Saturday, 05 February 2022 12:38

የቅናት ቁልቁለት

Written by  በሐናንያ መሐመድ (ከአፋር)
Rate this item
(6 votes)

 ዳዊት፤ ‹‹የደወሉላቸው ደንበኛ ቴሌፎን ለጊዜው መስመሩን እየተነጋገሩበት ነው›› የሚለውን የሞባይሉን ድምጽ ሲሰማ በንዴት ጦፈ፡፡ ‹‹ከማን ጋር እያወራች እንደሆነ መገመት የሚያቅተኝ በግ አይደለሁም፡፡ ህእ… በእኔ ላይ ከደረበችው አንድ ሀብታም ወይም አብሯት ካደገ የሰፈር ዱርዬ ጋር ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ጋጠ-ወጥ፡፡ ከሰው ሚስት ጋር ከሚባልግ ቢያርፍ ይሻለው ነበር፡፡ ሴት እንደ አሸን በፈላበት በዚህ ዘመን ከእኔ ሰምሃል ጋር ምን አያያዘው?›› እያለ አልጋው ላይ ቁጭ ብድግ በማለት ተቁነጠነጠ፡፡ ቅናቱ ከልክ እያለፈ መሆኑን አልተገነዘበም፡፡
ለነገሩ ይህንን የሚረዳበት ጊዜ አልነበረውም፡፡ ተሳደበ፡፡ ተበሳጨ። ብዙ ነገሮችን እያሰበ በድጋሚ የመደወያውን ቁልፍ ተጫነ፡፡
ዳዊት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰምሃል ባህሪይ እየተለወጠበት እንደሆነ ተሰማው። ‹‹ምናባቴ ባደርግ ይሻለኛል፡፡ ከዚህ በፊት እኔ ካልደወልኩ ትደውልልኝ ነበር፡፡ ሀኒ… ማሬ… ናፈከኝ እያለች በየደቂቃው እንዳላጨናነቀችኝ፣ አሁን አገሯ ስመጣላት እንደ ሰባራ ዕቃ ትወርውረኝ!›› ብሎ ሞባይሉን አልጋው ላይ ወረወረው፡፡ መልሶ አነሳና ወደ ጆሮው አስጠጋ፡፡ ‹‹የደወሉላቸው ደንበኛ ቴሌፎን ለጊዜው ጥሪ አይቀበልም›› የሚል መልዕክት በድጋሚ ሲሰማ ንዴቱ የበለጠ ናረ፡፡ ቁጣው ከሰምሃል ወደ ስልኩ የመልእክት ድምጽ ተቀየረ፡፡ ‹‹ቆይ ይቺ ሴት መዋሸት አይሰለቻትም? በዚህ ሰዓት እንኳን፣ አትተኛም፡፡ ከሰምሀል የምትለየው እሷ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ስለምትዋሽ ብቻ ነው፡፡ ውይ… ምክንያታችሁ ብዛቱ! አሁን ተይዟል ብለሽ ተዘግቷል እንደምትይው፣ ሰምሃልንም ብጠይቃት ከወንድሜ ወይም ከአባቴ አለዚያም ከእናቴ ጋር እያወራሁ ነው… ቤት ረስቸው፣ ‹ሳይለንት› ነበረ፣ ‹ላይብረሪ› ገብቼ ነው --- ሚሊዮን ምክንያት ትደረድራለች፡፡  ሴቶች መልካችሁ እንጂ የሚለያየው ውስጣችሁ አንድ ነው፡፡ እውነቴን ነው ስትዋሹ ደግሞ ለነገ አትሉም። አሁን ብደውል ሌላ ትያለሽ ደግሞ›› አለና የመደወያውን ቁልፍ ነካ፡፡ ‹‹መስመሮች ሁሉ ለጊዜው ዝግ ናቸው›› የሚል መልዕክት ሰማ፡፡ ዳዊት አንጀቱ ብግን አለ፡፡
ሰምሃል መካከለኛ ቁመት፣ ፍንጭት ጥርስ፣ ሰልካካ አፍንጫ፣ አጭር ጸጉር፣ ደልደል ያለ ሰውነትና የደስደስ ያለው ፊት የታደለች ኮረዳ ነች፡፡ ብዙ ጊዜ ጉርድ ቀሚስ መልበስ ትወዳለች፡፡ ቤተ-ክርስቲያን መሳም ታዘወትራለች፡፡ ጡቶቿ በተፈጥሮ የሰውን ትኩረት የሚስብ አቀማመጥ ያላቸው ሲሆኑ በጡት መያዣ ስለማትጠረንፋቸው በነጻነት ሲታዩ ያጓጓሉ፡፡ ሰምሃል ከዳዊት ጋር ስትሆን ማዳመጥን እንጂ መናገርን አትመርጥም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የትኛው ቃል እንደሚያስቀይመው፣ የትኛው ወሬ እንሚያስደስተው ለመገመት ትቸገራለች። ያስቀዋል ብላ ያወራችው ወሬ ብዙ ጊዜ አጋጭቷቸው ያውቃል፡፡ ዳዊት ደግሞ የራሱን ንጹህ አፍቃሪነት እንጂ ፍቅረኛውን እንዴት መንከባከብ እንዳለበት በቅጡ አያውቅም፡፡ ይህንንም ቢሆን ሰምሃል ትረዳለታለች፡፡
ዳዊት እንደ እብድ ብቻውን እያወራ ዝብርቅርቅ ግምቱን ለመፈተሽ ሞከረ። አንድም ተጨባጭ ነገር ለማግኘት  አልቻለም። ለውጥንቅጥ ግምቶቹ ሁሉ መልሱ ሰምሃል ጋ ደውሎ ማረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ መልሶ ፈገግ አለና፤ ‹‹አውቃለሁ፤ አይሰለችሽም፤ እርግጠኛ ነኝ አሁንም ሌላ ትያለሽ›› አለ የመደወያ ቁልፉን እየተጫነ፤ ‹‹የደወሉላቸው ደንበኛ ቴሌፎን ለጊዜው መስመሩን እየተነጋገሩበት ነው፡፡ እባክዎን ትንሽ ይጠብቁ›› አለችው፡፡ ብቻውን ከት ብሎ ሳቀ፡፡ መልሶ ኮስተር ጀነን በማለት ‹‹ምንድን ነው? እባክዎን ትንሽ ይጠብቁ ማለት? እባክህን … ይቅርታ.. አፈቅርሃለሁ.. ያላንተ መኖር አልችልም… እንዳላጣህ እፈራለሁ… ምናምን እያላችሁ በቅቤ ምላሳችሁ ወንድን  እንደ ባሪያ ትገዛላችሁ፡፡ እኔም ስራዬን ትቼ ስንት ኪሎሜትር አቋርጬ የመጣሁት ‹ጠረንህ…፣ ጨዋታህ፣ ሳቅህ ናፈቀኝ›  ስላለችኝ ነው፡፡ አይ…ውሸት….ወይ ውሸት ------ አይሰለቻችሁም፡፡ በተለይ ሰምሃል  ደግሞ በደንብ ተክናበታለች፡፡ ‹ዴቭ እባክህ ተረዳኝ ፤ ስልኬ ባትሪ ዘግቶብኝ ነው….ሻወር ነበርኩ.. ቤት ረስቼው ወደ ሱቅ ሄጄ ነበር…› ሚሊዮን ምክንያቶች ከአፏ አይጠፉም›› አለ፡፡ ነገሩን ሲያስበው በጣም አናደደው፡፡
‹‹ይቅርታ እና እባክህ የሚሉ ቃላትን ማናባቱ ነው የፈጠረብን፡፡ መቼም ሴቶች ናችሁ የምትፈበርኳት፡፡ ኧረ ሴቶች…›› ደግሞ ፈገግ አለ፡፡ ብቻውን ከት ብሎ እንደ ጅል ሳቀ፡፡ ‹‹ቴሌ እራሱ ይህን ስለተረዳ ነው መልዕክት አቀባይዋን  ሴት ያደረገው፡፡ ወንድ ቢሆን አይዋሽለትማ፡፡ ጎርነን ባለ ድምጹ፤ ‹ባክህ ደንበኛህ ካፍቴሪያ ናት፡፡ ከሰው ጋር እየተጀናጀነች ነው፡፡ ደብርሀት ዘግታህ ነው፣ አትልፋ› እያለ ያጋልጣችሁ ነበር። ግን የሴት ነገር፣ አይ ሴቶች… ሴቶች….›› እያለ ሞባይሉን ከተከራየው አልጋ ላይ በንዴት ወርውሮት ጃኬቱን ደረበ፡፡ ሳያገኛት ወደ መጣበት እንደሚመለስ ሲያስብ እልህ ተናነቀው፡፡ እምር ብሎ ሳያስበው በፍጥነት በሩን ዘግቶ ወጣ፡፡
ቻግኒ እንደ ወትሮዋ ደመቅ እንዳለች ናት፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በጣለው ዝናብ ምክንያት አየሩ ቀዝቀዝ ብሏል፡፡ በመጠኑ ብን ብን….የሚለውን ካፍያ ሰዉ ከቁብ ሳይቆጥረው ሁሉም በየፊናው ውር ውር ይላል፡፡ አንዳንድ ሕጻናት ይሯሯጣሉ፣ ውሃ ያንቦጫርቃሉ፤ ጭቃ እንዳይነካቸው ተጠንቅቀው የሚሄዱ ጥንዶች፣ የማገዶ እንጨት የተሸከሙ ሰዎች፣ ወደ ቤታቸው ለመግባት የሚቻኮሉ ሰራተኞች፣ ጠግበው እያገሱ የሚገቡ ከብቶች፣ ፍየሎችና በጎች፣ የሚፈነጥዙ ጥጆች እና ግልገሎች፣ ሸንኮራ አገዳ በመብላት ሥራ የተጠመዱ ከብት ጠባቂዎች፣ አኩርፈው ይሁን መርቅነው  አንጋጠው ወይም አጎንብሰው የሚሄዱ ወጣቶች…. ሁሉም የሰርክ ህይወታቸውን ተያይዘውታል፡፡
ዳዊትም በዚህ ሰዓት ከሰምሃል ጋር ተቃቅፎ መተኛት ነበር የተመኘው። ስትስመው ----- ሲስማት፣ ልብሶቿን አውልቃ ራቁታቸውን በአንሶላውና በእነሱ መካከል በሚካሄደው ግብግብ፣ አልጋውን ሙቀት ሲያግመው በቁሙ አለመ፡፡ ዳዊት ጥሎበት ዝናም ሲጥል መተኛት ይወዳል። በምኞቱ ተናደደ፡፡ ‹‹ጤፍ በሚቆላ ምላሷ እየሸወደች ታቃጥለኝ እንጂ!›› አለ እንደገና በንዴት እየተንጨረጨረ፡፡
እንደ እብድ እየተወራጨ መጓዝ ጀመረ። ‹‹ቆይ አገር አቋርጬ የመጣሁት ለእሷ ስል አይደለም እንዴ? ችግር የለም በመጣሁበት መኪና ነገ በሌሊት ምልስ እላለሁ” ብሎ አሰበ፡፡ ወድያው ሀሳቡን ከለሰና÷ ‹‹ኧረ ለማን ብዬ! እኔ የዘለለው ልጅ፣አይዞሽ ያላትን ጎረምሳ ዋጋውን ሳልሰጠው ዝም ብዬማ አልመለስም፡፡ አንገቱን እቆለምመዋለሁ፡፡ ምናባቷ፣ እሷ ማን ስለሆነች ነው፡፡ ሴት እንደሆነ ሞልቷል።›› ከራሱ ጋር እያወራ፣ ወዴት እንደሚሄድ ሳያውቅ፣ ሁለት እጁን ሱሪው ኪስ ውስጥ ከቶ፣ እግሩ ወደመራው መጓዝ ጀመረ፡፡
*  *  *
ሰምሀል፤ ዳዊትን ስንት ኪሎሜትር አቋርጦ እንዲመጣ ያደረገችው፣ የጋብቻ ቀናቸውን ከወንድሟ ጋር ተመካክረው እንዲወስኑና ከቤተሰቦቿ ጋር ልታስተዋውቀው ነው፡፡ ለሰምሃል ዳዊት ማለት እስትንፋሷ ጭምር ነው፡፡ ያለእሱ መኖር ምድርን እንደ መቃብር አስፈሪ ያደርግባታል፡፡ ሁሌም ትናፍቀዋለች፡፡ ፈገግታው፣ ሳቁ፣ ቁጣው፣ ቅናቱ … ከመሬት ተነስቶ የሚፈጥረው ጠብ… ይገርማታል። ይህን ሁሉ የሚያደርገው፣ ከልክ በላይ የሚቀናውም ስለሚወደኝ ነው----ትላለች። ክፉኛ ደብድቧት እንኳን አትቀየመውም፡፡ ይልቅ የሚደብራት ዝም ካላት ነው፡፡
የ28 ዓመቱ ዳዊት መሀመድ ዘለለው፤ አጭር ቆፍጣና ሲሆን ሉጫ ጸጉሩን ለውበቱ ድምቀት በማሽሞንሞን ይጠቀምበታል። ጥርሱ የበለዘ ቢሆንም ሲስቅ ግን ፈገግታው ልብን ይሰርቃል፡፡ ጨዋታ አዋቂ፣ የሚያዳምጡትን ሰዎች አብዝቶ አክባሪ ነው፡፡ ማንበብና ስፖርት መስራት ይወዳል። በዚህም ምክንያት ደረቱ መለስተኛ ስታዲዬም ያክላል፡፡ ሰምሃልም በዚህ ደረቱ ትማረካለች፡፡
የሰምሃል ወንድም ዘካርያስ የከባድ መኪና ሾፌር ነው፡፡ ስራው ስለማያስቀምጠው  ከፍቅረኛዋ ዳዊት ጋር ለማስተዋወቅ ተቸግራ ነበር፡፡ ከዘካርያስ ጋር ሁሉንም ነገር በግልጽ ያወራሉ፡፡ የራሱን ምስጢር ግን ብዙ አይነግራትም፤ ‹‹ያው የሾፌር ህይወት…›› ብሎ ያልፈዋል፡፡ ሰምሃል ግን ምንም ነገር ቢሆን አትደብቀውም፡፡ እሱም የትኛውም አገር ደርሶ ሲመጣ ሁሌም ትንሽ ነገር አንጠልጥሎላት መምጣቱን አይዘነጋም። ዘካርያስና ሰምሃል ወንድምና እህት ሳይሆን ፍቅረኛሞች ነው የሚመስሉት፡፡
‹‹አንተ ዛክ ካርዴን ጨረስክብኝ!››  አለችው፤ ስልኳን ብዙ ሰዓት ከተለያዩ ሰዎች ጋር ሲያወራበት ስለቆየ፡፡
‹‹ቢጨርሰውስ ወንድምሽ አይደል›› አሉ እናታቸው፡፡
‹‹አንቺስ ልጅሽ አይደል እንዴ? ለምን ያንቺን ስልክ አትሰጪውም፡፡ እኔ’ኮ የሚፈልገኝ ሰው ስላለ ነው ማም›› አለች ሰምሃል፡፡
‹‹እናንተ ከተገናኛችሁ መከራከሪያ መች ታጣላችሁ›› እየቋጩ የነበረውን ኩታ ይዘው ወደ ጓዳ ገቡ፡፡
ዘካርያስም ስልኩን ዘግቶ ‹‹አቤት አቤት… የንግድ ሸሪኮችሽን ለማነጋገር እንዳይሆን? ገባኝ ኤክስፖርት ያደረግሽው እቃ የት እንደደረሰ ለመጠየቅ ነው..  የለም ተሳስቻለሁ፣ መኪኖችሽ የት እንዳደሩ ለማወቅ ነው›› አላት እያሾፈባት፡፡
‹‹አንተ ንቀኸኛል አይደል…?›› ጸጉሩን ይዛ ጎተተችው፡፡
‹‹እ…ሺ፣እሺ በቃ፤ ካርድ ልሙላልሽ በእናትሽ ልቀቂኝ›› አላት እያመመው፡፡
"አለቅህም"‹‹እሺ ባባትሽ››
"አለቅህም"›
‹‹እሺ… እእ.. . በዴቭ›› አላት ቀስ ብሎ፡፡
‹‹አሁን እለቅሃለሁ››
‹‹አንቺ ጣሳ ራስ! ትናንት ተገኝቶ ከአባትና ከእናት በለጠ፤ ይሄኔ ውሻ በጨው የማይቀምሰው እንዳይሆን››
‹‹ስላላየኸው ነው” አለች በኩራት፤ “መልክ በሊዝ ቢሸጥ ሁልሽም ሮጠሽ ከዴቭ ትገዢ ነበር››
‹‹መልክ ታጥቦ አይጠጣ፡፡ ለማንኛውም እስኪ እናያለን፤ ቅድምያ ምን እንዳሰብሽ ንገሪኝና ደውለን እንጠራዋለን››
እንደለመዱት ተቃቅፈው ከቤት ወጡ፡፡ ካርድ ለመሙላት ከአንድ ሱቅ ገቡ፡፡ ሰምሀል ሁሌም ከዘካርያስ ጋር ስትሄድ ደረቱ ውስጥ ሽጉጥ ብላ፣ እጁን በትከሻዋ ላይ ደርባ ነው። ከሱቁ እንደገቡም …  “እንዴ ልጄ መቼ መጣህ?” አሉት፤ ባለሱቁ እንደመደሰትም እንደመደናገጥም እየዳዳቸው፡፡
‹‹አሁን ገባሁኝ፤ ጋሽ እንድሪስ›› አላቸው የተከበረ ሰላምታ እያቀረበላቸው፡፡
‹‹ልጄ የሆነ ነገር ሳልነግርህ፡፡ ባለፈው ይህ የሱቅ ስራ ትንሽ ሞተብኝና አንተን አሰብኩህ››
‹‹ምን ነበር?››
ወደ ጆሮው ተጠጉ፡፡ ‹‹ይሄን ኮንትሮባንድ የሚባለውን ንግድ ልጀምር አስቤ ነው። አብረን ብንሰራ ብዬ ላማክርህ ነበር›› አሉት ከአፉ የሚወጣውን መልስ በጉጉት እየጠበቁ፡፡
‹‹ምን ዓይነት ስራ ነው የፈለጉት?”
‹‹የትኛውም አይነት፡፡ በተለይ ይሄ ፓስታ፣ ኦሞ፣ መኮረኒ  … የሱቅ እቃዎች ሸቀጣሸቀጥ ነገር›› አሉት፡፡
‹‹እንደዱሮው አይደለም እኮ----አሁን ነገሮች ትንሽ ጠበቅ ብለዋል›› አላቸው፡፡
ወገባቸውን በዱላ የተዠለጡ ያህል ተሰማቸው፡፡ መጀመሪያም ፈርተው ነበር፡፡ የኑሮው ውድነት፣ የቤት ኪራይ ሲጨምር… ግራ ቀኙ ሲጠብባቸው ነበር ይህን ያሰቡት፡፡ ‹‹አዬ ልጄ  እውነትህን ነው! ዘመኑ ተበላሽቶ፤ እንደዱሮማ አይደለም፡፡ ዘመኑ ተበላሽቷል፣ ይሄ የማይሆን ጊዜ፣ ይሄ የዘመን ድሪቶ፣ ይሄ ውሻ የሆነ ዘመን ….›› እየተብሰለሰሉ ተራገሙ፡፡
ሰምሀል የወንድሟን ጀርባ በአቀፈችው እጇ ጠበቅ አድርጋው ሳቀች፡፡ ዘካሪያስ ዝም እንድትል በዓይኑ ገረመማት፡፡ ኮንትሮባንድ መከልከሉ ዘመኑን ማስወቀሱ ሰምሃልን አስገርሟታል፡፡ በረባ ባልረባው የኛ ዘመን እያሉ ይህን ዘመን የሚተቹ ሰዎችን ስትጠላ ለጉድ ነው፡፡
የሰምሃልን ሳቅ ያዩት ሸክ እንድሪስ፤ ‹‹ምን ያስቅሻል ልጄ? እውነቴን እኮ ነው፡፡ ታውቂ የለም ድሮ የሽልንግ ገዝተሽን ሦስት አራት ከረሜላ በነጻ ሲመረቅልሽ፡፡ ታስታውሻለሽ? እቃ በገዛሽ ቁጥር አይንሽ ቅልው ቅልው ይል ነበር፡፡ እስኪ አሁን የቱ ሱቅ ነው ለልጆች ምርቃት የሚሰጥ? ምርቃት ተብሎ ድሮ የሚዘገነው ዛሬ ብዙ ሽልንግ  ያወጣል›› አሉ በሃሳብ ተውጠው ድምጻቸው የበለጠ እየደከመ፡፡
‹‹አዎ ልክ ነዎት አባት፣ እኔ ስንት ጊዜ ከረሜላና ብስኩት በነጻ በልቻለሁ። ለማንኛውም  እንመካከራለን›› አላቸው ዘካርያስ፡፡ ፊታቸው መልሶ በደስታ በራ፡፡ ‹‹አንተ እኮ ድሮም የተባረክ ልጅ ነህ፡፡  ስንቱ ሰፈር ለሰፈር ድዱን ሲያሰጣ አንተ ይሄው ለቤተሰብህ ቀርቶ ለኛም መመኪያ ሆንክ›› አሉት፡፡ አባታቸው ከሞተ ጀምሮ ቤተሰቡን ቀጥ አድርጎ የሚያስተዳድረው ዘካርያስ ነው፡፡ ትምህርቱን አቋርጦ ሾፌር የሆነውም ቤተሰቡን  በገንዘብ ለመደጎም ሲል ነበር፡፡
ዝም ብላ ታዳምጣቸው የነበረችው ሰምሃል፤ ‹‹ካርዱን…›› ብላ ጎሸመችው፡፡ ‹‹እእ..ካርድ ይስጡኝ›› ብሎ ድፍን መቶ ብር ሰጣቸው፡፡ ካርዷን በእጃቸው ይዘው፤ ‹‹እየው ልጄ ለማንም እንዳትተነፍስ፡፡ እነ ገረመዲን እና እነ መቻል ይቺን ከሰሙ ሌላ ችግር ነው የሚፈጠርብኝ፡፡ በምስጢር ያዘው እሺ ልጄ›› አሉት ሀሳቡን እንዳይቀይር በመፍራት፡፡ በንግድ ሥራቸው ከሁሉም የሚደብራቸው ግብር፣ ቫትና ታክስ የሚባሉት ናቸው፡፡
‹‹እሺ ምንም ችግር የለውም›› አላቸው ዘካርያስ፡፡
‹‹አዎ! አንተማ ልጄ ሁሉን ነገር ታውቃለህ፡፡ ባልወልድህም እኮ አሳድጌሀለሁ፡፡ አላህ ጀዛህን ይክፈልህ … በረካ ሁን.. ያሳድግህ… ከውስል ድረስ.. ዑምርህን ያስረዝመው….›› እያሉ ከሱቁ  እስከሚርቁ ድረስ ምርቃት ሲያዘንቡበት ዘካርያስ  ገረመው፡፡ የተናገሩትም ከልባቸው እንደሆነ አሰበ፡፡ ጭንቀታቸው ተጋባበት፡፡
ሰምሃል አፍና የነበረውን ሳቅ መራቋን ካረጋገጠች በኋላ ለቀቀችው፡፡ ምን ሆና ነው ብለው መንገደኞች ዞረው እስከሚያይዋት ተንከተከተች፡፡ ‹‹አንቺ ኧረ ቀስ›› አላት ዘካሪያስ፤ የእህቱ ሁኔታ ገርሞት፡፡
ካፊያው አንዳንድ ጊዜ በርታ፣አንዳንድ ጊዜ ብን ብን ይላል፡፡ ‹‹ሰውነቴ ራሰ እኮ›› አላትና አንድ ካፍቴሪያ ሲደርሱ  ካፍያውን ለማምለጥ ገስግሰው ገብተው ተቀመጡ፡፡
‹‹ቅድም መጥቷል ነበር ያልሺኝ አይደል?›› ጠየቃት፡፡
‹‹አዎ አልጋ እንደያዘ ነግሮኛል፡፡ ተመካክረን ካንተም ጋር ተዋውቃችሁ አብረን እንድንወስን ብዬ ነው፡፡ ስላንተ ብዙ ያውቃል፡፡ ከኔ በላይ ይወድሃል፡፡ በተለይ ፍቅራችንን አለመቃወምህን ስነግረው ተገረመ፡፡ ‹ለካ እንዲህ ዓይነትም ወንድ አለ› አለኝ፡፡ በፎቶ ያውቀሃል፡፡ ግን ዘኪ እኔም በጣም ነው የማመሰግንህ፡፡ አንተ ከጎናችን ባትሆን ምናልባት እዚህ ላንደርስ እንችል ነበር›› አለችው፡፡
‹‹ይህ እኮ ያንቺ ህይወት ነው፡፡ ስለ አንቺ መወሰን ያለብሽ  አንቺ ብቻ ነሽ፡፡ ደግሞ ሁለታችሁም የተማራችሁ ናችሁ፡፡ እኔ  የመኪና መሪ ጨብጬ ዘመኔን የምገፋ  ካንቺ የተሻለ ምን አውቃለሁ?›› አላት፡፡
‹‹አንተ ደግሞ አትሞጣሞጥ፡፡ ስትመሰገን ተቀብያለሁ ነው የሚባለው›› አለችው በመቅበጥ፡፡
‹‹አንቺ ታላቅሽ እኮ ነኝ፣ ትሰደቢኛለሽ እንዴ?››
‹‹እንዴ ዘኪ አሁን’ኮ እኔ ነኝ ታላቅህ፡፡ በቅርቡ ወልጄ ለእናቴ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ አስረክባታለሁ፡፡ በቃ ተበልጠሃል››
‹‹አቤት ጉራ›› አላት የታችኛው ከንፈሩን በሹፈት በመገልበጥ፡፡ “ይልቅ ደውይለትና አስተዋውቂን፤ ምን እንዳሰበ ከእሱ ልስማ ደግሞ››
ሰምሃል ደወለች፡፡ ስልኩ አይነሳም። ‹‹ስለደከመው ሻወር እየወሰደ ወይም ተኝቶ ይሆናል›› አላት፡፡ ደጋግማ ሞከረች፤  አይነሳም፡፡
‹‹ተይው ትንሽ ቆይተን እንደውልለታለን። በነገራችን ላይ ያቺ እሌኒ  እዚህ አገር አለች?››
ሰምሃል በሳቅ ተንከተከተች፡፡ ከካፍያው ሽሽት የተጠለሉና ካፍቴሪያው ውስጥ የሚጠቀሙ ሰዎች ዞረው አዩአቸው። ሰምሃል ሳቋን ስትለቅ ገደብ የላትም። በዚህም ምክንያት ብዙ ጊዜ ሳታጠፋ ከመምህሮቿ ጋር ተጋጭታለች፡፡
‹‹እንግዲህ የቻግኒን ቆንጆ ሁሉ እየጠየቅኽ አድክመኝ! ዳር ዳር የምትለው ስለማርታ ለመጠየቅ ነው አይደል? የሆነ ሰው አግብታ ወደ ውጪ ልትሄድ ነው እየተባለ ነው። ግን በጣም ጥሩ ልጅ ናት›› አለችው፡፡
ጭንቅላቱን ከፍ ዝቅ በማድረግ መስማማቱን ገለጸላት፡፡ ከዚህ በላይ  ስለ ማርታ መጠየቅ አልፈለገም፡፡
ሰምሃልም፤ አባ እንደሻው ባለፈው ሞቱ እኮ… እገሊት አገባች … እንትና ከሚስቱ ተፋታ… ታረቁ… በከተማዋ የተከሰቱትን አዲስ የምትላቸውን ሁሉ ተረከችለት፡፡
ዛክ አያውቀውም ብላ የምታስበውን እየሳቀች፣ ኮስተር እያለች እንደወትሮው አወራችለት፡፡ በዛክ አእምሮ ውስጥ ግን የማርታ ወደ ውጪ መሄድ ተሰንቅሮ ቀረ። ለቤተሰቡ ህልውና ሲል የልጅነት ፍቅሩን ማጣቱን የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው፡፡ ይህ ለቤተሰቤ የከፍልኩት መስዋዕት ነው በማለት ራሱን ያጽናናል፡፡
*  *  *
ዳዊት ወደ ቻግኒ ለመሄድ ሲነሳ ጓደኛው፤ ‹‹ለሴት ብርህን እንጂ ልብህን አትስጥ›› ብሎ መክሮት ነበር፡፡ ዳዊት ግን  ‹‹ሰምሃልን በደንብ አውቃታለሁ:: ለሦስት ዓመታት በፍቅር ስንኖር አንድም እንከን አላገኘሁባትም›› በማለት ሽንጡን ገትሮ ተከራክሮላታል፡፡ እዚህ ሲመጣ  ነገሩ ሁሉ ተገልብጦ ጠበቀው። ምን እንደተፈጠረ ግራ ገባው፡፡ ‹‹ምናልባት የማላውቀው የልጅነት ፍቅረኛ ሊኖራት ይችላል?›› ተጠራጠረ፡፡ ‹‹ለማንኛውም አጣርቼም ቢሆን እደርስበታለሁ›› እያለ ካፍያውን  ከቁብ ሳይቆጥረው ከራሱ ጋር ሲሟገት ነበር የሰመሀልን ሳቅ የሰማው፡፡ ለዳዊት ሳቋ ቀለቡ ነው፡፡ በሆነ ባልሆነው እያሳቃት ይደሰታል። ሰምሃል ከአንድ ወንድ ጋር ተቃቅፋ ስትሄድ፣ ስታሽካካ፣ ደረቱ ላይ ስትለጠፍ በዓይኑ በብረቱ ተመለከተ፡፡ አንጀቱ በገነ፡፡ ለመጀመሪያ  ጊዜ የሰምሃል ሳቅ አስጠላው። ክህደቷ አንገበገበው፡፡ ‹‹ለካ የእኔን ብር እየላፈች ለአጅሬው ሆኗል የምታቀብለው? ምነው ይህን ከማይ ባልመጣ --- እንደወደድኳት ብኖር›› በልቡ ተመኘ፡፡ ‹‹በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ….ለካ ጓደኛዬ እውነቱን ነበር›› እቆመበት ደርቆ ቀረ፡፡
የገጠመውን ለጓደኛው ደውሎ ሊነግረው ስልኩን እኪሱ ሲዳብስ፣ከመኝታ ቤቱ ጥሎት መውጣቱን አስታወሰ፡፡ ‹‹አሁን ምናባታቸው ላድርጋቸው፡፡ በቃ  የእኔና የእሷ ፍቅር አከተመለት፡፡ መልአክት መስላ እንዲህ ጉድ ትስራኝ!›› አጉተመተመ በጸጸት፡፡ ‹‹ለነገሩ በዓይኔ አይቼ እንዲቆርጥልኝ አስባ ይሆናል የጠራችኝ››
ዳዊት ለሰምሃል ያልሆነው ነገር አልነበረም። ህይወቱንም ቢሆን አሳልፎ ቢሰጣት አይጸጸትም፡፡ ተጋብተው፣ልጅ ወልደው፣ ለወግ ማዕረግ በቅተው፣ እንዲኖሩ ነበር ምኞቱ፡፡ አገር አቋርጦ የመጣውም ለዚሁ ዓላማ ነበር፡፡ በርሀ ለበርሀ እየተንከራተተ ያገኛትን ብር በየወሩ ከመላክ ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ ከዚያም አልፎ የዩኒቨርሲቲ ምግብ አልመቻት ሲል ‹ነን ካፌ› በማድረግ፣ እንደሀብታም ልጅ ነው አንደላቆ ያስተማራት፡፡ ‹‹ወይኔ ዳዊት! ፍየሉን እንደ በግ›› አሉ አበው፡፡ ቀስ እያለ  የሚገቡበትን ለማየት በርቀት ተከተላቸው፡፡ እንባው ሳያስበው በጉንጩ ወረደ፡፡ ካፍያውም በማልቀሱ እንዳያፍር አስቦለት ይመስል በረታ፡፡ የሰምሃልና የዘካርያስም እርምጃ ጨመረ፡፡ ወንድነቱን ተፈታተነው፤‹‹እስኪ የሚሆኑትን አያለሁ›› አለ፤በንዴት እየበገነ፡፡
ዘካርያስና ሰምሃል ከሩጫ ባልተናነሰ እርምጃ ከካፍቴሪያው ገብተው ሲቀመጡ በርቀት ተከታተላቸው፡፡
‹‹ጭራሽ  ክንዱ ላይ ተኛችበት እኮ፡፡ ሁለቱንም ገድያቸው እጄን ለፖሊስ ብሰጥ ይሻላል፡፡ የእኔ ጓደኞች ቤት ሰርተው፣ መኪና ገዝተው ሲዘንጡ እኔ እሷን ለማስተማር ላይ ታች ስል ያጠፋሁት ብር፣ የእሷ ዓይነት መቶ ልጃገረድ ይገዛልኝ ነበር፡፡ ኧረ እስስት ናት! ይቺ አጋሰስ፣ የቀን ጅብ ጋር ነበር የኖርኩት? ለካ ያ ሁሉ የፍቅር ቃላት የውሸት ነበር? ወይኔ ጓደኛዬ ምክርህን አልሰማ ብዬ›› በቁጭት በገነ፡፡ ጓደኛው ታምራት፤‹‹አገሯ ፍቅረኛ እንዳይኖራትና በኋላ ተንሳፋፊ እንዳትሆን›› ነበር ያለው በዘመኑ የ‹ቢ.ፒ.አር.› ቋንቋ። ‹‹በዚህ ዘመን አንገት ደፊ የምትላት ልጅ እንኳን ቢያንስ ሦስት ፍቅረኛ ይኖራታል። አንዱ ለገንዘብ፣አንዱ ለፍቅር፣ ሌላው ለምትፈልገው ዓላማ አለዚያም ለወሲብ። ተመልከት፤ እንኳን እነሱ እኔን አታይም። ተማሪ አለችኝ፣ ባለትዳር አለችኝ፣ የቡና ቤት ልጅ አለችኝ፡፡ እንዳንተ ፍቅር ምናምን እያልኩ ብጃጃል፣ ይሄኔ በአስማት የቆመ ፓስታ እመስል ነበር››፡፡
‹‹ተንሳፋፊ እንዳታደርግህ›› የጓደኛውን ንግግር ቃል በቃል ደጋገማቸው፡፡ ‹‹እውነትህን ነው ተንሳፋፊ አደረገችኝ፤ ደሟን ነው የምመጠው ይቺ ውሻ!››
ዙሪያ ገባውን ሲመለከት አንድ ቁራጭ አጣና አገኘ፡፡ አነሳው፡፡ እነሱ ከአንድ ጥግ ስር ሆነው በነጻነት ይሳሳቃሉ፡፡ ‹‹ይሄ ይሆናል ድንግልናዋን የወሰደው›› አለ ቃላት አውጥቶ ጥርሱን በንዴት እያንቀጫቀጨ፡፡ ሁለቱንም ከገደለ በኋላ ራሱንም ለማጥፋት ወሰነ፡፡ እርምጃውን ጨምሮ፣ በብስጭት እንደ ኤርታአሌ እሳተ ጎሞራ እየተንተከተከ፣ ሰምሃልና ወንድሟ ወደተቀመጡበት ወንበር አመራ፡፡ …
(ከአዲስ አድማስ ድረገጽ ተወስዶ በድጋሚ ለንባብ የበቃ፤Saturday, 17 October 2015)

Read 1300 times