Saturday, 12 February 2022 12:31

የተስተጉዋጎለ ምጥ፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

   Obstructed Labor በአማርኛው የተስተጉዋጎለ ምጥ የሚባለው በአብዛኛው በሳይንሳዊ አጠራሩ cephalo-pelvic disproportion, Malposition በሚባሉ ችግሮች ምክንያት የሚከሰት ነው፡፡ obstructed Labor ወይም የተስተጉዋጎለ ምጥ ማለት ጽንስ በመወለጃው ወቅት በምጥ እየተገፋ ሳለ ነገር ግን በመስመሩ ማለፍ እና መወለድ ሳይችል ሲቀር የሚገለጽበት ነው፡፡ ምጥ የሚስተጉዋጎልበትን ምክንያት ባለሙያዎች እንደሚገልጹት Power-ኃይል እና Passenger-ተሳፋሪ እንዲሁም Passage- መተላለፊያው በሚል ይገልጹዋቸዋል፡፡
Power…ልጅን ለመውለድ ደካማ የሆነና ያልተቀናጀ የምጥ ሁኔታ ወይንም የማህጸን መኮማተር ካለ ለተስተጉዋጎለ ምጥ እንደ አንድ ምክንያት ይሆናል።
Passenger … ጽንስ እንደተሳፋሪ የሚቆጠር ሲሆን በመወለጃው ሰአት ወደሚወለድበት መስመር ለመግባት ጭንቅላቱ ትልቅ ወይንም የጽንሱ አቀራረብ በትክክለኛው መንገድ ካልሆነ እና በእናትየው ዳሌ ማለፍ ካልቻለ ምጡን የተስተጉዋጎለ ያደርገዋል፡፡
Passage … ልጅ የሚወለድበት መስመር መተላለፊያ ነው፡፡የሴትየዋ ዳሌ ጠባብ ከሆነ እና ጽንሱ ያልተስተካከለ ቅርጽ ካለው ወይንም በአካባቢው እንደ ቲዩመር ያለ ሌላ እንቅፋት የሚሆን ነገር ካለ ለተስተጉዋጎለ ምጥ ይዳርጋል፡፡
በወሊድ ወቅት በምጥ የተያዘች ሴት በትክክል ልትረዳ ከምትችልበት ባለሙያ እጅ ወይንም የጤና ተቋም ካልሆነች ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት በወሊድ ወቅት ለህልፈት ወይንም ለህመም የመዳረግ እድልዋ ሰፊ ነው፡፡ በተፈጥሮአቸው አጫጭር ቁመት ያላቸው እና በህጻንነታቸው የተመጣጠነ ምግብ ያላገኙ ሴት ልጆች የተራዘመ ወይንም የተስተጉዋጎለ ምጥ በህይወት ዘመናቸው ሊገጥማቸው ይችላል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በ1995 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ቁመታቸው አጫጭር የሆኑ ሴቶች ከረዣዝሞቹ በ60 % ያህል ልዩነት ለተራዘመ ወይንም ለተደናቀፈ ምጥ ተዳርገዋል፡፡ የእናቶች ሞት የሚከሰተውም በአብዛኛው በተራዘመ ምጥ ጊዜ በማህጸን መፈንዳት ወይንም በወሊድ ጊዜ በሚከሰት ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ ሳቢያ መሆኑን Science direct የተሰኘው ድረገጽ ያስነብባል፡፡  በወሊድ ጊዜ ሞት የሚደርሰው በተራዘመ ወይንም በተደናቀፈ ምጥ ምክንያት እርጉዝዋ ሴት በህክምና እርዳታ ካላገኘች ወይንም በአፋጣኝ በቀዶ ሕክምና አገልግሎት መረዳር ካልቻለች ነው፡፡
ኢትዮጵያ የእናቶችና በወሊድ ወቅት የሚደርስ የሞት መጠን በአለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ከተመዘገበባቸው አገሮች መካከል ናት ፡፡ የዚህም ምክንያቶች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ አንዱ ሲሆን በተለይም በገጠር ከህክምናው አገልግሎት እርቀው የሚገኙ እና በማህጸን ላይ የሚደርስ ውስብስብ የሆነ የጤና ችግርን ለመከላከል አስቸጋሪ በሆነበት የሚደርስ መሆኑ ተጠቃሽ ነው፡፡ የወላድዋ የማህጸን አካባቢ ወይንም ዳሌ ጥበት እና የህጻኑ ጭንቅላት ወይንም ክብደት መጠን አለመመጣጠን ምክንያት በሚደርሰው የተስተጉዋጎለ ምጥ ምክንያት የሚፈጠረው ችግር ኢንፉክሽን፤ የደም መፍሰስ፤ የማህጸን መፈንዳት፤ ፊስቱላ፤ የእናት ሞት፤ እንዲሁም የጽንስ መታፈንና ሞት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
cephalopelvic disproportion (CPD) በሚል የሚጠራው ይህ ችግር በሚወለደው ጽንስ ውፍረት ወይንም የጭንቅላት ትልቅነት የሚከሰተው ብቻ ሳይሆን በተለይ የአንዳንድ ሴቶች የማህጸን አካባቢ የዳሌ ጥበት እና ምንም ያህል ምጥ ቢገፋ ልጅን ለማሳለፍ የማይችል ሲሆን ነው፡፡ ይህ አይነት ችግር በተለይም ከህክምናው አካባቢ እርቀው የሚገኙ ሴቶች ወደ ሕክምናው ጣቢያ እስኪደርሱ ድረስ በሚደርሰው አስከፊ ምጥ ምክንያት ማህጸናቸው አስከመፈንዳት የሚደርስ እና ለሞት የሚዳርጋቸው ሲሆን ህጻኑም በመታፈን ምክንያት ህይወቱን ያጣል፡፡
cephalopelvic disproportion (CPD) የተባለውን ችግር ከሚያስከትሉት ምክንያቶች በሚል httpa://americanpregnancy.org የሚከተሉትን አስነብቦአል፡፡
በተፈጥሮው ወይንም ከዘር በተወረሰ ምክንያት፤ በስኩዋር ሕመም…ወዘተ በመሳሰሉት ምክንያቶች ህጻኑ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ሲኖረው፤
ትክክለኛ ያልሆነ የጽንስ አቀማመጥ፤
ጠባብ የሆነ የዳሌ አጥንት፤
የዳሌ አጥንት በትክክል ቅርጹን ያልያዘ ወይንም የተበላሸ ፤ ያልተስተካከለ ቅርጽ ካለው፤  
cephalopelvic disproportion (CPD) የተባለውን ችግር እና በዚያም የተራዘመ ምጥ እንዲከሰት ምክንያት ይሆናል፡፡
ይህ ችግር ከመድረሱ በፊት የእርጉዝዋ ሴት አካላዊ ተፈጥሮ በምርመራ መታወቅ ያለበት ሲሆን አስቀድሞውኑ ከታወቀ ልጁ የመወለጃው ወቅት ሲደርስ በአፋጣኝ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ህጻኑንም እናትየውንም ማትረፍ ይቻላል። ይህንን አስቀድሞ የማወቅ ሁኔታ አሰራሩ ስለሌለ በተለይም በገጠር አካባቢ ለሚኖሩ ሴቶች አደገኛ የሚባል ሲሆን በከተማውም ቢሆን ለቀዶ ሕክምናው ውሳኔ የሚሰጠው በምጥ ለመውለድ አስቸጋሪ ሲሆን እንጂ ይህች ሴት አካልዋ ልጁን ለማሳለፍና ለመውለድ የሚያበቃ መጠን የለውም ከሚል ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከUSAID and the US National Institute of Health ባገኘው ድጋፍ ይህ ችግር በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምን ይመስላል የሚለውን ለማወቅ የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ላይ ነው፡፡ የዚህ ጥናት ጥቅም አንዲት ሴት የመውለጃዋ ቀን ከመድረሱ አስቀድሞ የሰውነትዋ መጠን ታውቆ ቅድሚያ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ዝግጅት እንዲደረግ ጠቋሚ ሀሳቦችን ለማቅረብ የሚያስችል ነው ፡፡
ይህ ፕሮጀክት የዳሌ አፈጣጠርን በቀላሉ ሊባል በሚችል ቴክኖሎጂ ልጅ በመውለድ እድሜ ላሉ ሴቶች አስቀድሞውኑ የተፈጥሮ ሁኔታን ለማወቅ የሚያስችል እድል እንዲሰጥና በወደፊት የወሊድ ወቅት የህክምናው አገልግሎት ሊደርስ የሚችልን ችግር አስቀድሞ መፍታት የሚያስችል አሰራርን ለመዘርጋት እድል የሚሰጥ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ስራ ላይ ውሎ ሲጠናቀቅ የትኛዋ ሴት ምን አይነት የምጥ ሁኔታ ሊገጥማት ይችላል የሚለውን አስቀድሞ ለመዘጋጀት የሚያስችል በአይነቱ አዲስ የሆነ ፤በአቅም የሚስተናገድ እና ለአጠቃቀም ቀላል የሆነ፤እንደልብ የሚንቀሳቀስ መሳሪያን በመጠቀም በ CPD. ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ሞት ማስቀረት ይቻላል የሚል እምነት አለ፡፡
ይህንን ውጥን ከዳር ለማድረስ ጥናቱ የሚካሄድባቸው የስራ ተቋማት በሆስፒታሎችና በጤና ጣቢያዎች ሲሆን እነሱም የሚከተሉት ናቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጥቁር አንበሳ Specialized Referral ሆስፒታል፤በትግራይ መቀሌ
ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ኮሌጅ እና አይደር Referral ሆስፒታል፤በአማራ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፤ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዛቦች ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና Referral Teaching ሆስፒታል፤ በምስራቅ ኦሮሚያ አዳማ አጠቃላይ ሆስፒታል እና Medical ኮሌጅ፤በምእራብ ኦሮሚያ ጂማ ዩኒቨርሲቲ Specialized  ሆስፒታል፤ናቸው፡፡
የተራዘመ ወይንም የተስተጉዋጎለ ምጥ በተለይም በዳሌ መጥበብ ምክንያት የሚደረገው ምርመራ እርግዝናው እንደተከሰተ ጀምሮ ባለው የክትትል ጊዜ የእርጉዝዋን ሴት ዳሌ መጠን ከተለያየ አቅጣጫ ዘመኑ በፈጠራቸው ቴክኖሎጂዎቸ  በመታገዝ ማወቅ ትልቁ ተግባር ይሆናል፡፡ የልጁን መጠንም ለማወቅ እንደአልትራሳውንድ ያሉ መሳሪያዎች እገዛ ያደርጋሉ።
በኢትዮጵያ ይህን ችግር ለማስወገድ እንዲያስችል አንዲት ሴት የእርግዝናዋ ጊዜ ከ12-42 ሳምንት በሚሆናት ጊዜ  ለምርመራው ስራ ላይ እንዲውሉ የታቀዱት መሳሪያዎች 3D- Kinect Camera… 3D- Structure camera…እና traditional tape measurement የተባሉ ሲሆኑ እነዚህንም በቀላሉ መጠቀም ስለሚቻል በተለያዩ መስተዳድሮች በስራ ላይ እንዲውሉ የጥናቱ ውጤት ይጠበቃል፡፡ በዚህም በተራዘመ እና በተስተጉዋጎለ ምጥ ምክንያት የሚያልፈውን ሕይወት እና የሚደርሰውን ሕመም ማስቀረት ይቻላል የሚል እምነት አለ፡፡

Read 22811 times