Tuesday, 25 January 2022 10:29

የአፍሪካ ዋንጫው ወደ ጥሎ ማለፍ ገብቷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       ዋልያዎቹ ዋጋቸውን ጨምረው ተመልሰዋል

                33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ጥሎ ማለፍ የተሸጋጋረ ሲሆን በምድብ 1 ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ  ቡድን ትናንትና ዕለት ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ ለ11ኛ ጊዜ ሲሆን በኬፕቨርዴ  1ለ0 እና በካሜሮን 4 ለ1 ሲሸነፍ ከቡርኪናፋሶ ጋር 1ለ1 አቻ በመለያየት   በአንድ ነጥብና በ4 የግብ እዳ  ከምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ይዞ አጠናቅቋል።
ከዋልያዎቹ ስብስብ 3 ተጨዋቾች 270 ደቂቃዎችን በመጫወት የሚጠቀሱ ሲሆን እነሱም  ተክለማርያም ሻንቆ፣ አስቻለው ታመነ እና አማኑኤል ዮሐንስ ናቸው። አማኑኤል ዮሐንስ ከቡርኪናፋሶ ጋር በተደረገው ግጥሚያ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለት ጎሎችን ያስቆጠሩት ደግሞ ዳዋ ሁጤሳ በካሜሮን ላይ እንዲሁም ጌታነህ ከበደ በቡርኪናፋሶ ላይ  በፍጹም ቅጣት ምት ነበር። ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ  በ3ቱ የምድብ ጨዋታዎች 13 ተጨዋቾችን ቀይረው ያስገቡ ሲሆን አምስት በመክፈቻው ከኬፕቨርዴ ጋር ባደረጉት ጨዋታ፣ አምስት ከካሜሮን ጋር ባደረጉት ሁለተኛ  ጨዋታ እንዲሁም ሶስት ተጨዋቾችን ደግሞ  ከቡርኪናፋሶ ጋር ባደረጉት የምድቡ የመጨረሻ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አፍሪካ ዋንጫ ከመጀመሩ በፊት አጠቃላይ የቡድን ስብስቡ በ750 ሺ ዩሮ ተተምኖ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድቡ ካደረጋቸው 3 ጨዋታዎች በኋላ የዋጋ ተመኑ ወደ 3.3 ሚሊየን ዮሮ አድጓል፡፡ በትራንስፈርማርከት (Transfermarkt) ድረ ገፅ ላይ በዝርዝር እንደሰፈረው 28 ተጨዋቾች የሚገኙበት የዋልያዎቹ ስብስብ ከ50 ሺ-300 ሺ ዩሮ ዋጋ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ግብ ጠባቂዎቹ ተክለማርያም ሻንቆ እና ፋሲል ገ/ሚካኤል 125 ሺ ዩሮ፤ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂዎች ጀማል ጣሰው 75 ሺ ዩሮ እንዲሁም ፍሬው ጌታሁን 50 ሺ ዩሮ ዋጋ ወጥቶላቸዋል። ከተከላካዮች አስቻለው ታመነ እና ያሬድ ባዬህ 150 ሺ ዩሮ፤  ረመዳን የሱፍ 100 ሺ ዩሮ፤ ደስታ ዮሐንስ፣ አስራት ጡንጆ እና ሱሌማን ሀሚድ 75 ዩሮ እና አህመድ ረሽድ 75 ሺ ዩሮ ተተምነዋል። ከአማካዮች ጋቶች ፓኖም 175 ሺ ዩሮ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ይሁን እንዳሻው፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ፍጹም አለሙ 100 ሺ ዩሮ ሲሰጣቸው መሱድ መሐመድ 75 ሺ ዩሮ፣ በዛብህ መለዮ 50 ሺ ዩሮ ደርሰዋል። አማካዩ ሽመልስ በቀለ አንድም ጨዋታ ባይሰለፍም በ300 ሺ ዩሮ የዋጋ ተመን የኢትዮጵያ ውዱ ተጨዋች ነው። በአጥቂ መስመር አቡበከር ናስር 200 ሺ ዩሮ፣ መስፍን ታፈሰ 175 ሺ ዩሮ፤ አማኑኤል ገ/ሚካኤልና ሙጅብ ቃሲም 100 ሺ ዩሮ፤ ፍሬው ሰማንና ዳዋ ሁጤሳ 75 ሺ ዩሮ ዋጋ አግኝተዋል።
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው ከነበሩት በ2019 ዋንጫውን ያሸነፈችው አልጀሪያና የምዕራብ አፍሪካዋ ጋና ከየምድባቸው ለማለፍ ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከየምድቡ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ያገኙት እንዲሁም ምርጥ 3ኛ የሆኑ 4 ብሔራዊ ብድኖች  ወደ ጥሎ ማለፍ ገብተዋል።ከምድብ 1 ካሜሮንና ቡርኪናፋሶ፤ ከምድብ 2 ሴኔጋልና ጊኒ ከምድብ 3 ሞሮኮና ጋቦን፤ ከምድብ 4 ናይጀሪያና ግብጽ፤ ከምድብ 5 አይቬሪኮስትና ኢኳቶርያል ጊኒ እንዲሁም ከምድብ 6 ማሊና ጋምቢያ ሲሆኑ በምርጥ ሶስተኛነት ጥሎ ማለፍ የገቡት 4 ቡድኖች ደግሞ ኬፕቨርዴ ከምድብ 1 ማላዊ፣ ከምድብ 2፣ ኮሞሮስ ከምድብ 3 እና ቱኒዝያ ከምድብ 4 ናቸው።
በምድብ ማጣርያው 36 ጨዋታዎች ተደርገው 68 ጎሎች የተመዘገቡ ሲሆን የካሜሮኑ ቪንሰንት አቡበከር በ5 ጎሎች ኮከብ ግብ አግቢነቱን እያመራ ነው። በጥሎ ማለፉ ጃንዋሪ 23 ላይ ቡርኪናፋሶ ከጋቦን እና  ናይጀሪያ ከቱኒዚያ፤  ጃንዋሪ 24 ላይ ጊኒ ከጋምቢያ እና ካሜሮን ከኮሞሮስ፤  ጃንዋሪ 25 ላይ  ሴኔጋል ከኬፕቨርዴ እና ሞሮኮ ከማላዊ፤ ጃንዋሪ 26 ላይ ማሊ ከኢኳቶሪያል ጊኒ እንዲሁም አይቬሪኮስት ከግብፅ ይገናኛሉ።


Read 1116 times