዚቢሽን ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የባህል፣ የኪነጥበብ፣ ዕደ ጥበብ እና ሌሎች ክልላዊ እሴቶችን ለጎብኝዎች የሚያቀርቡበት ዕድል ይፈጠራል። እሁድ ጥር 23 ላይ መነሻና መድረሻውን በመስቀል አደባባይ የሚያደርግ የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ የሚካሄድ ሲሆን ታዋቂ አትሌቶችና ሌሎች እንግዶች ይሳተፉበታል። ከጎዳና ላይ ሩጫው ጋር ተያይዞም ስፖርታዊ የአካል እንቅስቃሴ የጤና ችግር ያለባቸው፣ አረጋውያን፣ ህጻናትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ይከናወናል። “ቡናችን ለሚሊዮኖች” እና “ኑ ቡና ጠጡ” በሚሉ መሪ ቃሎች 1 ሺ ስኒ በረከቦት ቀርቦ ቡና በባህላዊ መንገድ የሚፈላ ሲሆን እስ 10 ሺ ሰዎችን ለማስተናገድ ታስቧል። ባህላዊ የገና ጨዋታ፣ የፈረስ ጉግስ፤ የግመል ግልቢያ እና የቡድን የገመድ ጉተታ ለዲያስፖራው ማህበረሰብ  የተዘጋጁ ሌሎች አዝናኝ ስፖርታዊ ሁነቶች ናቸው። በወዳጅነት ፓርክ ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ሌሊት 6 ሰዓት የሚቆይ ታላቅ የሙዚቃ ኮንሰርት በመዝጊያው ስነስርዓት የተዘጋጀ ሲሆን አንጋፋ እና ታዋቂ  አርቲስቶች በሀገር አንድነት ላይ ያተኮሩ ሙዚቃዎችን  ያቀርባሉ። ግጥሞች፣ ስነጽሁፎችና የባህላዊ አልባሳት ትርዒት ከሙዚቃ ኮንሰርቱ ጋር ተሰናስለው እንደሚቀርቡ የተገለፀ ሲሆን የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ እና ውዝዋዜ እንደሚቀርብም ታውቋል።


Read 1090 times