Thursday, 10 February 2022 00:00

ፑቲን አሜሪካ ሆን ብላ ወደ ጦርነት እየገፋችን ነው አሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      የሩስያና የዩክሬን ፍጥጫ ተካርሯል

             ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተባባሰ የመጣው የሩስያና የዩክሬን ፍጥጫ ከሰሞኑ የበለጠ ተካርሮ መቀጠሉንና አሜሪካም፣ ሩስያ ዩክሬንን ልትወር አሰፍስፋለች ስትል ማስጠንቀቋን ተከትሎ፣ የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ወደ ጦርነት ልታስገባን እየጎተጎተችን ነው ሲሉ አሜሪካን መውቀሳቸው ተነግሯል፡፡
ሩስያ ከሳምንታት በፊት 100 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮቿንና የጦር ሃይሏን ወደ ዩክሬን ድንበር ማስጠጋቷን ያስታወሰው ሮይተርስ፤ ይህም አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ሩስያ ዩክሬንን ልትወር ተዘጋጅታለች የሚል ስጋታቸውን እንዲገልጹ እንዳደረጋቸው የዘገበ ሲሆን፣ የሩስያው ፕሬዚዳንት ግን በጉዳዩ ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ የጦርነት ዕቅድ እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡
ሩስያ ከአሜሪካ ሊቃጣ የሚችልን ማንኛውም አይነት ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆኗን የጠቆሙት ፑቲን፤ አሜሪካ ይሄን ያህል የምትንገበገበው የዩክሬን ደህንነት አስግቷት እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡
የጦር ሃይላችንን በግዛታችን ውስጥ በየትኛውም አካባቢ የማንቀሳቀስና የውጭ አደጋን የመከላከል መብታችን የተጠበቀ ነው ያሉት ፑቲን፤ አሜሪካ ወደ ጦርነት እንድንገባ እየገፋፋችን ያለችው ማዕቀብ እንዲጣልብንና በኢኮኖሚ እንድንደቅቅ በማሰብ ነው ሲሉ መውቀሳቸውንም አመልክቷል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘሌንስኪ ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ከገቡ ጉዳዩ የሁለቱ አገራት ብቻ ሳይሆን የመላው አውሮፓ እንደሚሆን ከሰሞኑ መግለጻቸውን የዘገበው ቢቢሲ በበኩሉ፤ ዩክሬን ዜጎቿን ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች እያስገባች በስፋት ማሰልጠን መጀመሯንና በ3 አመታት ውስጥ ተጨማሪ 100 ሺህ ወታደሮችን ለማሰልጠን ማቀዷንም ጠቁሟል፡፡
ፍጥጫው እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎም፤ ብሪታኒያ፣ ፖላንድና ዩክሬን ባለፈው ማክሰኞ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ከሩስያ ሊቃጣ የሚችለውን ጥቃት በጋራ ለመመከት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ሩሲያ የዩክሬን አካል የነበረችውን የክሪሚያ ግዛት እ.ኤ.አ በ2014 በሃይል ከተቆጣጠረችበት ጊዜ አንስቶ ሩሲያን በተመለከተ  በምዕራባውያን አገራት መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ያስታወሰው ዘገባው፤ በሰሞኑ ሁኔታም እየተካረረ መምጣቱን አክሎ ገልጧል፡፡


Read 5067 times