Tuesday, 08 February 2022 00:00

ኮሮና የፈጠረው 234 ሺህ ቶን ቆሻሻ ሌላ የጤና ስጋት ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በመላው አለም ከ10 ቢሊዮን በላይ የኮሮና ክትባቶች ተሰጥተዋል


           የኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ያለፉት 2 አመታት በመላው አለም ከ234 ሺህ ቶን በላይ የሚመዝን ቆሻሻ መፈጠሩንና ይህ ቆሻሻ እጅግ አሳሳቢ የጤና ስጋት መሆኑን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
ባለፉት 2 አመታት በመላው አለም አሮጌ ማስኮች፣ የክትባት ጠርሙሶች፣ አገልግሎት የሰጡ ሲሪንጆችና መመርመሪያ መሳሪያዎችን ጨምሮ ከ234 ሺህ ቶን በላይ የሚመዝን ቆሻሻ መፈጠሩን የጠቆመው ድርጅቱ፤ የአካባቢ ብክለትና የጤና ስጋት በመሆኑ መንግስታት ቆሻሻውን በአግባቡ ለማስወገድ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ ባለፈው አንድ አመት ያህል ጊዜ በመላው አለም ከ10 ቢሊዮን በላይ የኮሮና ክትባቶች መሰጠታቸውና እስካለፈው ረቡዕ ድረስ በመላው አፍሪካ ከ214 ሚሊዮን በላይ የኮሮና ክትባቶች ለተጠቃሚዎች መሰጠታቸውን፣ የተጠቂዎች ቁጥርም ከ10.8 ሚሊዮን ማለፉን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ 60 በመቶ ያህሉ ወይም 4.8 ቢሊዮን ያህል ሰዎች ቢያንስ አንድ ዙር የኮሮና ክትባት መውሰዳቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ከ20 በላይ የተለያዩ አይነት የኮሮና ክትባቶች በአለም የጤና ድርጅት እውቅና ተሰጥቷቸው አገልግሎት ላይ መዋላቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በአለማችን ታሪክ ይህን ያህል ክትባት በዚህ ፍጥነት ተሰጥቶ እንደማያውቅ መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፤ ያም ሆኖ ግን የክትባት ስርጭቱ ፍትሃዊነት የጎደለውና በድሃና ሃብታም አገራት መካከል ያለው የክትባት ሽፋን በእጅጉ ልዩነት ያለው መሆኑንም አመልክቷል፡፡
አነስተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ሙሉ ለሙሉ ክትባት የወሰደው ከአጠቃላዩ ህዝብ 5.5 በመቶው ብቻ መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገራት በአንጻሩ እስከ 72 በመቶ የሚደርሰው ህዝብ መከተቡንም አክሎ ገልጧል፡፡
ከወራት በፊት ባወጣነው ሌላ ዘገባ፣ የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በመላው አለም በሚገኙ 193 አገራት ውስጥ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ከ8 ሚሊዮን በላይ የፕላስቲክ ቆሻሻ መፈጠሩንና አብዛኛው ቆሻሻም በውቅያኖሶች ውስጥ እንደተጣለ አሶሼትድ ፕሬስ መዘገቡን አስነብበናል፡፡
በውቅያኖስ ውስጥ ከተጣለው 26 ሺህ ሜትሪክ ቶን ያህል የፕላስቲክ ቆሻሻ መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ከሆስፒታሎች የወጣ እንደሆነና ቆሻሻው ለውሃ አካላት ስነምህዳር ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል ነው መባሉንም የጠቆመው ዘገባው፣ እስከ ሃምሌ ወር ድረስ በአለም ዙሪያ ከኮሮና ጋር በተያያዙ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ሳቢያ እንስሳት ለሞት የተዳረጉባቸውና የተጎዱባቸው 61 ያህል ክስተቶች መመዝገባቸውንም መግለጹ ይታወሳል፡፡

Read 4298 times