Saturday, 05 February 2022 12:01

“ጉዞ ከሄኖክ ጋር 2” ዛሬ ይከፈታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ሰአሊ አለባቸው ካሳ “ጉዞ ከሄኖክ ጋር” (Travel with Enok 2) በሚል  ርእስ ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀው የጠልሰም ስራዎች አውደ ርዕይ ዛሬ እንደሚከፈት ታወቀ፡፡  “ጉዞ ከሄኖክ ጋር” 2 በሃያት መኖርያ ቤቶች ዞን 5 መንገድ ቁጥር 12 በሚገኘው የስነጥበብ ማእከል ከጥር 29 እስከ የካቲት 13 ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡
በኢትዮጵያ የጠልሰም ጥበብ መፅሃፈ ሔኖክን ብዙ እየተጠቀምንበት ባለመሆኑ ሰዓሊ አለባቸው  “ጉዞ ከሄኖክ ጋር” የሚል ፕሮጀክት በመቅረፅ የጠልሠም ጥበብን ለማስተዋወቅ  አስቧል፡፡  ከመፅሃፈ ሄኖክ  5 መፅሃፍት የሚያደርገውን ጉዞ በየዓመቱ በተከታታይ በሚያቀርባቸው ኤግዚብሽኖች በመስራት ነው፡፡ ባለፈው አመት በተመሳሳይ ወቅት “ጉዞ ከሄኖክ ጋር” በሚል ርእስ ለመጀመርያ ጊዜ ባቀረበው የጠልሰም  ትርኢት ሰአሊዎችና የስነጥበብ አፍቃሪያን ምትሃታዊ ተሰጥኦውን ተመልክተዋል፡ ፡ሰአሊው የጠልሰም ስራዎቹን በአስደናቂ የቴክኒክ ቅልጥፍና ፤  አሰራሮችና በዳበሩ ጭብጦች ይሰራቸዋል፡፡  እንደገና ጥቅም ላይ በሚውሉ ጣውላዎችና የቆዩ  እንጨቶችን  ቀርጾ አክሪሊክ ቀለማትን ይቀባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ የሚስላቸው የጥበብ ምልክቶች በእንጨት ላይ በዲጂታል መንገድ የታተሙ ይመስላል።
ትውልዱ በደሴ የሆነው ሰአሊ አለባቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አለ  የስነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የተመረቀ ሲሆን ፤ ባለፉት 15 አመታት በተለያዩ የቡድን ኤግዚብሽኖች ላይም ተሳትፏል፡፡  ከጠልሰም ጥበብ ጋር  ከተገናኘ በኋላ በአስደናቂ የጥበብ ስራዎች ተመልሶ የመጣ ሲሆን በቀለማት ያሸበረቁት ስራዎቹ በኢትዮጵያ የጠልሰም ጥበብ በአጭር  ጊዜ ለመታወቅ እያበቁት ናቸው፡፡



Read 1050 times