Saturday, 29 January 2022 00:00

ፍርሃትን ማሸበር... (ካሊጉላ እንደገና...)

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(1 Vote)

  "--ይህችን ዓለም በበላይነት የሚያስተዳድራት ፍርሃት ነው፡፡ ከስልጣን መውረድን መፍራት፣ ውርደትን መፍራት፣ እጦትን መፍራት…ፍርሃት፣ ፍርሃት፣ ፍርሃት… ብዙ መልኮች ያሉ ፍርሃት፡፡--"
          
              ‹‹የካሊጉላ›› ተውኔት ደራሲ ጌታ አልበርት ካሙ፣ ዘመኑን ሙሉ ሲሰብከው የኖረውን የወለፈንድ ፍልስፍና በሕልፈቱ በገቢር ከውኖታል፡፡ እ.ኤ.አ ጥር 4 ቀን 1960 የተውኔት ትዕይንቱን አቅርቦ ከሆነች የፈረንሳይ ከተማ ወደ ፓሪስ ለመመለስ ሙሉ የባቡር ትኬት አዘጋጅቶ እየጠበቀ ነበረ፡፡ በሰላም ፓሪስ የሚያደርሰውን ሙሉ የባቡር ትኬት በእጁ ይዟል፡፡ ድንገት ግን መልዓከ ሞትን አስከትሎ አሳታሚውና ወዳጁ ሚሼል ጋሊማርድ መኪናውን እያሽከረከረ የባቡር ጣቢያው አጠገብ መጥቶ ቆመ፡፡ ጋሊማርድ ባቡር ጥበቃውን አቋርጦ በመኪና አብሮት ይጓዝ ዘንድ ካሙን ወተወተው፡፡ ካሙ ለፎቢያነት የቀረበ የመኪና ፍርሃት ቢኖርበትም የወዳጁን ውትወታ መቋቋም አልቻለም፡፡ ጥሪው ግን የሞት ጥሪ ነበር፡፡ ሁለቱም ፓሪስ ከመድረሳቸው በፊት ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ አሸለቡ፡፡  ከሕልፈቱ በኋላ አስከሬኑ ሲመረመር  ያልተጠቀመባት የባቡሯ ትኬት የኮቱ ኪስ ውስጥ ተገኝታለች፡፡ ካሙ አኗኗሩ እንደ አሟሟቱ ሁሉ ጥድፍድፍ ያለ ነው። በትንሽ ዕድሜው የኖቤል ሎሬትነት የተቀዳጀው ሁለተኛው ጠቢብም እሱ ነበር።  
‹‹ካሊጉላ›› ከ37 እስከ 41 እ.ኤ.አ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሮም የንግስና ዙፋን ላይ ተሰይሞ መላውን የሮማን ኢምፓየር አንቀጥቅጦ በገዛው ንጉሥ ቄሳር ካሊጉላ ሕይወት መነሻነት የተፃፈ፣ ነገር ግን ለሕይወት ሌላ አተያይ የሚፈነጥቅ ድንቅ ተውኔት ነው፡፡ ይህ ተውኔት ከጥቂት ዓመታት በፊት በተመልካች እጦት ከመድረክ ተገፍትሮ ከመውረዱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በየሳምንቱ ማክሰኞ ለእይታ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡
ለካሊጉላ ይህች ዓለም የተሰራችበት ስልተ ምት ልክ አይደለም፡፡ በአንድ ቃለ ተውኔቱ ላይ ‹‹ሰዎች ያለቅሳሉ ምክንያቱም ይህች ዓለም ልክ አይደለችም›› ይላል፡፡ እናም ይህን ልክ ያልመሰለውን አፈጣጠር ለማስተካከል በምስራቅ የምትወጣውን ፀሐይ በምዕራብ ማውጣት ፈለገ፤ በጠፋችው የሚወዳት ሴት ዱሪሲላ ምትክ ጨረቃን የራሱ ለማድረግ ተመኘ፤ በዚች ንቅሳታም ዓለም ፋንታ ሌላ የተሻለች ዓለም ለመፍጠር ሻተ፤ ኸረ ከዚያም በላይ የሮማውያን አማልክት ቬኑስና ጁፒተር ለመሆን ቋመጠ፡፡
ሆኖም የካሊጉላ እብደት የአንድ ብቻ እብደት አልነበረም። የሕይወት ምርምር ጭምር እንጂ… ያበደው ንጉሥ ካሊጉላ፤ የመላዋ ሮም ገዢ በመሆኑ፣ የእርሱ አድራጎት በግዛቱ ስር የሚኖሩ ህዝቦችን ሁሉ ሕይወት የሚረብሽ ሆነ፡፡ በካሊጉላ እብደት ስር የተናወጠው ዓለም፣ የተገማሸረ መልክ እልፍ የሚዋነቡ ጥያቄዎችን አዝሎ ብቅ አለ። የካሊጉላን የእብደት አድራጎት ተከትሎ መላው ዓለም (የያኔዋ ሮማ) በነውጥ ታመሱ። ፍትሕ፣ ፍቅር፣ ጥበብ፣ ክብር፣ ጀግንነት፣ እምነት ሁሉ ለፈተና ቀረቡ። ሆኖም አንዳቸውም ማሸነፍ ተስኗቸው ዓለም እርቃኗን ቀረበች፡፡ ምክንያቱም አማልክቱ ሳይቀር ሸሽተዋልና፡፡
“ካሊጉላ” ተውኔት የተምታታ እውነት፣ የሚጣረስ ሀቅ፣ የማይገጥም መሻትና ፍርሃት የሚንጣቸው ባይተዋር ገፀ ባህርያት የሚመላለሱበት ትዕይንት ነው፡፡ ዓለም በተለይም ህላዊነት ፀንቶ የቆመበት መሰረትስ ይሄው ጥርጣሬ ሳይሆን ይቀራል? አዎ ህላዊነት (Existence) ፀንቶ የቆመው እንደ ባርነትና ነፃነት፣ መወለድና መሞት፣ ብርሃንና ጨለማ፣ … ዓይነት ተቃራኒ ስሜቶችና እውነቶች እሽክርክሪት መሆን አለበት፡፡
በዚህ ሁሉ ትዕይንት መሀል አንዲት የሰለለች ጥያቄ ብቅ ትላለች፡፡ በእውን ይህችን ዓለም አንቀጥቅጦ የሚገዛት ፍቅር፣ ገንዘብ፣ ሞት፣ ስልጣን ወይስ ፍርሃት? መልሱ ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል ነው፡፡ ይህችን ዓለም በበላይነት የሚያስተዳድራት ፍርሃት ነው፡፡ ከስልጣን መውረድን መፍራት፣ ውርደትን መፍራት፣ እጦትን መፍራት…ፍርሃት፣ ፍርሃት፣ ፍርሃት… ብዙ መልኮች ያሉ ፍርሃት፡፡
ራሳችሁን ነፃ አድርጋችሁ ይህችን ግብስብስ ዓለም ብትመለከቷት፣ ሰብዓዊያን በሙሉ ይህን የፍርሃት ነውጥ በመሸሽ፣ እንደ ዶሮ ጫጩት ሲተራመሱ ማየት ትችላላችሁ፡፡ ሌላው ቢቀር የኤሊ ቆዳ ሻካራነት ስያሜ ማጣት ቢያሳስበን መልስ ለመሻት ‹‹በድሮ ጊዜ ኤሊ ከአእዋፋት ጋር ለግብዣ ሰማይ ቤት ተጠርታ…›› የሚል ለዛ ቢስ ተረት መፈጠሩን ወደድን፡፡
እንዲህ ከሆነ የዚህች ዓለም ጌታን ማንነት ጥያቄ ለመመለስ አዕላፍት መላምታዊ መልሶች ቢፈጠሩ የሚደንቅ አይሆንም።
ለሕይወት የዋህ አረዳድ ያለው አዕምሮአችን እንጂ ኃያል አስመስሎ የሚያሳየን፣ የሰው ልጅ እኮ ፈሪና ድንጉጥ ፍጡር ነው፡፡ ንጉሥ ቄሳር ካሊጉላ፣ በተውኔቱ መሃል በአንድ ቃለ ተውነቱ ላይ እንዲህ ይላል፡- “ፍርሃት በካባው ውስጥ ያለውን ሰው ማንነት ያሳያል፡፡”
እንደ አቡነ አትናቲዎስ፤ (ከ327-373 ዓ.ም ግብፅ አቡነ ሰላማን ቀብተው የላኩት) መላውን ዓለምን መቃወሙስ ይቅር፡፡ እንዴት ሰው በማያምንበት ነገር ላይ የቅርብ አለቆችን እንኳን መቃወም ይሳነዋል? በ325 ዓ.ም በኒቂያ ጉባኤ “ክርስቶስ ሰው እንጂ አምላክ አይደለም” የሚለው የአርዮስ አስተሳሰብ ተወገዘ፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ የጳጳሱ አቡነ እስክንድርን ህልፈት ተከትሎ፣ አቡነ አትናቲዮስ መንበረ ስልጣኑን ተረከቡ፡፡ ጥቂት ዓመታት  ቆይቶ  አርዮስ  የነገሥታቱን  ይሁኝታ በማግኘት አቡነ አትናቲዮስን ለብቻቸው በደሴት ውስጥ አሳሰራቸው። በዚህ ወቅት አንድ  ወዳጃቸው፤ ‹‹The whole world is against you›› በሚል ለተላከላቸው መልእክት ሲመልሱ ‹‹If the world goes against the truth, then Athunasius will goes against the world›› ብለዋል፡፡ ‹‹ዓለም እውነቱን መቃወምን ከመረጠ አትናትዮስ ዓለምን ይቃወማል›› እንደማለት፡፡
የብርሃኑ ድንቄ ‹አልቦ ዘመዳዊ›፤ ‹‹እምቢ አሻፈረኝን ካልተለማመድክ መኖርን አታውቃትም፡፡›› ገደምዳሜ ምክር እዚች ጋ በገቢር ይሰራል፡፡ ግን ስንቶቻችን እንኳን መላውን ዓለም የቅርብ አለቆቻችን፣ አስሮ ባስቀረን ፍርሃታችን ላይ እምቢ አሻፈረኝ እንላለን?
 በጎተ ኢንስቲቲዩት ትብብር ተተርጉሞ በታተመው ‹‹ከህግ ፊት›› የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ውስጥ የካፍካ አንድ አጭር ልብወለድ ላይ የሚገርም ታሪክ አንብቤያለሁ፡፡ ሰውየው ባላገር ቀመስ ነው። ለጉዳይ ‹ሕጉ› ጋ መቅረብ ፈልጓል፡፡ ሆኖም ጥበቃው ከበር እንዲያልፍ ሊፈቅድለት አልቻለም፡፡ ‹‹ተመልከት፣ እኔን እንደምንም ብታልፍ ቀጥሎ የሚጠብቅህ ጠብደል ጥበቃ ነው፡፡ እሱን ካለፍክ ደግሞ ይበልጥ ግዙፍ በር አስከልካይ ያጋጥምሃል፡፡›› ተባለ። እናም እምቢተኝነቱን አሽቀንጥሮ ጥሎ ደጅ መጥናት ጀመረ፡፡ መታያዎችን ያመጣል፡፡ ግን አጮልቆ ከማየት ውጭ የመጀመሪያዋን በር እንኳን ማለፍ አልቻለም፡፡ በመጨረሻ ጅጅት ብሎ ሸመገለ፡፡ ጆሮዎቹ እንኳን ጮክ ካላሉ ለመስማት ተቸግረዋል፡፡
ሰውየው ከእርጅናው የተነሳ ተመልሶ መምጣት እንደማይችል የተረዳው ጥበቃው፣ በሩን ለመጨረሻ ጊዜ ከርችሞ ከመዝጋቱ በፊት እንዲህ አለ፡- ‹‹ይህ በር የተከፈተው ላንተ ብቻ ነበር፡፡ በዚህ በኩል ህጉ ጋ መድረስ የምትችለው አንተ ብቻ ነበርክ፡፡ እነሆ አሁን እዘጋዋለሁ፡፡›› ‹ሕጉ› እንዲያው ህግ ሳይሆን ተምሳሌት (metaphor) መሆኑ ነው፡፡ ሕጉ የሰውየው ዕጣ-ፈንታ ነበር፡፡ ይህ ሰው ከመድፈር ይልቅ የመሽቆጥቆጡን መንገድ መረጠ፡፡ ማንኛችንም ዕጣ-ፈንታችንን የምንተልመው በደፈርነው ልክ ነው፡፡ የተደነቀው ሩሲያዊ ፈላስፋ ጆርጅ ጉርጂፍ እንዲህ ይላል፡- ‹‹Unless a Dicipline is not ready even to steal from the Master, He is not going to get it.››
ግሪካዊያን ሆኑ አፍሪካዊን ስነ ተረቶች እንደሚሉት፤ ለሰው ልጅ የኑረት ዘዴ መሻሻል ወሳኝ ግብዓት የነበረው እሳት ከአማልክቱ ጥበብ በታከለበት አደገኛ ስርቆት የተገኘ ሀብት ነው፡፡ ለዚህም ፕሮሜተስ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎበታል፡፡ በታላቁ ዜውስ ትዕዛዝ በሰንሰለት ታስሮ ለዘለዓለም ጭልፊቶች ጉበቱን ይቦጠቡጡ ዘንድ ተጥሏል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው፤ ሰው ‹ሰው የመሆን ህሊናውን ያገኘው› በመተላለፉ አመጽ ውስጥ በበለስ ፍሬዎች መካከል ነበር፡፡ ለዚህም አሻፈረኝ ባይነቱ፣ ማርና ወተት ከሚፈስባት የኤደን ገነት ወደ እሾህና አሜኬላ የሚበቅልባት ምድር ተግዟል፡፡ እዚች ጋ ቆም ብለህ የጆን ስትዋርት ሚልን ‹‹It is better to be a human being dissatisfied than a pig satisfied. Better to be Socrates dissatisfied than a fool satisfied. ›› የምትል አባባል አስበህ እንኳንም አትልም!
ቪንሰንት ቫን ጎ በበኩሉ በጥቅምት 2፣ 1884 እ.ኤ.አ ለወንድሙ ቲዮ ስለ ሰዓሊያን ፍርሃት ሲጽፍ የሚከተለውን ሀሳብ አንስቷል፡-
‹‹If one wants to be active, one mustn’t be afraid to do something wrong sometimes, not afraid to lapse into some mistakes.... Many painters are afraid of the blank canvas, but the blank canvas IS AFRAID of the truly passionate painter who dares — and who has once broken the spell of ‹‹you can’t.›› Life itself likewise always turns towards one an infinitely meaningless, discouraging, dispiriting blank side on which there is nothing, any more than on a blank canvas.››
ራሱ አልበርት ካሙ በ‹‹Happy death›› ልብወለዱ እንዳለው፤ አንዳንድ ጊዜ ራስን ከማጥፋት ይልቅ ራስን ማሰንበት የበለጠ ጀግንነት ይፈልጋል፡፡ በእርግጥም ደፍረው የመጀመሪያውን የብሩሽ ጥፊ እስኪያሳርፉበት ውጥሩ ሸራ እንኳን አተያዩ የጠበኛ፣ የወደረኛ  ዓይነት ይሆናል፡፡ የፍርሃቱን ጥፍነና ላሸነፈ ለእርሱ ግን እንኳን ውጥሩ ሸራ ምድር ትርበተበታለች፡፡ ጋሽ ስብሃት እንዳለው፤ ‹‹ተዘጋጀህም አልተዘጋጀህም ጥሪው እንደሁ አይቀርልህ...›› እናስ ድፈር እንጂ ባይሆን የምር ኖረህ ሞትህን የጀግና ማድረግ ነው፡፡

Read 1493 times