Saturday, 29 January 2022 00:00

በጎ አድራጊዎች በድርቅ የተጎዱ ማህበረሰቦችን እንዲደግፉ መንግስት ጥሪ አቀረበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በድርቅ ምክንያት ለተረጂነት መጋለጣቸውን አለማቀፍ ተቋማት ያስታወቁ ሲሆን መንግስት በበኩሉ አለማቀፍና የአገር ውስጥ በጎ አድራጊዎች እና ለጋሾች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከትናንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርቱ፣ በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ የማስጠንቀቂያ መልዕክቶችን አስተላልፏል።
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣በኦሮሚያ ጉጂና ቦረና ዞን እንዲሁም በደቡብ ቆላማ አካባቢዎች በተከሰተውና በአጠቃላይ ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ያጠቃው ድርቅ፤ በጎረቤት ኬኒያ (ሠሜን ምዕራብ ኬኒያ) እንዲሁም በሶማሊያ (ማእከላዊ ደቡብ ሶማሊያ) ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለችግር አጋልጧል- ብሏል ሪፖርቱ።
እንደ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ፕሮግራም መረጃ፤በአየር ፀባይ መለወጥ ምክንያት በአካባቢዎቹ በበልግና በክረምት ወራት ይጠበቅ የነበረው ዝናብ አለመዝነቡን ተከትሎ የድርቁ አደጋ ተባብሶ በአሀኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ በአጠቃላይ 9 ሚሊዮን ያህል ዜጎችን ለእርዳታ አጋልጧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ የተከሰተው ድርቅ የከፋ አደጋ መደቀኑን ከትናት በስቲያ ያስታወቀ ሲሆን ድርቁ በእንስሳት ግብአት ላይም የከፋ ጉዳት እያደረሰ ነው ብሏል፡፡
ከሰሞኑ የአዲስ አበባ አስተዳደር እነዚህ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ለመደገፍ ጥረት ማድረጉን የጠቆመው መግለጫው ሌሎች አካላትም የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝበው የተጠናከረ ድጋፍ ያደርጉ ዘንድ መንግስት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በሳምንቱ መጀመሪያ እነዚህን በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች የጎበኙ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የክልል መንግስታት ችግሩን በጊዜያዊነት ለማቃለል ጥረት እያደረጉ መሆኑን፣ ነገር ግን ይህ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ የሃገር ውስጥና ዓለማቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና እነዚህን አካባቢዎች እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Read 739 times Last modified on Friday, 04 February 2022 05:34