Tuesday, 25 January 2022 10:34

የኢትዮጵያ U-20 ሴቶች ቡድን ወደ ዓለም ዋንጫ ግስጋሴውን ቀጥሏል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ U -20 ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ሁለት የማጣሪያ ምዕራፎች  ይቀሩታል። በአሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል የሚመራው ብሔራዊ ቡድን በ3ኛው ዙር የደርሶ መልስ ማጣሪያ  የመጀመሪያ ጨዋታውን ከታንዛንያ  ጋር ለማድረግ ትናንት ወደ ዳሬሰላም አቅንቷል።
 በ3ኛው ዙር አፍሪካ ዞን በሚቀጥለው ማጣሪያ በዳሬ ሰላም  በሚገኘው ቤንጃሚን ማኮፖ ስታዲየም ኢትዮጵያና  ታንዛኒያ  ሲጫወቱ  በሌሎች ጨዋታዎች ኡጋንዳ  ከጋና፤ ሞሮኮ ከሴኔጋል እንዲሁም ካሜሮን ከናይጄሪያ ይገናኛሉ፡፡ የታንዛኒያና የኢትዮጵያ አሸናፊ ወደ ዓለም ዋንጫ ለመግባት የመጨረሻ የደርሶ መልስ ግጥሚያ የሚያደርገው ከኡጋንዳ እና ጋና አሸናፊ ጋር ነው፡፡
ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል ቡድኑ ወደ ዳሬሰላም ከመጓዙ በፊት  በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ሀገሬን በጥሩ ነገር ማስጠራት እፈልጋሁ። “  በሴካፋ የመጣውን ነገር ታውቃላችሁ። በዓለም ዋንጫም ዳግም ታሪክ መስራት እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያዊ  ብሆንም ሰፋ ስናደርገው አፍሪካዊ  ነኝ።” ሲል ተናግሯል።
የኢትዮጵያ U-20 ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዞን በተደረጉ ማጣሪያዎች አስደናቂ ውጤት ማስመዝገቡ የሚታወስ ሲሆን  በ1ኛ ዙር ማጣሪያ ሩዋንዳን 8 ለ0 እንዲሁም በ2ኛ ዙር ማጣሪያ ቦትስዋናን  8 ለ2 አሸንፈዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የሴካፋ ሻምፒዮናም ዋንጫውን  አግኝተዋል።  
በኮስታሪካ አስተናጋጅት በሚካሄደው የዓለም ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ አፍሪካ  በሁለት ብሔራዊ ቡድኖች ትወክላለች፡፡
ከ3ኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች  በፊት በ49 ጨዋታዎች  173 ጎሎች  ተቆጥረዋል። የኢትዮጵያዋ ረድኤት አስረሳሃኝ በ5 ጎሎች  ኮከብ ግብ አግቢነቱን ከሞሮኮዋ  ሶፊያ   ቦውፊቲን እና ከናይጀሪያዊዋ ሜሮሲ ኢዳኮ ጋር ትጋራለች፡፡

Read 3091 times