Wednesday, 16 February 2022 00:00

ሰሜን ኮርያ አለምን የሚያስደነግጥ የሚሳኤል ሙከራ አደርጋለሁ አለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ባለፈው ወር ብቻ ሰባት ያህል የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራዎችን ያደረገችው ሰሜን ኮርያ ባለፈው ማክሰኞ ደግሞ፣ አሜሪካን ድምጥማጧን ማጥፋት የሚችል የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ በማድረግ አለምን በድንጋጤ ክው አደርጋለሁ ማለቷን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የሰሜን ኮርያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ አገሪቱ ከአዲሱ የፈረንጆች አመት መባቻ ጀምሮ በተደጋጋሚ እያደረገቻቸው ያሉት የሚሳኤል ሙከራዎች የጦር ሃይል አቅሟን ለተቀረው አለም የሚያሳዩ ናቸው፡፡
በአለማችን ውስጥ ከሚገኙት ከ200 በላይ አገራት ውስጥ የሃይድሮጅን ቦምብ፣ አህጉር ተሻጋሪ ባላስቲክ ሚሳኤልና ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ያላቸው እጅግ ጥቂቱ ብቻ ናቸው ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ ባለፈው ማክሰኞ የተመሰረተበትን በዓል ያከበረው የሰሜን ኮርያ ጦር ግን እነዚህን መሳሪያዎች ከአፍ እስከ አፍንጫው መታጠቁን አመልክቷል፡፡
አሜሪካ ባለፈው ሰኞ ለሰሜን ኮርያ ባስተላለፈችው መልዕክት፣ ለኒውክሌር የጦር መሳሪያዎችና ለሚሳኤል ምርምርና ምርት የምታወጣውን ከፍተኛ በጀት ህዝቧን ለሚጠቅም ነገር እንድታውለው መምከሯን ያስታወሰው ዘገባው፤ አሜሪካ በሰሜን ኮርያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ባለፈው ሳምንት ያቀረበችውን የውሳኔ ሃሳብ ቻይና እና ሩስያ እንዳዘገዩባት አመልክቷል፡፡

Read 1340 times