Saturday, 12 February 2022 12:41

ደመ መራሩ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(7 votes)

  ‹‹ልጄ ደምህ መራር ነው›› ብለው ነበር እናቱ፡፡ ወንድምና እህቱ የተማከሩ ይመስል በአንድ ላይ ከግራና ከቀኝ እንደ ቢንቢ በጥፊ ሲጨፈልቁት አይታ፤ ብዙ ጊዜ ተዉ ብላ ይዛቸዋለች፡፡ በአለንጋ ገርፋቸዋለች፡፡ ለምን ታናሽ ወንድማቸው ላይ እንደሚጨክኑ አታውቅም፡፡ ምክንያት የላቸውም ለጥላቻቸው፡፡ በቃ… ምቱት ምቱት ያሰኛቸዋል፡፡ አያቱ አይናቸው በመድከሙ ምክንያት ከቦታ ቦታ እጃቸውን ይዞ የሚመራውም፣ የሚላላከውም ይኸው ታናሽየው ነበር፡፡ ያልተተፋ ምራቅ ሳይደርቅ የተላከበት ደርሶ ይመጣል። ማንም ቢልከው የትም ቢልከው ‹እሺ› ብሎ ይሮጣል፡፡ ሲመለስ፤ የላከው ሰው ኩርኩም ያቀምሰዋል። አቅማሹ፤ ለምን?... ተብሎ ሲጠየቅ መልስ የለውም፡፡ እሱም አያለቅስም፡፡ አያቱ ብቻ ይወዱታል፡፡ ግራ እና ቀኝ ጫማቸውን ሁሌ አዟዙረው ነው የሚጫሙት፡፡ እሱ፤ ሁሌ ሳይሰለች ግራውን ወደ ግራ፣ ቀኙን ወደ ቀኝ ያስተካክልላቸዋል።
‹‹በጣም ያናድደኛል›› ትላለች እህቱ፡፡
ምሳ ሲቀርብ፤ አያቱ አይናቸውን ጨፍነው ይፀልያሉ፡፡ ከእሳቸው ጋር ይፀልያል። አይኑን ሲገልጥ እህቱና ወንድሙ ፊቱ የተጨለፈለትን ቀይ ስር በልተው ሲሳሳቁ ያገኛቸዋል፡፡ አያቱ ፊት የተጨለፈላቸውን  ግን አያትየው አይናቸውን በገለጡበት ነው የሚበሉባቸው፡፡ አያት አይናቸው ሲገለጥም እንደተጨፈነ አያዩም፡፡ የደከመው አይናቸው ጠፍቷል፡፡ እሳቸውም ሞቱ፤ የጫማቸውን ግራና ቀኝ ሳይለዩ፣ የመንገዳቸውንም፡፡ እሱም የተዛነፈን ጎንበስ ብሎ እያስተካከለ አደገ፡፡
ተማረ፤… ተማሪዎቹም አስተማሪዎቹም አይወዱትም ነበር፡፡ ስራ ያዘ፤ አሰሪውም ሰራተኛውም ይጠላዋል፡፡ የወደቀ ቁሻሻን አንስቶ በቁሻሻ መጣያ ስለሚጥል፡፡ የታመመ የስራ ባልደረባውን ሙዝና ብርቱካን ይዞ ሄዶ ስለሚጠይቅ፡፡ ለመጠየቅ መምጣቱን ታማሚው ሲያውቅ፣ በር ላይ ሰው ልኮ ‹‹የለሁም›› ያስብላል፡፡ የገዛውን ፍራ-ፍሬ በር ለከፈተው ሰጥቶ ይመለሳል። ያገቡ አይጠሩትም፡፡ የሞተባቸው እንዲያስተዛዝናቸው አይፈልጉም፡፡ ለምን ቢባሉ፤ ምክንያቱን እነሱም አያውቁትም። እሱም እንደሚጠሉት እንኳን አያውቅም። አይቀየምም፡፡ ጥላቻን እሱ ፍቅር አድርጎ ነው የሚያነበው፡፡ ማንም ባያምነውም… እሱ ግን ሁሉንም ያምናል፡፡
በስራ ባልደረቦች መሀል መተማመን እንደዚሁም መደጋገፍ አስፈላጊ እንደሆነ ለማስተማር አንድ አሰልጣኝ ወደ መስሪያ ቤቱ መጣ፡፡ በጨዋታ መልክ ብዙ ነገር አስተማራቸው፡፡ ስልጠናው እንደዛ ስለሆነ በባህርይው፡፡ ጨዋታው ላይ፤ አሰልጣኙ አጫዋች፣ ሰልጣኞቹ ተጫዋች እሱ ግን መጫወቻ ነበር፡፡
በአንዱ ጨዋታ ወቅት፤ እሱ ወደኋላ ሲወድቅ ሁለት ባልደረቦቹ ከውድቀቱ ጀርባ እጃቸውን አጠላልፈው ይይዙታል። ይቀልቡታል፡፡ የጨዋታው መልእክት፡- ስህተት መስራትን መቀበል፣ መውደቅ እንዳለ መቀበል፡፡ በመውደቅ ላይ ያለውን የስራ ባልንጀራ የሚያድኑት ባልደረቦቹ መሆናቸውን በጨዋታ መልኩ ማስረገጥ ነበር፡፡
እሱ ሲወድቅ ከኋላው መቅለብ የነበረባቸው እጆች ከዱት፡፡ ለምን? ቢባል፤ እጃቸው እንቢ ስላላቸው፣ አዲሱ ሸሚዛቸው ውስጥ ተሽጦ የነበረ እስፒል በዛ ቅፅበት ስለወጋቸው… የአወዳደቁ እርግጠኝነት እነሱንም ወደሱ ውድቀት እንደሚስባቸው ስላሰጋቸው… ወዘተ፡፡ ምንም መልስ ምክንያት ይሆናል፡፡
ሲወድቅ እንደሚያድኑት ከማመኑ ኃያልነት የተነሳ፣ ጭንቅላቱን ወደ ኋላ አሹሎ ነበር የወደቀው፡፡ ወለሉ ሲፈነክተው አቧራ ሲቦንን ታየ፡፡ እንደ ከረንቦላ ኳሶች ግጭት የመሰለ ጠንካራ ድምፅ ተሰማ፡፡ ወለል የራስ ቅልን ሲያሸንፈው የሚመነጭ ደረቅ ድምፅ ነው፡፡
ባይጎዳ ጥሩ ነበር፤ ተጎዳ፡፡ እንደዛ ከተጎዳ ሞቶ ቢገላገል ጥሩ ነበር፡፡ አልሞተም። ‹‹ጭንቅላቱ የተነካው ያኔ ነው›› ይላሉ የሰፈሩ ሰዎች፡፡ ‹‹ደህና ምን የመሰለ ወጣት ነበር እኮ በናታችሁ›› ይላሉ፤ ከንፈራቸውን ለመምጠጥ ሲያሞጠሙጡ፡፡ ጠበል አልወሰዱትም፤ የታመመበት ምክንያትን ስለሚያውቁ፡፡
የሆነ የፕሮቴስታንት አማኞች ጉባኤ ግን ወሰዱት፡፡ ከወሰዱት በኋላ ‹‹ክርስቶስ እየሱስ ያድናል›› ማለት ጀመረ፤ በመንገድ ላይ እየዞረ፡፡ ጠዋት አራት ኪሎ፣ ማታ ኮተቤ፣ እኩለ ቀን ሳሪስ… ከኮተቤ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል፡፡ መርካቶ፡፡ ነገም ‹‹ክርስቶስ እየሱስ ያድናል›› ማለቱን ይቀጥላል፡፡ የሆነ ሰው መፅሐፍ ቅዱስ ሰጠው፡፡ እግሩና መፅሐፍ ቅዱሱ እኩል ይወዛወዛሉ፡፡ አንዱ በመሬት አንዱ ከጭንቅላቱ በላይ ከፍ አድርጎት፡፡ በአየር ላይ፡፡ ወደ ሰማይ፡፡
‹‹ማርያም ታማልዳለች›› እያለ የሚጮህበት አንድ ሌላ እሱን የመሰለ ተጓዥ አለ፡፡ መንገድ ላይ ሲገናኙ፣ እሱ ይሸሻል፡፡ ያኛው እየተከተለ በጆሮ ግንዱ ይጮህበታል። የራሱ መፈክር ግን አይጠፋበትም፡፡ የዛኛውንም መፈክር አይቃወምም፡፡
ሰው በሌለበት መንገድ ላይ መፈክሩን እየደገመ ሲጓዝ፣ ለሁለት ሆነው በግራና በቀኝ በኩል በአንድ ቅፅበት ጨፍልቀውታል። እንደ ልጅነቱ ግን የኋለኛው በጥፊ ሳይሆን በድንጋይ ነው፡፡ ይደማል፡፡ ደሙ ቶሎ ይቆማል፡፡ ይቆስላል፤ ቁስሉ ቶሎ ይደርቃል። ምግብ የሚያበሉት አሉ፡፡ ምግቡን የሚነጥቁት ግን ይበዛሉ፡፡ የሚያለብሱት አሉ፤ ልብሱን እንዳይለብስ የሚሹት ግን ያይላሉ፡፡
መፈክሩን ሲያሰማ አስቁመው ሊሞግቱት የሚፈልጉ ቢኖሩም፣ እሱ ግን ተናግሮ ብቻ ይሄዳል፡፡ ሰዓትን አቁሞ ማነጋገር አይቻልም። መስበር ግን ይቻላል፡፡ የሱ እግሮች ግን እንደ ሰዓት እጆች ቢሰበሩም አይቆሙም፡፡
እሱን የጠላው ሰው አይደለም፡፡ እህትና ወንድሙ፣ ተማሪዎቹና አስተማሪዎቹ፣ መንገድና ተጓዦቹ አይደሉም፡፡ እሱን የጠላው ሰይጣን ነው፡፡ እሱን እንደሌላው የሰው አይነቶች ሊገራው ቢሞክርም እንቢ ስላለው፤ ጠላው፡፡ እህቱና ወንድሙ ሲመቱት እልኸኛ ሆኖ ቢማታ ኖሮ… በኩርኩም በመቀጠል የሚገጨው አይኖርም ነበር፡፡ ሰይጣንን፤ በተጎዳ ቁጥር እየጠነከረ አስቸገረው፡፡
አንድ የሀይማኖት ሰባኪ መንገድ ላይ አነቀውና እንደሚከተለው ተናገረው፤ ‹‹ስማ በአንተ ምክንያት እኛ አንሸነፍም፤ አለም የእኛ ናት፡፡ የሰው ልጅን በሙሉ በስልጣናችን ስር ተቆጣጥረናል፡፡ በአንተ ምክንያት አንሸነፍም፡፡… የእኛና የሱ ጦርነት በሰው ልጅ የስጋ አለም ላይ እስከተካሄደ ድረስ እኛ አንሸነፍም፡፡ እሱ አያሸንፈንም። ይሔን ብትቀበል ስቃይህ ይቀንስልሀል፡፡ ካልሆነ የባሰውን እናሳይሃለን››
‹‹ክርስቶስ እየሱስ ያድናል›› አለ ሰባኪው። ኮሌታውን ሲለቀው አልፎ ተራመደ። ኮሌታው ሰፍቶታል፡፡ ከስቷል፡፡ አንድ አይነት ነገር እያወሩ፣ ለምን አንዱ ሌላውን እንደሚጨቀጭቅ በጎናቸው ያልፍ የነበረ ሰው አልገባውም፡፡ መቼም አይገባውም፡፡
ለጥቂት ወራት በመንገድ ላይ አልታየም። ጠፋ፡፡ የት ሄደ ብሎ የጠየቀም ግን የለም። ከዛ ብቅ አለ፡፡ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ከበረሀ የመጣ ነው የሚመስለው። አሁን ኮሌታ የለውም፡፡ ከወገቡ በላይ ራቁቱን ነው፡፡ ጭንቅላቱ ብዙ ፀጉር ይዟል፡፡ ሰውነቱ ጥላሸት ተቀብቷል፡፡ ማን እንደሆነ ማንም አያውቅም፡፡ ድሮም አይናፈቅም፤ ከተመለሰም በኋላ አይታወስም፡፡
ለብዙ ቀናት በተለያዩ ህንፃዎች ላይ ለመውጣት ሲሞክር እየተከለከለ፣ እየተገፈተረ፣ ዱላ እየቀመሰ ሰነበተ፡፡ በተለይ ቁመታቸው ረዘም ያሉ ህንፃዎች አላስቀርበው አሉ፡፡ ከብዙ ሳምንታት ሙከራ በኋላ ጠባቂ የተዘናጋበትን ክፍተት ተጠቅሞ ወደ አንደኛው አናት ወጣ፡፡ ማንም ተው አላለውም፡፡ የሆነ ነገር ግን ‹በል› ብሎታል፡፡
ወጥቶ እንደጨረሰ፤ በደረጃ የወጣውን የስቃይ ከፍታ ያለ ደረጃ ወደ ታች ተወረወረ። ጭንቅላቱን እንደ ጦር ጫፍ አስቀድሞ… እንደ እምነቱ መጎዳት አልነበረበትም፡፡ እስቲ ‹‹ራስህን ከዚህ ከፍታ ጣል›› ተብሎ የተፈተነው መሲህ ለመወርወር ካመነታበት ርቀት የእርሱ ተወካይ ተምዘግዝጎ ተፈጠፈጠለት፡፡ ‹‹ጋን ከጀርባ ወድቆ ገል ሆኖ ቀጠለ››
ለሱም መጀመሪያ ጭንቅላቱ ወድቆ አካሉ ብቻውን ቀጠለ፡፡ አካሉም ከከፍታው ወድቆ አካለ ስንኩል ሆኖ መሬት ላይ በብርኩማ መንፏቀቅ ቀጠለ፡፡ አእምሮው ሞቶ፣ አፉ ዲዳ፣ ጆሮው ደንቆሮ ሆኖ… ቀጠለ። በአካልም፣ በአእምሮም በማይለካ ሌላ የነብስ ግዛት፡፡… ከፎቅ ላይ ወድቆ እንደዳነ ያዩ የስጋን ቻይነት ደግመው አረጋገጡ፡፡ ለስጋቸው በድጋሚ ሰገዱ፡፡ ከእምነቱ ላይ ወድቆ ስጋው የተጎዳ የመሰላቸው ደግሞ… ከእምነታቸው እንዳይወድቁ በፀሎታቸው ለመኑ፡፡ እምነታቸውም ጥፍሩን በእነሱ ነብስ ውስጥ አድምቶ ጨበጠ። እምነታቸው ድሮውኑ ሽንፈታቸው ስለነበር… ለአሸነፋቸው ኃይል መደላደልን አመቹ፡፡
እሱ ብቻ መሬት ላይ እየተንፏቀቀ ወደ ድሉ ተጓዘ፡፡ አሁን ፈተናው ቀንሶለታል። ከእንግዲህ የሚኮረኩመው የለም፡፡ የሚኮረኩመውም ቢኖር የሚኮረኮምበት ቦታ በሰውነቱ ግዛት ላይ አልነበረም፡፡ በመሸነፍ አሸንፎአል፡፡ እሱ መሸነፍ… ማሸነፍን አያውቅም፡፡ እሱ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ መጓዝ በጀመረበት አቅጣጫ ተጉዞ ወደ መጨረሱ ተቃርቧል፡፡ መልካምነቱ በጨመረ ቁጥር ሰውነቱ እየቀነሰ መጣ። ሳይሞት በህይወት እያለ ሰውነቱ አለቀ፡፡ የተረፈ ነገር ስለሌለ ማንም አልቀበረውም፡፡ ህይወት ጦርነት እንደሆነ ሳያውቅ፤ ያለ አጋር፣ ብቻውን ትልቁን ጠላት አሸነፈው፡፡ ከፍተኛ ድል ለወሬ ነጋሪ አይደርስም፡፡ ለራሱ ከባለ ድሉ ጆሮም እንኳን አይደርስም፡፡ ብቸኛው ንፁህ ጣዕም ያለው ደም በቆሸሸው ጣዕም  መሀል መራራ ነው፡፡ ጦርነቱ በግለ ነብስ ላይ እስከ መጨረሻው ይቀጥላል፡፡

Read 1153 times