Print this page
Saturday, 05 February 2022 12:43

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

 ምንሽን ወድጄ ነው?

መተት ይሁት ምትሃት - የነካኝን እንጃ
ወሰድ መለስ አርጎ - በኑሮ መሄጃ
ወዝውዞ ሲጥለኝ - እንደ ደረቅ ቅጠል
ደጃፍሽ ላይ ጣለኝ - ፍቅር ይሉት በደል!
በገዛ ጤናዬ - እብደት አስለምጄ - ቀልብ እንዳጣሁልሽ
ገና መች አወኩኝ............................
ምን...ሽ ድል አድርጎኝ - እንደወፈፍኩልሽ!
ከለበስሽው ሥጋ - ከሚታየው ገጹ
ከፊትና ኋላሽ - ከቁመናሽ ቅርጹ
ምን ልጥቀስ ከመልክሽ - የቱ ነው የጣለኝ?
የትኛው ግብርሽ ነው - ከራስ የነጠለኝ?
ዝናብ መሀል ቆሜ - ሙቀት እያላበኝ
ቀኔን ሰውቼልሽ - እድሜ እየቸገረኝ
ከእንጦጦ ተራራ - ቃሊቲ ላገኝሽ - በእግሮቼ እያመራሁ
ምንሽን ወድጄ ነው? .............................
የቤት እብድ ሆኜልሽ - ከፎቶሽ ጋር ሆኜ - ለብቻ ማወራው?
እንደ ላባ ትራስ - ለስላሳው ሰውነት
የዳበስኩት ገላሽ - ያ የምድር ገነት
የሳሮን አበባ - ወዝሽ የቀለመኝ
እንደ ባህር ውሃ ....................
ትዝታሽ አዳፍቶ - አንስቶ ሚጥለኝ
በድን አካል ይዤ ................
ደርሶ እንደ ጤነኛ - ልዝናና ያሰብኩት
ምንሽን ወድጄ ነው ?................
በኔ ደሀ ገላ - አለሁኝ እያልኩኝ - ግማሽ ሞት የሞትኩት?
እፍንፍን አድርጎ ..................
አጥብቆ ባቀፈኝ - ክንድሽ ስር ተኝቼ
ጣትሽ ሲዳብሰኝ - ይህን ዓለም ትቼ
ከንፈርሽ ሲስመኝ ....................
በሰመመን ዓለም - እግዜሩን ረስቼ
በህይወት ዘመኔ ......................
እንደዚህ በቁሜ - እኔ አላውቅም ሞቼ!
ስምሽን በቁልምጫ - ከንፈሬ ላይ ጽፌ
በርሽ ላይ ምቆመው - የኔን በር አልፌ
መሄጃና መምጫው - ሲጠፋብኝ ውሉ
የሰፈሬ ህጻናት .....................
አበደ እያሉ - በኔ ቁዘማ ላይ - ይወራረዳሉ
ይሄ ሁሉ እዳ - በላዬ ሚወርደው
ከሰው ዝቅ ያልኩልሽ - ምንሽን ብወድ ነው ?
እንደ ሄኖስ ፊደል - ጠፈር ላይ የሳልኩሽ
እንደ አክሱም ቀርጬ - ልቤ ላይ የጣልኩሽ
እንደ ፋሲል አጥር - ስሜ ላይ የጻፍኩሽ
መሀላ ስገባ ..................
የኔን ስም ረስቼ - ባንቺ ስም የማልኩሽ
ዥንጉርጉር ገጽሽን ..............
ብዙ አመልሽን ……………..
በቁስል ትከሻ - በአንቀልባ ያዘልኩሽ
ምንሽን ወድጄ ነው - ብዬ እየጠየኩ
ይህን ሁሉ መስመር - ግጥም እያወረድኩ
በጥያቄ ናዳ - አልደክምም እቴዋ
አንዴ አይጣል እንጂ - እንደ ሳምንት ጽዋ
ሰው እጁን ከሰጠ - ልቡ ከተነካ
ቀፎ ነው አካሉ - እንደ ማንኪያ ሹካ
ፍቅር ድል ያረገው .................
መች መስፈርት ይቆጥራል?....
እንደ ምስር ስፍር - ሚዛን እየለካ?
(ነፃነት አምሳሉ አፈወርቅ)

Read 1834 times
Administrator

Latest from Administrator