Monday, 14 February 2022 00:00

የፔሩ ፕሬዚዳንት በ6 ወራት 4 ካቢኔ መስርተዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ለኬንያው መሪ ዘመናዊ መኪና መግዣ 2.6 ሚሊዮን ዶላር ተጠይቋል

             ከ6 ወራት በፊት ወደ ስልጣን የመጡት የፔሩው ፕሬዚዳንት ፔድሮ ካስቴሎ ከሰሞኑ ካቢኔያቸውን ለ4ኛ ጊዜ እንደገና በመመስረት ለ3 ቀናት ብቻ በስልጣን ላይ በቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሚርታ ቫስኩዌዝ ቦታ አኒባል ቶሬስን መሾማቸው ተነግሯል፡፡
በፔሩ የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የአገሪቱን ካቢኔ በተደጋጋሚ ለማፍረስና ለመመስረት ምክንያት መሆኑን የዘገበው ሮይተርስ፤ ለ3 ቀናት ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሚርታ ቫስኩዌዝ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በፖሊስ ሃይል አስተዳደር ጉዳይ  ባለመስማማታቸው ሳቢያ በቅርቡ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውንና ፕሬዚዳንቱም በቦታቸው አኒባል ቶሬስን መሾማቸውን እንዲሁም ሌሎች የካቢኔ ለውጦችን ማድረጋቸውን አመልክቷል፡፡
አገሪቱ በ2020 ብቻ በአምስት ቀናት 3 ፕሬዚዳንቶችን መቀያየሯንም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የኬንያ ፓርላማ ሰሞኑን በሚያደርገው የበጀት ማሻሻያ ውሳኔ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ዘመናዊ መኪኖችን ለመግዣ የሚውል 2.6 ሚሊዮን ዶላር እንዲያጸድቅ የውሳኔ ሃሳብ መቅረቡን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ፓርላማው ለፕሬዚዳንቱ ቢሮ የሚይይዘው በጀት ከአምናው የ47.7 በመቶ ጭማሪ እንዲኖረው መጠየቁን የጠቆመው ዘገባው፤ ለኡሁሩ ኬንያታ የሚመደበው የነዳጅ ወጪም በአራት እጥፍ ያህል በመጨመር 870 ሺህ ዶላር እንዲሆን የውሳኔ ሃሳብ መቅረቡን አመልክቷል፡፡
ከመንግስት ካዝና 1 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎ የፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ቤት በዘመናዊ መልኩ እንዲታደስ መጠየቁንና ፓርላማው የበጀት ማሻሻያውን ያጸድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2597 times