Saturday, 12 February 2022 12:43

የቀለጠ ሻማ! (ምናባዊ ወግ)

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(3 votes)

     ፩
የብቸኝነት ነፋስ በሚነፍስበት  የህይወት  ማሳ ውስጥ ብቻዬን  የበቀልኩ አረም ነኝ። መልከ ጥፉነቴ እንኳን ለሴት ለወንድ ቢቸር ለዓይን ይቀፋል። የሰውነቴ ቅርፅ አልባነት፣ የፀጉሬ መከርደድ፣ የአፍንጫዬ ጎራዳነት፣ ድፍርስ ትልልቅ አይኖቼ፣ አሻሮ የመሰለ ቀለሜን ላየ እንኳን በእግዜር በሰይጣን እጅ መፈጠሬን ይጠራጠራል። ይሄ መልከ ጥፉነት ከእናቴ ልውረሰው ወይም  ከአባቴ አላውቅም። ምክንያቱም እናቴንም ይሁን አባቴን አላውቃቸውም ነበር። ለስም እንኳን የተረፈ አንድም ዘመድ አላውቅም። ማን እንዳመጣኝ ሳይታወቅ ወይም ሳይመዘገብ ...  በበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ አደግሁ፣ ተማርኩ፣ ስራ ያዝኩና ብቻዬን ይህቺን ንፉግ ዓለም ተጋተርኩ።
ግን...  ግን....
...የወንዶችን እቅፍ አልሞቅሁም። የተባዕትን  የስሞሽ ተዓምር አላየሁም። በፍቅር ለመተቃቀፍ ትንግርት እንግዳ ነኝ።  በወንድ አዕምሮ ውስጥ በፍቅር መታሰብ ለእኔ ባዳ ነው። አካሌን የማጋራው አንድ ወንድ የለም። ህይወቴ የፍቅር ደሃ ነው ያለው ማን ነው? ወንዶች እንደ ተዘጋ የመቃብር ድንጋይ እረስተውኛል። ዓይናቸው ውስጥ አልሞላም። የፍቅር ህይወቴ ኦናውን እንደተዘጋበት ቤት ሽታው ይጎፈንናል። የምሞቃት  የፍቅር ፀሃይ ገና አልወጣችም።
አርስቶትል፤ ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ እግዜር ወይ አውሬ ሊሆን ይገባዋል ይላል። ኒቼ ይቀጥልና፤ አርስቶትል ተሳስቷል፣ ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ ፈላስፋ ሊሆን ይገባዋል ይላል። እኔ እግዜርም፣ አውሬም ፣ፈላስፋም አይደለሁም... ግን ብቻዬ እየኖርኩ ነው። ከአንድ ጓደኛዬ ውጪ የሚያስታውሰኝ አንድም ሰው የለም።
ቅር ይላል አይደል? ለሴት በወንዶች አለመፈለግ...  ሶስት አስር የእድሜ እርከንን አልፎ ፍቅርን አለማወቅ? ወጣትነት በምንምነት አፎት ውስጥ ሲገባ ያስከፋል አይደል? ልጅነት እናት አባትን ሲያጣ ያስነባል አይደል? የብቸኝነት አየር ዝንተ ዓለም መተንፈስ፣ በዓለም መረሳት፣ በዓለም አለመፈለግ ትንሽ አያነጫንጭም? ሳይሞቱ መከፈን ቅር ይላል አይደል? በአንድም ሰው ህይወት ውስጥ ቦታ አለመያዝ ያሳዝናል አይደል? ብቻውን ኖሮ ብቻውን የሞተ ሰው የቀብሩ የዝምታ ድባብ  ክርስቶስን ከሰማይ ወደ ምድር ይጠራል። የሰይጣንን ክፋት ይቀሰቅሳል። ዝምታ አንዳንዴ ማዕበል ይሆናል። የተከፋ ሰው ዝምታ እንባ ነው። የሰው ልጅ ትከሻ ምን ሰፊ ቢሆን እንዴት  ሊያወሩ ፈልጎ አለማውራትን፣ ሊያፈቅሩ ፈልጎ አለማፍቀርን፣ ሊጓዙ እየተመኙ መቆምን፣ መሳቅ እየሻቱ ማልቀስን ይችላል? ተዉ ተዉ...የሰው ልጅን መስቀል ክርስቶስ እንኳን አይችለውም። የሰው ልጅን አንገት መድፋት እግዜር እንኳን አይታገሰውም። ምድር ላይ የሚነፍሰው የሃዘን ነፋስ ነው።  
የፍቅር ጥላዬ ስር አንድም ሰው አርፎ፣ ተጠልሎ አያውቅም። ከአንድ ጓደኛዬ በቀር ደፍሮ አጠገቤ የሚቆም ማንም ሰው የለም። ማንም ወንድ እኔን በፍቅር ዓይን ተመልክቶ አያውቅም። ይሄ የአለመፈለግ ድር ያደራበት ህይወቴን በዝምታ እታዘባለሁ። ተፈጥሮና ሰዎች አግልለው ወደ ዳር አውጥተውኛል። አልከፋም እልና እንባ አይኔ ላይ ይመጣል። ጠንካራ ነኝ እልና ጉልበቴ ሲብረከረክ ይሰማኛል። ነፍሴ በማይታይ እሳት ስትቃጠል ይታወቀኛል። አካሌን አልወደውም። ህይወቴን አልወደውም። ሰዎችን አልወድም...ብቻ ለአንዲት ጓደኛዬ  ፍቅር ይሰማኛል። እሷ ከዚህ ዓለም የበቀለች አንድ የእኔ ሰው ናት። ዓለም በመልኬና በሴትነቴ ስትገፋኝ እሷ ስር ተጠልያለሁ። ትመጣለች። ታስቀኛለች። እነዚያ ነጫጭ ጥርሶቿ ብልጭ ሲሉ ሁሉንም ነገር ያስረሳሉ። ታቅፈኝና እንደምትወደኝ ትነግረኛለች። አንድ መስሪያ ቤት ስለምንሰራ ምሳ አንድ ላይ እንበላለን። ቡና እየጠጣን እንጨዋወታለን። አንዳንዴ በየክለቡ እየዞርን እናብዳለን። ብዙ እንጠጣለን። ተቃቅፈን አንዳችን ቤት እናድራለን። አንዳንዴ እንደ እናት እቅፍ አድርጋኝ ይነጋል። አገቷ ስር ገብቼ አለቅሳለሁ።
“ጀመረሽ ደግሞ” ትለኛለች።
እሁድን የምናሳልፈው አንድ ላይ ነው። ቡና አፍልተን ፣ እጣኑን አጫጭሰን ስለ አለቃችን ጋሽ ታሪኩ ጨቅጫቃነት እናወራለን። ጋሽ ታሪኩ የኢህአፓ አባል  ነበሩ ይባላል። አዲስ ሰው ሲያገኙ ድንገት ብድግ ይሉና የኢህአፓ አባሎችን  ግለ ታሪክ ስለማንበቡ ይጠይቃሉ።  ዲሞክራሲያ ስለሚባለው ጋዜጣ ይተርካሉ። መንግስቱ ስለሚባል ሰው በላ (በሳቸው አባባል) ይናገራሉ። መልካቸው እንዲህ ነው ተብሎ ለመናገር ያዳግታል። ቀይም፣ ጠይምም፣ ጥቁርም አይደሉም። ጉንጫቸው አካባቢ ቀላ ይላሉ። ግንባራቸው ደግሞ ፍፁም ጠይም ነው። ትንንሽ ዓይናቸው ሰው ልብ ስር የሚጨነቁር ይመስላል። በረሃ እራሳቸውን እያሹ ዛሬ ስብሰባ አለ ይላሉ። ስብሰባ ላይ እሳቸውን መተቸት ዘበት ነው። ስለ እሳቸው መጥፎ ነገር መናገር ከተጀመረ እስቲ እሱን ተወውና ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ ይላሉ። በደንብ የሚያቀርቡት መልከመልካሙን ሙሉጌታን ነው። “ባልወልደውም ልጄ ማለት ነው። እዩት እስኪ፣ መልዓክ አይመስልም" ይላሉ። እውነትም ሙሉጌታ መልዓክ ማለት ነው። ስልምልም አይኖቹ፣ ለዓለም ክፋት የታወሩ ናቸው። ቀይ መልኩ ላይ የተሰካ ቀጥ ብሎ የወረደ አፍንጫ አለ። ድምፁ ከመንግስተ ሰማያት በተዓምር የፈሰሰ ይመስላል። ዓይን ለዓይን ስንተያይ እደነግጥ ነበር። አጠገቤ ቆሞ ደስ የሚል ፈገግታውን ሲያቀብለኝ ልቤ መምታት ይጀምራል። አንድ ቀን ቢሮዬ መጥቶ “የ2 ሺህ ዓ.ም ፋይል አቀብይኝ የኔ ቆንጆ” ሲለኝ፤ ሰማይና ምድሩ ተገለባበጠብኝ። ለደቂቃ ዝም አልኩ። ፋይሉን እያየሁት አጣሁት። ዓይኔ ታወረ። የልቤ ምት አየለ። ትንሽ ፋታ ወስጄ ተደነባብሬ አንድ ፋይል አንስቼ ሰጠሁት። በዚያ ተዓምረኛ ድምፁ አመስግኖኝ ወጣ። ከተፈጠርኩ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ማንም የኔ ቆንጆ ብሎኝ አያውቅም። ምክንያቱም ቆንጆ አይደለሁም። እሱ ግን በዚያ ድምፁ ነፍሴን አሞቃት። ስቀርበው ደስ የሚል ናትራን ይሸተኛል። ዓይን ለዓይን ስንተያይ አንገቴን አቀረቅራለሁ። ፍቅር ይሁን ምን አንዳች ነገር ይሰማኛል። አንድ ቀን ሉሊት (የምወዳት ጓደኛዬ) አብሮን ክለብ ይሂድ አለችኝ። ተያይዘን በእሷ መኪና ወጣን። አጠገቡ ተቀምጬ ፈሰስኩ። ቢያቅፈኝ ብዬ ተመኘሁ። ያወራል። የሚለውን ግን አልሰማውም። አንድ ክለብ ገብተን መጠጥ አዘዝን። የማላውቀው ሙዚቃ ይሰማል። የሚደንሱ ሰዎች አሉ። ሴቶች በአጭር ቀሚስ ደምቀዋል። ቀለሙን የሚቀያይረው መብራት የሙሉጌታን ውበት አልሸሸገውም። ውሲኪው ተቀዳ፣ ሙሉጌታ ቢራ አዘዘ... ጠጣን። ሙሉጌታ እኔን መርጦ እንደንስ አለኝ። የዳንስ ችሎታዬን አጠራቅሜ ጨፈርኩ። ሞቅ ብሎኝ ነበር። ወገቤን ያዘኝ። ነፍሴ ጋለች። ንዳዱን አልቻልኩትም። ከዚያን ቀን ጀምሬ የእኔ ቢሆን ብዬ ተመኘሁ። አካሌን ብሰጠው፣ ቢያቅፈኝ ቢስመኝ ብዬ ተመኘሁ። ዳንሱን ጨርሰን ሉሊት ጋ ስንሄድ ደስ በማይል ፈገግታ ተቀበለችን። በጣም ትጠጣ ነበር። ደሞዝ ውስኪ ለመጠጣት ባያበቃንም፣ የሉሊት አባትን ገንዘብ ተመክተን እንጠጣለን።
አንዳንዴ ስላለቀ፣ ስለተረሳ፣ ስለ ተዘነጋ ፍቅር ያወራሉ። ግር ይለኛል።  የሰው ልጅ ልብ ለፍቅር ዝንተ ዓለም አይነጥፍምና ነው። አንዳንዴ የተጣሉ ጥንዶች አንድ ሰሞን መፋቀራቸውን እንኳን እስኪዘነጉት፣ ጥላቻ ውስጥ ተዘፍቀው ሳይ እገረማለሁ። ሁሉም ተጎዳድቶ ፊቱን ያዞራል። ሁሉም አንድ ሰሞን ተዋዶ ይሰለቻቻል። ሁሉም ትላንትን በዛሬ ይለውጣል። ፍቅርን በጥላቻ ይተካል። ሁሉም አስመሳይ ናቸው። የኔ ፍቅር እንዲህ እንዳይሆን እሰጋለሁ። ለወደደ እና ላፈቀረ ጀርባ እንደመስጠት ሞት  አለ?  የሚፈልገንን፣ በስስት የሚያየንን አልፈልግህም ብሎ መገልመጥ  ያስከብራል ? እግራችን ስር የወደቀውን መርገጥ ጥሩ ነው? ለእኛ ፍቅር ሲል የተሰቀለው ላይ መትፋት አያስተዛዝብም? በፍቅር የሳመን መንከስ እንዴት ነው? ድንቁርናን ባላውቀውም ጥላቻ ውስጡ  እንዳደፈጠበት ትልቅ ደንቆሮ ያለ አይመስለኝም። ለመውደድ ጊዜ አይጠፋም። ለማፍቀር ቦታ አይመረጥም። ፍቅር ትላንት እና ዛሬን ወይም ነገን አያውቅም። መሰለቻቸት በፍቅር አለም ውስጥ የለም።
ታድያ ይሄ ሙሉጌታ ብዙ የድሮ ነገሬን ነጠቀኝ። ብወደውም መናገሩ አስፈራኝ። ፍቅሬን ሸሸግሁት። ልቤ ውስጥ አኖርኩት። እንዲህ አይነት መልከ መልካም፣ እንደ እኔ አይነት መልከ ጥፉ ሊወድ እንደማይችል እርግጠኛ ነበርኩ። ግን አንደኛው የአዕምሮዬ ክፍል፣ ፍቅር መልክ እንደማያይ ይነግረኛል። ደግሞ እጨነቃለሁ። ለሉሊት እንኳን ለመናገር አልደፈርኩም። ብቻ ተጨነቅሁ። ሳየው እጨነቅ ጀመር። ክለብ እንውጣ ሲባል እሱ አለ ስትለኝ ምክንያት ፈጥሬ መቅረት ጀመርኩ። ፍቅርን ፈራሁ። እውነትን መጋፈጥ አልቻልኩም። ክንብንብ ብዬ እተኛለሁ። እሱን አስባለሁ። አጠገቤ እንደሆነ አልማለሁ። ፊቴን ደጋግሜ በመስታወት ማየት ጀመርኩ። አቋሜን ማስተዋል ጀመርኩ። ለልብስ ግድ የሌለኝ ልብስ  እያማረጡ መግዛት አስፈለገኝ። እሱ ፊት ቆንጆ ሆኜ ለመታየት የማላደርገው ጥረት አልነበረም። አንድ ቀን በህልሜ አየሁት። አቅፎኛል። አልጋ ላይ ነን። ግንባሬን አስሬ ይስመኛል። “አንቺ እኮ የምትወደጂ ልጅ ነሽ” ሲለኝ ነቃሁ። አልቦኛል። ሉሊት ጋር ደውዬ ህልሜን ነገርኳት:: “ቅዠት ነው ባክሽ” አለችኝ። ባልቀበለውም ስለምወዳት አመንኳት። እና ቅዠት ነው ብዬ ደመደምኩ።
ፍቅር ደንበኛ ሌባ ነው። ፍቅር  የሚሰርቀው እውነተኛውን ዓለም  ነው። ካፈቀርነው ሰው ምላስ ሃሰት እንደጉድ ቢዘንብ ሃቅ ነው ብለን በሶስቱ ስላሴ እንምላለን። ባፈቀርነው ሰው ላይ  ኃጢያት  ቢዥጎደጎድ ፅድቅ ነው ብለን እንክዳለን። ያፈቀርነው እንደማይፈልገን ብናውቅ እንኳን ሲያብል መሆኑን ለራሳችን እየነገርን ልባችንን እናባብላለን። ያፈቀርነውን ሰው ከሌላ ሴት ጋር ብናየው እህቱ ናት እንላለን። ፍቅር የእውነትን ስር ነው፣ እንደ አረም ነቅሎ የሚጥለው። አፍቃሪ የጠራ አዕምሮ የለውም። ይሸወዳል፣ ይታለላል፣ ያምናል። እና እላችኋለሁ፤ ጅል ለመሆን ተዘጋጁ። ምናልባት የሃሴት መንገድ እሱ ነው። ጀለስ ሆይ፤ ካልተስማማህ በአራዳ ዓይን ተያይተን እንተላለፍ።
አንድ ቀን ምሳ ስንበላ ሙሉጌታ መጣ። ሉሊት ተነስታ አጎረሰችው። አጠገባችን ተቀምጦ ስለ ምግቡ መጣፈጥ ማውራት ጀመረ።
“አንቺ ቆንጆ አታጎርሺኝም” አለኝ...በደንብ ጠቅልዬ አጎረስኩት...ድንገት ከሉሊት ጋር አይን ለአይን ተያየን። ደስ በማይል አይን ስታየኝ አንገቴን ሰበርኩ። ያስቀየምኳትም መሰለኝ። በቃኝ ብላ ተነሳች። እኔና ሙሉጌታ ብቻ ቀረን።
“በትርፍ ጊዜሽ ምን ታደርግያለሽ?” አለኝ
“የአንዳንድ መንቻኮችን ፍልስፍና አነባለሁ” አልኩት።
“እብድ እኮ ነሽ”
“አዎ እብድ ነኝ። ግን በእብደት አንተ ትበልጠኛለህ”
“ሃሃሃሃ”
ስንሳሳቅ ሉሊት መጣች። “ኧረ ሰዎች ወደ ስራ፤ ሰዓት ሄዷል” ብላ አዋክባ አስነሳችን። ፊቱ ሲጨልም አየሁ። ሁለታችንም ተነሳን። ወደ ቢሮዬ ተመልሼ የሉሊትን ነገር አሰብኩ። ሰሞኑን ልክ አይደለችም። በእርግጥ ምን እንደሆነች አላውቅም። እና ስለምወዳት ብቻ ምንም ልላት አልፈለኩም። ዝም ብቻ ... ጊዜ እየበረረ ማየት...ጊዜ በረርክ በረርክ ያለው ባለቅኔ ትዝ አለኝ...
አዎ ጊዜ ምን እንዳተረፈ ባያውቅም ይበራል። ዓይናችን ሥር ዓለም ትለወጣለች፣ ህይወት ይቀየራል። የፀሃይ መግባትና መውጣት...የጨረቃ መድመቅ...የከዋክብት ውበት...የጠቆረው ሰማይ...ዝናብ ያረገዙ ደመኖች ሁሉም እንደ አይን ጥቅሻ በቅፅበት ሊቀሩ ይችላሉ።
አሁን ከራሴ ጋር ልበድ። እብደት የሚያክመው የህይወት ህመም ውስጤ በማቆጥቆጥ ላይ ይገኛል።

ሙሉጌታ በሰበብ ባስባቡ ቢሮዬ መምጣት ጀምሯል። አንድ ሰሞን ደስ ይለኝ ነበር። እያደር ግን ትንሽ ግር አለኝ። የሚያየኝ በስስት ነው። ንግግሩ ላይ የኔ ቆንጆን መሰንቀር ይቀናዋል። ጠዋት ስንገናኝ አጥብቆ ያቅፈኛል። በዚህ ጊዜ ሉሊት ፊት ላይ ግልፅ ያልወጣ ቅሬታ አነባለሁ። በዚህ ሁኔታ ነገሮች ማለፍ ጀመሩ። ሉሊትን ከማስከፋ ብዬ ሙሉጌታን እሷ ፊት እኮሳተርበት ጀመር። ክለብ ከኛ ጋር ልምጣ ሲል እንደለመድኩት ሰበብ ፈልጌ እቀራለሁ። አሁን አሁን በዚህ ስራ ሉሊት መደሰት ጀምራለች። አንድ ቀን እንደውም “ዛሬ ከእናንተ ጋር ላምሽ ቅዳሜ ነው”  ሲል “ደስ ይለናል፣ እሷ ግን ደብሯታል አብራን መሆን አትችልም” አለችው። ምንም አይነት ድብርት አይሰማኝም ነበር። ለእሷም ተደብሬያለሁ ብዬ አልተናገርኩም። ብቻ ዝም ብዬ ወደ ቤቴ አዘገምኩ።
አንድ ዕለት ከቢሮ ሶስታችን ስንወጣ "ሰርፕራይዝ አለሽ" አለችኝና አንድ ካፌ ውስጥ ተያይዘን ገባን። ሉሊት ሳቅ በሳቅ ሆናለች። በጣም ደስ እንዳላት ያስታውቃል። ሙሉጌታ በዛው ልክ ፊቱ ዳምኗል። ያ ቆንጆ መልኩ አኩርፏል። ቡና ከጠጣን በኋላ “በይ ሰርፕራይዙን ወዲህ በይ ልቤ ቀጥ ልትል ነው” አልኳት። ትንሽ ዝም አለች። በመሃል ሙሉጌታ “ሌላ ቀን ይሁን" አለ።
“No...anyways እኔ እና ሙሉጌታ ከዚህ በኋላ ፍቅረኞች ነን” አለችና መሳቅ ጀመረች።
 እነዚያ ነጫጭ ጥርሶቿ ላይ ተንኮል ባነብም ዓይኔን አላመንኩትም። ሳቋ በግድ ይመስላል ወይ ለማናደድ። እጇን ሰዳ አቀፈችው። ዝም አልኩ። ልቤ ይመታ ጀመር። ሁለት መንታ መንገድ ፊቴ ተዘርግተዋል። የትኛውን ልምረጥ? አንደኛውን መምረጥ ግድ ይላል። እናም ሉሊትን መረጥኩ። ተነሳሁና አቀፍኳት ፣ ሳምኳት። እሱንም አቀፍኩት። ደስ እንዳለኝ ነገርኳቸው። እንደውም በእኔ ወጪ ቅዳሜ ልጋብዛቸው ቃል ገባሁ።
ድርጊቴ ማስመሰል አልነበረም። ስለ እሷ ደስ ብሎኛል። ግን ውስጤ ባዶነት ተሰማው። የህይወቴ ማሳ ላይ የሚነፍሰው የብቸኝነት ነፋስ ከፋ። በረደኝ። እቅፍ ፈለኩ። መሳም ፈለኩ። መወደድ ፈለኩ። ሁሉም ነገር አማረኝ። ሰው እራበኝ። የእራሴ የምለው ሰው። በፍቅር የሚይየኝ ሰው። እና ያቺ ቅዳሜ ደረሰች። ለባብሰን ወጣን። መንገዱ አስጨናቂ ነበር። ምን እንደማወራ ጠፋኝ። ሙሉጌታ አይን አይኔ እያየ ምን እንደማስብ የሚገምት ይመስላል። እና የቸኮልኩት መጠጥ ቀምሶ ለመስከር ነው። አዕምሮዬን ፍዝ ላደርገው ነው የቸኮልኩት። ለምንምነቴ ለማልቀስ ነው የቸኮልኩት። ለሞቴ ሙሾ ላወርድ ነው የቸኮልኩት። ለምወዳት ጓደኛዬ ደስታ ፅዋዬን ላነሳ ነው የቸኮልኩት። አንዳንዴ ህይወት ፈጥና ብትራመድ ጥሩ ነበር።
ገብተን አንድ ጥግ ላይ ቦታ ያዝን። መጠጡ መጣ። ሉሊት የለመደችውን ውስኪ አዛለች። በዚህ ወጪ ደሞዜ እንደሚያልቅ አታውቅም ብዬ በሆዴ ቀልጄ ሳቅሁ። ሙሉጌታ እንደለመደው ቢራ አዘዘ። እኔም የለመድኩትን ውስኪ ይዤ በፍጥነት መጠጣት ጀመርኩ። የስካር አምላክ ይመስገንና በፍጥነት ሞቅ አለኝ።
ደነሱ...ጨፈሩ...አበዱ...ሁሉንም ነገር ታዘብኩ። የሉሊት ደስታ ያስደስታል። ለመጀመሪያ ጊዜ ፍቅሬን በመደበቄ በእራሴ ኮራሁ። ለጓደኛዬ ሻማ ሆኜ ብበራ አልቆጭም አልኩ። እኔ ከእሱ ጋር ሆኜ አይታ ብትጎዳ መቼም ለእራሴ ይቅርታ አላደርግለትም ነበር። ደስ አለኝ...ተያይዘን አበድን፣ ጨፈርን...ህይወት ላይ ዳንኪራ እረገጥን። መታዘቤን አራግፌ ጣልኩ። በጓደኛ ሳቅ እንደመሳቅ ያለ  እውነተኛ ደስታ እንደሌለ አወቅሁ። ፍቅርን ከመጀመሪያው ሀሁ ቆጠርኩ። ስለ መውደድ ዝቅ አልኩ። ሞቅታው ተጨምሮ ብቸኝነቴ ለጊዜው ጠፋ። ተነፈስኩ....ፈሰስኩ...

በማጣት ማግኘት አለ። ስለ ፍቅር የወደቀ ነገር ሁሉ አይሰበርም። በሞት መዳን ይመጣል። በእንባ ሳቅ ይገለጣል። የሃዘን ሰማይ ላይ ደስታ ደመና ሆኖ ይታያል። ብቻ በመሆን ሙሉነት አለ። ዓለም እንዲህ ናት ሊሏት የምታስቸግር ትንግርተኛ ናት። ግን ደግሞ በመኖር መድከም አለ። እግዜር የጣለብንን ሁሉ ተሸክሞ በመኖር መዛል ይመጣል። በማቀርቀር መውደቅ ይመጣል። ያየነውን አለማመን አለ።
እናም...
...የምወዳት ጓደኛዬን አጣኋት። ስደውል "ከሙሉጌታ ጋር ነኝ ማውራት አልችልም" ትለኛለች። ሳገኛት ለደቂቃ እንኳን ተረጋግታ አታወራኝም። ስቀርባት ትርቃለች። ይሁን ከተደሰተች ብዬ ስርቃት ደግሞ ፈልጋኝ ትመጣ ነበር (በኋላ ብተወውም)። ምን እንደምላት አላውቅም። እንደ ድሮ አቅፋኝ አዳር ሙሉ እንድናወራ እፈልጋለሁ። እንደ ድሮ እንደምትወደኝ እንድትነግረኝ እፈልጋለሁ። እንደ ድሮ ችግሬን እንድታዳምጠኝ እፈልጋለሁ። የድሮዋን ሉሊት እናፍቃለሁ። አንዳንዴ እያሰብኳት እንባ ጉንጬ ላይ መንጠባጠብ ይጀምራል። ማንም በሌለኝ ሰዓት አጠገቤ ነበረች። አሁን ግን አጣኋት። እናም ነገርኳት። ተለውጠሻል አልኳት። የድሮዋ አንቺ አይደለሽም አልኳት። “የማይለወጥ ነገር የለም” ብላኝ አለፈች።
 አንድ ቀን ስልኬ ላይ መልዕክት ገባ። ሳየው ሙሉጌታ ነበር። “አፈቅርሻለሁ” ይላል። “እኔ ደግሞ አላፈቅርህም” ብዬ ላኩለት። “ዋሽተሻል” አለኝ። መልስ አልሰጠሁትም። ለመጀመሪያ ጊዜ ያፈቀረኝን ብወድ ለጓደኛዬ አስረክቤ ነበር። በህይወቴ የምፈልገውን ነገር ሁሉ ወስዳለች። ግን በኔ ቅር ብሏታል። እናም ህይወት አስጠላኝ። ባዶነቴ ገነነ። ካልተፈለጉ አለመገኘት ጥሩ ነው። ጥፋ ከዚህ ሲባሉ አመስግኖ መራቅ አሪፍ ይመስላል። ለሰላምታ እንኳን ዘጋችኝ።   ከፋኝ። በእኔ እና በእሷ መሃል የገባው ሙሉጌታ እንደሆነ ገባኝ። እሱ ወደ እኔ ያያል። እኔ ወደ እሷ አያለሁ። መንገዳችን ተለያይቷል።
 ስራ ቀየርኩ። ስልኬን ቀየርኩ። ቤት ብቻ መቀየር ስላልቻልኩ የድሮ ቤት መኖር ጀመርኩ። ጊዜ ሄዶ ጊዜ መጣ። እራሴን መጥላት ጀመርኩ። ዓለምን መጥላት ጀመርኩ። ሉሊትን መናፈቅ፣ ሙሉጌታን ማፍቀር ቀጠልኩ። አንዳንዴ ሉሊትና እኔ ብቻ ሆነን የምንሆነው አይኔ ላይ ይመጣል። ስራ ከቀየርኩ በኋላ አንድም ቀን ፈልጋኝ መጥታ አታውቅም። ሉሊት በእኔ ጨክና አታውቅም ነበር፤ አሁን ግን ጨከነች። እኔን የዚህን ያህል ጊዜ አኩርፋኝ አታውቅም ነበር። ዛሬ የማይሆን ሆነ። የማይደረግ ተደረገ።
ፍፁም ብቸኛ ሆንኩ። ሰው ሳይ ነብር እንዳየች ሚዳቆ መደንበር ጀመርኩ። እውነት እውነት እላችኋለሁ ሰው ክፉ ነው። እንዳፈቀርከው እያወቀ እንኳን ይገፋሃል። ከእሱ ውጪ ሌላ ሰው እንደሌለህ እየገባው እንኳን ያርቅሃል። ያሳለፍናቸው ውብ ጊዜያት ውሸት መሆናቸውን አመንኩ። እና አንድ የሰይጣን ሃሳብ ጭንቅላቴ ውስጥ ይመላለስ ጀመር። አዎ! እራሴን ማጥፋት ፈለኩ። ለመኖር ታከትኩ። ለፍቅር ደከመኝ። ናፍቆትን መቋቋም፣ ፍቅርን መታገስ አልቻልኩም።  እናም አንድ ቀን ብዙ የእንቅልፍ ኪኒን ገዝቼ ቤቴ ገባሁ። ከዚያ በፊት ለሉሊት ደብዳቤ ልፅፍላት ቁጭ አልኩ።
መፃፌን ጀመርኩ።
“የኔ ሉሊት እንዴት ነሽ? እኔ ደህና ነኝ ብዬ አልሸነግልሽም። ደህና አይደለሁም። ሁሉም ነገር አድክሞኛል። ሁሉም ነገር ታክቶኛል። ናፍቆትሽን መቋቋም አልቻልኩም። ሙሉጌታን ምናልባት ካንቺ በፊት አፍቅሬው ነበር። ህይወቴ ሙሉ መሆን ጀምሮ ነበር። ፍቅርን ማወቅ ከጅሎ ነበር። ግን እንደወደድሽው ሳውቅ የኔን ፍቅር አውጥቼ ጣልኩት። ላንቺ ደስታ እኔ ደስ አለኝ። ላንቺ ፍቅር እንደ ሻማ እየቀለጥኩ ልበራ ወሰንኩ። አሁንም ደስተኛ ሆነሽ መኖርሽን እናፍቃለሁ። ከሙሉጌታ ጋር እንዴት ናችሁ? ያኔ አብራችሁ መሆናችሁን ስትነግሪኝ ገርሞኝ መጀመሪያ በዝምታ ብዋጥም ላንቺ ደስታ ተደስቻለሁ። እና እንዴት ነሽ ሉሊቴ? ...እውነት እውነት ናፍቀሺኛል። ድሮአችን ናፍቆኛል። እቅፍሽ ናፍቆኛል። እብደታችን ናፍቆኛል..”
ፅፌ ሳልጨርስ የቤቴ በር ተንኳኳ።  ልቤ ፈራ። በዚህ ሰዓት እኔ ጋር የሚመጣ ማን ነው? ተንስቼ ከፈትኩ። ማመን አልቻልኩም። ፈዝዤ ቆምኩ። ሉሊት ናት። ምንም ሳትናገር አቅፋኝ ማልቀስ ጀመረች። ተቃቅፈን አለቀስን። ወደ ውስጥ ገባች።  ሳንነጋገር ተግባባን። አንዲትም ቃል ሳይወጣን ይቅርታ ተለዋወጥን። ቡና ላፈላላት ጉድ ጉድ ማለት ጀመርኩ። ስለ ሙሉጌታ ጠየኳት፤ ውጪ መሄዱን ነገረችኝ።
“ናፍቀሺኛል” አለችኝ። አቅፌ ሳምኳት። “በድዬሻለሁ” አለችኝ...”ዝም በይ” አልኳት።
“በዚህ ሰዓት ባትመጪ ምናልባት ላታገኚኝ ትችያለሽ” አልኳት።
“ለምንድነው የማላገኝሽ”
“እራሴን ላጠፋ ነበር” ብዬ መድሃኒቱን አሳየኋት።
“በስማም” ደነገጠች።
ቡናው ተፈላ። እጣኑን አጨስኩ። እንደ ድሮዋችን ወሬ ጀመርን። እንደ እግዜር ህይወት ነው የጨመረችልኝ። እናም በመኖሬ ተደሰትኩ። በዓለም ረካሁ። ደስታ በደምስሬ ሁላ ተመላለሰ። ...ዳግመኛ መኖር ቀጠልኩ።

Read 1547 times