Saturday, 05 February 2022 12:13

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(2 votes)


                         ሰው አክባሪ ትውልድ እናፍራ!!!

            “ግብረገብነት እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ሰዎችና ከራሱ ሕይወትና እድገት፣ መብትና ነፃነት፣ ጥቅምና ፍላጎት፣ ክብርና  ዓላማ አንፃር ማድረግ የሚገባው ወይም ማድረግ የማይገባው ድርጊት፤ መሆን የሚገባው ጠባይ ወይም መሆን የማይገባው ጠባይ ነው” ሲል የአቡነ ጎርጎሪዮስ  ት/ቤቶች የግብረገብ ትምህርት መማሪያ መፅሀፍ ይገልፃል፡፡
ታዲያ ግብረገብነት መገለጫዎቹ በርካታ ኢትዮጵዊ እሴትን የያዙ ድርጊቶች  ሲሆኑ ከነዚህ መሀከል አንዱ ሰው አክባሪነት ነው፡፡ ሰው ክቡር ፍጡር ነው፡፡ ልጆችም ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያድጉ ኢትዮጵያዊ እሴትን በማወቅና በመተግበር የሰውን ክቡርነት በመረዳት እንዲያድጉ የቤተሰብ፣ የመምህራንና የማህበረሰብ ኃላፊነት ነው፡፡
ሰውን ማክበር በርካታ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን ልጆች በልጅነታቸው እያወቋቸው ማደግ ከሚገቡ የሰው አክባሪነት ድርጊት መገለጫዎች መሀከል የታላላቆችን ትእዛዝ ማክበር ፣ ወላጆችን ማክበር፣ ለታላላቆች የመቀመጫ ቦታ መልቀቅ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ተከባብረውና ተሳስበው ጊዜያቸውን ማሰለፍ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ሆኖም ልጆች አድገው ነገ ሰው አክባሪ ይሆኑ ዘንድ ፍሬውን መዝራትና በተገቢው ሁኔታ ማሳደግ መጀመር የሚኖርብን በልጅነት እድሜያቸው ላይ ነው፡፡
የአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤቶችም  ይህንን ሀገራዊ ሀላፊነት በመረዳት በስነምግባር የታነፀ ትውልድን ለመገንባት ወላጆች ልጆቻቸውን በስነምግባር አንፆ ማሳደግ ከሚኖርባቸው ኃላፊነት ጎን ለጎን  ለተማሪዎቹ የግብረገብ ትምህርት ማስተማሪያ መጽሐፍትን በማዘጋጀት እያስተማረ ይገኛል፡፡
በትምህርት ዘርፍ ሱፐርቫይዘር የሆኑት አቶ ማስተዋል ጌጤ፤  “ሰውን ማክበር ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ማለት ነው። በዚህም ተማሪዎቻችን ግቢ ውስጥ ሲገቡ ከጥበቃ ጀምረው  ከመምህራኖቻቸው ጋር እንዲሁም ከጓደኞቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት  በየዕለቱ የሚተገብሩት ጉዳይ ነው” ብለዋል።
አንድ ተማሪ ሳይንሱን ብቻ እንዲያውቅ አይደለም የምናስተምረው ያሉት ሱፐርቫይዘሩ በዕውቀት፣ በክህሎትና በሰብዕናም ጭምር የጎለበቱ ተማሪዎች  እንዲሆኑ እየተሰራ ነው። በመሆኑም እውቀት ከትህትና ጋር አብሮ ሲመጣ  ውጤታማ ይሆናል” ብለዋል።
የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የግብረገብ ትምህርት፣ ነገ ልጆች አድገው በሚያደርጓቸው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ አሻራ ማሳረፍ ሲችል፣ ለሀገርም በስነምግባር የታነፁ ብቁ ዜጎችን ለማበርከት ያስችላል፡፡

_______________________________________

                           የዛሬውን ቀን በታሪክ ውስጥ ስናስታውሰው...

              ታላቁ ንጉስ፣  ንጉስሚካኤል፣ ንጉሰ ጽዮን ወትግሬ ወወሎ ወጎጃም ወጎንደር ልክ በዛሬው ቀን ጥር 27 ቀን 1842 ዓ.ም. ነበር በተንታ ሚካኤል የተወለዱት።
ንጉሥ ሚካኤል የአፄ ምኒልክ ቀኝ እጅ፣ ከአድዋ ጀግኖች መካከል አንዱ የነበሩ፤ ከአፄ ምኒልክ ጦር በመቀጠል 15ሺ ከፍተኛውን የእግረኛ እና ፈረሰኛ ተዋጊዎች ያሰማሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር የፈረሰኛ ተዋጊ የነበራቸው ፤በብቸኛነት በአድዋ ጦር ግንባር በ3 አወደ ውጊያ ታላቅ ተጋድሎ የፈፀሙ፤ በፈረሰኛ ተዎጊዎቻቸው ተለይተው የሚታወቁ ፤ጣሊያንን ያርበደበዱ ጀግና ንጉስ ናቸው።
የወሎ ግዛት የመሰረቱ፤ ወሎን ለ35 አመት እስከ ንጉስነት ያስተዳደሩ፤ ደሴ ከተማን የመሰረቱ፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያስጀመሩ፤ የልጅ ኢያሱ እና የወይዘሮ ስህን አባት፤ የእቴጌ መነን አያት ..የአፄ ምኒልክ አማች እና፤ ቀኝ እጅ ነበሩ።
በአድዋ ጦርነት ወቅትም ለነበራቸው ጀግንነት ተከታዩ ግጥም በዘመኑ አዝማሪ ተዚሞላቸው ነበር!
ማን በነገረዉ ለጣልያን ደርሶ፤
ሚካኤል መጣ ረመጥ ለብሶ::
መልካም 172ኛ አመት የልደት በዓል ንጉስ ሆይ!

_____________________________________________


                     “ሀይማኖት ህብረተሰብን ማደንዘዣ ሀሺሽ ነው”
                            ክቡር መተኪያ ኃይለሚካኤል


            እድሜ ለእነዋለልኝና ለስልሳዎቹ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተ አለም አራማጆች ይሁንና፤ ከህገ ልቡና እስከ ህገ ኦሪት ብሎም እስከ ህገ ወንጌል ተቀብላ ህዝብን በሀይማኖትና በስነ ምግባር ያነጸችን ሀገር እንደ ኋላ ቀር ቆጥረው፣ አብዮት ካላመጣንላት አሉ። ለውጡስ ባልከፋ። ለራሳቸው ያልገባቸውን ህዝቡን ካላሳወቅንህ ብለው የርዕዮተ አለማቸው ጣዖት የሆነውን የካርል ማርክስ ጥቅስ እየጠቀሱ፤
religion_is_an_opium_for_the_people “ (ሀይማኖት ህብረተሰብን ማደንዘዣ ሀሺሽ ነው) በማለት በተለይ የተዋህዶ ቤተክርስትያን ላይ አይናቸውን ጥለው የቻሉትን ያህል ሲያሳድዷትና ሲያጎሳቁሏት ኖረዋል። ፓትርያርኳን በሲባጎ አንቀው ገድለዋል። ጳጳሳቶቿን አስረዋል፣፣አዋክበዋል። ቀሳውስቶቿን የስቃይ አይነት አስቆጥረዋቸዋል። ሲኖዶሷን ለሁለት ከፍለው የኢትዮጵያውና ስደተኛው አስብለው ምዕመኑን አደናግረዋል።
ይህ አልበቃቸው ብሏቸው አማንያኑን ሲያሳድዱ፣ የኦርቶዶክስ ያሉትን ሁሉ ሲቆርጡና ሲፈልጡ የኖሩ ሁሉ ዛሬ በወንበራቸውም ይሁን በህይወት የሉም። የ2010 የመንግስት ለውጥ እንደመጣ ከብዙ ጊዜ በሁዋላ “ፈርሀ እግዚአብሄር አገኘን” ብለን አምላክን ስናመሰግንና፣ “ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን የቀደመ ክብሯን አገኘች፤ ሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ አውርደው አንድ ሆኑ” ብለን ደስ ብሎን ሳንጨርስ ነገሮች መልካቸውን ቀየሩ። “ሀይማኖት ህብረተሰብን ማደንዘዣ ሀሺሽ ነው” ባዮችን የሚያስታውስ የሚመስል ድርጊት ሲፈጸም አስተዋልን። ዝማሬ ላይ በነበረ ምዕመን ላይ የአስለቃሽ ጭሱ ሲገርመን ጥይት ተተኮሰ። እንዲህ ያለ ጥፋት ሲከሰት ቢሆን ቢሆን አይቀጡ ቅጣት የሚቀጣ ሌላው ቢቀር በአጽንኦት የሚገስጽ መሪ ሁሌም እንናፍቃለን። ሳይቃጠል በቅጠል የሚል ልቡና የሰጠውና መፍትሄ ይዞልን የሚመጣ መሪ እንሻለን። የምናከብራቸውን አባቶቻችንን የሚያከብርልን ባለስልጣን እንፈልጋለን። ፍትህን ከሰማይም ከምድርም እንጠይቃለን።




______________________________________________

                          አንድ ሆነን ተፈጥረን ለምን አንድ መሆን አቃተን ?

                          (በድጋሚ ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ የተለጠፈ)
                                    ተስፋዬ አለነ

               ሁሌም ጭንቅላቴን የሚያሳምመኝ አንድ ነገር አለ፡፡ ‹‹አንድ_ነን›› ተብሎ አንድ ያለመሆናችን ጉዳይ፡፡ ፈጣሪ በአምሳሉ እንደቀረፀን ተነግሮን አደግን፡፡ በገሃዱ ዓለም ላይ አንድ መሆናችንን የሚያሳይ ምንም ነገር አጣን፡፡ ለተፈጠረው ልዩነት ተጠያቂው ማንም ይሁን ማን፣ ማናችንም ኅብረትና አንድነት ርቆናል፡፡
አንድነት እንኳን ከተግባራችን የሰው ስም ከመሆን ተርታም እየተወገደ ይገኛል፡፡ በሆነው ባልሆነው ዘር እያጣቀሱ መቆራቆሱ በተለይም በዚህ ‹‹የፌዝ-book›› መድረክ ገንኗል፡፡ አንዱ የአንዱን ነገድ ስም እየጠቀሰ አንዱን ባሻው የቃላት ጦር ይሸቀሽቃል፡፡ ያም መልስ ብሎ አላስፈላጊ የቃላት ቦምቡን ይወረውራል፡፡ በዚህ መሀል የሚጠፋው ጊዜና ገንዘብ ብቻም ሳይሆን የሚጠፋፋው ሰው ጭምር ያሳዝነኛል፡፡ በረባ ባልረባው ነገር ስንበላላ፣ ስንጠላላና ስንኮራኮም አብራ የምታኖረንን አንዲቷን ሀገራችንን እንዳንረሳት እሰጋለሁ፡፡
 ይህች ለዘመናት በድህነት መጫኛ የተውተበተበች ሀገር ሕዝቦች መሆናችንን ማንም ልብ ይላል፡፡ ድህነቱ ሲነገረው አንገቱን የማይደፋ አንድም ወገን የለኝም፡፡ ድህነታችን ለዘላለም በአደራ የተሠጠን ይመስል አልተላቀቀንም፡፡ አንድ የሚያደርገን ሰው ወይም መሪ አንጠብቅ፡፡ እኛ አንድ ለመሆን ከልብ በመነጨ ስሜት እንነሳሳ፡፡
አምላክ አስቀድሞ አንድ እንድንሆን በአምሳሉ ቀርጾናል፡፡ ከተመሳሳይ አጥንት፣ ስጋና ደም አዋህዶ አበጅቶናል፡፡ የአንዳችንን ደም ቀይ የሌላችንን ነጭ አላደረገም፡፡ አንዳችንን ከአጥንት፣ አንዳችን፣ ከብረት አልገነባም፡፡ የአንዱ አዳም (አደም) ብዜቶች ነን፡፡ አንዳችን የአንዳችንን አስተሳሰብና አመለካከት እናክብር፡፡ አንዳችን የአንዳችንን መልካም ነገር ማሞገስ እንልመድ፣ ያልተመቸንን ደሞ በቅንነትና ሌሎችን ሊያርምና ሊያስተምር በሚችል መንገድ እንጠቁም፡፡
ሰሞኑን በዚህ በርካታ ቁም ነገሮችን በተለዋወጥንበት፣ ከያለንበት ጫፍ እርስ በርስ በተዋወቅንበት፣ እውቀትን በሸመትንበትና ለዓመታት ተጠፋፍተን ከቆየናቸው ዘመድ አዝማዶቻችን ጋር በተገናኘንበት መድረክ ላይ የሚለቀቁት ሃሳቦች የሚያለሙን ሳይሆኑ የሚያጠፋፉን ሆነው ተመልክቻቸዋለሁ፡፡ እነኚህ ሃሳቦች ባለቤታቸው ማንም ይሁን ማን፣ ለኔ እጅግ ከስርዓት ያፈነገጡ ከማንነታችንም ጋር ፍጹም የሚጣረሱ ናቸው፡፡ ሲያሻን በነገዳችን፣ ሲለን በኃይማኖታችን መጠራጠዙ የትም አያደርሰንምና እዚሁ ጋ እናቁመው፡፡
 ሁላችንም የየራሳችንን የቤት ስራ እንስራ፡፡ ከባህል ዘፈኖቻችን ጀምረን ማረም የሚገባን ብዙ ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ የባህል ዘፈኖቻችን በአብዛኛው ብሔርተኛ ሆነዋል፡፡ እያንዳንዱ ስለመጣበት ነገድ ጀግንነትና አውራነት እንጂ ስለሌላው ግድ የሌለውና አያገባኝም እያለ ያለ ዓይነት ስሜት ይሰማኛል፡፡
በተለይም ‹‹የባህል›› እየተባሉ የሚወጡት ዘፈኖቻችን ላይ ጥላ እንዳያጠላ እሰጋለሁ፡፡ በባህል ዘፈኖቻችን ውስጥ መጠቀስ የሚገባቸው ብዙ የጋራና የሚያዳምሩን ነገሮች ስላሉን እነሱን ማነሳሳት ቢቻል መልካም ነው፡፡
 በሰለጠነ መንገድ ብንወያይ መልካም እንደሆነ አምናለሁ፡፡ የዚህች ሀገር ዜጎች እስከሆንን ድረስ የዚህች ሀገር ማንኛውም ጉዳይ ይመለከተናል፡፡ ፖለቲካውም፣ ኢኮኖሚውም፣ ማኅበራዊ መስተጋብራችንም ለኛው እስከሆነ ድረስ የኛው ነው፡፡ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ሃሳባችንን መሰንዘራችን ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም፡፡ ወደ አንድነት ለመምጣት ‹‹አንድነት›› የሚለውን ሃሳብ ማክበር ይገባናል፡፡ በጨዋነት መወያየት ሲጠቅም እንጂ ሲጎዳ ታይቶም ተሰምቶም አያውቅምና፡፡ ሁላችንም ለራሳችን ይህን ጥያቄ ልንጠይቅ ይገባል፡፡ አንድ ሆነን ተፈጥረን ለምን አንድ መሆን አቃተን ? እስቲ በጨዋ ቋንቋ እንወያይበት!!



Read 1756 times