Saturday, 12 February 2022 12:10

እጀባ...በ‘ባዶ ሜዳ!’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

--ልብ ብላችሁ እንደሆነ የሆነ የስብሰባው ተካፋይ ‘ሀሳብ’ ያለውን ነገር ከተናገረ በኋላ የሚቀርበው ድጋፍ ለሀሳቡ ሳይሆን ለሰውየው ነው የሚመስለው፡፡ “ከእኔ ቀድሞ የተናገሩትን ተሳታፊ ሙሉ ለሙሉ እደግፋለሁ፣” ይባላል አንጂ...አለ አይደል...#ቀደም ብሎ የቀረበውን ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ እደግፋለሁ...” ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ!--;
               
               እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...ሴኔጋል በማሸነፏ የተደሰተውን ህዝባችንን ስታዩ ይቺ ግብጽ ስለሚሏት ሀገር ያለውን ስሜት ነው የምትረዱት፡፡ እንጂማ... ሴኔጋል የምትባለው ሀገር የት ትሁን የት የምናውቅ ምን ያህል እንደምንሆን ራሱ አጠያያቂ ነው። ግን አወቅናትም፣ አላወቅናትም መልካም ነገር መስማት እየናፈቀን ባለበት ሰዓት እነ ማኔ አንጀታችንን ስላራሱልን፣ አንድዬ አንጀታቸውን ያርስላቸውማ!
እናማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...መጀመሪያ ላይ ፍጹም ቅጣት የተሰጠ ጊዜ ሳላህ በረኛውን ሲመክረው ማኔ ሄዶ እንደማቋረጥ ያለው ነገር ምን ይመስለኛል መሰላችሁ... “ፍጹም ቅጣት ምት እንዴት እንደምመታ ስለሚያውቅ ሹክ እያለው ነው፣” ብሎ ይመስለኛል፡፡ ደግሞም በረኛው ያለብዙ ችግር የማኔን ምት ማዳኑን ስታዩ፣ ግብጻዊው መሀመድ ሳላህ ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔ የሊቨርፑል ቡድን ጓደኛውን ዘዴውን አሳብቆበት መንገድ ላይ እንዳሰጣው ትጠረጥራላችሁ፡፡ ግብጽን ወደድንም ጠላንም ሳላ ማኔን በዘዴ ሹክ ብሎ ከሆነ ነገርዬው... አለ አይደል... “ከሀገር የሚበልጥ ነገር የለም” ነው፡፡
ስሙኝማ...ጨዋታ ካለቀ በኋላ ሳድዮ ማኔ ለሳላህ በጆሮው ምን ብሎት ይሆን ማለቱ ሊከብድ ይችላል፡፡ አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ እንደምናየው ከማጽናኛ ውጪ የሆነ ነገር ነው ብሎ ማሰቡ አሪፍ አይደለም፡፡ እነሱ ፕሮፌሽናሎች ናቸው፣ ከአፍሪካ ዋንጫ በኋላም ህይወት ይቀጥላል፡፡ ዘጠና ደቂቃ ሲጫወቱ ውለው ቢያሸንፉም፣ ቢ,ሸነፉም ሰላምታ ሳይሰጣጡ ሜዳ ጥለው ለሚወጡ የሀገራችን ተጫዋቾች ምሳሌ ነው፡፡
ቲም ሳላህና ቲም ማኔ... በፍጹም ቅጣት ምት ቢለያዩም፣ ያው በጨዋታው ግብጾቹ በተለይ በመጀመሪያው ግማሽ ተበልጠው ነው ያየነው፡፡ እናላችሁ... መቼም የየትኛውም ሀገር ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ቢሆኑ “ሀገራችን ይዘናት እንገባለን” ብለው እርግጠኞች የሆኑባት ዋንጫ  ከዓይናቸው ስር ላፍ ስትደረግ ሆዳቸው መባባቱ ያው ተፈጥሯዊ ነው። የግብጾቹ ለቅሶ ግን አልበዛባችሁም! አለ አይደል...የተወሰደባቸው ዋንጫ ሳይሆን ሀገር ነው እኮ ያስመሰሉት...ያውም ሴኔጋሎች ያንን ሁሉ ጎል ስተው!
እናማ... ‘ድራማዋ’ ትንሽ የበዛችብን ስለመሰለን ነው፡፡ ለነገሩ...ካይሮ ላይ አል ሲሲ ዓይናቸው ቀልቶ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማን ያውቃል! ያውም ከስድሳ ሺህ በላይ የፖለቲካ እስረኞች አሉባት በምትባል ሀገር፡፡ ስለሆነም የግብጽ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በመሸነፋቸው ልባቸው ተሰብሮ ቢያለቅሱም፣ ‘ከኮታ በላይ’ ያለቀሷት ግን ምን ያህል ልባቸው እንደተሰበረ ለአለቆቻቸው ማሳያ ሳትሆን አትቀርም፡፡
(ለነገሩ የእኛዎቹም እኮ እንደአቅሚቲ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ግንማ... ለአንዳንዶቻችን ‘ግልጥና ግልጥ’ ያልሆነው ነገር ይቅርታ የተጠየቀው “የችሎታችንን ያህል አልተጫወትንም፣” ነው፣ ወይስ “አቅማችን እዚህ ድረስ ስለሆነ ምን እናድርግ!” ነው?” ነው!)
እኔ የምለው ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...... ምን መሰላችሁ...እዚህ ሀገር የ‘ባዶ ሜዳ’ አጃቢነት አልበዛባችሁም! ለምንፈልገው ወገን፣ ግለሰብም ይሁን ቡድን፣ አንደኛው የታማኝነት ማሳያ ሙሽራና ሙሽሪት በሌሉበት አጃቢነት ሆኖላችኋል፣ የ‘ባዶ ሜዳ’ ጭብጫቦ ሆኖላችኋል፣ ስር፣ ስር እየተከተሉ “ሆ! ሆ!” ሆኖላችኋል፡፡ እናላችሁ... የታማኝነት ማሳያ አጀብ ነገሮችን ቀሺም እያደረጋቸው ነው፡፡
የምር ግን አጀብ የሚያምረው የተለየ ቅጥልጥሎሽ ሰበቦች የማያስፈልጉት ሠርግ ሲሆን ነው፡፡ ልክ ነዋ.... ጸጥ ብሎ የዋለው አዳራሽ ቀውጢ የሚሆነው ሁለት ሰዓት አሳልፈው የመጡት ሙሽሮችን አጅቦ በሚመጣው የአጀባ ግብረ ሀይል ነው። ደግሞ ሙሽሮች ሁለት ሰዓትም አረፈዱ አራት ሰዓት “ሀይ ሎጋ” እየተባለ ቪዲዮው ደስ አይልማ!
እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...አንድ ሰሞን ሰርግ ያሳምራሉ የተባሉ አጃቢዎች ትንኮሳ ሲያበዙ የነበረው ትዝ ይላችኋል፡፡ እስቲ አስቡት በሰላም በወዳጄ ሰርግ ልታደም ብለው ሄደው፣ ልክ ሙሽሮች ሲገቡ “ይበላሀል ጅቦ!” ብሎ እጀባ ትንኮሳ ካልሆነ ምን ይሆናል! ኮሚክ እኮ ነው፡፡ “እየሰበረ ሰጠው ለአሞራ!” ካሉ በኋላ “የአብረሀምና የሳራ ጋብቻ ያድርግላችሁ; ማለት ትንሽ አያስቸግርም! “አቧራው ጨሰ!” በሚል አጀብ የሚሞሸሩ እሱና እሷ፣ በሁዋላ ጎጇቸው ውስጥ አቧራው ቢጨስ የማን ያለህ ሊባል ነው! አሀ... “እየሰበረው ሰጠው ለአሞራ...” እየተባለ የተጨፈረበት ሰርግ...አለ አይደል... “ማነው ሰባሪው ማነው ተሰባሪው?” የሚል ሞገደኛ ጠያቂ ሊመጣም ይችላል፡፡ “በአንድ በኩል አለቃዬ፣ በሌላው ባል ተብዬው እየፎከሩብኝ መግቢያ፣ መውጫ አሳጥተውኛል፤ ጭራሽ ልደሰት፣ አእምሮዬን ላሳርፍ ብዬ የመጣሁበት ሰርግ ላይ ‘እየሰበረው ሰጠው ለአሞራ...’ ይሉብኛል የምትል ተጋባዥ ማነው ካሣ የሚከፍላት! ቂ...ቂ...ቂ...
በነገራችን ላይ...አለ አይደል... አንዲቷ ቃል አንድ መቶ አስራ አንድ ጊዜ በምትበጣጠስበት በዚህ ዘመን አንዳንድ የሰርግ ዘፈኖች ስንኞች ይሻሻሉልንማ! ልል ነዋ...ለምሳሌ “እየበሉ እየጠጡ ዝም፣ የጋን ወንድም...” የምግብ ለሥራ አይነት ሊመስል ይችላላ፡፡ “ያበላናችሁ፣ ያጠጣናችሁ እንድትጨፍሩ ጉልበት እንዲሆናችሁ ነው እንጂ ተርፎን መሰላችሁ እንዴ!” አይነት ሆኖ ሊተረጎም ይችላላ! (አሀ...ነገ እኮ እንዴት እንደምናስነጥስ ሁሉ ትርጉም ቢበጅለት አይገርምም ለማለት ምንም አልቀረንም እኮ። ፈረንጅ “ኢትስ ዛት ባድ!” እንደሚለው ነው፡፡)
እናማ “እየበሉ እየጠጡ ዝም...” ወይ ግጥምዬው ይነካካ፣ ወይ ደግሞ ጥሪው ወረቀት ላይ የሚጠበቅብን በግልጽ ይስፈርልን፡፡ “በሰርጋችን ላይ ለመዝፈንና ለመጨፈር ተዘጋጅተው ለሚመጡት እንግዶቻችን ጉልበት እንዲሆናቸው ምግብና መጠጥ መዘጋጀቱን ስንገልጽ በደስታ ነው፣” አይነት ይባልልንማ! አለበለዛ “እየበሉ እየጠጡ ዝም...” በተባለ ቁጥር “ይቺ ነገር እኔን ለማለት ፈልገው ነው...” እያልን ለምን እንሳቀቃለን! ቂ...ቂ...ቂ...
እናላችሁ...የሰርጉስ ይሁን፣ በሌሎች ነገሮች ለመታየትና፣ ታማኝነትን ለመግለጽ በባዶ ሜዳ የአጃቢነቱን ሚና የምንወስድ እየበዛን ነው ችግር የሆነብን፡፡ አለ አይደል...ብዙ ስብሰባዎች ለምን የሚደብሩ ይመስለኛል መሰላችሁ... አጀቡ ለሀሳቦች ሳይሆን ሀሳብ ለተባለው አቅራቢዎች መሆኑ። እናንተ ሀሳቦችን ለማዳመጥ ሄዳችሁ ግለሰቦች ሲወዳደሱ ለመስማት ሦስት ሰዓት ሙሉ  መቀመጥ አሪፍ አይደለማ!
እናማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ዝም ብሎ በባዶ ሜዳ የ“ሆ! ሆ!”  አጃቢነት ቀሺም ነገር አይመስላችሁም! እኔ የምለው የሚጨበጥ ሀሳብ የሚባል ነገር በሌለበት፣ እዚህ ግባ የሚባል ነገር በሌለበት በባዶ ሜዳ “ሆ! ሆ!” ማለት እንደው የተበላው እንጀራ ‘ደረት ላይ አይንተከተክም!’ ልክ ነዋ... እንጀራው አፍ ቢኖረው ኖሮ... “ቀን ማታ ስትጠቀጥቀኝ ዝም የምለው እኮ አእምሮህን ልታሰፋ፣  አስተሳሰብህን ልታዳብር ሀይል የምሆንህ መስሎኝ እንጂ ለባዶ አጃቢነት ነበር እንዴ ‘ማኛ፣ ሰርገኛ፣’ እያልክ መከራዬን ስታበላኝ!” የነበረው ይል ነበር፡፡ ግን እኮ አጃቢነቱ በአብዛኛው የሀሳብና የእምነት መመሳሰል ጉዳይ ሳይሆን የእንጀራ ማግኛና መሶብ የመሙያ እየሆነብን ነው የተቸገርነው!
ልብ ብላችሁ እንደሆነ የሆነ የስብሰባው ተካፋይ ‘ሀሳብ’ ያለውን ነገር ከተናገረ በኋላ የሚቀርበው ድጋፍ ለሀሳቡ ሳይሆን ለሰውየው ነው የሚመስለው፡፡ “ከእኔ ቀድሞ የተናገሩትን ተሳታፊ ሙሉ ለሙሉ እደግፋለሁ፣” ይባላል አንጂ...አለ አይደል...#ቀደም ብሎ የቀረበውን ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ እደግፋለሁ...” ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ! እናማ...“እሳቸው በተናገሩት ላይ የምጨምረው የለኝም...” ከተባለ በኋላ ሃያ አንድ ደቂቃ ከሠላሳ ሴኮንድ ማይክ የሙጥኝ ማለት...አለ አይደል...አብዛኛውን ጊዜ አጀባ ነው፡፡  እናላችሁ...ሚጢጢዬ ቡቺ ውሻ በሌለችበት “ይበላሀል ጅቦ” አይነት እጀባ ልብ ለልብ አያቀራርብም፡፡ እናላችሁ በሚያሳዝን መልኩ ዘንድሮ ምንም አይነት የሚጨበጡ ሀሳቦች፣ ወይም አሳማኝ ምክንያቶች የሌሉባቸው ‘ጎሳንና ጎሳን ብቻ ያማከሉ አጀቦች፤’ ‘የሀር ልጅነት አጀቦች፤’ ‘የመንደርተኝነት አጀቦች፤’ ”የሀይማኖታዊ እምነቶች አጀቦች፤” ብቻ...ምን አለፋችሁ...አንዳችም አሳማኝ ምክንያት የሌላቸው እርስ በእርስ በመጠቃቀም፣ ወይም የራስ ያልሆኑ ወገኖችን በመጥላትና በመሳሰሉት በአንድ ሺህ አንድ መልካም ያልሆኑ ሰበቦች የሚፈጠሩ አጀቦች ለማንም ምቾት እየሰጡ አይደሉም፤ ወደፊትም የሚሰጡ አይደሉም!
አንድዬ፣ ይቺን ሀገር “በቃሽ!”፣ ህዝባችንን “በቃህ!” ይበልልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1914 times